አዳዲሶች የካቢኔ አባላት የብሔር ተወካይ እንዳልሆኑ ፤ መሆንም እንደማይገባቸው ፤ ውክልናቸው የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማስገንዘባቸው ይታወሳል። የካቢኔ አባላት በአካባቢ መንፈስ ታጥረው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የምናስባትን የበለጸገች ኢትዮጵያ የመፍጠሩን ተግባር ሊገዳደሩት እንደሚችሉም አመልክተዋል ።
በርግጥ ባለሥልጣናት ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ሆነው ለአንድ ቡድን ሲሉ በአገር ሀብትና በዜጎች ላይ ሲያዙ በኖሩባት አገር ቀጣዮቹ ባለሥልጣናት መምሰል ያለባቸውን ከወዲሁ ማስገንዘብ አስፈላጊም ተገቢም ነው። እንደ የማንቂያ ደወል ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል።
በአሸባሪው ህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ሥልጣን ለተገቢው ዓላማ ባለመዋሉ የተፈጠረውን አይተናል፤ሰምተናል። አሸባሪው ትህነግ የአገርን ሀብት ለራሱና ለጥቅም ተጋሪዎቹ መበልጸጊያ አድርጎ በስፋት ተንቀሳቅሷል። በዚህም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ አገራዊ ሀብቱ የበይ ተመልካች ሆኖ ኖሯል።
ቡድኑ በመንግሥት ውስጥ መንግሥት ሆኖ ለሃያ ሰባት ዓመታት አገር ገዝቷል። በእነዚህ ዓመታትም በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአገር ሀብት ዘርፏል። በመንደርተኝነት መንፈስ የአገራዊ ሀብት ሽሚያ በትናንቷ ኢትዮጵያ ሥር የሰደደ ችግር ሆኖ ቆይቷል። ያ ዘመን ለይስሙላ ካልሆነ በቀር ሥልጣን የኢትዮጵያውያንን ልማት ለማፋጠን የዋለበት አልነበረም፤ ይልቁኑም ኢትዮጵያ በስውር የምትወጋበት ነበር እንጂ።
አካባቢያዊነት በእጅጉ በተንሰራፋበት በዚያ ዘመን ከትንሽ እስከ ትልቅ ከግለሰብ እስከ ብሔረሰብ የባለሥልጣናት መጫወቻ ሆነዋል። አካባቢያዊነቱ ከክልል እስከ ዞን ድረስ ወርዷል፤ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የክልል መሥሪያ ቤት እስከመምሰል የደረሱበት ሁኔታም ተከስቷል። በአካባቢያዊነት፣ በጓደኝነት ፣ በእምነትና በርዕዮተ ዓለም መሳሳብ የተንሰራፋበት ሁኔታ ነበር። የወንዝ ልጅ ቦታ ሲሰጠው ሌላው ሲገፋ ኖሯል። እነዚህ አካሄዶች ቡድኖችን፣ ግለሰቦችን ጠቅመዋል። በአንጻሩ አገሪቷንና እና ሕዝቧን ግን በእጅጉ ጎድተዋል።
ይህ ግፍ የመረራቸው ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት በዚህ አገር በመጣው ለውጥ ያን የግፍ አገዛዝ አሸቀንጥሮ መጣል ተችሏል፤ ለውጡ በፈጠረው ምቹ ሁኔታም ዜጎች ይመራናል ያሉትን መርጠው አዲስ መንግሥት ተመስርቶ ሥራ ጀምሯል።
ኢትዮጵያም ወደ አዲስ የአስተዳደር ሥርዓት ተሸጋግራለች። ስለሆነም በየትኛውም መልኩ የቀደሙት አስተዳደሮች ቅሪት አሁን ባለው መንግሥት ባለስልጣናት ዘንድ መታየት የለበትም። ሚኒስትሮችም ሆኑ በየደረጃው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሁሉ ከምንም ቅድሚያ የኢትዮጵያዊነትን አመለካከት በመላበስና ከአካባቢያዊነት አመለካከት ራሳቸውን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል።
በምርጫው የወከላቸው ኅብረተሰብ እንዳለ ሆኖ፤ የዚህን ኅብረተሰብ ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመስራት ሊሆን ይገባዋል። ከዚህ ውጪ በካቢኔ የተሰጣቸውን ሥልጣን ለአካባቢያዊነት መጠቀም አይገባም፤ መሞከርም የለበትም ፤ ይህን ማድረግ የመላውን ኢትዮጵያዊ አደራ መብላት ከመሆኑም በላይ ተጠያቂነትም ያስከትላል። የካቢኔው ሥልጣን ሰፊ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ማገልገያ መሆኑን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።
የካቢኔ አባላቱ ኃላፊነት ማዕከል ማድረግ ያለበት ኢትዮጵያዊነትን ሊሆን ይገባል። የቀደመው ዘመን መንደርና አካባቢን የማገልገል መነቃቃት በሕዝባችን ላይ የተፈጸመ በደል ነው። ይህ አይነቱ አመለካከት በአዲሲቱ ኢትዮጵያ እንዳበቃለት አውቀው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማገልገል በአግባቡ መዘጋጀት አለባቸው።
አዲሶቹ የካቢኔ አባላት የአካባቢያዊነት ሰለባ ሳይሆኑ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። በአካባቢያዊነት አቀንቃኞች አጀንዳም እንዳይጠለፉ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። በሚሰሩት ሥራም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ማዕከል ማድረግም ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊነትን ቀለም እና የኢትዮጵያዊነትን አጀንዳ ብቻ ይዞ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህንን በአግባቡ ተገንዝበው በዕለት ከዕለት ሥራቸውም በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ ሲችሉ ለአገር በጎ ተግባር በመሥራት ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ችለዋል ይባላል። በታሪክም ውስጥ የሚኖራቸው ስፍራ የደመቀ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም