ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ከተመሰረቱባቸው ከፍ ያሉ ሰብአዊ እሴት አንጻር ከሁሉም በላይ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ። በሴቶች እና ህፃናት ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም አጥብቀው ይሠራሉ፤ ድምጻቸውን ከማሰማትም ወደኋላ አይሉም። ፍትህ ሲጓደል፤ በደል ሲፈጸም ቆመው መመልከት ምርጫቸውም አይደለም። ለማንም አይወግኑም፤ ገለልተኞች ናቸው። መስፈርታቸውም ሰብአዊነት ብቻ ነው።
ከተመሰረቱበት ዓለም አቀፍ መርህ በተቃራኒ የቆሙም አሉ ፤ በግብረ ሰናይ ድርጅት ወይም በእርዳታ ድርጅት ስም መቋቋማቸው በራሱ አሳፋሪ የሆኑ ፤ ለግለሰቦች ፣ ለቡድኖችና ለሀገራት ጥቅም እራሳቸውን ያስገዙና ለዚሁ የተሰጡ ናቸው። ምስጋና ለ‹ጊዜ› ይግባውና ዓላማቸውን እንድናይ፣ እንድንጠራጠር ብዙ እንድንመረምራቸው እድሉን ሰጥቶናል።
ምሳሌ እየጠቀስኩ ሃሳቤን ልሰንዝር። እንደሚታወቀው በሰሜኑ የአገራችን ክልል የተፈጠረውን ችግር ሁላችንም የምናውቀው ነው። ችግሩ እንዴት ተፈጠረ ፣ ለምን ተፈጠረ ወዘተ ለኛ ብዙ መመራመር የሚያስፈልገው የአደባባይ ሚስጥር ነው። እንደ አገር በገጠመን በዚህ ችግር አንዳንዶች ሊሳለቁብን ሞክረዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ያረጀ ያፈጀውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ለማስፈን ችግራችንን እንደ አንድ አድል ለመጠቀም ሲደክሙ አስተውለናል። ለዚህ ዓላማቸው ማስፈጸሚያም አሸባሪውን ህወሓት መሳሪያ አድርገው መርጠውታል። ለዚህም በዓለም አቀፍ የግብረ ሠናይ ድርጅት ሰራተኞች በኩል አሸባሪው ቡድን እንዲታገዝ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።
ለዚህ ማሳያ በተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ የሆኑት ቶማስ ቶምሰን ከጁንታው ከፍተኛ አመራሮች (ጌታቸው ረዳ) ጋር መታየታቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎችም በስፋት ሲንሸራሸር አይተናል። ቢቢሲም የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይን አናግሯል። በምን አጋጣሚ ጌታቸው ረዳ እና ቶማስ ቶምሰን የተገናኙት? ሲልም ጠይቋል። ቃል አቀባዩም ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን ዛሬ ላይ ስናስታውሰው ነገሮች ይበልጥ ፍንትው እና ጥርት ብለው ይታያሉ።
በትግራይ ህዝብ ስም የራሱን እና የውጭ አገር አለቆቹን ዓላማ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለቱን የተያያዘው አሸባሪው ህወሓት በእርዳታ ስም ከተቋቋሙ ከነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአገርን ጥቅም በሚጎዳ፤ ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ዓለም አቀፍ መርህ በሚጻረር መልኩ ድጋፍ እያገኘ ነው። ይህንኑ ተከትሎ መንግስት እንደመንግስት ካለበት ሃላፊነት አኳያ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገድዷል።
ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ተቀምጧል። ምክር ቤቱ ከህግም ሆነ ከሞራልም አንጻር አንዲት ሉአላዊትን አገር ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በወሰደቻቸው እርምጃዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ስብሰባዎች መጥራቱ በራሱ በብዙ አነጋጋሪ ቢሆንም ፣ እውነታው ግን ዓለም እየሄደችበት ያለውን መርህ አልባ መንገድ አመላካች ሆኗል።
አንዳንዶች ‹ምነው ምክር ቤቱ ሌላ ሥራ አጣ እንዴ ?› ለማለት ቢገደዱም እውነታው ግን የስራ ማጣት ሳይሆን ከመርህ የመውጣትና ይህንኑ ለማየትና ለመመለስ ፈቃደኝነት ከማጣት የመነጨ ነው። የሰሜኑ ግጭት ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምክር ቤቱ 10 ስብሰባዎችን አድርጓል። ስብሰባዎቹ በመርህ ደረጃ መደረግ ያልነበረባቸው ቢሆኑም በመደረጋቸው ግን ዓለም ወዴት እየሄደች ነው? ዓለም አቀፍ ተቋማትስ በዚህ መንገዳቸው መጨረሻቸው የት ይሆን እያስባለ ነው።
የምክር ቤቱ የሰሞኑ ስብሰባ አስቸኳይ ከመሆኑ በላይ የስብሰባው አጀንዳ በአልተገባ ተግባራቸው ከኢትዮጵያ ስለተባረሩት ሰባት የተመድ ሠራተኞቹ መሆኑ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ አድርጎታል። ሰራተኞቹ ምን ሲሰሩ ተገኙ የሚለውን ከማጣራትና የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የመንግስትን ውሳኔ ለማውገዝ መቸኮሉ ትዝብት ላይ ጥሎታል።
መንግስት ሠራተኞቹን ያባረረው በድርጅቱ በኩል የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ደጋግሞ ካሳሰበ በኋላ ነው። ውሳኔውን አንዳንዶች የዘገየ እና የመንግስት ቸልተኝነት የታየበት እንደሆነም ድምጻቸውን ከፍ አድገው ሲያሰሙ ነበር። የሆነው ሆኖ የመንግስት ውሳኔ በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ነው። ውሳኔውን ለመወሰንም ከበቂ በላይ ነው።
ግለሰቦቹ ለአሸባሪው ቡድን የግንኙነት መሳሪያዎች በማስተላለፉ፤ ሰብአዊ ድጋፍን ፖለቲካዊ በማድረግ ለቡድኑ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት፤ ከዚህም ባለፈ ሀገርና መንግስትን የሚያጠለሹ መረጃዎችን በመፍጠርና በማሰራጨት ተጠያቂ የሆኑ ናቸው።
ሠራተኞቹ ከአገር እንዲወጡ የተደረገው የሀገሪቱን ሉአላዊት የሚገዳደሩ ያልተገቡ ተግባራትን ጨምሮ ለብሔራዊ ደህነነት ስጋት የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በመገኘታቸው ነው። መንግስት ይህንን ማድረግ ካልቻለ ድንገትም የመንግስትነቱ መገለጫ ምን ሊሆን እንደሚችል አጠያያቂ ይሆናል። ከመዘግየቱ ውጪ ውሳኔው ተገቢ ስለመሆኑ ስለ መንግስት በቂ ግንዛቤ ላለው አካል ብዙም የሚቸግር አይሆንም።
የሠራተኞች መባረር ሰራተኞችን ቀጥሮ ሲያስተዳድር ለነበረው ዓለምአቀፉ ተቋም እራሱን እንዲያይ የሚያነቃው እንጂ ፤ብዙ የሚያስጮሀው እንደማይሆን ይታመናል። ተቋሙን መጠቀሚያ ማድረግ የሚፈልጉ ሀይሎችም መንገዳቸው አለም አቀፋዊ መርህን የሚያደበዝዝ ፤ከዛም በላይ የተቋማቱን ተአማኒነት የበለጠ አደጋ ውስጥ እንደሚከት ሊያስተውሉት ይገባል። ነገ ላይ በነዚህ ተቋማት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊከብዱ እንደሚችሉ ማሰብም ተገቢ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በሚፈበረኩ እውነታዎች የተንበርካኪ ስሜት የሌላት ፤ ጭቆናን የማትቀበል ፤በነጻነቷ የማትደራደር ፤ ትናንት ብዙ ጀግኖችን ያፈራች ዛሬም ብዙ ጀግኖች ያሏት አገር መሆኗን መረዳቱ ደግሞ ከስህተቶች ፈጥኖ ለመማር የተሻለ እድል የሚሰጥ ነው።
አሸባሪው ህወሓት የመጨረሻ ግብአተ መሬቱ እስኪፈጸም ሀገርና ህዝብን ዋጋ የሚያስከፍል የአልሞት ባይ ተጋዳይነት የደመነፍስ መወራጨት ማድረጉ የማይቀር ነው፤ ይጠበቃልም ። ለትግራይ ሕዝብ የተቆረቆረ በማስመሰል እርዳታ እንዳይደርስ ተከለከልን የሚለው ጩኸቱ ፤ የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በመጣስ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ወረራ ማካሄዱ የዚሁ እውነታ አካል ነው።
በአሸባሪው ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልል ትምህርት ቤቶችን ከጥቅም ውጪ ሲያደርግ ፤ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ሲያስቀር፤ ከአንድ ሺ 400 በላይ የጤና ተቋማት ሲወድሙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለምን ዝምታን መረጠ?
ህጻናትን ለጦርነት ሲመለምል ፤ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽም የመንግስታቱ ድርጅት መንግስት እየወቀሰ ባለበት ደረጃ ስለምን አሸባሪው ለማውገዝ አልደከመም? የአማራ እና የአፋር ክልሎች ህዝቦች በቡድኑ ጥቃት ለሞትና ለስደት ሲዳረጉ ሲደርስበት የመንግስታቱ ድርጅት ዝምታን የመረጠው ስላልሰማ ነው? በአገሪቱ ላይስ እርምጃ እንዲወሰድ ፤ማዕቀብ እንዲጣል መፈለጉ ጤነኛ ነው?
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2014