መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የአዲስ ምዕራፍና አዲስ ተስፋን ያነገበው የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት ተግባራዊነት ተበስሯል ። በዕለቱም የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ዘመናቸውን በይፋ ጀምረዋል ። የተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ መሠረት አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀረበውን ሹመት አጽድቋል። በዚህ መሠረት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል ። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አዲስ ምዕራፍ ከታየበት ዕለት ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባዋቀሩት ካቢኔ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃዋሚ አመራሮች በካቢኔ ውስጥ ቀርበው በሚኒስትርነት ተሹመዋል ።
ይህም በአገሬ ሰማይ ስር ሌላ አዲስ ታሪክ ሆኗል ። ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚነት ወደ ተፎካካሪ ፓርቲነት እሳቤ ያሻገሯቸውን ፓርቲዎች ስልጣን የሚሰጡ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንሰማ ነበር ። የገቡትን ቃል በመፈጸም “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ “ የሚለውን አባባል በተግባር ኖረው አስመልክተውናል ። በእርሳቸው የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ በተመሳሳይ በአካታች የፖለቲካ አስተሳሰብ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሥልጣን ማጋራቱ ትልቅ ትርጉም ይሰጣል ። በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የመንግሥትን ሥልጣን ዕድል መቀበላቸው ተመሳሳይ መልዕክት ይሰጣል ። በኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተፈጠረ ሲባል የቆየው አዲስ ምዕራፍ እየለመለመ እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርጎኛል ።
ምክንያቱም ቀደም ሲል ከመጣንበት መንገድ ፍጹም ተቃርኖ ነበረውና ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች( ኢህአዴግ / ህወሓት በአምሳሉ የፈጠራቸውን አያካትትም ) ለአንድ አገር የሚሰሩ በማይመስል መልኩ ሆድና ናጫ ነበሩ ። ለአገር አንዱ አሳቢ ፤ ሌላው አገር አፍራሽ አድርጎ ከመፈራረጅ በዘለለ አንዱ አሳዳጅ አንዱ ተሳዳኝ የሆነ ስንኩል የታሪክ ትውስታ ነበራቸው ። ይሄ በደርግም ሆነ በህወሓት ዘመን የተስተዋለ፤ ገዥውም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመጠላለፍ የሚሮጡ ነበሩ ።
የአገሪቱ ፖለቲካ መልኩ ይህን የመሰለ ቢሆንም ፤ የአገሬ ሕዝብ በአገሩ ሉዓላዊነት ( ባንዳውን አይመለከትም ) ተደራድሮ አያውቅም ። በኢትዮጵያ ታሪክ እንደምናውቀው በውስጥ ጉዳዮች ቅራኔ ፣ ልዩነቶች እያሉ አገር ስትወረር በአንድነት የመመከት ልምድ ከጥንትም አብሮን የኖረ ነው ። ዛሬም ያልተለየን በጎ መገለጫችን መሆኑን በተለያዩ ሁነቶች ተመልክተናል ። ሆኖም ወደ ፖለቲካው ስንመለስ መልኩ ሌላ ነበር ። ታዲያ ዛሬ የት ላይ ነን ?! ካልን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የትናንት ጥቁሩ ጠባሳ ተሽሮ ዛሬ በአዲስ ታሪክ ተቀይሯል ።
በሕዝብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል መሰል ታሪክን መመልከት ችለናል ። በአሁን ወቅት በሥልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ምድር በሰላማዊ መንገድ ከመታገል ትይዩ ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ በአንድነት በአንድ ልብ የሚቆሙበት ጊዜ ተፈጥሯል ። በተጨባጭም በአባይ ጉዳይ ልዩነትን ወደ ጎን አድርጎ ‘ግድቡ የኔ’ ነው በአንድነት ቆመው አሳይተውናል ። በአሸባሪው ቡድን እና ቀለብ ሰፋሪዎቹ የከፈቱብንን ጦርነት ለመመከት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ታሪኩ ተደግሞ ተመልክተናል ።
የፓርቲ እና የርዕዮት ዓለም ልዩነቶች ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በታች መሆናቸውን በተግባር አስመልክተውናል ። ከነበረው የጠላትነትና “እኔ ነኝ ለአገር የሚበጅ ሀሳብ ያለኝ” ከሚል እኛ ነን ወደ ሚል ከራስ አገርን ያስቀደመ የሰለጠነ ፖለቲካ ወደ ማራመድ ተደርሷል ። አገር ስትነካ ጸብና ቁርሾውን አስቀምጦ …. በይደር ትቶ የአገር ዳር ድንበርን ለማስከበር እንደተዋደቁት አያቶቻችን በአስቸጋሪው ወቅት በምርጫ አሸናፊ የሆነው የብልጽግና እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች አብረው ቆመዋል ። በዚህም የጥላቻ ግንብ ተንዶ …….. ኢትዮጵያን ቀድማለች ።
ምንም እንኳን ታሪክ የማይረሳው ጥቁት ነጥብ ጥሎ ያለፈ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ወደፊት ባስፈነጠረው የመስከረም 24 ክስተት ፤ በአካታች የፖለቲካ አስተሳሰብ ሁለቱ ወገኖች አብረው ለመስራት በመወሰናቸው የተደሰተውን ሕዝብን ፤ ደስታ በአንድነት በተሳካ ሁኔታ በማገልገል ደስታውን ዘላቂ ማድረግ ይኖርባቸዋል ። ከዚህ አኳያ ከፌደራል እስከ ክልል የተሾሙ የተፎካካሪ/ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የተሰጣቸው ስልጣን ዳረጎት አድርገው መቁጠር የለባቸውም ።
ይልቁኑስ ሕዝብን እንዲያገለግሉ ታሪካዊ እድል እንደሆነ በመረዳት – ኢትዮጵያን አስቀድመው ማገልገል ይኖርባቸዋል ። ሕዝብን አስቀድሞ መሥራቱ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ታሪክ ሆኖ ይፃፋል ። በተቃራኒው ከሆነም ውጤቱ በተገላቢጦሽ ይጻፋል ። ሹመቱን እንደ መደለያ ፣ አፍ ማዘጊያ ….. አድርጎ በመቁጠር ዳተኝነት ማሳየት ፈራጁ ሕዝብ ነውና ከእዩኝ እዩኝ ደብቁኝ እንዳይሆን ነገሩ ኢትዮጵያን በቅንነት ማገልገል ይገባል ።
በተመሳሳይ በምርጫ አሸናፊው የብልጽግና ፓርቲ ትኩረቱ ወንበር ሳይሆን ሕዝብ አክብሮ በተቀናጀ መልኩ የመረጠውን ሕዝብ ማገልገል ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ። ኢትዮጵያን ባስቀደመ መንፈስ የመሥራት ፍላጎትን ወደ ተግባር መቀየር የሚቻለው በአዲሱ መንግሥት ለተካተቱ የተፎካካሪ / ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንቅፋት በመሆን ሳይሆን ድልድይ መሆን ሲቻል ነው ። ስለዚህ ብልጽግና ፓርቲ አገርን ለማገልገል በሚደረገው ደፋ ቀና እንቅፋት ሳይሆን ብርታትን በመሆን ተመስጋኝ ሥራን ሰርቶ ማለፍ ይቻላል ። አገሩን እንደሚወድ አንድ ዜጋ ያለኝን ስጋት አሮጌው ሥርዓት ዋቢ አድርጌ ልግለጽ ።
በዘመነ ኢሕአዴግ /ህወሓት በልኩ ጠፍጥፎ የሰራቸው ተቃዋሚዎችን በአገሪቱ በርካታ ፓርቲዎች እንደሚገኙ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፊ እንደሆነ ፣ በአገሪቱ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀምባቸው ነበር ። ገዥው ፓርቲ ራሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ለማለት ለይስሙላ ይጠቀምባቸው ነበር። ትናንት ዛሬ ባይሆንም ፤ ዛሬ የትናንት ውጤት በመሆኑ አዲሱ መንግሥት ለተፎካካሪዎች የሰጠው ሹመት የትናንቱ ኢህአዴግ/ ህወሓት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያማከለ የመንግሥት ምስረታ አደረኩኝ ለማለት መሆን የለበትም ።
በእርግጥ ይህ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት በሰጡበት ወቅት ለፓርላማው ገልጸዋል፤ የሰጧቸው ቦታዎችም የ10 ዓመቱ የፍኖተ ብልጽግና በቁልፍ ዘርፍነት ካካተታቸው መካከል መሆናቸው ታይቷል፡፡ ይሁን እና መንግሥት ኢትዮጵያን በማስቀደም የተደረገ መሆኑን ከፖለቲካዊ አሻጥር የፀዳ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር በታማኝነት ፣በቅንነት ….. ለማገልገል በሕዝብ ፊት ለማገልገል የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማድረግ ይገባል ።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም ተቀናጅቶ መሥራት ከቻለ ድህነት ዛሬ ያጠቆረው ሰማይ በብርሃን የፈካን ነገን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይቻላል ። በሁለቱም ወገን ታማኝነታቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ከዛ ውጭ ምንም የተለየ ታማኝነት ሊኖራቸው አይገባም። ለማንም በምንም አይነት አድሎ ሳይኖር፤ ሁሉም በችሎታው ተመዝኖ በብቃቱ ሥራውን የሚሰራበት ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል ።በተለይ ከሌብነት ጋር የተያያዘ ነገር ማጥራት ዋና ሥራ መሆን አለበት ። በመስከረም 24ቱ ክስተት – ከ “ እኔ ነኝ” ወደ እኛ “ የተቀየረው ራስ ወዳዱ ፖለቲካችን የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ተቀናጅቶ በመስራት ከተደገመ ለትውልድ የፈካ እንጂ የጠለሸ ታሪክን አናወርስም ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም