ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የገጠማትንና ሳትወድ በግድ የገባችበትን ጦርነት ህግ በማስከበር ለመቋጨት ብዙ ርቀቶችን ተጉዛለች። ወደ ጦርነቱ ከመግባቷ በፊት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንዲነጋገርና ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆን የተለያየ ጥረት ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ባህልና ወግ መሠረትም በቡድኑና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን ችግር በሽምግልና ለመፍታት በኃይማኖት አባቶች፣በሀገርሽማግሌዎችና ተሰሚነት ባላቸው አካላት ተሞክሯል። እናቶችም እንባቸውን እያፈሰሱ ተንበርክከው የቡድኑን መሪዎች ተማጽነዋል። የቡድኑ መሪዎች ግን የሚራራ ልብ አልነበራቸውም። ይልቁንም ጭካኔያቸውን በማጠናከር አሻፈረኝ ብለው የትግራይን ህዝብ ባልተገባ መንገድ በመቀስቀስ ከወንድሙ ጋር ደም እንዲፋሰስና በቁርሾ ጥላቻ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል።
“ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንወርዳለን“ በሚል ፍጹም አጋንታዊ በሆነ አስተሳሰብ ከውጪ ጠላቶች ጋር በማበር ለእኩይ አላማው ሌት ተቀን እየተጋ ነው በበሬ ወለደ የሐሰት ፕሮፓጋንዳም የአለምን ህዝብ ለማሳሳት እየሰራ ነው።
ለትግራይ ህዝብ ሞትና ስደት ፤መከራና ስቃይ የማይገደው ይህ አሸባሪ ቡድን፤ ዛሬም የትግራይን ህዝብ ላልተገባ ስቃይና መከራ ዳርጓል።በአመት አንድ ጊዜ ዝናብ ጠብቆ በማምረት ላይ የተመሰረተውን የግብርና እንቅስቃሴ በማደናቀፍ ህዝቡን ለችግር ዳርጓል፣
የክልሉ ህዝብ የግብርና ስራውን ትቶ ከወገኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያልተገባ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የመላው ህዝባችንን -የልማትና የሰላም ጥሪ ጥሶ የንፁሐንን ደም ማፍሰስንና ዜጎችን ማፈናቀሉን ቀጥሎበታል።
ቡድኑ እራሳቸውን በትምህርት አሻሽለው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ ብሎም ለሀገር ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል ለጦርነት በመማገድ ተስፋቸውን አጨልሞታል።
አማራጭ ያጣው የትግራይ ህዝብምአፈር ገፍቶና ደክሞ ነገ ብወድቅ ያነሳኛል፣ብቸገር ከጎኔ ይቆማል ብሎ ያሳደገውንና ያስተማረውን ልጁን ለሞት ለመገበር ተገዷል። በዚህ ቡድን አሸባሪነት የተነሳም አቅመ ደካሞች ቤታቸው ማረፍ አልቻሉም። አዲስ የዘመን መለወጫና የተለያዩ ክብረበዓላትንም እንደቀደመው ጊዜ በቤታቸው ውስጥ ሊያጣጥሙ አልቻሉም።
ቡድኑ ቤቴ ጎጆዬ የሚሉት አሳጥቷቸው ከፍ ባለ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ሰርተው መብላት እየቻሉ ምጽዋት ጠባቂ አድርጓቸዋል። ምጽዋቱም በአግባቡ እንዳይደርሳቸው እንቅፋቶችን በመፍጠር ጉሮሮአቸው ላይ ቆሟል።
ይህ አሸባሪ ቡድን በሥልጣን ላይ በቆየባቸው 27 አመታት ከምዕራቡ ዓለም ጋር በፈጠረው መርህ አልባና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ተግባሩ የምእራቡ አለም ወገንተኝነት የፈጠረለት ሲሆን ይህም የልብ ልብ ሆኖታል።በጥፋት ላይ ጥፋት እንዲያስብና እንዲፈጽም እያደረገውም ይገኛል።
የምእራቡ አለም የቡድኑን ጩኸት በማስተጋባት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ከማሳደር ባለፈ፤ የቡድኑን ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማ በመደገፍ ታሪክ ሊረሳው የማይችል ጥፋት እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው አካል ጋር መንግሥት እንዲደራደር ከመጠየቅ ባለፈ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን እየወተወተ ይገኛል።ይህንን ማድረግ ካልቻለ ብዙ የማእቀብ ማስፈራሪያዎችንም በየቀኑ እያወጣ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወገኖች በላይ ሊያስብለት የሚችል እንደማይኖር በማሰብ የትግራይ ህዝብ የመኸሩ የግብርና ጊዜ እንዳያልፍበት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ አጋርነቱን አሳይቷል።ይህ በሆነበት ሁኔታ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥትን ታጋሽነትና ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪነት ከቁብ ሳይቆጥር በጥፋተኝነት በመፈረጅ ይባስ ብሎ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል፣አጥፊውን የሚያበረታታ እርምጃ እየወሰደ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪው ህወሓት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም አንዳንድ መንግሥታትና ከእርሱ ጋር ቅርበት ያላቸው ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነታ አጣመው በማቅረብ በሀገሪቱ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ በጭፍን አይን ያወጣ እርምጃ መውሰዳቸው ትዝብት ላይ እየጣላቸው ነው።
እውነታው ለወትሮ ዴሞክራሲ ያደገባቸው እየተባሉ ተሞክሮአቸው እየተቀመረ እኛ አፍሪካውያን ልምድ እንድንቀስምበት ይደረግ የነበሩ ሀገራት የዴሞክራሲ ጥግ እስከምንድረስ ነው ተብሎ እንዲፈተሸ እድል ሰጥቷል። ዴሞክራሲያቸው የእነርሱን ጥቅም የሚያስጠብቅና ጉልበታቸውንም የሚያሳዩበት እንደሆነ በተጨባጭ ማየት አስችሏል።
እነዚህ በዴሞክራሲ አደጉ የሚባሉት፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተደርገውም ይታዩ የነበሩት የምእራቡ ሀገራት የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ዋነኛ መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነም ማረጋገጥ ተችሏል። በሰብአዊ ድጋፍ ስም የሚያደርጉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት በየትኛውም መመዘኛ ፍትሐዊና ሚዛናዊ አለመሆናቸውን ያመላከተ ነው።
የምእራቡ አለም በተለይም አሜሪካ ለሰላም እጆቹን ዘርግቶ፤ ከጅምሩ ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ብዙ መንገድ የተጓዘውን ፣ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጃ ጦሩን ከጦርነት ቀጣና በማስወጣት ለሰላም ያለውን ብርቱ ፍላጎት በተጨባጭ ካሳየው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን ከመቆም ይልቅ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ለአሸባሪው ህወሓት ህይወት ለመስጠት በብርቱ እየሰራ ነው።
በርግጥ ምእራቡ አለም በተለይም አሜሪካ በመንግስት ላይ የተለያዩ ማእቀቦችን ከመጣል አንስቶ በአለም አቀፍ መድረኮች ጫና ለማሳረፍ እየሄደችበት ያለው ያልተገባ መንገድ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ በአሜሪካ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል፤የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪ ብሎ በምክር ቤቱ የፈረጀውን ቡድን ለመታደግ የአሜሪካ መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ለሽብርተኛነት ያለው ትርጓሜ ጉራማይሌ እንደሆነ ለመታዘብ አስችሏቸዋል።
ሰላማዊት ከአራት ኪሎ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም