በዓለም የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የዝንጀሮ ፖለቲካ የሚል የፖለቲካ ፍልስፍና እንደሌለ አወቃለሁ። ይሁን እንጂ በአሸባሪው ትህነግ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድን የዝንጀሮ ፖለቲካ ብዬዋለሁ። ለምን የዝንጀሮ ፖለቲካ ተባለ? የሚል ካለ ምክንያቱን እነሆ፦
በአንድ የዝንጀሮ መንጋ ውስጥ አንዲት እናት ዝንጀሮ ወንድ ልጅ ከወለደች በልጇ እና በእሷ የሚደርስባቸው ግፍ ከኮሶ እጅጉን የመረረ ነው። ምክንያቱም የተወለደው ዝንጀሮ ወንድ ከሆነ የወደፊት መንጋው መሪ ሊሆን ይችላል በሚል ፍራቻ እና ስጋት በመንጋው የሚገኙ ትላልቅ ወንድ ዝንጀሮዎች በአዕምሯቸው ክፋትን ስለሚያረግዙ ነው። በዚህም ምንም የማያውቀውን ሕፃን ዝንጀሮ ለመግደል ይተጋሉ።
ይህን ተከትሎ እናት ዝንጀሮ ልጇን ለማትረፍ ከመንጋዋ ለመነጠል ትገደዳለች። ከመንጋቸው በተነጠሉበት ወቅት ምናልባትም ልጅ እና እናትን እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ለአስከፊ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ። ገና ለገና የወደፊት የመንጋው መሪ ይሆናል በማለት የራሱን የመንጋ አባል ማሰቃየት እና መግደል የዝንጀሮ ሁነኛ መታወቂያ ባህሪው ነው።
ይሄን ወደ እኛ ሀገር ፖለቲካ ስናመጣው አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት እንደፈለገው ያለማንም ከልካይ ሲፈነጭባት ቆይቷል። በነዚህ ዓመታትም ሥልጣኔን ሊገዳደሩ ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን ማህበራት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ምሁራንን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በሙሉ አንድም ገድሏል ወይም አስሯል፣ ከሀገር አባሯል፣ የተቀሩትን ከሥራ እና ከትውልድ መንደራቸው በማፈናቀል ቀደም ብለው የገነቡትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን አፍርሶ ለአዕምሮ በሽተኛነት ዳርጓል።
እነዚህን ዜጎች በየመንገዱ እንዲወድቁ በማድረግ የሰዎች መሳቂያ እና መዘባበቻ አድርጓል፣ አብዛኛውን ሕዝብ ደግሞ መብቱን ረግጦ በመያዝ ሀገሩን እንዲጠላ በማድረግ መለኪያ ሊገኝለት የማይችል ግፍ ፈጽሟል። በኢትዮጵያውያን ማንነት ላይ አይቀልዱ ቀልድ ቀልዷል። ይህንንም ለመተግበር በዋናነት የተጠቀሙት የዝንጀሮን ደመነፍሳቸው መንገድ ነበር።
የወያኔ የዝንጀሮ ፖለቲካ ቀማሪዎች ምዕራባውያን ሲሆኑ አስፈጻሚው ደግሞ ከሆዱ ውጪ ሌላ የማይታየው የእኩይ ተግባር ፊታውራሪው ሀገር ጠሉ ወያኔ ነበር። ምዕራባውያን ወያኔን ተጠቅመው በኢትዮጵያ የዝንጀሮ ፖለቲካ ሲተገብሩ አያሌ ማህበራት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ምሁራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ላይ እልቆ መሳፍርት ሰቆቃ አድርሰዋል። እነኝህ ማህበራት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ምሁራን እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለግፍ የዳራገቸው ብቸኛው ሀጢያታቸው የሀገራቸውን ጥቅም በማስቀደማቸው እና ለምዕራባውያያን የነዋይ ሴሰኝነት ባለመሸነፋቸው ነው።
በምዕራባውያን እቅድ ከአሸባሪው ህወሓት የክፋት መርዝ ለችግር ከተዳረጉት ማህበራት ውስጥ አንደኛው «ስደተኛው የመምህራን ማህበር» እየተባለ የሚጠራው ማህበር አንዱ ነው። ይህ አንጋፋ ማህበር (ኢመማ) ውልደቱ በ1941 ዓ.ም ነው። ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለቆመለት ዓላማ ማለትም ለመምህራን መብት መጠበቅ፣ ለአካዳሚክ ነፃነት መስፈን፣ ለመደራጀት መብትና ለትምህርት ጥራት ከፍ ያለ መስዋእትነት ከፍሏል።
ለምሳሌ በ1959 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ካደረገው የመምህራን ደመወዝ እስኬል ጋር ተያይዞ ችግር በተፈጠረ ጊዜ ማህበሩ በምክንያት እና በመርህ ላይ ተመስርቶ ለትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ደመወዝ እንዲሻሻል ጥያቄ በማቅረብ የደመወዝ መሻሻል እንዲደረግ አድርጓል። በዚህም ድርጊቱ የሙያ ማህበሩ ከፍተኛ ከበሬታ እንዲያገኝ አስችሎታል።
በመቀጠልም በ1965ዓ.ም ዝግጅቱ ተጠናቆ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ለመዋል በዓለም ገንዘብ አበዳሪ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ (The World Bank) አማካይነት የተቀረጸውን የትምህርት ዘርፍ ክለሳ (Education Sector Review) በመባል የሚታወቀውን የድሃ ልጆች እንዳይማሩ የሚያደርገውን የትምህርት ፖሊሲ በመቃወም ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን ብርቱ ትግል ማድረግ የቻለ አንጋፋ ማህበር ነበር።
ዳሩ ምን ይሆናል! ይህ ማህበር በኢትዮጵያ እያለ እኩይ ተግባራቸውን በሀገራችን ላይ መፈጸም እንደማይችሉ የተረዱት ምዕራባውያን ሀገር ጠሉን እና የጥፋት ፊታውራሪ የሆነውን አሸባሪውን ህወሓት በመጠቀም ለሀገሩ እድገት በመስራት አንቱታ ያተረፈውን ማህበር ለስደት ዳርገውታል።
ይህ አልበቃ ብሏቸው በታኅሣሥ ወር 2006 ዓ.ም በተወሰኑ ክልሎች በዞን መስተዳድር ርዕሰ ከተሞች ከሚገኙ የትምህርት ቤቶች በኮታ የተመረጡ መምህራንን በመሰብሰብ ለምዕራባውያን ያደረ ለቡድኑ ተለጣፊ ማህበር በመመስረት በትምህርቱን ዘርፍ ላይ ቀልደዋል።
አሸባሪው ህወሓት የትምህርት ዘርፉን ለመጉዳት በአንደኝነት የጥፋት በትሩን የመዘዘው የመምህራንን ኑሮ ማኮሳመን ላይ ነበር። በዚህም የመምህራን የኑሮ ደረጃ ቁልቁለት ወርዶ ተፈጠፈጠ። የእውቀት አባት የሆነው መምህር በኑሮ ደረጃው ከተማሪዎች ዝቅ ብሎ ተቀመጠ። በዚህም ጥሩ እውቀት የነበራቸው እና ተተኪውን ትውልድ መቅረጽ የሚችሉ መምህራን የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሲሉ ራሳቸውን ከመምህርነት ሙያ በማግለል ወደ ሌላ ሙያ በገፍ ተሰደዱ።
በተለያዩ ምክንያቶች ወደሌላ ሙያ ከመሰደድ የተረፉት መምህራንም አሸባሪው ህወሓት በምዕራባውያን ታግዞ ባወጣው ጸረ ኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በተማሪዎች እና በማህበረሰቡ ተቀባይነት እና ተደማጭነት እንዳይኖረው ተደረገ። በማህበረሰቡና በተማሪዎች ተቀባይነት እና ተደማጭነት ያጣው መምህሩ ስለዓለም እና ስለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለተማሪዎች የሚሰጠው ትምህርተ ሰሚ አጣ። በዚህም ተማሪዎች ዓለም እና ኢትዮጵያ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ እንዳይችሉ የእውቀት በሩ ተከረቸመባቸው።
በዚህም በሀገራችን የሚገኙ ተማሪዎቻችን ለሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር እና ዓለም ስለደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ ያላቸው ግንዛቤ የተንሻፈፈ እንዲሆን አደረገ። ከቀን ወደ ቀን የተማሪዎቻችን ስለሀገራቸው ያላቸው ግንዛቤ እየወረደ ሂዶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ወላጅ መርቆ የሸኛቸው ተማሪዎች ተልዕኮአቸውን ወደጎን ጥለው በቋንቋ ተቧድነው ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን መርጠው ወያኔ በቀደደላቸው የጥፋት ቦይ መፍሰስ ጀምረዋል። ለችግር ፈቺነት ተስፋ የተጣለበት ተማሪው ከችግር ፈቺነት ወደ ችግር ፈጣሪነት ተሸጋገረ።
በ2010 ዓ.ም የምዕራባውያኑ የጥፋት አሽከር አሸባሪው ህወሓት ከሥልጣን ተወግዶ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን በመሪነት በተረከቡ ማግስት ጊዜ ሳያጠፉ አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመቱ ያበላሻቸውን ሀገራዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለምአቀፋዊ እና ቀጣናዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ያለእረፍት ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ እና አውሮፓ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ እሩቅ ምሥራቅ ጃፓን፣ ቻይና ወዘተ ድረስ በመሄድ ኢትዮጵያውያንን ብሎም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያስደመሙ ሥራዎችን ሰሩ ።
በዚህም የኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የነበራትን ግንኙነትን በማሻሻል ወደብ አልባዋን ኢትዮጵያን ከበርበራ ወደብ ድርሻ በመግዛት ባለወደብ አደረጉ። ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበር በአሰብ ወደብ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦች እንዲኖሯት አደረጉ። ከኢኮኖሚያዊ ተግባር ባለፈ በወደቦች ዙሪያ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል እንዲኖራት በማድረግ በታሪክ ሲዘከር የሚኖር አኩሪ ገድል ፈጸሙ።
ስለወደብ ካነሰሁ አይቀር ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ «ሞት የተፈረደባቸው 17 ሺ ሰራዊት በምጽዋ» በሚል ከጻፈው መጽሐፍ አንድ አባባል ልዋስ። በመጽሐፉ እንደተገለጸው ብርጋዴር ጄነራል ተሾመ ተሰማ በምጽዋ ግንባር በነበረው ውጊያ ይመሩት የነበረው ጦራቸው በተደጋገሚ ባደረገው ጦርነት ሳቢያ ቁጥሩ በመመናመኑ ጦራቸው ወደ ምጽዋ ይሸሻል። ጦራቸውን ይዘው እየተዋጉ በሚሸሹበት ወቅት እጅ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ። ጄኔራሉ እጅ ከሰጡ እንደማይገደሉ እና ወደ ውጭ ሀገር እንዲወጡ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹላቸው በድምጽ ማጉያ ይገለጽላቸዋል።
ጄኔራሉም የተደረገላቸውን ጥሪ ሳይቀበሉት ቀሩ። ለዚህም በዋናነት የጠቀሱት ምክንያት የኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ ነበር ። ስለወደቡም እንዲህ አሉ «አንድ ቤት ሲሰራ መስኮት እና በር ይሰራለታል። መቃብር ከሆነ ግን መስኮትም በርም አይሰራለትም። ስለዚህ ሀገሬ መቃብር ሆና ከማያት መሞቴን እመርጣለሁ!» አሉ። እንዳሉትም የሚቻላቸውን እያደረጉ ሲዋጉ እና ሲያዋጉ ቆይተው እጄን አልሰጥም በማለት ለሀገራው ሲሉ ራሳቸውን በራሳቸው ገደሉ። የባህር በር ለአንድ ሀገር ያለውን ጠቀሜታ የጄኔራሉ ንግግር እና መስዋዕትነት በግልጽ የሚያሳይ ነው። አሸባሪው ህወሓት ግን የባህር በር እንዳይኖረን በማድረግ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት መቃብር ውስጥ በመጨመር በኢትዮጵያ ስቃይ ከበሮውን እየደለቀ ሲጨፍር የኖረ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን እያንዳንዷን እርምጃ የሚቆጥሩት ምዕራባውያን በአሸባሪው ህወሓት ዘመን እንደፈለጉ የሚያደርጓትን ኢትዮጵያን እንደሚያጡ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ይህን ተከትሎም ሆነ ብለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የስም የማጥፋት ዘመቻ (character assassination) በማካሄድ የዶክተር ዐቢይ አስተዳደርን በሆነ ባልሆነው መውቀሱን እና መክሰሱን ሥራዬ ብለው ከያዙት ውለው አደሩ።
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ የቆየ መሆኑን ለመረዳት በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈው እና በከያኒ ደበበ እሸቱ ወደ አማርኛ የተተረጎመው “Abessinien: Die schwarze Gefahr” ወይም «የባሩድ በርሜል» የተሰኘውን መጽሐፍ ማየት በቂ ነው።
የባሩድ በርሜል ጸሐፊው ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ከኦስትሪያ በአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሰራ የተላከ ዲፕሎማት ነበር። በ1926 ዓ.ም የዲፕሎማት ሥራውን እና ከዲፕሎማቲክ መብቱ ጋር የሚፃረር ተግባር ሲያከናውን በመገኘቱ ከአዲስ አበባ ተገዶ እንዲወጣ ተደረገ። ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ከአዲስ አበባ መባረሩን የሚያስታውስ ማንም ሰው ከሰሞኑ ከያዙት አላማ እና ተልዕኮ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የተባረሩትን ሰባቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ማስታወሱ አይቀርም ።
በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈው መጽሐፍ አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከምዕራባውያን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለውን ተፅዕኖ ለመረዳት ስለሚስችል መጽሐፉን በወፍ በረር ማየቱ ተገቢ ነው።
መጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ላይ «በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምንድን ነው?» በሚል ርዕስ ተነስቶ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል። መጽሐፉ ስለ ሀገሪቱ መልክዓ ምድራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነት ያትታል፣ ቅኝ ተገዥ ከሆነው ከሌላው ዓለም ሕዝብ የሚያገኙትን ክብርና ታዛዥነት ኢትዮጵያ ውስጥ ማጣታቸውን ሳይደብቅ ይነግረናል። ይህንን የኢትዮጵያውያን ኩራት ማኮስመን ካልተቻለ እና በቸልተኝነት ከታለፈ ወደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ተሸጋግሮ ዋጋ ያስከፍናል ሲል ይመክራል።
የኢትዮጵያውያን ኩራት እና የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ማኮስመን እንደሚገባ ለአውሮፓውያን ይመክራል። የአማራ ብሔር ለውጭ ኃይሎች ያላቸው ጥላቻ ለሁሉም የውጭ መንግሥታትና ዜጎች አሳሳቢ መሆኑን፤ የአማራ ብሔርን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያን እንዳትነሳ አድርጎ ማጥፋት እንደሚቻል ይገልጻል።
ይህንን የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ እቅድ ለሚመለከት ማንም ሰው አሸባሪው ህወሓት በ1968 ዓ.ም በእጅ የጻፈው ማኒፌስቶው መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሐፍ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ መገንዘብ ይቻላል። ቡድኑ ከፍጥረቱ ጀምሮ የምዕራባውያን የጥፋት አሽከር መሆኑን ያመላክተናል።
ምዕራፍ ሁለት «ጥቁር መጽሐፍ የኢትዮጵያውያን የጥቃት ስንዘራ» በሚል ርዕስ ተነስቶ ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጡ የሚገጥማቸውን መከራና ሰቆቃ ይዘረዝራል። ለውጭው ዓለምም ለጥቁር አሜሪካውያን ሳይቀር ኢትዮጵያ ማለት ለእንግዳ ክብር የማትሰጥ የምድር ሲዖል እንደሆነች አድርጎ ያለግብሯ ግብር እና ያለታሪኳ ታሪክ ለመስጠት ይሞክራል።
ይህን የኢትዮጵያን ክብር ለማውረድ ሲጣጣር የሚመለከት ማንኛም ሰው የአሸባሪው ትህነግ እና ግብረ አበሩ ኦነግ ሸኔ የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ነው ብለው ታሪኳን ለማሳነስ የጀመሩት እሩጫ መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ጽሑፍ መሆኑን ለመረዳት ዕድል ይሰጠዋል ።
የዶክተር ዐቢይ በ2013 ዓ.ም ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ምርጫው ኢትዮጵያ የምታሸነፍበት ምርጫ እንደሚሆን ሲናገሩ በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር። ኢትዮጵያ የምታሸነፍበት ምርጫ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ያልጓጓ አልነበረም። የምርጫውም ቀን ደረሰ። ምርጫውም ምዕራባውያን እንዳሰቡት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በአቀዱት ልክ ተቀዶ ተተገበረ። ምዕራባውያን ያለሙት ሁከት እና ብጥብጥ ቅዥት ብቻ ሆነ። ቀጥሎም የአዲስ መንግሥት ምስረታው ቀን ደረሰ። ዶክተር ዐቢይም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዝንጀሮ ፖለቲካን በመቅበር አዲስ የፖለቲካ አካሄድ ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ መሪዎች ሊያስተምር የሚችል ተግባር አከናወኑ። በአሸባሪው የትህነግ ዘመን የነበረውን ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በዝንጀሮ ፖለቲካ መብላት ላይመለስ ተቀበረ። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በምርጫ ቢሸነፉም እንደስጋት ሳይሆን ለሀገረ መንግሥት ግንባታው እንደአጋዥ ተቆጠሩ። እስከሚኒስትርነት ባለው የኃላፊነት ደረጃ ተሾሙ። ይሄ አይደል ኢትዮጵያ አሸነፈች ማለት !።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014