ትናንትን ለዛሬ መንደርደሪያነት፤
“ሥልጡን” የሚሰኙት ሀገራት አዲስ መንግሥት ሲያዋቅሩ ፕሬዚዳንቶቻቸው አለያም ጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ከእነ ካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር በመቶ ቀናት ውስጥ በሚሠሩት ሥራ እንደሚገመገሙ ዕድሜ ሳይገድባቸው ከትንሽ እስከ ትልቅ ዜጎቻቸው በሚገባ ይረዱታል፤ ተፈጻሚ እንዲሆንም ይጠይቃሉ፡፡ የመቶ ቀናቱ የመፈታተሻ ጊዜያት ሲጠናቀቅም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉድለት ስኬቱን እየዘረዘሩ የሚተቹት አብጠልጥለውና ያለ ይሉኝታ ነው።
የዚህ “የመቶ ቀናት” የመንግሥታት መገምገሚያ ባህል ታሪካዊ አመጣጥ መቼና በምን ምክንያት እንደተጀመረ ለማወቅ ያገላበጥኳቸው ማመሳከሪያ ሰነዶችና የፈተሽኳቸው መጻሕፍት በሙሉ ጥርት ያለ ፍንጭ ሊሰጡኝ ስላልቻሉ የነገረ አመጣጡን ምክንያት ለመግለጽ አዳግቶኛል፡፡ በዚሁ በተገደበው የመቶ ቀናት ውሎና አዳር የተፈሹ የዓለም አቀፉ የስኬትና የክሽፈት ታሪካዊ ክስተቶች ግን ዓይነታቸውም ሆነ ቁጥራቸው የትዬለሌ የሚሰኝ እንደሆን ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡
ከታላላቅ ዓለም አቀፍ ጦርነቶች እስከ ፊልም ተመልካቾችና የመጻሕፍት ሥርጭቶች፣ ከፕሬዚዳንቶች ክራሞት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ውሎ አምሽቶዎች “መቶ ቀናት” መነሻና መድረሻ ሆነው ብዙዎች በክሽፈታቸው ተተችተዋል፣ ጥቂቶች እየተወደሱ ተደን ቀዋል፣ በርካቶችም አይመጥኑም ተብለው ተወግዘዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን እንደመጡ ብዙ ዜጎች “መቶ ቀናት” የሙከራ ጊዜ ቆርጠውና ከሌሎች ኮርጀው ሊገመገሙ ይገባል እየተባለ በስፋት መነገሩና መጻፉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም “ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ፤ የሚኒስትሮች መቶ ቀናትስ?” በሚል ርዕስ ዘለግ ያለ አንድ ጽሑፍ በጋዜጣ ላይ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን በጀመሩ ማግሥት ከመቶ ቀናት ገደብ አሻግረው በማየት የተራመዱበት ፍጥነትና የወሰዷቸው ተከታታይ የተግባር እርምጃዎች አጃኢብ አሰኝተው አስገርመውን ነበር፡፡ ለምሳሌ እንዲያግዙን አንድ ሁለቱን ብቻ እናስታውስ።እያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በሚኒስትሩ አማካይነት በሚቆጣጠረው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፊት በመቅረብ ስለ ሥራ እቅዶቹና ስለ አፈጸጻማቸው በቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ሲፈራረሙ ተመልክተን ነበር፡፡ ዕቅዳቸውም በአንድ ገጽ ተጠቃሎ እንዲቀርብ በመወሱኑ በየሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ግድግዳና አሳንሰሮች ውስጥ ሳይቀር ተለጥፎ አላፊ አግዳሚው እንዲመለከተው መደረጉም አይዘነጋም፡፡
ይህ ጉዳይ የወረት ሆኖ እንዳይቀር ዜጎች መብታ ቸውን ተጠቅመው ብዙ አምተዋል፣ የተጠራጠሩም ብዙዎች ነበሩ፡፡ እንደተፈራው አልቀረም ጉዳዩ ለቴሌቪዥን ፍጆታ ከዋለ በኋላ ተድበስብሶ ቀርቷል ወይንም ግምገማውን ሕዝብ በግላጭ እንዳይመለከተው ስለተፈለገ በዝግ ቢሮ ውስጥ ተከናውኗል፡፡ አዋቂው አንድዬ ብቻ ነው፡፡ ምን ያህሉ ዕቅድ እንደተፈጸመ፣ ምን ያህሉ በምኞት እንደቀረ፣ ምን ያህሉ ዕቅድም “ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ፤ መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ” እየተባለ በዘፈን ምርጫ ጥበብ እንደታለፈ የሚያውቁት ባለጉዳዮቹ ናቸው፡፡
እንዲያም ቢሆን ግን በዓይናችን አይተን ስላደነቅናቸው ውጤቶችና ስኬቶች “አሹ” ብለን ባንመርቅ ውለታ ቢስ እንሆናለን፡፡ ተድበስብሰው ስለቀረቱና ሆን ተብለው ስለተገፈተሩት አለያም ሀገሪቱ በገጠማት ፈተናዎች ያልተከናወኑ ዕቅዶችን በተመለከተ ጊዜው ሲፈቅድ ወደፊት ከጋዜጣ ጽሑፍ ከፍ ባለ የመጽሐፍ ጥራዝ ሰንደን ለትውልዱ ማስተማሪያነት ለማስተላለፍ እንሞክራለን፡፡
የብልጽግና ፓርቲ መሩ መንግሥት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ ሥልጣኑ ላይ ከተሰየመ አሥር ያህል ቀናት አስቆጥሯል፡፡ አቤት የጊዜው ሩጫ! በመግቢያው ክፍል ከጠቀስነው የመቶ ቀናት የተግባር መፈተሻ የጊዜ ገደብ አሥር ቀናት ሲቀነሱ የሙከራ ጊዜው ወደ ዘጠና ቀናት ዝቅ ብሏል ማለት ነው፡፡ ቀነ ገደቡ አስፈላጊ ይሁንም አይሁን ከመቶ ቀናት ይልቅ ከእኛ ዐውድ ጋር የሚገጥመው የዘጠና ቀናት ገደብ ቢሆን ይበልጥ ይገልጸን ይመስለናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ አንድ አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኛ ቋሚነቱ የሚረጋገጠው በዘጠና ቀናት ውስጥ መሆኑ መከራከሪያውን ይበልጥ ያጠናክረዋል። ለማንኛውም የመቶ ቀናት ፍልስፍናውን እዚህ ላይ ገታ አድርገን ጆሮውን የማይነፍገን ከሆነ ሕዝባዊ ምኞታችንንና ፍላጎታችንን ለአዲሱ መንግሥታችን ቆንጥረንና አንድ ሁለት እያልን ማሳያዎችን በማመላከት በመልካም ምኞት አጅበን እንደሚከተለው ይድረስ እንላለን፡፡
አንድ፡- የስብሰባ ባህል ይለወጥ፤
የሀገራችን የመንግሥት ተቋማት የተንዛዛና የተሰላቸ “የስብሰባ ባህል” ተቋማቱን ከሚመሩት ሹማምንት አስተሳሰብ ውስጥ በሲሪንጅ መጦ የሚያወጣ ቴክኖሎጂ ቢፈጠር ደስታውን አንችለውም፡፡ ደስታ ብቻ ሳይሆን እንደ ረመጥ እያንገበገበን ስለኖረም “ስዕለትም” ቢሆን አክለንበት ከዚህ ክፉ ደዌ ብንላቀቅ አንጠላም። ጩኸታችን ወደ ፈጣሪ ዘንድ ከመድረሱ አስቀድሞ (እስካሁንም ደርሶ ሊሆን ይችላል) ሥልጣነ በትሩን የተቀበለው አዲሱ “ምስለ ሙሴ” መንግሥታችን ይህንን በቢሮክራሲው ውስጥ እንደ ቀይ ባሕር ተንጣሎ የተገሸረውን ክፉ መሰናክል በበትሩ ከፍሎ እፎይ ቢያሰኘን በዕልልታ አጅበን አደባባይ በመውጣት ደስታችንን የምንገልጸው በማግሥቱ ይሆናል።
መቸም ምኞት አይከለከልምና የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ተጠፍንጎ የተተበተበበትን የስብሰባ ጎጂ ልማድ የሚያስወግድ አንድ ግብረ ኃይል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሥር ተቋቁሞ ተቋማቱን እየፈተሸ ምኞታችንን ቢፈጽምልን ደስታችን ይበልጥ ሙሉ ይሆን ነበር፡፡ ይህንን የቢቸግር ሃሳብ ለምን እንደሰነዘርን እኛ ብዙኃን ተጠቂ ዜጎች በሚገባ እንረዳለን፡፡
በርካታ የመንግሥት ሹመኞች የሕዝቡን ጥያቄ ይሆናል፣ አይሆንም ወይንም እስከ… ድረስ ውጤቱን እናሳውቃለን እያሉ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ በስብሰባ ቋጥኝ ሥር ራሳቸውን ከልለው የሚውሉባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ የስብሰባ ልማድ ወደ ባህል ደረጃ ለመሸጋገሩ (ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል እንዲሉ) ጥሩ ማሳያ የሚሆነውን አንድን ጉዳይ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ሹሙ/ባለሥልጣኑ ቢሯቸው እያሉም ቢሆን በጸሐፊያቸው አማካይነት “ስብሰባ ላይ ናቸው” ማሰኘታቸው ፀሐይ የሞቀው ሀገራዊ ችግራችን ነው፡፡ አቤት ውሸት አለ ኮሚዲያኑ!
ቴክኖሎጂው በተራቀቀበት በዚህ ዘመን ስብሰባንም ሆነ ምክክርን “በቨርችዋል” አማካይነት ባሉበት ማድረግ እየተቻለ ለምን “የስብሰባ ሱስ” እንደተጣባን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በዜጎች መንገላታት ደስታ የሚሰማቸው ሹሞችን ከዚህ በሽታ የሚያላቅቃቸው ኃይል ማንና እንዴት እንደሆነ ማሰቡ በራሱ አታካች ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱ መንግሥት ይህንን የተንዛዛ የስብሰባ ባህል አስወግዶ እኛንም ሆነ ራሱን ነፃ እስካላወጣ ድረስ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። የስብሰባ ሱሰኞች የሚፈወሱበት የማገገሚያ ተቋም ካለም ወደ ሕክምና ቢልካቸው አይከፋም፡፡
ሁለት፡- የድርጅት አባልነት ማስፈራሪያ አይሁን፤
ጉራጌዎች በማሳ መሃል የሚቆምን የወፍ ማስፈራሪያ (Scarecrow) አውከሬ በማለት ይጠሩታል። አውከሬ አብዛኛውን ጊዜ እስትንፋስ አልባ “ምስለ ሰው” ነው። ወፎች ወደ ገበሬው ማሳ እንዳይገቡ የመከላከልም ሆነ በጩኸት የማባረር አቅምና ችሎታ የለውም። ችሎታው በአርቴፊሻል ቁመና ማሳው ውስጥ ገዝፎ በንፋስ ኃይል መወዛወዝ ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የድርጅት አባላት የብቃት አናሳነታቸውን የሚሸፍኑት “የፓርቲ አባልነታቸውን” እንደ ጋሻ እየመከቱ በመፋለም እንጂ በውጤት ተወዳድረው በማሸነፍ አይደለም፡፡
አዲሱ መንግሥት ሥርዓት እንዲያሲዝልን የምንጠ ይቀው “በዘጠና ቀናት ውስጥ” እንኳ ባይሞላለት የፈለገውን ቀናት ያህል ጨምሮ በራሱ አውከሬዎች ላይ ፍተሻውን ከወዲሁ ቢጀምር ይበጅ ይመስለናል። “ካብ አይገባ ድንጋይ” በሆኑበት “ልጆቹ” ላይም ቆፍጠን እንዲል እንመክራለን፡፡ ያለፈው መከራ ብዙ ስላስተማረን ያ ጭጋግ ተመልሶ እንዲመጣ አንፈቅድም፡፡
የገዢው ፓርቲ አባላት ብቻም ሳይሆኑ በየቢሮክራሲው ውስጥ ድርሻ ያላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትም በትንሽ በትልቁ እየተነጫነጩ “የእከሌ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ ተገፋሁ፣ ዕድገት ተከለከልሁ፣ ተገለልኩ ወዘተ.” እያሉ ለገላጋይ ማስቸገራቸውን ትተው በተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነትና መደብ ላይ ብቃታቸውን ቢያሳዩ ይበልጥ ይከበራሉ፡፡ የብቃታቸውን ውሱንነት ለማካካስ ሲሉ ግን ኡኡታቸውን አጉልተው ቢጮኹ ሕዝቡ ስለተሰላቸ “አባ ከና” የሚላቸው የሚያገኙ አይመስለንም፡፡ ይሄም ሲባል ግን ገና ለገና መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠቅልሎ የያዘው የአሸናፊው ፓርቲ ልጆች ቢሮክራሲው መመራት ያለበት በእኛ ብቻ ነው ብለው ሌሎቹን እንደ እንጀራ ልጅ ሊቆጥሩ አይገባም፡፡ የሚሞክሩት ከሆነም አስተዳዳሪ “አባታቸው” ከወዲሁ መላ ሊያበጅ ይገባል፡፡
ሌላም ስጋት አንዳንዶች የብልጽግና ፓርቲ አባል አይደለንም እያሉ እያወጁልን የተመረጡት ግን በብልጽግና ፓርቲ ጥላ ሥር ተጠልለው ነው፡፡ ከእነዚሁ መካከል አንዳንዶች የሹመት ከፍታ ላይ መድረሳቸውን በመገረም እየተከታተልን ነው፡፡ እንዲያው አይበለው አያርገውና “በብልጽግና ፓርቲ ስም የተመረጠ ነገር ግን የብልጽግና ፓርቲ አባል አይደለሁም” የሚል በተቃርኖ ሃሳብ ውስጥ ያለ አንድ የመንግሥት ኃላፊ ቢያጠፋና የፈረደበትን “ተገዢ ሕዝብ” ቢበድል ገለልተኛው የፍትሕ ሥርዓት ጣልቃ እስኪገባ ድረስ ለጊዜው ጉዳዩ ወደ ጆሮ”‟ው እንዲደርስ የሚደረገው ወደ የትኛው አካል ነው?
ብልጽግና ፓርቲስ ቢሆን በእኔ ስም ተወዳደረ እንጂ “የእኔ ልጅ አየደለም” ሊለን ነው ወይንስ መላው ምንድን ነው፡፡ ለእውቀትም ሆነ ለጥንቃቄ ሊረዳን ስለሚችል በዚህ ጉዳይ ላይ “ገዢዎቻችን ሆይ!” ማብራሪያ ብትሰጡን አንጠላም፡፡ ባለፈው ጽሑፌ አጽንኦት ሰጥቼ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እኒህን መሰል ባለሁለት ክንፍ ፖለቲከኞች “ለሥጋው ጾመኛ ነኝ፤ ከመረቁ አውጡልኝ” መርሃቸውን ደግመው ደጋግመው ቢፈትሹ አይከፋም። እስከመቼስ በአንካሳ ልብ ይጓዛሉ? ይህን መሰሉን መሸነጋገል እያየን “ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢነቀል በአንዱ ተንጠልጠል” የሚለውን ብሂል አዘውትረን ብንጠቅስ ይፈረድብን ይሆን?
ሦስት፡- የሪፎርሙ ቅድሚያ በዜጎች እምባ ለወረዙ ተቋማት ይሁን፤
የብዙ መንግሥታዊና የአካባቢ አስተዳደሮች አገልግሎት አሰጣጥ ምን መልክ እንዳለው ለእኛ ለዜጎች እንግዳ አይደለም፡፡ ምናልባትም እንግዳ ሊሆን የሚችለው ወደላይ ከፍ ላሉት ሹማምንት ሊሆን ይቻላል፡፡ የሀገራችን የአገልግሎት አሰጣጥና አገልግሎቱን ለመስጠት ኃላፊነት የተሰጣቸው የአብዛኞቹ ሹመኞችና ሠራተኞች ባህርይና ሰብዕና ምን እንደሚመስል ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች እንደ ጌቶች፣ አገልግሎት ጠያቂዎች ደግሞ እንደ ተመጽዋች የሚቆጠሩባቸው ብዙ ተቋማት መኖራቸውም ከሃሜት አያስቆጥርም፡፡
በዚህ ጸሐፊ እምነት ከቀበሌ እስከ ከተማ አስተዳደር ያሉት መዋቅሮች መንግሥት አራት ዐይናማ ሆኖ ቢፈትሻቸው እውነቱ ይገለጥ ነበር፡፡ የአስተያየት መስጫ ሳጥን በየኮሪዶሩ ላይ ከመደርደር ይልቅ “የዜጎች እምባ የሚጠራቀምበት ባልዲ” ቢዘጋጅ እውነቱ በራሱ አፍ አውጥቶ ይናገር ነበር፡፡ አንድ ዘለላ ምሳሌ እናስታውስ። በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ዜጎች የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ለመውሰድ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ ይይዛሉ መባል የተጋነነ ሀሜት የሚመስላቸው ካሉ ተሳስተዋል፡፡ የሚጠራጠሩ ካሉም ቀበሌዎችንና በተለይም የአዲስ አበባ ከተማን ወረዳዎች መፈተሽ ይችላሉ፡፡
ለስኳርና ለመሠረታዊ ፍጆታ ግብይት ከሌሊት ጀምሮ እስከ ሥራ መግቢያ ሰዓት ድረስ ድንጋይ እየደረደሩ ወረፋ የሚያዝበት ከተማ ቢኖር አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የላይኞቹ ሹመኞች ወረድ ብለው እውነቱን እንዲያጣሩ እንመክራለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረጃ እያጣቀሰ ደጋግሞ ስለጻፈ ዛሬ መረርና ጠንከር ብሎ በዘመነ አዲሱ መንግሥት እውነታውን ቢገልጽ አግባብ ብቻ ሳይሆን ተገቢ መሆኑንን ጭምር ያምንበታል፡፡
የድንጋይ ነገር ከተነሳ ጎንደሬዎች የደርግ መንግሥት ጉልበቱ እየተፈታና ኃይሉ እየዛለ ወደ ሞት ባሽቆለቆለበት ዋዜማ ሥርዓቱን የሄሱበት አንድ ሕዝባዊ ግጥም በእጅጉ ፈገግ ያስደርጋል፡፡ በአካባቢው አዲስ መንገድ ተቀይሶ ግንባታው ሲጀመር ቡልዶዘሮች ትልቁን ቋጥኝ እየደረመሱና እየከሰከሱ ጋራጋንቲ በማፍሰስ ጥርጊያውን ሲያሳምሩ የተመለከቱ የጎንደር ዙሪያ “አፈ ሊቆች” እንዲህ አሉ ይባላል፡፡
”ድንጋይ አይሞት ሲሉ ሞት ተፈረደበት፣
እየከሰከሱ መኪና ነዱበት፤
እስኪ በል ተፈጨው እስኪ በል ተቦካ፣ እስኪ በል ተጋገር፣
አንተም ስንፍናውን አብዝተኸው ነበር፡፡
እኛ ግፉዓን ዜጎች በአዲሱ መንግሥት ትልቅ ተስፋ አሳድረናል፡፡ ይሁን እንጂ በድምጻችን ይሁንታ የሰጠነው የብልጽግናው መንግሥታችን ጩኸታችንን አልሰማ ብሎ “እንደ አሮጌ ጅብ አትጩኹብኝ” የሚል ምላሽ በመስጠት የደረቀውን የእምባችንን ከረጢት እንድንጨምቅ ቸል ብሎ ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞችና የከተማ አስተዳደሮች እንደለመዱት እንቀጥል የሚሉ ከሆነ “ውርድ ከራሳችን” እንደ ጎንደሮች መሰል ቅኔያዊ ግጥም ፈጥረን ብሶታችንን መወጣታችን አይቀርም፡፡ ዳሩ እምባችን ተሟጦ ደርቆ አንድ ዘለላስ ጠብ ማለት ይችል ይሆን? ነፍሰ ሄሩ በዓሉ ግርማ ሆይ ግጥምህን እባክህ ለዚህ ዐውድ አውሰን?
እምባ እምባ ይልኛል ይተናነቀኛል፣
እምባ ምን አባቱ ደርቋል ከረጢቱ፣
ሳቅ ሳቅም ይለኛል ስቆ ላይስቅ ጥርሴ፣
ስቃ እያስለቀሰች መከረኛ ነፍሴ፡፡‘
የርዕሴን ጉዳይ ድምድማት ላብጅለት፡፡ አዲሱን የብልጽግና መሩን መንግሥት የምንፈትነው በመቶ ወይንም በዘጠና ቀናት ስኬት መሆን አይገባውም። መሻታችን ለመቶ ዓመት የሚዘልቅ ጠንካራ መሠረት እንዲጥልልን ነው፡፡ አጀማመሩም ይሄንንው ስለ ሚያረጋግጥልን አደራችንን አክብደን ትከሻው ላይ እንጥልበታለን፡፡
በተረፈ ጭል ጭል የሚለው ሰላማችን ፏ ብሎ እንዲበራ ቅድሚያ ይስጥልን፡፡ ህመምተኛው ኢኮኖሚያችንና የኑሮው ትኩሳት እንዲያገግም ፈጥኖ ያክምልን፡፡ የውጭ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው ከዘገምተኝነት ወጥቶ ከዘመኑ ጋር ይሽቀዳደም፡፡ እኛ ዜጎችም ከጎኑ መሆናችንን አምኖ “ልክ እንደ ፓርቲው ውልዳን” ይመንብን እንጂ “ቤትኞች” ስላልሆንን ብቻ አያግልለን፡፡ ቢያንስ የምንጽፈውን አንብቦ ሰምቻችኋለሁ ብሉ ድምጹን ያሰማን፡፡ ለነገሩ የመረጥነው እኛ ብዙኃን እንጂ የእርሱ አባላት ቁጥርማ መች ከዙፋኑ ያቃርበው ነበር፡፡ ዜጎቼ ብለህ ስትጣራ አቤት እንድንልህ፤ መንግሥታችን ሆይ ብለን ለመፍትሔ ስንጠራህ ፈጥነህ አቤት በለን፡፡ ሰላም ይሁን!
ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2014