ሰው ግን ‹‹ለውጥ›› የሚለው ቃል ትርጉም አልገባውም ልበል? ለነገሩ የአንድ ቃል ትርጉም የሚታወቀው በገባበት ዓረፍተ ነገር ዓውድ ነው። ይልቅ ይሄንን ለቋንቋ ተመራማሪዎች እንተወውና ወደ ለውጣችን እንመለስማ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ወዲህ ‹‹ለውጥ›› የሚለው ቃል የብዙ ንግግሮች ማስጀመሪያ ሆኗል። ገና ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ‹‹መደመር›› የሚለው ቃል ነበር ፋሽን የሆነው። ምንም እንኳን አብሮ የመጣ ቢሆንም ‹‹ለውጥ›› የሚለው ቃል በኋላ እየሰፋ መጣ። ይሄ የሆነበት ምክንያት አለው። ለውጥ የሚታወቀው እየቆየ ሲሄድ በመሆኑ ነው።
ከግለሰቦች ጀምሮ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ ‹‹ከለውጡ በፊት›› እና ‹‹ከለውጡ በኋላ›› የሚል ድንበር ተበጅቷል። ወደው አይደለም! ብዙ ለውጥ ስላለ ነው። ባለሥልጣን ተለውጧል፣ የመገናኛ ብዙኃን ባህሪ ተለውጧል፣ ራሱ ሕዝቡም ተለውጧል (አንባቢ ሆይ አስተሳሰቡን ማለቴ እንደሆነ ይረዱልኝ)። አገሪቱስ? እሷም ተለውጣለች!
እንግዲህ ለውጥ በመኖሩ ተስማማን አይደል? አሁን ዋናው ጥያቄ ‹‹ለውጡ ምንድነው?›› የሚለው ነው።
በአንድ የመጽሐፍ ውይይት መድረክ ላይ ነው። ከአስተያየት ሰጪዎች አንደኛው ‹‹ከለውጡ ወዲህ›› ሲል አወያዩ አቋረጠውና ‹‹ለውጥ ግን አለ ብለህ ታምናለህ?›› ብሎ ጠየቀው። ይሄው የለውጥ ‹‹አለ›› ‹‹የለም›› ጉዳይም ትንሽ መወያያ ሆኖ ቆየ። ይሄን ነገር ያነሳሁት እዚያ የነበረውን ውይይት ለመግለጽ ሳይሆን ምሳሌ እንዲሆነኝ ነው። አወያዩ ለውጥ መኖሩ እንዴት እንዳልታየው ገርሞኝም ጭምር ነው። ይልቅ የለውጡን አይነት ነው መወያየት ያለብን እላለሁ።
ለውጥ አለ፤ ድብን አድርጎ ለውጥ አለ! ይሄንን ጉዳይ በስፋት የሚያስተጋቡት መገናኛ ብዙኃን ስለሆኑ ከመገናኛ ብዙኃን ነው የምጀምር። መገናኛ ብዙኃን ላይ ለውጥ አለ። ታዲያ ይሄን ነገሬን ያጠናክርልኝ ዘንድ አቶ ጃዋር መሐመድ በፋና ኤፍ ኤም 120 ደቂቃ ፕሮግራም ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት የተናገረውን ነገር መግለጽ ፈለግሁ።
‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ለውጥ እንዴት አየኸው?›› ስትል ጠየቀች ጋዜጠኛዋ። ጃዋርም መለሰ። ‹‹መለስ መለስ መለስ ይል የነበረ ቴሌቭዥን አብይ አብይ አብይ ነው ያለው፤ ይሄ ለእኔ ለውጥ አይደለም›› ነበር ያለው።
የለውጡ ነገር ጃዋር እንዳለው ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙኃን (በተለይም የመንግሥት) ከነበሩበት ነው የተገለበጡት። ይሄ ለውጥ ሊሆን ይችላል። ይሄንኑ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ምሳሌም ላንሳማ!
አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ነሐሴ 14 የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትም ልዩ ዕትም ነበር የሚሆነው። መጣ ከተባለው ለውጥ ወዲህ ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳን ልዩ ዕትም ሊሆን ስለአቶ መለስ ዜናዊ አንዲት መጣጥፍ እንኳን አልተጻፈም! ታዲያ ይሄ ነገር እንዴት ነው ጎበዝ? (ይሄንኑ ጋዜጣ እዚሁ ራሱ አምድ ላይ መተቸት ቻልኩ ማለት ነው? ለውጥማ አለ!)
ሁለት ነገር መጠርጠር ነው እንግዲህ!
አንድ፤ የዝግጅት ክፍሉ ኃላፊዎች ከመንግሥት በሚመጣ ትዕዛዝ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት ማለት ነው፤ አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ፤ እንዳታደርጉ የተባሉትን ደግሞ ይተዋሉ።
ሁለት፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ሙት ዓመት ማክበር አግባብ አለመሆኑን አምኗል ማለት ነው። በቃ እስከዛሬ ተሳስተናል፤ ከዚህ በኋላ መስተካከል አለብን፤ የአቶ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ሽፋን የሚያስፈልገው አይደለም ብሎ አምኗል ማለት ነው።
ሁለቱን መገናኛ ብዙኃን ምሳሌ የጠቀስኩት አንጋፋ ስለሆኑ ነው፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲባል ወደሰው አዕምሮ የሚመጡትም ሁለቱ ናቸው (በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ልብ አይባሉም)።
ሌላው የተለወጠው ደግሞ ሕዝቡ ነው(ኧረ እንዲያውም ዋናው ለውጥ)፤ በዚህ አጋጣሚ መገናኛ ብዙኃኑንም የለወጣቸው ሕዝቡ ነው። ‹‹መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነው›› ይባላል አይደል? ግን የአገራችንን መገናኛ ብዙኃን አይንና ጆሮ የደፈነው ራሱ ህዝቡ ነው! (መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን አመለካከት መቀየር አለበት እንደሚባል አውቃለሁ)
እስኪ የሕዝቡን ለውጥ እናስተውል!
የመገናኛ ብዙኃን አሁን እያደረጉ ካሉት ውጭ መዘገብ አይችሉም፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ይቆጣል። ጎበዝ አንዳንዴ እኮ ሕዝብም ትክክል ላይሆን ይችላል። አንድ ነገር ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚባለው ነገር ትክክል ነው። የሕዝብ ቁጣ የተነሳበት ነገር ሁሉ ሕዝብ ትክክል ነው ስለሚባል እንደ ስህተት አይታይም፤ በዚህም ብዙ ውድመት ደርሷል። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይን የሚተች ዘገባ ቢሰራ ከመንግሥት ይልቅ ሕዝቡ ይቆጣል። ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ ቢሰራ ‹‹ለውጡን ያልተቀበለ›› ተብሎ ዘመቻ ይደረግበታል፤ ለአብዛኛው ሕዝብ ለውጥ ማለት በአንድ ወገን ብቻ ያለው ሆኖበታል። ይሄን የሕዝብ ቁጣ በመፍራትም መገናኛ ብዙኃን ሕዝቡ የሚፈልገውን ብቻ ይሰራሉ ማለት ነው።
እንደግለሰብ እንኳን ነፃ ሀሳብ ማራመድ ላይቻል እኮ ነው! ከለውጡ በፊት መንግሥት ነበር የሚያስቸግረው፤ አሁን ደግሞ ሕዝቡ ነው እያስቸገረ ያለው። ከለውጡ በፊት የነበረው የሕዝቡ ወቀሳ ‹‹የሀሳብ ነፃነት ይከበር›› ነበር። አሁን ግን ህዝቡ የሀሳብ ነፃነት እያከበረ አይደለም። አንድ ሰው የተለየ ሀሳብ ሲናገር ‹‹ለውጡን ያልተቀበለ›› ተብሎ በደቦ ይዘመትበታል።
ለማንኛውም ለውጥ አለ!
አብሮ የመንጋጋቱ ነገር እንዳለ ሆኖ ግን የማይካድ ለውጥ አለ። በቀደመው ኢህአዴግና በዳግማዊው ኢህአዴግ የነበረው ሁኔታ የተለያየ ነው። ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንም ብዙ ብለውለታል። ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ሰላማዊ ወዳጅነት ቀላል ጉዳይ አይደለም። የአገራቸው አፈር የናፈቃቸው ወገኖች አገራቸው መግባት ቀላል ነገር አይደለም፤ ወጣቱ የሚያነበው ጋዜጣና መጽሔት መኖሩ ቀላል ነገር አይደለም። እንኳን ለአሳታሚውና ለመገናኛ ብዙኃኑ ባለቤቶች ለአንባቢም የሚያሳቅቅ ጊዜ ነበር።
ግና ይሄ ሁሉ ሲሆን አገሪቱ ውስጥ ያለው መፈናቀል ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም። ‹‹ከለውጡ ወዲህ!›› በተባለው ጊዜ ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የማይደረጉ ዘግናኝ ድርጊቶችን አይተናል(የለውጡ አካል ይሆኑ?) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር አንድነትን እየሰበኩ የዘውግ ፖለቲካ ሊያሸነፍ እየተገዳደረ ነው።
የለውጧን ነገር በሁለቱም እንየው። ጥሩ ለውጥ አለ፤ የደረሰ ጥፋትም አለ። መገናኛ ብዙኃን ተለውጠዋል፤ ግን የተለወጡት ወደገዥው ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ባለሥልጣንም ስለተለዋወጠ ‹‹ለውጥ›› አለ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 16/2011
በዋለልኝ አየለ