የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ያለው ሕዝብ ነው። በየትኛውም ዘመን በኢትዮጵያዊነቱ ተደራድሮ የማያውቅ፤ ወደ ፊትም በነጻ ህሊናው ሊደራደር የሚችል የማንነት ዝንፈት ውስጥ የሚገባ ሕዝብ አይደለም። በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ለዚህም ዋጋ የከፈለ፤ ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ የሆነ ነው።
የቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክም ይህንን እውነታ እንደሚያጸና አንድ ሁለት ብሎ በተጨባጭ ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል። በቀደሙት ዘመናት ስለ ሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ የጦር ሜዳ የጀግና ሞት የመረጡ እንደ አጼ ዮሐንስ ዓይነት ለሀገራቸው ቀናኢ ጀግና መሪዎችም የተገኙት ከዚህ ሕዝብ ነው።
ከቅርቡ የኢትዮጵያ ታሪክም በ1960ዎቹ በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት የኢህአፓ መስራች የሆነው ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይን ጨምሮ ብዛት ያላቸው የትግራይ ሕዝቦች በተለያዩ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በኢትዮጵያዊነታቸው ተማምነውና ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሰንቀው በጽናት ታግለዋል፤ ከፍያለ የሕይወት ዋጋም ከፍለዋል።
በዚህ ነባራዊ ሀገራዊ እውነታ ውስጥ የተከሰተው እና ገና ከፍጥረቱ ከታሪክና ከራሱ ጋር የተጣላው አሸባሪው ህወሓት፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን ይህንን በኢትዮጵያዊነቱ የሚታመን ሕዝብ ከፍጥረታዊ ማንነቱ በመነጠል የአዲስ ማንነት ባለቤት ለማድረግና ከወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ለመነጠል ብዙ መንገድ ተጉዟል።
ገና ከፍጥረቱ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ የሚነጥል ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የገባበት እውነታ ነበር። ይህ ድፍረቱ በኢትዮጵያዊነታቸው በማይደራደሩ በትግራይ ልጆች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ሊከሽፍ ችሏል። የአስተሳሰብ መሠረቱም ከቡድኑ መስራቾች የማንነት የሥነ ልቦና ቀውስ የመነጨ እንደሆነም በትግሉ ውስጥ የነበሩ ተጋዮች በተለያዩ ጊዜያት አንስተው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የቡድኑ መስራቾች በማኒፌስቷቸው አስፍረውት የነበረው የትግራይ ሕዝብን ማንነት የሚፈታተን ሀሳብ በወቅቱ በኢትዮጵያዊነታቸው በሚኮሩ የትግራይ ልጆች መስዋዕትነት ይምከን እንጂ፤ መስራች ግለሰቦች ከታሪክ ተምረው ከተዛነፈ አስተሳሰባቸው መመለስ ባለመቻላቸው አስተሳሰቡ ዛሬም ቢሆን የሀገራዊ ችግር ምንጭ መሆኑ አልቀረም። የትግራይ ሕዝብ ማንነት ላይ በጀመሩት መቆመር ነጋቸውን ለማደላደል ከማሴር አልተመለሱም።
የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና የተገነባ፤ ከማንም የማይበልጥና የማያንስ፤ ከሁሉም ጋር በወንድማማችነት መንፈስ በፍቅር ተከባብሮና ተቻችሎ የጋራ ዕጣፈንታውን የተሻለ ለማድረግ የሚተጋ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ የተለየ ዕጣ ፈንታ የሚኖረው አይደለም።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሥልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ዕጣ ፈንታው ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አልነበረም። የቡድኑ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ባልተገባ ሕይወት በሀገር ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓና አሜሪካ ሲፋንኑ፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ በሴፍቲኔትና ከዚህ ብዙ ባልተለየ እርዳታ ዓመታቱን በብዙ የሕይወት ፈተና ለመግፋት የተገደደ ነበር።
በበረሀ ትግሉ ወቅት ልጆቻቸውን የገበሩ እናቶች ከድል ማግስት ጀምሮ አስታዋሽ አጥተው ለጎዳና ሕይወት መዳረጋቸው፤ በትግሉ አካላቸውን የገበሩ በሕይወት መትረፋቸውን የሚረግሙበት፤ የሥልጣን ሽኩቻ በፈጠረው ግጭት የተለያዩ ተቀጽላ እየተሰጣቸው ለእስርና ለስደት መዳረጋቸው ለትግራይ ሕዝብ ዛሬ የሚነገረው እውነት አይደለም።
በትግሉ ወቅት ጎልተው ይሰሙ የነበሩት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ተጨፍልቀው እና አስተዋሽ አጥተው በሰማዕታቱ መቃብር ላይ ፍጹም አምባገነናዊ አገዛዝ መፈጠሩ፤ የትግራይ ሕዝብ ራሱ የዚህ አምባገነናዊ ቡድን ጭካኔ ሰለባ መሆኑን ይመሰክራል።
ይህ ያለፈ የቡድኑ ፍጥረታዊ ባህሪውም ሆነ ባህሪው በፈጠረው ቀውስ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በትግራይ ሕዝብ ስም መሽጎ እያደረገ ያለው የሽብር ተግባር ቡድኑ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ሕዝባዊ የሆነ አንዳች ባህሪ እንደሌለውና ለዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ መሠረት ባለቤት አለመሆኑን በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
ቡድኑ ሁሌም መልኩን እንደ እስስት እየቀያየረ በትግራይ ሕዝብ ተስፋ ከመቆመር የወጣበት ጊዜ የለም፤ ለህልውናው መቼም ቢሆን በትግራይ ሕዝብ ደም ከመነገድና ከዚህ በሚገኝ ትርፍ ህልውናውን ከማስቀጠል የሚመለስበት አማራጭ የለውም። ይህን አማራጭ እስከ መጨረሻው ለመሞከር የሚያስችል ሰብአዊነት የለውም።
ለትግራይ ሕዝብ አዲስ ማንነት ከመስጠት የጀመረው የቡድኑ የጥፋት ጉዞ፤ እንደ ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ህልውና ላይ እስከ መቆመር የደረሰና ሕዝብን ባልተገባ ትርክት የህልውና አደጋ ውስጥ በመጨመር በዚህ በሚፈጠር እልቂት እስከ መቆመር የደረሰ ሴራና ክፋት የተሞላ ነው። ለዚህም ነው ይህንን እውነታ የትግራይ ሕዝብ በአግባቡ ሊረዳውና ይህንን አጥፊ ኃይል በቃህ ሊለው የሚገባው ወቅት አሁን ነው የሚባለው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም