በአምቦ ከተማ ባለፍት ስድስት ወራተ 26 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ እንዳቀረቡ የከተማዋ ኢንቨስትመንት ጽፈት ቤት ገለጸ።
ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ቱራ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በአምቦ ከተማ ከቀድሞው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በስድስት ወራት ብቻ 26 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበዋል።
ባለሀብቶቹ የብረታ ብረትና ቆርቆሮና ሚስማር ፋብሪካ ፣የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ፣የእምንበረድ ፋብሪካ፣ የጂብሰም ማምረቻ በማቋቋም ለመንቀሳቀስ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል።
የባለሀብቶቹን ጥያቄ ከተመለከተ በኃላም የስድስቱን ባለሀብቶች ጥያቄ ጽፈት ቤቱ መቀበሉን ገልጸው ፤የተቀሩትን 20 ባለሀብቶች ደግሞ ከክልሉና ፌደራል መንግሰት ጋር በመሆን ጥናት በማድረግ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምላሽ የሚሰጥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ያገኙት ስድስት ባለሀብቶች 290 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደተመዘገበና ከስድስቱ ሁለቱ የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ በመክፈት ወደስራ የገቡ ሲሆን ፤አራቱ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ ታውቋል።
አቶ ታሪኩ አክለውም፤ በአምቦ ከተማ በተመሳሳይ ባለፍት ስድስት ወራት የኢንቨስትመንት ፍላጎት ያላቸው 31 ዴያስፖራዎች ወደ ከተማ በመምጣት ምልከታ እንዳደረጉ ገልጸዋል ።
ሶስቱ ዴያስፖራ የኢንቨስትመነት ጥያቄን አቅርበዋል።በአሁኑ ወቅት የአምቦ ከተማ ኢንቨስትመንት በመነቃቃት ላይ እንደሆነም አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኢንቨስተመንት አዋጅ ከጸደቀ ከ80 ዎቹ ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም በአምቦ ከተማ 128 የልማት ፕሮጀከቶች በ900 ሚሊየን ብር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው ፤እነሱም የከተማዋ ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶች እንደነበሩ ከጽፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዳንኤል ዘነበ