ባለንበት ዘመን ዲፕሎማሲና ከዲፕሎማሲ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት የሚሹ ሆነዋል። በዓለም አቀፍ መድረክም ራስን ለመግለጽና ተቀባይነት ለማግኘት የሚኖራቸውም ተጽእኖም ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል። ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሁለንተናዊ ዝግጁነትም ለነገ የሚባል የቤት ስራ አይደለም።
በተለይም እንደኛ በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ያሉ ሀገራት ህዝቦች ለጀመሩት ለውጥ ስኬት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላቸው ዝግጁነት ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው። ስለ ጀመሩት ለውጥ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እንዲረዳቸውና እንዲደግፋቸው ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦም ከፍያለ እንደሚሆን ይታመናል።
የለውጥ አስተሳሰቦች በዓለም አቀፍ ተግዳሮት እየተፈተኑ ባሉበት ፈተናዎች የዲፕሎማሲውን መንገድ ሁለንተናዊ አቅም አድርገው በተጠናና በተቀናጀ መልኩ አደባባዮችን እየሞሉ ባሉበት በዚህ ባለንበት ዘመን ራስን በዲፕሎማሲው መስክ ከፍ አድርጎ መገንባት የዓለም አቀፍ የፈተና መድረኮችን በስኬት ለመሻገር ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት በዲፕሎማሲው መስክ ከፍ ያለ ዝግጁነት፤ ከዚህ የሚመነጭ ተቀባይነት እንደነበራት ታሪክ በጉልህ ቀለም ያሰፈረው እውነታ ነው። ለዚህም አንድም በብዙ ዋጋ ያስጠበቀችው ነጻነቷ የፈጠረላት ከፍ ያለ ማንነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስለሀገሩ ከራሱ በላይ አሳቢ ትውልድ ባለቤት መሆኗ ለስኬቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
በዘመነ ደርግም ቢሆን ይህ እውነታ ይደብዝዝ እንጂ እሱን ተከትሎ ወደ ስልጣን እንደመጣው የአሸባሪው ህወሓት መላቅጡ የጠፋ ዲፕሎማሲ አልነበረም። በዘመነ ህወሓት ቡድኑ ይከተለው ከነበረው ፍጹም ሀገር አፍራሽ እና ሀገር ጠል ፖለቲካ አንጻር ሀገሪቱ በዘመናት ያካበተቻቸው የዲፕሎማሲ አቅሞች ተንኮታኩተው ሀገር መርህ አልባ በሆነ የውጭ ግንኑነት ብዙ ዋጋ እንድትከፍል ተደርጋለች።
ይህ መርህ አልባ የዲፕሎማሲ መንገድ ቀጣይ በሆነውም የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነትም ሆነ፤ አጠቃላይ በሆነው የዲፕሎማሲው ዘርፍም ሆነ የሰው ሀብት ልማቱ ላይ ያስከተለው መጠነ ሰፊ ችግር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተጨባጭ እየተስተዋለ ነው። በዚህም ሀገር እንደ ሀገር እንድትከፍል እየተገደደች ያለው ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።
ሀገራዊ የዲፕሎማሲ ስራው ከፍ ባለ ዕውቀት፤ የሀገርና ህዝብ ህፍቅር መገዛት ሲገባው፤ የአገዛዙ ባለውለተኞች የውለታ ክፍያ እስኪመስል ድረስ ከመርህ ባፈነገጠና የግለሰቦችንና የቡድኖችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲቃኝ ተደርጓል። እርሶም ይሞክሩት እስኪመስል ድረስ ሁሉም በአገዛዙ ቡራኬ እየተሰጠው በዓለም አቀፍ መድረኮች መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን ተደርገናል።
የሀገሪቱን እና የህዝቦቿን መሻት ከፓርቲ ፍላጎት አሳንሰው የሚያዩ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ቀርቶ ራሳቸውን እንደ ግለሰብ በአግባቡ መግለጥ የማይችሉ ተጧሪ ፖለቲከኞች የሚተረማመሱበት፤ የሀብት መሰብሰቢያና መጦሪያ ማዕከል ተደርጎ ተወስዶም ነበር።
በዓለም አቀፍ አደባባይ ስለ ሀገር የሚሞግት ጠፍቶ ሀገራዊ ጉዳዮች በሚገዙ ባለሙያዎች ለማስተናገድ የተገደድንበት፤ በዓለም አቀፍ አደባባይ አሸናፊና ተሸናፊነታችንን እንኳን በአግባቡ መረዳት ተስኖን ህዝባችን ከፍ ላሉ የልብ ስብራቶች የተዳረገበት እውነታም የዚህ ታሪክ አካል ነው።
ባለሙያነት ከፖለቲካ ማንነት ጋር ተቀያይጦ ፤ግልጽ በሆነ ሙያና በሙያ ስብእና ሊመራ የሚገባው የዲፕሎማሲው ዘርፍ የሀገርና የህዝብን ጥቅም በሚሸጥ፤ ባልተገባ ነገንና ነገዎችን ታሳቢ ባላደረገ መርህ አልባ ግንኙነት እንዲመራ ተደርጎም ቆይቷል።
ይህ የትናንቱ ታሪካዊ እውነታ የቱን ያህል ለዛሬው የለውጥ ጉዟችን ተግዳሮት እንደሆነ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በዲፕሎማሲው ዘርፍ እያጋጠሙን ያሉ ተግዳሮቶች በተጨባጭ የሚያመላክቱት ነው። የዲፕሎማሲ ተቋሙን በበላይነት ሲመሩ የቆዩ ግለሰቦች ሳይቀሩ በሀገርና በፓርቲ መካከል ያለው ተፈጥሯዊ ልዩነት በአግባቡ መረዳት አቅቷቸው ምን ያህል የሀገር ፈተና እንደነበሩ ማየት ይቻላል።
ብዙ ሊሰራበት በሚገባው የዲፕሎማሲ ዘርፍ ይህንን ሀገራዊ እውነታ ለመቀልበስ የለውጡ ኃይል ገና ከመነሻው አንስቶ እየሄደበት ያለው መንገድ፤ ዛሬን ለመሻገርም ሆነ ነገ ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ለጀመርነው ታሪካዊ ጉዞ ብሎም የተበላሸውን በማረም አዲሱን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚሸከም ባለሙያም ሆነ ተቋም ለመገንባት ለምናደርገው ሀገራዊ አቅም ከፍ ያለ አቅም እንደሚፈጥር ይታመናል።
ከዚህ አንጻር አዲሱ መንግስት የዲፕሎማሲውን ዘርፍም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን በሁለንተናዊ መልኩ በማዘመን የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት እንዲወጣ ለማስቻል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሲሆንም አገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ማግኘት የሚገባትን ክብርና ጥቅም በሚገባ ማግኘት ትችላለች!