ሀገራችን ኢትዮጵያ የስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ተከትሎ አዲስ መንግሥት መስርታለች። የመንግሥት ምስረታው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ መሆኑ ደግሞ ታሪካዊ ያደርገዋል። ይህ ብቻ አይደለም በሕዝብ አብላጫ ድምጽ ያሸነፈው ፓርቲ ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብን በብቃትና በታማኝነት ለማገልገል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እራሱን ያዘጋጀበት መሆኑም ሌላው አዲሱ ገጽታው ነው።
ሕዝብ ይሆነኛል ይጠቅመኛል ያለውን ፓርቲ መርጦ ወደ ሥልጣን ሲያመጣ በምክንያት እና በተስፋ ነው። በመረጠው ፓርቲ በኩል ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት፤ ለዘመናት ያጣውን የመልማትና የመበልጸግ መሻቱ ምላሽ እንዲያገኝ ነው። ከዚህ የተነሳም መንግሥት በምርጫ የማሸነፉን ያህል በመራጩ ሕዝብ ልብ ውስጥ አሸናፊ ለመሆን ብዙ የቤት ሥራዎች አሉበት።
አዲስ የተመሰረተው መንግሥት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከትናንት እንዲያሻግር ብርቱ እምነት የተጣለበት ነው። የጀመረችውን የብልጽግ ጉዞ ወደሚጨበጥ ተስፋ የመቀየም ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሀገሪቱ እንደ ሀገር የመቀጠል ታሪካዊ ጉዞ የመምራት ታላቅ ኃላፊነት አለበት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሻቀበ የመጣውንና ነዋሪዎችን እያስመረረ ያለውን የኑሮ ውድነት በማስተካከል ለማህበረሰቡ ምቹ የገበያ ሥርዓትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከመንግሥት ምስረታው በፊትና በኋላ ከሕዝብ የተነሱ አንዳንድ አስተያየቶችን ለማዳመጥ ዕድሉ ነበረኝ። ከአስተያየቶቹ መካከል አብዛኞቹ አዲሱ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ካለፈው በበለጠ ሊተጋና ሊበረታ እንደሚገባ የሚናገሩ ናቸው። የጀመረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ጨርሶ ወደ ልማት እንዲመለስ የሚሹ ብዙዎች ናቸው። በዛው ልክ ወቅታዊውን የሀገራችንን የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት መፍትሄ እንዲያገኝለት አደራቸውን ያስተላለፉም በርካቶች ነበሩ።
የግለሰቦቹ አስተያየት እንዳለ ሆኖ እንደኔ እንደኔ አዲስ የተመሰረተው መንግሥት የኢትዮጵያውያንን ጥያቄ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚተጋበት ወቅት ነው እላለሁ። የሚጠብቁትም የቤት ሥራዎች ይህንኑ የሚፈልጉ እንደሆኑም ይሰማኛል። በሁሉም ዘርፍ የተጀመረውን ሀገራዊ መነቃቃት ከዳር ለማድረስ የተሻለ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል።
የከፍታ ጉዟችን የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ተግዳሮቶች በስኬት በአሸናፊነት መንፈስ ጀምረን እንድንጨርስ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት በትውልዱ ላይ የተዘራውን የጥላቻ አረም ነቅሎ በመጣል በምትኩ በሕዝቦቿ ፍቅር ላይ የተገነባች የበለጸገች ኢትዮጵያን የመፍጠርም ተስፋ ተጥሎበታል።
የአሜሪካንንና መሰል ሀገራትን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ጠንካራና አስተማማኝ የፖለቲካ ሥርዓት ከመገንባት በተጨማሪ በእውቀትና በልምድ የዳበሩ ስለ ሀገራቸውና ሕዝባቸው የሚከራከሩ አምባሳደሮችን በመሾም በማንኛውም ጉዳይ ላይ ትርፍ የምናመጣበት አሰራር እንደሚኖር ተስፋ ከሚያደርጉት ውስጥ ነኝ።
ለዘመናት በኋላ ቀርነቱ የሚታወቀውን ግብርና በማዘመን የአርሶ አደሮቻችንን ሕይወትና ምርታማነትን በመጨመር ማህበረሰቡ በትንሽ ወጪ ሕይወቱን መምራት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር የአዲሱ መንግሥት ቀጣይ እቅድ መሆን አለበት ብዬ እናገራለሁ። በፍርድ ቤቶችና በፍትህ መስጫ ተቋማት ላይ የሚያጋጥሙ ሕግና ሥርዓትን ያልተከተሉ አሰራሮችን የሚገመግምበትና እልባት የሚሰጥበት የሥራ ዘመን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ።
በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ወጪ የሚስተናገድበትን መንገድ መፍጠርና ከአቅም በላይ ለሆኑ ህክምናዎች ውጪ ሀገር ድረስ በመሄድ የሚጠፋውን ገንዘብ እዚሁ ሀገር ቤት ህክምናው የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሌላው የቤት ሥራው ነው እላለሁ።
የትምህርት ጥራትን በማምጣት ትውልዱ ለሀገርና ሕዝብ የሚሰራበትን አዲስ አሰራር መዘርጋት እንደ ሀገር የላቀ በረከት ያለው በመሆኑ አዲሱ መንግሥት ይሄን ጉዳይ ጊዜ ሰጥቶ ያየዋል ብዬ አስባለሁ። በሥራ ፈጠራ መስክ ላይም ከመቼውም ጊዜ በላቀ አዲሱ መንግሥት ለወጣቱ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ተስፋ ያለው ትውልድ ተስፋ ላላት ሀገር ያበረክታል ብዬ አምናለሁ። እንደ ክፍተት በሚታዩ ማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ።
በጀመርነው የለውጥና የተስፋ ጎዳና ላይ ሆነን የአዲሱን መንግሥት ወደ ሥራ መግባት የምንጠብቅ ብዙዎች ነን። ባለፈው የመንግሥት ሥርዓት ያጣናቸው ብዙ ነገሮች በአዲሱ መንግሥት የሥልጣን ዘመን እንዲመለሱልን የምንሻ ብዙዎች ነን። በዘርና በብሔር የቆሸሹ አዳፋ መልኮቻችን በኢትዮጵያዊነት እንዲተኩና ወንድማማች ማህበረሰብ እንዲፈጠር የሁላችንም የጋራ መልዕክት ነው።
አንድ ሀገር አንድ ማህበረሰብ ለሀገር እድገት ያለውን አስተዋጽኦ እያንዳንዱ ዜጋ እንዲረዳና ለሀገሩ እንዲሰራ አዲሱ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ይተጋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ከሁሉ በላይ እንደ ዓይናችን ብሌን የምናየውን ታላቁን የአባይ ግድብ በተጠናከረና በላቀ የአመራር ክህሎት ፍጻሜውን ያሳየን ዘንድ እምነታችን የላቀ ነው።
ሁላችንም እንደምናውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ናት። ከፊታችን የበራና የወገገ ቀን አለ። በብዙ ኢትዮጵያውያን የተሳለ የትንሳኤ ዋዜማ ላይ ነን። በተለይ ያለፉት ሦስት ዓመታት ይሄን እውነት ያንጸባረቁ ከመሆናቸውም በላይ የለውጡ መንግሥት ለዚች ሀገር ምን ማለት እንደሆነ በደንብ ያየንባቸው ናቸው።
ቀጣዩ ጊዜም ኢትዮጵያን በመሳልና ኢትዮጵያዊነትን በመቀለም የተዋጣለት እንደሚሆን ቅንጣት ጥርጥር የለኝም። የዛሬ ደማቅ ብርሃኖቻችን በለውጡ መንግሥት የሰላ ብዕር የተሳሉ ነበሩ። የዛሬ ደማቅ ማለዳዎቻችን፣ ደማቅ ስኬቶቻችንና ደማቅ ተስፋዎቻችን የለውጡ መንግሥት የአመራር ጥበብ የፈጠራቸው ናቸው።
ለውጥ ያለትጋት ምንም ነው። ለውጥ ያለአንድነትና መተባበር ዋጋ የለውም። ለውጥ ያለው አስተሳሰብ ውስጥ ነው። አዲስ መንግሥት ስለመጣ፣ አዲስ ዓመት ስለደረሰ ለውጥ የለም። ለውጥ ማሰብ ነው። ለውጥ ትጋት ነው። ለውጥ ጊዜን፣ ኃይልንና፣ እውቀትን በአንድነት መጠቀም ነው።
እኛ ሀገር ቀደም ባለው ዘመን በለውጥ ስም የሆነው ይሄ አይደለም። የቀደመው የፖለቲካ ባህላችንና ከዚህ የመነጨው ታሪካችን ስክነት ያልታየበት፤ በጠራ እውቀት የተመራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በኃይል የተገዛ ነበር። እንዲህ መሆኑም ለዘመናት ዋጋ ሲያስከፍለን ኖሯል። ኃይል ውስጥ ስኬት የለም። ኃይል ውስጥ ህልም የለም። ዓለም ላይ ከትናንት እስከዛሬ የተከሰቱ ለውጦች ሁሉ ሀሳብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ሀሳብ ፍሬ የሚያፈራው በጊዜና በእውቀት ሲደራጅ ነው።
የትናንት ለውጦቻችን በለውጡ መንግሥት አነቃቂነትና አነሻሽነት የሆኑ ናቸው። ያለፉት ሦስት የስኬት ዓመታት በመንግሥት የአንድነትና የመደመር ፍልስፍና የመጡ ናቸው። ይሄ ዓለም ውብ የሆነው በሀሳብ ነው። ቀጣይ ለምትፈጠረው ሀገራችንም ሀሳብ ያስፈልገናል። እኛ ከመንግሥት መንግሥትም ከእኛ የሚወስደው በጎ ሀሳብ ያስፈልገናል። አብዛኞቹ ትናንታዊ መከራዎቻችን የከሸፉት በሀሳብ ማጣትና ባለመደማመጣችን ነው። ሀገራችንን በሀሳብ ካላዳንናት፣ ሀገራችንን በሀሳብ ካላሻገርናት በምንም አንታደጋትም። አሁን ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው ሀገራችን ሀሳብ ያስፈልገናል..አሸናፊ ሀሳብ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ተስፋዎች መሀል የበቀለች ግን ደግሞ እሾኮቿ የበዙ ጽጌሬዳ አበባ ናት። ሀገራችን ከእሾሁ መሀል ወጥታ ሰላሳና ስልሳ መቶም እንድታፈራ እኛ ልጆቿ አለንልሽ ልንላት ይገባል። አንዳንዶች ልክ እንደሾሁ በሀገራችን ተስፋና መነሳት ዙሪያ የበቀልን አረሞች ነን። አንዳንዶቻችን ደግሞ ተስፋዋን እውን ለማድረግ ከመከራዎቿ ጋር የምንፋለም ቀናና ታማኝ ልጆቿ ነን። አንዳንዶችም አሉ በምን አገባኝነት ስለሀገራቸው ግድ ሳይሰጣቸው ከዳር ቆመው የሚያዩ። እናንተስ ከየትኛው ወገን ናችሁ? በሀገራችሁ ተስፋ ዙሪያ የበቀላችሁ እሾክ ናችሁ ወይስ ከእሾኩ ጋር የምትፋለሙ ታማኝ ዜጎች? ምንም ልትሆኑ ትችላላችሁ ለሀገራችሁ የምትሰሩበት፣ ስለሀገራችሁ ድምጻችሁን የምታሰሙበት ትክክለኛው ሰዓት ላይ ናችሁ። እኔና እናንተ ነገ ለምትፈጠረው ሀገራችን፣ ነገ ለሚፈጠረው ትውልድ፣ ነገ ለሚፈጠረው ኢትዮጵያዊ ታሪክ ተዋናዮች ነን። ከአዲሱ መንግሥት ጎን በመቆም ተስፈኛዋን ሀገራችንን ወደ ፊት ማራመድ ይጠበቅብናል።
ካለእኔና እናንተ መንግሥት ብቻውን ኃይል የለውም። የመንግሥት ኃይሉ ሕዝብ ነው። ጥያቄዎቻችን መልስ የሚያገኙት መንግሥት ጥያቄዎቻችንን እንዲመልስ ስንሞግተውና አብረንው ስንሰራ ነው። እንደምናውቀው የመንግሥት ምስረታውን ተከትሎ ሕዝብ ከመንግሥት የሚጠብቀው ብዙ ነገር አለ እነዛ ሁሉ የሕዝብ ፍላጎቶች በመንግሥት ብቻ የሚሆኑ ሳይሆኑ መንግሥት ከሕዝብ ጎን፣ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚፈጸሙ ናቸው።
መንግሥት ለእያንዳንዳችን ሥራ፣ ለእያንዳንዳችን ቤት እንዲሰጠን ግዳጅ ያለበት የሚመስለን ብዙ ነን። አካባቢያችንን እንዲያጸዳልን፣ የሰፈራችንን ደህንነት እንዲጠብቅልን የምንሻ አለን። ለሁሉም ነገር እጃችንን አጣጥፈን መንግሥትን የምንጠብቅ ብዙ ነን። ሁሉም ቦታ የሆነ ሁሉንም በራሱ ሊያደርግ የሚችል መንግሥት ዓለም ላይ የለም። የመንግሥት መሰረት እኔና እናንተ ነን። እኔና እናንተ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን መንግሥት ነን።
መንግሥት የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የመጣው ከሕዝብ ነው። እርሱም መንግሥት ማለት ሕዝብ..ሕዝብ ማለት መንግሥት ነው የሚል ነው። ሀገራችንን ከድህነት የምናወጣው ለምንም ነገር መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ሳይሆን የዜግነት ግዴታችንንም በመወጣት ነው። ካለሕዝብ ተሳትፎ በመንግሥት ብቻ የበለጸገ ሀገር የለም ሊኖርም አይችልም። በእድገትና በሥልጣኔ ልቀው ልንደርስባቸው የሚያሮጡን ኃያላን ሀገራት የሕዝባቸውና የመንግሥታቸው የአንድነት ውጤቶች ናቸው።
ሀገር ጌጥ ናት..አልቦ አሸንክታብ። እንደ ሀገር ውብ ነገር የለም ..እርግጠኛ ነኝ እናተም በዚህ እውነት ትስማማላችሁ። ለሀገራችን እኛ ከበቂ በላይ ነን። ብዙ ወጣቶች፣ ብዙ የተማሩ ምሁራን አሉ፤ እያንዳንዳችን አንዳንድ ጠጠር ብናዋጣ ሀገራችንን ከፊት ማቆም ያቅተናል ብዬ አላስብም። አዲሱን የመንግሥት ምስረታ ታከው የተነሱ ጥያቄዎች በአንድነት በመቆም የሚመለሱ እንደሆነ ሁላችንም ልናውቅ ይገባል።
አብዛኞቻችን የሚሆነንን የፖለቲካ ፓርቲ መርጠናል። አብዛኞቻችን በአዲሱ መንግሥት በኩል ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ እንሻለን። ይሄ ያለና የሚኖር የሕዝብና የመንግሥት ትስስር ነው። ዋናውና ትልቁ ነገር ግን ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ ምን እያደረግን ነው የሚለው ነው? ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በአንድ ግለሰብ ወይም ደግሞ በአንድ ቡድን ብቻ የተሳለች ሀገር የለችም። ሁሉም ሀገራት የመንግሥታቸውና የሕዝባቸው አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው።
ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ ከመንግሥት ጋር አብረን መድከም፣ አብረን መልፋት ይኖርብናል። ካለእኔና እናንተ መንግሥት ብቻውን የሚመልሰው ጥያቄ የለውም። ካለእኔና እናንተ መንግሥት ብቻውን የሚፈጥረው ተዓምር የለም። የመንግሥት ግብዐቶች እኛ ነን። በሀሳባችን፣ በጥያቄዎቻችን ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለሀገራችንም ሆነ ለመንግሥት የለውጥ ግብዐት መሆን ይጠበቅብናል።
የአብዛኞቻችን ችግር እጃችንን አጣጥፈን መንግሥት ሥራ እንዲሰጠን መጠበቃችን ነው። የአብዛኞቻችን ችግር ሀገር መለወጥ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ እንደሆነ ማሰባችን ነው። ጥያቄ እየጠየቅን መልሱን ለመንግሥት ብቻ መተዋችን ነው። ለውጥ የጋራ ነው..በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ መንግሥት ብቻውን ያመጣው ለውጥ የለም። ለውጥ የመንግሥትና የሕዝብ ነው። በአስደናቂ ለውጥ የታጀቡት ያለፉት ሦስት ዓመታት እንኳን በመንግሥት መሪነት በሕዝብ ተሳትፎ የመጣ ነው።
አሁንም ቢሆን ጥያቄዎቻችንን ለመንግሥት መተው ብቻ ሳይሆን በጋራ በመቆም መመለስ ይጠበቅብናል። ጥያቄዎቻችን ሰላም ከሆነ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ያስፈልጉናል። ጥያቄዎቻችን ልማት ከሆነ መጀመሪያ ለልማት የሚተጋ አእምሮን ማዳበር ይኖርብናል። ጥያቄዎቻችን እድገት ከሆነ መጀመሪያ እጆቻችንን ለሥራ መዘርጋት ግድ ይለናል። ጥያቄዎቻችን በአዲሱ መንግሥት በኩል እውን እንዲሆኑ ከሁሉ በፊት እኛ የለውጡ አንድ አካል የመሆን ሚናችንን መጫወት ይኖርብናል እላለው። አበቃሁ..ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም