ማርጀታችን ሲታወቀን ሁላችንም የኖርንበትን ጊዜ ወደ ኋላ ለመመለስ ይቃጣናል። ይሁንና ይህ የሚሰራው በሳይንስ ልብወለድ ላይ ብቻ ነው። ይሁንና በገሃዱ ሳይንስ ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚያደርጓቸው መጥፎ አመሎች ለእርጅና እንደሚያበቁና ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሰዎች የወጣትነት ዕድሜ እንዲሰማቸው የሚያደርጉና ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ የሚያስችሉ መንገዶች እንዳሉ አረጋግጧል።
ለመሆኑ ዕድሜዎ በቶሎ እየገሰገሰ እንደሆነ ይሰማዎታል? ያለዕድሜዎ እያረጁ እንደሆነስ ያስባሉ? መቼስ ማንም ቢሆን በቶሎ ማርጀት የሚፈልግ የለም። ገና በለጋ ዕድሜዎ እንዲህ ዓይነት ስሜት ከተሰማዎና እርጅና ከተጫጫንዎት ከታች ከተዘረዘሩት ውስጥ በከፊል ወይም ሁሉንም እየከወኑ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ረጅም ዕድሜ ለመቆየት ከፈለጉ ለጤናው ሲሉ ከነዚህ ድርጊቶች ራስዎን ይቆጥቡ ይላሉ የጤና ባለሞያዎች።
1ኛ፡- ጭንቀት
በአሁኑ ጊዜ ተመራማሪዎች ጭንቀት ምን ያህል ሰውነትዎን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ እንደሚገኝ እያስጠነቀቁ ነው። ጭንቀት በልብ በሽታ የመያዝ ዕድልዎን ከመጨመሩም በላይ ለከፍተኛ የደም ግፊትና ለሌሎች ፅኑ ህመሞች እንደሚዳርግም እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። ሌላ ልጨምርልዎ! ጭንቀት ቶሎ በማስረጀት ዕድሜን በማሳጠር ረገድም ወደር አልተገኘለትም።
እንደ ሀርቫርድ ሜዲካል ትምህርት ቤት ሪፖርት ከሆነ ደግሞ ስር የሰደደ ጭንቀት ‹‹ቴሎሚርስ›› የተሰኙትንና በእያንዳንዱ ሴሎቻችን ውስጥ የሚገኙ የዲ ኤን ኤ መዋቅሮችን ዕድሜ እንደሚቀንስም ያሳያል። የሴሎሜትር ዕድሜ ባጠረ ቁጥር ደግሞ ሴሎቻችን እየሞቱ ይሄዳሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሴሎሜትር እጥረት ያለባቸው ሰዎች ለከፋ የልብና የካንሰር በሽታዎችም ጭምር ይጋለጣሉ።
2ኛ፡- ቀይ ስጋን በተደጋጋሚ መመገብ
መቼም እኛ ኢትዮጵያውያን ከስጋ ጋር ያለን ቁርኝት የተለየ ነው። ለስጋ ያለን ፍቅርም የሚገርም ነው። በተለይ ደግሞ ለጥሬ ስጋ በቀዩም ሆነ በጮማው ቢቀርብልን እንክት አድርገን እንበላለን። እርስዎም ቢሆኑ ስጋ ወዳድ ሊሆኑ ይችላሉ።
ልንገርዎ አይደል! ሳይንቲስቶቹ ቀይ ስጋን አዘውትሮ መመገብ ለጤናዎ ጎጂ ነው ይልዎታል። በበርገር ውስጥ ዕለት በዕለት የሚመገቡት ቀይ ስጋም ዕድሜዎን በማሳጠር ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው ሲሉ ያስጠነቅቅዎታል። ይህ ሲባል ግን ስጋን ከነአካቴው አይመገቡ ማለት አይደለም። ይቀንሱ እንጂ።
ቢ ኤም ጄ በተሰኘውና በእንግሊዝ ሜዲካል ማህበር የሚታተመው የሜዲካል ትሬድ ጆርናል ላይ በታተመው ጥናት መሰረት ደግሞ ቀይ ስጋን በብዛት መመገብ ካንሰርን፣ የስኳር በሽታን እና የልብ በሽታን ከማስከትል በዘለለ በማንኛውም ምክንያት በስምንት የተለመዱ በሽታዎች የመሞት ዕድልን እንደሚጨምር አረጋግጧል።
ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 71 የሆኑ 537 ሺህ አዋቂዎች የጤና መረጃን በመተንተን በጣም ቀይ ስጋን የሚበሉ ሰዎች በትንሹ ከሚበሉት በ26 በመቶ የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል። ለዚህም በቀይ ስጋ ውስጥ የሚገኙ እንደ ‹‹ናይትሬት›› እና ‹‹ሄም›› የመሰሉ ንጥረ ነገሮች አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
ከዚህ በተቃራኒ እርስዎ የዶሮ ስጋና ዓሣን ጨምሮ ነጣ ያሉ ሥጋዎችን የሚመገቡ ከሆነ ቀይ ስጋን አዘውትረው ከሚመገቡ ሰዎች የመሞት ዕድልዎ እጅግ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ሳይንቲስቶቹ ይመክርዎታል።
3ኛ፡- የፀሐይ መነፅርን አለማድረግ
ለእርስዎ የፀሐይ መነፀርን ማድረግ እንደቅንጦት ወይም መዘነጫ መስሎ ሊታይዎት ይችላል። ለሌሎች ደግሞ የፀሐይ መነፅርን ማድረግ ከቆዳ ካንሰር ራስን ለመከላከል መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ነገር ግን የፀሐይ መነፅር ማድረግ ወጣትም ጭምር ያስመስልዎታል።
እንደ ሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ደግሞ የፀሐይ መከላከያ መነፅሮችን አለመጠቀም ከጊዜ በኋላ ለአልታራ ቫይዮሌት ጨረር በማጋለጥ ቆዳዎን ሊጎዳ ይችላል። በፀሐይ ጨረር መጋለጥ ምክንያት ደግሞ ቆዳዎ የፊትዎና የዓይንዎ አካባቢ ቆዳ ሊያስረጅ ይችላል። ይህን ችግር ለማስወገድ የጤና ባለሞያዎች ለዓይንና ዓይን አካባቢ ያሉ ቆዳዎችን ሊከላከሉ የሚችሉ ሰፋ ያሉ የፀሐይ መከላከያ መነፅሮችን ሰዎች እንዲያደርጉ ይመክራሉ።
4ኛ፡- ከልክ ያለፈ አልኮል መጠጣት
ከልክ ያለፈ አልኮል አዘውትረው ይጠጣሉ? እንግዲያውስ ዕድሜዎን እያሳጠሩ እንደሆነ አይዘንጉ። መጠጥን መጎንጨት ሲጀምሩ ስሜትዎ እየተነቃቃ ሄዶ ወደ ወጣትነት ዘመንዎ የመመለስ ስሜት ውስጥ የገቡ ሊመስልዎ ይችላል። ሀቁ ግን ዕድሜዎን እያሳጠሩ አልያም ራስዎን እያስረጁ ነው።
አልኮልን አንዴ ሲጠቀሙ ቆዳውን ያደርቃል ያቃጥላልም። ይህም የፊት መፋቅ፣ እብጠት እና የደም ሥሮች መሰበርን ያስከትላል። ይህ ሁሉ ተዳምሮም በዕድሜ ከፍ ያሉ ወይም ያረጁ ያስመስልዎታል። በመሆኑም ቶሎ ማርጀት ካልፈለጉ ከአልኮል መጠጥ ጋር ያለዎትን ውል አሁኑኑ ያቋርጡ።
5ኛ፡- ስኳርን አብዝቶ መጠቀም
ስኳርን በሚመገቡት ምግብም ሆነ በሚጠቀሟቸው መጠጦች ውስጥ አብዝቶ መጠቀም ምንም ጥያቄ የለውም ቶሎ ያስረጅዎታል። ሰውነትዎ በተፈጥሮው ስኳር ያመነጫል። ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ስኳርን ከምግብና መጠጦች ውስጥ በተጨማሪነት ያገኛሉ። ይህ ሲባል ግን የስኳር ምንጩ ከተፈጥሮ ምግቦችና መጠጦች እንጂ በፋብሪካ ተቀነባበረው ከተዘጋጁት ውስጥ መሆን የለበትም።
ስለሆነም የስኳር ይዘት ያላቸውንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችንና መጠጦችን ካስወገዱ ጤናማ ክብደትና በልብና በስኳር በሽታ የመያዝ አነስተኛ ዕድል ይኖርዎታል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ጤናማ ሆነው እንዲቆዩና በቶሎ የማርጀት ዕድልዎንም እንዲቀንሱ ያስችልዎታል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014