በ“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብሂል የሚጓዘው አሸባሪው ህወሓት፤ እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ፣ እኔ ያልገዛሁት ህዝብ መኖርና መበልጸግ አይገባውም በሚል ትዕቢት ወደቀደመ የሽፍትነት እና የገዳይነት ምግባሩ ከገባ ሰነባብቷል። ይህ ቡድን እንደፈለገ ማድረግ በሚችልበት የ27 ዓመታት የስልጣን ጉዞው፤ የተዳከመች ኢትዮጵያንና እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑ ኢትዮጵያውያንን ለመፍጠር በስፋት ሰርቷል። እቅዱ ባይሳካለትም በህዝቦች መካከል እርስ በእርስ የመጠራጠርና የመከፋፈል ሴራን ሲጎነጉን እና ሲያስፈጽም ኖሯል።
ሆኖም ኢትዮጵያውያን የበዛ ማንነት ቢኖራቸውም አንድ ስነልቡና ያላቸው የአንድ አገር ልጆች ናቸው እና የዚህ ቡድን ግፍና በደል በዝቶባቸው ባስነሱት ማዕበል ቡድኑ በህዝብ ተገፍቶ ስልጣኑን ካጣ በኋላ፤ ለምዱን አውልቆ በግልጽ ማንነቱ ተከስቷል። ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት እና ለራሱ የሚሆን አገር ለመፍጠር እንዲችል የአገርና ህዝብ የሉዓላዊነት አጥር በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ተደቁሷል።
ይሄን አምኖ መቀበል የሞት ሞት የሆነበት ይህ የሽብር ቡድን ታዲያ፤ ህልውናውን ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ቀን ከሌት ከሚተጉለት ምዕራባውያን በተጓዳኝ ወደመሃል አገር ዘልቆ ለጉዳይ አስፈጻሚነት የሚጠቀምበት እና የሚጋልበው ፈረስ አስፈለገው። ለዚህ ደግሞ ቀላል ሆኖ ያገኘው ቀድሞውንም የሚያውቀውና የእሱው ስሪት የሆነውን አሸባሪውን ሸኔ መልሶ የእርሱ አገልጋይ ማድረግ ነበር። እናም ሁለቱ አሸባሪዎች ዳግም ለሽብርና ለጥፋት ተልዕኮ በጋራ ጋብቻ መፈጸማቸውን አሳውቀው መንቀሳቀስ ጀመሩ።
በዚህም አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች በኩል ወረራ በመፈጸም አገር የማፍረስ ተግባሩን በንጹሃን ላይ በሚፈጽመው ጭፍጨፋ እና በሚያደርሳቸው ውድመቶች እያረጋገጠ ሲሆን፤ ተላላኪው ሸኔ በበኩሉ ኦሮሚያ ክልልን ማዕከል አድርጎ በንጹሃን ላይ ያልተቆጠበ ግድያና ጭፍጨፋ በማድረስ የሽብር አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል።
ለዚህ ትልቁ ማሳያ ደግሞ ከሰሞኑ አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ማጥቃት በጀመረበት ወቅት፤ አሸባሪው ሸኔ በወለጋ ንጹሃንን የመጨፍጨፍ፤ በሰሜን ሸዋ ደግሞ ንብረት የማቃጠል ተግባራት ላይ መሰማራቱ ነው። ይህ የተቀናጀ አካሄድ ደግሞ ዋናውና ትልቁ ዓላማ ኢትዮጵያን የማፍረስ እና ኢትዮጵያውያንን መበታተን ነው። ይህ ድርጊት የእነዚህ ጸረ ህዝብ የሽብር ቡድኖች ህልማቸውን ለማሳካት የአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦችን ቀድሞ የማጋጨት እና የመነጣጠል አካሄድን የተከተሉ ስለመሆኑ በግልጽ ያሳየ ሆኗል።
የአሸባሪ ቡድኖቹ ይሄን አይነቱ የጥፋት የተልዕኮ ሰጪነትና ተቀባይነት (የአዛዥና ታዛዥ) ጉዞ አሁን ላይ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭትን ለመፍጠር ታልሞ በአንድ ክልል ውስጥ እና ክልል ዘለል ጥቃት መፈጸምን የትኩረት መበተኛ አቋራጭ መንገድ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛል። ለዚህ ደግሞ የወለጋው የንጹሃን ጭፍጨፋ እና የማጀቴው በጤፍ ሰብል ላይ በአሸባሪው ሸኔ አባላት የተፈጸመው የእሳት ቃጠሎ ተግባር አብይ ማሳያዎች ናቸው።
ይህ ቡድን ቀደም ሲልም በኦሮሚያ ክልል ሲፈጽማቸው ከነበሩ የሽብር ተግባራት ባለፈ፤ ከአሸባሪው ህወሓት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የህልም እንጀራውን ለማሳካት ሲል በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታ እና ግድም፣ በአጣዬ እና ከሚሴ አካባቢዎች የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ በርካቶችን እንዲፈናቀሉ እና ሃብት ንብረታቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ቤተ እምነቶች አቃጥሏል፤ በማሳ ላይ ያሉ ሰብሎችንም አውድሟል።
ዛሬም በዚህ መልኩ በማጀቴ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ባለ ሰብል እሳት በመለኮስ የጀመረው ይህ የጥፋት ተልዕኮ ከወዲሁ በንቃት ተይዞ መፍትሄ ካላገኘ እንደ ትናንቱ ወደ አጣዬ እና ከሚሴ ሊራመድ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። ምክንያቱም አዛዡ ህወሓት በራሱ ግንባር የሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል በዚህ በኩል በታዛዡ ሸኔ በኩል ድጋፍ እንዲሰጠው እና የመንግስትንም የህዝብንም የትኩረት አቅጣጫ እንዲያስቀይርለት ቀጭን ትዕዛዝ ተቀብሏልና ነው።
ከዚህ አኳያ የአሸባሪዎቹ የጥፋት ጥምረትና ተልዕኮ ትናንት የነበረ፤ ዛሬም ያለ እና ህብረተሰቡ፣ የየአካባቢው አስተዳደር እንዲሁም የጸጥታ ኃይሉ በንቃት ካልጠበቀው ነገም ሊቀጥል እንደሚችል ሊታሰብና ቀደም ብሎ ሊከሽፍ ይገባል። ስለሆነም የአሸባሪዎቹን ህወሓት እና ሸኔ የጥፋት ተግባራት መንግስትም የየአካባቢው ማህበረሰብም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት ይገባቸዋል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም