በአዲስ አበባ ከተማ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን ከሚንከባከቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል እንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ ላለፉት ሀያ ሶስት አመታት ይህን አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ በርካታ አረጋውያንን ሲታደግ ቆይቷል። ለዛሬ የሀገርኛ አምዳችን የድርጅቱን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰናይት ድንቁን በማነጋገር የማህበሩን እንቅስቃሴ ከመነሻው አንስቶ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።
እንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር የተመሰረተው በአስራ ዘጠኝ ዘጠና አመተ ምህርት ወይዘሮ ንጋቷ አስፋው በሚባሉ አንዲት በጎ አድራጊ እናት ነው። ወይዘሮ ንጋቷ በወቅቱ ቤተክርስቲያን ሲመላለሱ በርካታ አረጋውያን በቤተክርስቲያን ደጃፍ ቁጭ ብለው ሲለምኑ ሲያዩ ውስጣቸው ይረበሽባቸው ነበር። ለራሳቸውም እነዚህ አረጋውያን በተለያየ መንገድ ለሀገር የሰሩ ለህዝብ ውለታ የዋሉ ናቸው በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖር የለባቸውም እያሉ ይነግሩ ነበር። አንዳች ነገር ፈጥረውም ባላቸው አቅም እጃቸውን ዘርግተው የሚለምኑ አረጋውያንን ለመታደግ ይወስናሉ። እናም እሳቸው ይሄዱበት ከነበረው ቤተክርስቲያን ምንም ረዳት ጧሪ ቀባሪ ያልነበራቸውን አስር አረጋውያንን በማንሳት በቤተሰቦቻቸው ግቢ መደገፍ ይጀምራሉ።
ወይዘሮ ንጋቷ አረጋውያኑ እስከመቼ ይቆያሉ የሚለውን ባይወስኑም እኔ እስካለሁ ያገኘሁትን እያቀመስኩ አሰነብታቸዋለሁ ብለው ነበር። ከእነዚህ አረጋውያን መካከል ደግሞ የእነሱን ከልመና የተገኘ ገንዘብ ጠብቀው የሚኖሩ የልጅ ልጆች ያሏቸውም ነበሩ። እናም ወይዘሮ ንጋቷ በቋሚነት ችግኝ እያፈሉ በመሸጥና ሌሎች የገንዘብ ማግኛ መንገዶችንም በመጠቀም አረጋውያኑን መንከባከቡን ስራቸው አድርገው ይቀጥሉታል።
ስራውን ከጀመሩ ከጥቂት ግዜያት በኋላ ደግሞ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የገንዘብ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ይበቃሉ። በወቅቱ ጥሩ ዝግጅት በመደረጉና ብዙ ሰው ታድሞም ስለነበር በተገኘው ገንዘብ ማህበሩ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጎ ለመመስረት ይበቃል። በዚህ ሁኔታ የጀመረውን ጉዞ በማስፋፋት እንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በአሁኑ ወቅት በተለያየ ፕሮግራም ለስምንት መቶ ሀያ አራት አረጋውያን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ድጋፎቹ የሚደረጉትም በማእከሉ አላማ መሰረት አረጋውያኑ አገልግሎቱን ሲያገኙ እርዳታ ብለው ሳይሆን ሰርቼ አገኘሁ የሚል መንፈስ እንዲፈጠርባቸው በማድረግ ነው። በዚህም መሰረት የሚሰሩት ስራ ለማህበሩ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ ባይኖረውም ሰርተው መደገፍ ስላለባቸው በጥጥ ፈተላ፤ በምስር ለቀማና፤ በመሳሰሉት እንዲሰማሩ ይደረጋል።
አረጋውያኑ የመንቀሳቀስና የመስራት አቅም እስካላቸው ድረስ አትክልት በመኮትኮትም ቢሆን እንዲሰሩ ይደረጋል። በዚህም አካሄድ እየተደገፉ ካሉት ስምንት መቶ አረጋውያን አራት መቶ ሃያውን ተቀጣሪ ደመወዝ ተከፋይ ማድረግ ተችሏል።
የሚሰጣቸው ክፍያ ግን ስራቸውን ታሳቢ ያደረገ ከሆነ ዝቅተኛ ሊሆን ስለሚችል የሚከፈላቸው የሰሩትን ሳይሆን የሚያስፈልጋቸውን ታሳቢ በማድረግ ነው። በመሆኑም እነዚህ አረጋውያን በየወሩ ለአንድ ሰው የሚያስፈልገው የምግብ ድጋፍ ስንዴ፤ ጤፍ ዘይትና ሌሎች ድጋፎችም ይደረጉላቸዋል። ከምግብ ቁሳቁስ ባለፈም የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና የመሳሰሉት ይቀርቡላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ «ሄልብ ኤይድ ኢንተርናሽናል» የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት በሚያደርገው ድጋፍ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙም አረጋውያን አሉ።
አቅማቸው ጠንከር ያሉትን ደግሞ ከመንግስት በተመቻቹ ቦታዎች ላይ እንጀራ መጋገር የዘመናዊ ከሰል ማምረትና ተመሳሳይ ስራዎችም እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል። ቀሪዎቹ ደግሞ በማእከሉ በጥበቃ በወጥ ቤትና በየቤታቸው በአልጋ ላይ የዋሉ አረጋውያንን የመንከባከብ ስራ ይሰራሉ። ምንም መስራት ለማይችሉት ከማእከሉ ሙሉ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በተደረገ ስምምነት ለሁሉም አረጋውያን ነጻ የሙሉ ህክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል። ህክምናው ሙሉ የመድሀኒት ወጪንና ተኝቶ መታከም ካስፈለጋቸውም የአልጋን ክፍያ የሚያካትት ነው።
የህክምናውን አገልግሎት ከአስር አመት በላይ ሲሰጥ የነበረው በጣሊያናውያን የተቋቋመ ቅዱስ ዮሴፍ የሚባል ድርጅት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ከመንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ድጋፉን ከጎዳና ለተነሱ ሰዎች በማዛወሩ ላለፈው አንድ አመት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ እየሰጣቸው ይገኛል። ቅዱስ ዮሴፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሚደግፋቸው ወቅት እስከ ሶስት ሺ ብር ድረስ በየትኛውም ሆስፒታል መታከም የሚችሉበት አሰራር ነበር። በሌላ በኩል ቀለል ላለና የእለት ህክምና በቅርብ ስለሚገኝ በራስ ደስታ ሆስፒታል አገልግሎቱ ማግኘት እንዲችሉም ስምምነት ተደርጓል። በተጨማሪ በጎ ፈቃደኛ የህክምና ባለሙያዎች ከኮሮና መከሰት በፊት በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን እየመጡ ምርምራ ያደርጉላቸዋል።
የጤና መድን ካርድ ያላቸውም በመኖራቸው ለእነዚህ ደግሞ ወርሃዊውን ሶስት መቶ ብር ክፍያ በጎ አድርጊ እየተፈለገ እንዲከፍልላቸው ይደረጋል። ይህም ሆኖ ከመንግስት ሆስፒታል መድሀኒት ካልተገኘ ማእከሉ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መድሀኒቶቹን እንዲያገኙ ያደርጋል።
በተጨማሪ ከወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን የስነ ልቦናና ተጓዳኝ ትምህርቶችም እየተሰጧቸው ይገኛል። ይህም ሆኖ አብዛኛዎቹ አረጋውያን ከእድሜ ጋር በተያያዘ የስኳር የደም ብዛትና የመርሳት ችግር ታማሚዎች ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ የዕለት ከዕለት ክትትልና ድጋፍ የሚሹ ከፍተኛ የጤና እክል ያለባቸው አረጋውያንም አሉ። እነዚህ አረጋውያን ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስና መጸዳዳት የማይችሉ ናቸው። ከአረጋውያኑ መካከል የልጅ ልጆቻቸው ሆነው የጤና እክል የእእምሮ ህመምን ጨምሮ ያለባቸው አሉ። እነዚህ በወቅቱ መድሀኒት መውሰድ አለባቸው የአካል ጉዳተኞችም አሉ። በእነዚህ አረጋውያን ቤት በመሄድ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር አብሮ የማሳለፍ ፕሮግራምም ይከናወናል።
ሁሉም አረጋውያን ሊባል በሚችል ደረጃ በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው የቤት ኪራይ ይከፈልላቸዋል። እንደየሁኔታው መጠነኛ የሆነ የቤት እድሳት ይደረግላቸዋል። ከተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች እየተሰበሰበ በአመት ሁለት ጊዜ የአልባሳት ድጋፍ ይቀርብላቸዋል። በአሁኑ ወቅት የምግቡን ድጋፍ እያደረገ ያለው ማዘር ትሬዛ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቦች እንደየአቅማቸው ከአንድ እስከ አምስት አረጋውያንን ስፖንሰር በማድረግ ወርሃዊ የምግብ ድጋፍ እያደረጉ ያሉም አሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአባላት መዋጩ የማህበሩ አንዱ የገቢ ማስገኛ መንገድ ነው። አባላቱ በወር አስር ብር በአመት አንድ መቶ ሀያ ብር ይከፍላሉ ይህ ዝቅተኛው ክፍያ ሲሆን አባላት የፈለጉትን ያህል መጨመር ይችላሉ።
ዛሬ ላይ በማቆያው የሚውሉት አረጋውያን ቁጥር ከአስር የማይዘል ሲሆን እነዚህም የሚመጡት በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን ብቻ ነው። ይህ የተደረገበት ምክንያትም ግቢው ጠባብ በመሆኑና ክፍሎቹም ትንንሽ በመሆናቸው የኮሮና ስርጭት ስጋት በመኖሩ ነው። በግቢው በሚውሉበት ግዜ የምግብ አቅርቦት የሚሟላላቸው ሲሆን አቅማቸው የበረታ ራሳቸው ልብሳቸውን እንዲያጥቡ ይደረጋል። ለሌሎቹም ክፍላቸው እንዲጸዳ ይደረጋል። ቀሪዎቹ ደግሞ እዛው ባሉ በጎ ፈቃደደኞች ልብሳቸው እንዲታጠብ ገላቸውን እንዲታጠቡ ጸጉራቸውን እንዲስተካከሉ ይደረጋል። በመዋያው እንደ ገበጣ፤ ዳማ ካርታና ቴሌቪዠን መመልከትና ሌሎች የግዜ ማሳለፊያ መጫወቻዎች ያሉ ሲሆን የቤተ መጻህፍት አገልግሎትም እንዲያገኙ ይደረጋል። በግቢው ራሳቸው የሚያዘጋጁት የሻይ ቡና ፕሮግራምም በመኖሩ አረጋውያኑ በመሰባሰብ ያሳለፉትን ህይወት በማንሳት እየተጨዋወቱ የቀን ውሏቸውን በደስታ ያሳልፋሉ።
በማእከሉ ያሉት ተቀጣሪ ሰራተኞች ቁጥሩ ትንሽ ሲሆን በአንጻሩ በርካታ በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች አሉ። በዚህ በኩል የአካባቢው ወጣቶች ተሳትፎ ትልቁን ደርሻ የያዘ ነው። በተለይ እንደ ፋሲካ ገና ላሉ በአላት ከአካባቢው ነዋሪ ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ድጋፍ በማድረግ አረጋውያኑ አውዳመቶችን ቤተሰብ እንደላቸው ሆነው እንዲያሳልፉ የሚያደርጉት እነዚሁ የአካባቢው ወጣቶች ናቸው።
እነዚህ በጎ አድራጊ ወጣቶች በተመሳሳይ ከአካባቢው ነዋሪ ለግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶችንና ገንዘብ በማሰባሰብ እነሱ በጉልበታቸው የአረጋውያኑን ቤት የማደስ ስራ ይሰራሉ። በተለይ በክረምት ዝናብ የሚያፈሱ ብርድ የሚያስገቡ ቤቶችን ማደስ የሁልጊዜ ትብብራቸው ነው። እንደ ተቋም ማእከሉ ለክርስቲያኖች የትንሳኤን በአል ለሙስሊሞች የረመዳንን በአል ታሳቢ በማድረግ በበአሉ ቀጣይ እሁድ ዝግጅት ይደረጋል። እንዲሁም ለሁሉም አረጋውያን እ.አ.አ ኦክቶበር አንድ የሚከበረውን የአለም አቀፉ የአረጋውያን ቀን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅቶች የሚደረጉ ሲሆን በአጠቃለይ ሶስት አመታዊ በአላት በማእከሉ በጋራ የሚከበሩ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በጎ አድራጊዎች ለበአል ምን እናድርግ ብለው የተጠየቁትን የሚያቀርቡ ሲሆን አንዳንዶች በሬ አርደው የቅርጫ ስጋ ያመጣሉ ሌሎች ደግሞ ዶሮ ዳቦና ሌሎች ለበአል ዝግጅቶች የሚውሉ ነገሮችንም በማምጣት አረጋውያኑን እየደገፉ ይገኛሉ።
በግቢው ውስጥ ለሴቶች አረጋውያን የፈትል ቤት የሚጫወቱበትና ቡና የሚያፈሉበት ክፍል የተዘጋጀላቸው ሲሆን ለወንዶቹም ሽመና የሚሰሩበትና የሚጨዋወቱበት እንዲሁም በበጎ ፈቃደኞች የተሰባበሰቡ መጻሀፍቶችን የሚያነቡበት ቤተ መጻህፍትም አለ። በተጨማሪ አንዳንዶቹ አረጋውያን ለሚያሳድጓቸው ልጆችና የልጅ ልጆች በበጋ ቅዳሜ ቅዳሜ በክረምት ደግሞ በሳምንት ሶስት ቀን የማጠናከሪያ ትምህርት በበጎ ፈቃደኞች ይሰጣል። በተጨማሪ ለእነዚህ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስን ጨምሮ ድጋፍ ይደረጋል። አብዛኛዎቹ ልጆች የሚማሩት በመንግስት ትምህርት ቤቶች በመሆኑና በአሁኑ ወቅት መንግስት የደንብ ልብስም ሆነ የምግብ አገልግሎት እያቀረበ በመሆኑ ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት በዚህ ረገድ የሚደረገው ድጋፍ ደብተርና እስክርቢቶ ሲያልቅባቸው የመተካት ብቻ ነው።
ይህም ሆኖ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ድጋፍ እየተገኘም በግቢው መጥበብ ምክንያት የማይሰሩ ነገሮች አሉ። ቦታ ቢገኝ ማእከሉ በርካታ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅቱን አጠናቋል። አሁን ያለውን የሽመና ስራ የባልትና ውጤቶች በማምረት አጠናክሮ ለመቀጠል እቅድ አለው። በአሁኑ ወቅት አያት በሚል ስያሜ እያመረተ ያለው የባልትና ውጤት በአረጋውያኑ አዘጋጅነት ለሱፐር ማርኬቶች ለሱቆች እየተከፋፈለ ይገኛል። ካቶሊክ ገብርኤል የሚባለው አካባቢ መንግስት በሰጠው ሼድ ማእከሉ መነሻ ጥሪት በመስጠት አረጋውያኑ እንጀራ እየጋገሩ በመስራት እንዲተዳደሩ አድርጓል። በዚህም የባልትና ውጤቶቹ በተለይ እንጀራና ዳቦ ለሶስት አመታት ያህል ለራስ ደስታ ሆስፒታል በጨረታ አሸንፈው ሲያቀርቡም ነበር።
በአሁኑ ወቅት የማህበሩ መስራች ወይዘሮ ንጋት ድጋፍና ክትትላቸው ባይቋረጥም ኑሯቸውን በእንግሊዝ አገር አድርገዋል። ማእከሉም እየተዳዳረ ያለው ከስድስተኛ ክፍል ጀምረው በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግሉ በነበሩት የአሁኗ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰናይት ድንቁ ነው። ለአረጋውያኑ ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም አንዳንዶቹ ድጋፎች የሚደረጉት በፕሮጀክት ለተወሰኑ አመታት በመሆኑ ሲቋረጡ አረጋውያኑ ለችግር እንዳይዳረጉ ዘላቂ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም ለመክፈት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ በቅርቡ በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የብሎኬት ማምረት ስራ የሚጀመር ይሆናል። ለዚህም ኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ሁለት ትልልቅ የብሎኬት ማምረቻ ማሽኖችን የለገሰ ሲሆን ከመንግስት በኩል የማምረቻ ቦታ እንዲመቻች እየተሰራም ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት ከአረጋውያኑ ባለፈ ለወጣቶችም የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችልም ነው። በተጨማሪ የገቢ ማስገኛና የአረጋውያን መዋያ እንዲሁም ስራ መስሪያ ህንጻ ለማስገንባት እቅድ የተያዘ ሲሆን ቦታ ከተገኘ በፍጥነት ወደስራ የሚገባበት እድል መኖሩንም ዋና ስራ አስኪያጇ ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም