«ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሀብቶች አቧራ ለብሰውና ቋጥኝ ተጭኗቸው የሚገኙ በመሆናቸው አገራችንን ለመቀየር ሰማይ መቧጠጥ አይጠበቅብንም» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ ለተዋቀረው ካቢኔ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና በሰጡበት ጊዜ ነው።
በርግጥም ኢትዮጵያ የብዙ ሀብቶች ባለቤት ናት፤ የብዙ የከርሰ ምድር ገጸ በረከቶች፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሀብቶች ባለቤት ናት። ሀብቶቹ ከእርሷ አልፈው ለሌላው የሚተርፉ፣ አደግን ሰለጠንን በሚሉት አገሮች የማይገኙና እነሱንም አጀብ ጉድ የሚያሰኙ፤ ምነው የእኛ በሆኑና እንዲህ እንዲያ ባደረግናቸው ብለው የሚመኙአቸው ናቸው።
እንደ ሀገር የእነዚህ ሁሉ ሀብቶች ባለቤቶች ብንሆንም ለዘመናት በተጫነብን የስንፍና አርቆ ያለማሰብ ቀንበር እንዲሁም በየጊዜው የሚመጡ መሪዎቻችን በሚያሸክሙን ፖለቲካዊ አጀንዳ ምክንያት እርስ በእርሳችን ስንሻኮት በአግባቡ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል። እንኳን ልንበለጽግባቸው ስለመኖራቸው ሌሎች ሲነግሩን ነው የኖርነው።
ምንም እንኳን ይህ ሁኔታችን የሚያሳፍር አንገት የሚያስደፋ ለድህነታችን ቁንጮ ምክንያት ቢሆንም ፣ አሁንም አልረፈደም ተግተን ከሰራን ለውጥ እናመጣለን ብለን በአንድ ቃል ወደ ሥራ ከገባን እነዚህን አቧራ ለብሰውና ቋጥኝ ተጭኗቸው የተቀበሩ ሀብቶቻችንን ለልማት ለእድገት ልንጠቀምባቸው እንችላለን።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት «ኢትዮጵያን ለመለወጥ ሰማይ መቧጠጥ አይጠይቅም» ግን ደግሞ እጅና እግር አጣጥፎ በመቀመጥም የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። አእምሮን እና እጅን ለሥራ አዘጋጅቶ ፤ እኔም ለአገሬ የማግዛት ነገር አለኝ ብሎ መነሳት ይጠይቃል። በተለይም ደግሞ በቅርቡ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለሥልጣናት ይህን እውነታ አግባቡ ሊረዱት ይገባል። ለዚህ እውነት እራሳቸውን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎችንም ማብቃት ይጠበቅባቸዋል።
እኛም እንደ ሕዝብ ለዚህ አሻጋሪ እውቀት እራሳችንን ማስገዛት፤ ለአገራችን በአንድነት በመቆም ሀገር የምትበለጽገው በሥራና በሥራ ብቻ መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት፤ ለመማር ለማወቅ ተለውጦ ሌላውንም ለመለወጥ መትጋት ይጠበቅብናል። የሀገር ብልጽግና ጉዳይ የእከሌ ወይም የእከሊት ኃላፊነት ነው ከማለት ተላቀን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአገር ግንብታው ላይ የራሳችንን አሻራ ማስቀመጥ አለብን። በያገባኛል መንፈስ ጊዜ የለም በሚል ቅን ልቦና መስራት ይኖርብናል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአገሪቱ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስችል መልክ ተካሂዷል። በዚህም ኅብረተሰቡ ነገ ይመራኛል፣ ያስተዳድርኛል፣ መንገድ ያሳየኛል፣ ከስህተት ከጥቃት ይጠብቀኛል፣ አገሬን ለእኔና ለልጆቼ መኖሪያ እንድትመች አድርጎ ይገነባልኛል፤ ያለውን መርጦ ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት አባልነት ወክሎ ልኳል። ወኪሎቹም ከመስከረም አጋማሽ ጀምረው መንግሥት መስርተው ወደ ሥራ ገብተዋል።
በአሁኑ የመንግሥት ምስረታ አብላጫ የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ ቢሆንም ከተፎካካሪዎቹ ጋር አብሮ ለመስራት ቃል ገብቷል። በቃሉ መሠረትም ከክልል ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግሥት ኃላፊነት ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል።
በግሌ እነዚህ ተሿሚዎች ከቀደሙት ተሿሚዎች ሁሉ ለየት ባለ መልኩ የድርብርብ ኃላፊነቶች ባለቤት ናቸው ብዬ አስባለሁ፤ ለምን? ለምትሉ አገር ከዚህ በኋላ በእውቀትና በበሳል አመራር የምትመራበት ያላትንና የሌላትን ሀብት ለይታ አውቃ ወደ ሥራ የምታስገባበት ተሿሚውም ተመሪውም ከራሱ ብሔር ጎጥና መንደር ወጥቶ አንዲት ኢትዮጵያን አስቀድሞ የሚሰራበት ወቅት በመሆኑ ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ ከተሿሚዎች በትልቁ የምንጠብቀው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድም ያሉት ይህንኑ ነው «እናንተ ተሿሚዎች ለሀገራችሁ እንጂ ለመጣችሁበት ክልል ጥብቅና መቆም የለባችሁም» አዎ! ተሿሚዎች ለአገራችሁ ሽንጣችሁን ገትራችሁ መቆም ስትጀምሩ አገራችሁ ከእናንተ የምትጠብቀውን በቀላሉ ለማድረግ ከመቻላችሁም በላይ እርሷን ለማልማት ምናልባትም ሰማይ መቧጠጥ ላይጠበቅባችሁ ይችላል።
በርግጥም አዳዲሶቹ ተሿሚዎች ኢትዮጵያን ለመቀየር ሰማይ መቧጠጥ አይጠበቅባችሁም፤ አሻራ ለማስቀመጥም ሌላ ምንም ተዓምር አትፈጥሩም፤ ይህንን ሰሩ ተብላችሁ በትውልድ እንድትታሰቡ ሌላ ምንም ማድረግ ሳይሆን ከእናንተ የሚጠበቀው ትጋት፣ የዓላማ ዕናት፣ ታማኝነት፣ ሀቀኝነት ከሁሉም በላይ አገርን መውደድና ማስቀደም ነው። ይኸው ነው!
እናንተ በዓላማችሁ ስትጸኑ፣ ጽናትን ስትላበሱ፣ ጫናን መቋቋም ስትችሉ፣ ግፊት እና መከራ እንደሚያልፍ ስታስቡና በዛ መንፈስ ስትሰሩ የኢትዮጵያ ብልጽግና ቅርብ ይሆናል።
ኢትዮጵያችን አሁን ጨለማዋ ተገፎ ወደብርሃን እየገባች ነው፤ ይህም ቢሆን ግን በድህነቷ ላይ ተደምሮ ብዙ ቁልቁል ሊጎትታት የሚፈልግ ተግዳሮቶች አሉባት፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ተሻግራ ለልጆቿ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን እናንተ ተሿሚዎች ከመጠላለፍ ከመጠባበቅ ፖለቲካ ወጥታችሁ ልባችሁን ንጹህ አድርጋችሁ አፍና ተግባራችሁን አቀናጅታችሁ ሌት ተቀን ልትለፉላት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ልትሰሩላት ይገባል።
ይህንን ስታደርጉ ደግሞ መውደድም መጥላትም የሚያውቅበት ሕዝብ ባገለገላችሁት ልክ ሊያከብራችሁ፤ ስማችሁን ከራሱ ስም በላይ ከፍ አድርጎ ሊጠራ መሪ አድርጎ ሲመርጣችሁ በተጨባጭ አሳይቷል። እንደሚጠብቀው ካላገኛችሁ፤ እስከ ዛሬ እንደመጣበት መንገድ ኑሮውን አሳር ካደረጋችሁበት ያን ጊዜ በትውልድም በታሪክም የሚኖራችሁ ስፍራ የትና ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። ከዚህ ከታሪክና ከትውልድ ተጠያቂነት እራሳችሁን በሥራችሁ ጠብቁ። ሁላችሁም ሀገራችሁን ለማሳደግ ለመለወጥ አዋራ የቃሙትን ቋጥኝ ስር የተደበቁትን የእኛነታችንን አሻራዎች አውጥታችሁ ለመከበር የሚያበቃችሁን የራሳችሁን አሻራ አስቀምጡ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት 30 ዓመታት ባለፈባቸው የችግር ጊዜያት ምክንያት አሁን ላይ የሚያገለግሉትንና የሚገለገሉበትን ጠንቅቆ አውቋል፤ ባለሥልጣን ሥልጣን ሲይዝ ምን ማድረግ እንዳለበትም ተረድቷል፤ እናም አሁን ያለፈ አልፏል ነገር ግን ከዚህ ወዲህ ያላችሁ ባለሥልጣናት በሥልጣን ላይ መቀመጥ ሰው መሆንን የሚያስረሳ አለመሆኑ እንደውም ድርብ ኃላፊነት እንደሆነ በመረዳት ወደ ሥራ ግቡ። ሕዝባችሁንም ይህንን ልናደርግ ነውና አንተ በዚህ በኩል እርዳን በሉት ለዚህ ዝግጁነቱ ከፍ ያለ ነው።
መንግሥትም በገባኸው ቃል መሠረት ካንተ የምንጠብቀው ነገር አለ፤ ይህም ሹመኞችህን ልትመዝን የሚገባው በሰሩት ሥራ፣ በሀገር በወገን ላይ ባመጡት ተጨባጭ ለውጥ፣ የጎደፈውን የሀገራቸውን ታሪክ ባቃኑበት ልክ እንጂ ከዚህ ቀደም ባለፍንበት መንገድ ማለትም ባስፈጸሙት የፖለቲካ አጀንዳ ብዛት፣ በመለመሉት የአባል ቁጥር፣ አንዳንዴም ቁጭ ብድግ ባሉት መጠን ሊሆን አይገባም። ምናልባትም በዚህ መንገድ ለመቀጠል የሚያስብ ተሿሚም ካለ ከወዲሁ ራሱን ቢመረምር መልካም ነው ።
ከእናንተ የሚጠበቀው ከልዩነት በጸዳ ሁኔታ እጃችሁን ንጹህ አድርጋችሁ፣ በቅንነትና በፍጹም ታማኝነት ሀገራችሁንና ወገናችሁን አገልግሉ፤ ይህንን አድርጋችሁ ሀገራችን ከቆመችበት አንድ እርምጃ ከፍ ካለች ስማችሁ በታሪክ ውስጥ በደማቅ ሁኔታ ይጻፋል፤ ትውልድም ሲዘክረው ይኖራል። አበቃሁ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም