ፓርላማ ስልጣኑንና ሉዓላዊነቱን በቀጥታ ከሚወክለው ህዝብ ያገኛል። ከስልጣኑም ቀዳሚው የህዝብ ውክልና ሥርዓት ሲሆን ሥርዓቱ የሰልጣኖች ሁሉ ቁንጮ ነው። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 ዓ.ም የሥራ ዘመን በይፋ መከፈትን ባበሰሩበት ሥነሥርዓት ላይ ያረጋገጡትም ይሄንኑ እውነታ ነው። እንደ ፕሬዚዳንቷ የውክልና ሥርዓቱ የተለያየ ቅርጽና ይዘት ቢኖረውም እንደ ሀገር የዘጠና ዓመት ልምድ ተካብቶበታል።
በዚህ ዘመን ውስጥ ሴቶች በውክልና፣ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በመወከል የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑበትና ከሰባት አሥርት ዓመታት በላይ የተቆጠረበት ታሪክ ማሳያ ነው። የሴቶችን መብት፣ ደህንነት፣ ውክልና ተሳትፎ የማስጠበቁም ሂደት ከዚሁና በየጊዜው ከተካሄደ ምርጫ ጋር የተያያዘ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩበትና እያደገ የመጣ መሆኑን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት ዶክተር ምሥራቅ መኮንን በበኩላቸው ይናገራሉ።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት የለውጥ ዓመታት ውስጥ እድገቱ ትልቅ እመርታ አሳይቷል። ሴቶችን ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነትን፣ የመከላከያ፣ የትራንስፖርትና የሌሎች ተቋማት መሪነትን ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ መቆናጠጥ ደርሰዋል።
በ2011 ዓ.ም በነበረው የሚኒስትሮች ሹመት ከ20ው የካቢኔ አባላት 10ሩ ሴቶች የጾታ ስብጥራቸውን ከወንዶች ጋር ለማመጣጠን በቅተውም ነበር። በቅርቡ በተዋቀረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 22 ካቢኔ አባላት ውስጥ ስምንቶቹ መሆን ችለዋል። ትላልቅ ዘርፎችን በመምራት ረገድም ከወንዶች ልቀው ተገኝተዋል። ስኬታማነታቸውም በአንጻራዊነት ሲታይ ወደር እንደሌለው ተመስክሯል። እንደ አመራሮች ሴቶች እጅግ በጣም ትላልቅ ዘርፎችን እየመሩ ያሉበት አለ። ለአብነት ትራንስፖርትና ሎጄስቲክ ሚኒስትር የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ይጠቀሳሉ።
ይህ የተመደቡበት ቦታ ግዝፈቱ ሲታይ በብቃት መምራት እንደሚችሉ ያመላክታል። ሆኖም ሴቶች በዚህ መልኩ በፌዴራል መንግስት ደረጃ ተሳትፏቸው እያደገ ቢመጣም ወደ ክልል መንግስታት ካቢኔ ሲወረድ ቁጥሩ በግማሽ መቀነሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት የወጣው ይሄው መረጃ እንደሚያመላክተው በዞን ካቢኔዎች ደግሞ ወደ 18 በመቶ ዝቅ ያለበት አለ። የጾታ ክፍተቱ ከፍተኛነት የሴቶችን ተሳታፊነት ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ያለውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥም አላስቻለም።
በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮቹን በመፍታት ሙሉ ለሙሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱንም የሥራ ኃላፊዎች በየበኩላቸው ያወሳሉ። ከእርምጃዎቹ አንዱ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች አዲስ አወቃቀር እንዲካተት ማድረግ ነው። ሌላው በዚሁ አወቃቀር ውስጥ በማካተት ሴቶችን፣ ህፃናትንና ወጣቶችን በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ፍትሃዊ ተሳትፎና ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
የሴቶችንና ህፃናትን ጥበቃ ሥርዓት በማጠናከር ሁለንተናዊ ደህንነታቸውን ማስጠበቅና መብታቸውን ማስከበርም መካተቱን ይጠቁማሉ። ችግሮቹን በዘላቂነት ለመሻገር የመንግስትን የላቀ ትኩረት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እገዛና የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ መጠየቁንም ያክላሉ። አሁን ሴቶች ያሉበት ደረጃ በእጅጉ የሚበረታታ፣ ተስፋ ሰጪና በየጊዜው እያደገ የመጣ ነው እንደሆነም ያብራራሉ።
ይህ በፌዴራልና በክልል ያለ እድገት በሀገራችን በየጊዜው ከተካሄዱ ምርጫዎች ጋርም በብርቱ የሚሰናሰል ታሪክ አለው። ከአንደኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁለተኛው፤ ከሁለተኛው ሦስተኛው እያለ ስድስተኛው ላይ ሲደረስ ትልቅ እመርታ አሳይቷል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደሚናገሩት በተለይ ሴቶች በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ባላቸው ሚና በሦስቱ የለውጥ ዓመታት ውስጥ ከበፊቶቹ ዓመታት ከነበረው በበለጠ ጎላ ብለው የወጡ መሻሻሎች ታይተዋል። ባለፈው ዓመት ሴቶች በአስፈፃሚ አካላት የነበራቸው ተሳትፎ 50 በመቶ የደረሰበት ሁኔታ የነበረ መሆኑንም በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ተከትሎ አዲስ በተመሰረተው መንግስት ካቢኔ ከተካተቱት 22 አባላት መካከል ስምንቱ ሴቶች መሆናቸውም መሻሻሎች መኖራቸውን ያሳያል። ይሄ የሴቶች ቁጥር በመቶኛ ሲገለፅ 31 ነጥብ 8 ነው። ሆኖም ከቁጥር ባሻገር ያለውን የተቋም ግዝፈት፣ ስኬት፣ በብቃት መምራትና በዚህ ውስጥ የተካተተ ጾታዊ ስብጥር ተሳትፎን ማየት አለብን የሚል እምነት አላቸው።
በህግ አውጪው አካል ያላቸው ሚና ሲቃኝም በአራተኛው ዙር ሴቶች የነበራቸው ተሳትፎ 38 ነጥብ 8 እንደነበርም ይጠቅሳሉ። እስከ አሁን ባለው የምርጫ ውጤት ብልፅግና ፓርቲ ያሸነፈባቸው የምክር ቤት ወንበሮች 436 መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ 41 በመቶው ሴቶች መሆናቸውንም ይገልፃሉ። ይሄ ቁጥር የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደመጣ ያሳያል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2019 ያስጠናውን ጥናት መሰረት አድርገው በህግ ተርጓሚው በኩል የነበረውን የሴቶች ተሳትፎ እንደገለጹትም በጠቅላይ ፍርድ ቤት የነበረው 27 በመቶ ነበር።
በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የነበረው ተሳትፎ ደግሞ 18 በመቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። በሁለቱም ፍርድ ቤቶች ያለው ተሳትፏቸው በአጠቃላይ ከ30 በመቶ በታች ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለው 60 በመቶው የሴቶች ተሳትፎ ሲታይ ከሁለቱ እጅግ የተሻለ እንደሆነ ወይዘሮ ሙና ያብራራሉ። ይሁንና በህግ ተርጓሚውና በአስፈፃሚ አካላት ያለው የሴቶች ተሳትፎ በንፅፅር ሲታይ ሴቶች ወደ ሕግ ተርጓሚ እንዲመጡ በማድረጉ ረገድ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን የሚጠብቁት ቀጣይ ሥራዎች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም በዚህም መስክ ጅምር ሥራዎችና እየተሻሻሉ የመጡ ነገሮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም ብለዋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ላይ በቀጣይ እንደ መንግስትም መሰራት ያለበት ሥራ አለ። በክልል ሲታይ አዲስ በተዋቀረው መንግስት የህግ አውጪው አካል ላይ የተጀመሩ ሌሎችም በርካታ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች አሉ። ሴቶች ትላልቅ ዘርፎችን በመምራት እየመጡ ናቸው። ሆኖም ሊያዘናጓቸው እንደማገባ አሳስበዋል። ይልቁንም በዚሁ ልክ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በክልሎች ሰፋ ያለ የሴቶች ቁጥር የሚታይባቸውና በካቢኔ ደረጃ ብዙ ያልተካተቱባቸው ቦታዎች አሉ። በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ይሄን የማመጣጠን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በዚህ በኩል የፌዴራል አስፈፃሚ አካላት ጥሩ ተሞክሮ ይቀሰምባቸዋል። በተለይ አወቃቀሩ ሥራውን የተቃና ለማድረግ በመርዳት በኩል ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ወይዘሮ ሙና ያምናሉ።
ለአብነት በአዲሱ መንግስት አወቃቀር የቀድሞው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ወደ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተብሎ ወጣቶችን፣ ህፃናትን፣ አረጋውያንንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲያካትት መደረጉ በሴቶች ላይ የበለጠ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ሰፊ እድል ይሰጣል። አደረጃጀቶቹ በራሳቸው የሚፈልገውን ለመከወን ምቹ ናቸው። በትክክል ከተመሩ ብዙ ለውጥ ለማምጣትም ያስችላሉ። የተሾሙባቸው ሴቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉ መሆናቸውን ካለፈው ሥራቸው ማየት ይቻላል። ሆኖም ይሄን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
በርካታ ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣት ጉዳይ በሰዎች ወይም በፓርቲዎች ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ብቻ ሳይሆን የሴቶችም በመሆኑ ለትግበራው ይረባረባሉ። የኃላፊነት ሚናቸውን ሊወጡበት የሚችሉበት እድልም ከወንዶች እኩል ሊመቻችላቸው ይገባል። አሁን ያለው ተስፋ ሰጪና እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም በቀጣይ በየደረጃው መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ።
‹‹ነገ መሪ የምትሆነዋን ሴት ከታች ከዩኒቨርሲቲ ጀምረን ልናበቃትና ልንሰራባት ይገባል›› ይላሉም። አክለውም በተለይ ስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው አንደኛ ዓመት፤ አንደኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት ካቢኔውን የተቀላቀሉትና በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
አመራሮቻቸው የሚኒስትርነት ማዕረግ ማግኘት የቻሉት ሦስት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ብርቱ አስተዋጾ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ወደ አሸናፊው ፓርቲ መዋቅር ገብተው በጋራ እንዲሰሩ ከተደረገበት አንዱም ይሄንኑ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉትን እገዛ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአጋጣሚ ወደ ካቢኔው የመጡት ሦስቱም አመራሮች ወንዶች ናቸው። ይሁንና ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በገዢው የብልፅግና ፓርቲና ከታች ጀምሮ እየተካተቱ መምጣት አለባቸው። የፖለቲካ መርሐ ግብራቸውና ደንባቸው መጀመሪያ ሴቶችን ማሳተፍና ከጅምሩ ልምምድ እያደረጉ እንዲመጡ ማድረግ ይኖርበታል። ፓርቲዎቹ የሴት አባላቶችም ሆኑ አመራሮች ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ሙና በነዚህና በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ከተሾሙት ሴትና ወንድ የካቢኔ አባል አመራሮች ብዙ አስተዋጽኦ ይፈለጋል። ህዝቡም ሊያግዛቸው ይገባል። እንዲህ በጋራ በመሰራቱም አዲስ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል። ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገርም የጋራ ሥራው መጠናከርና ዘላቂ መሆን አለበት በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት ዶክተር ምሥራቅ መኮንን የምክር ቤቶች የሴቶች ውክልናና ተሳትፎ፤ በዚሁ ምክር ቤት አመራርነት ያላቸው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ይገልፃሉ። የመጀመሪያው ምርጫ አካባቢ ስምንት በመቶ፤ መካከል ላይ ደግሞ 16 በመቶ አካባቢ ደርሶ የነበረ መሆኑንም ያወሳሉ።
በአምስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከ40 በመቶ በላይ ሴቶች ወደ ምክር ቤቱ የመጡበት ሁኔታ መኖሩንና ተሳትፏቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። እንደሳቸው በ2013 ዓ.ም ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ወደ ምክር ቤቱ መግባት ችለዋል። አሁን ላይ ምንም እንኳን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ተጠናቅቆ 547ቱ ወንበሮች በማን እንደተያዙ ባይለይም አሁን ከተያዘው 427 ወንበሮች ውስጥ 180ዎቹ በሴቶች ተመራጮች መያዛቸውን ያነሳሉ። ከዚህ ተነስተውም አሁን ያለው የሴቶች የምክር ቤት ተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱንና በምክር ቤቱ በአመራር ደረጃ የነበረው ተሳትፏቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ይጠቅሳሉ።
‹‹ሩቅ ሳይኬድ የ2013 የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የነበራቸውን ተሳትፎ ብቻ ለማሳያነት ማንሳቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል›› የሚሉት ዋና ፀሐፊዋ ከ60 በመቶ በላይ ቋሚ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ሴቶች የምክር ቤት አባላቶች እንደነበሩም ያወሳሉ። እነዚህ ሴት አባላት ሥራቸውን በሚገባ ሲወጡ የነበሩና ለአዲሱ ምክር ቤት እያሸጋገሩ ያሉ ናቸው ብለዋል።
‹‹የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም›› የሚሉት ዶክተር ምሥራቅ በብቃትና በጥንካሪያቸው መመስረቱን ያሰምሩበታል። ፓርቲዎችና መንግስት የሴቶች መሳተፍና ወደ ምክር ቤቱ መምጣት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን እየተገነዘቡ በመምጣታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ያብራራሉ። የሴት ሚኒስትሮች ካቢኔ አባላትን ጾታ ስብጥር ለምን እንደ ፊቱ አልተመጣጠነም ስንል ለጠየቅናቸው የሰጡን ምላሽም አነሰ በዛ የሚለው በጣም አጥቦ ከማየት የመጣ ነው። የመንግስት የሥልጣን ቦታዎች ሚኒስትሮች ብቻ ሳይሆኑ በየደረጃው ሴቶችን ያሳተፉ ቦታዎችና ኃላፊነቶችም መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚሻም ይመክራሉ።
አንዳንዶቹ ከሚኒስትርነት በላይ ክህሎትና ዕውቀት የሚጠይቁም እንደሆኑ ያወሳሉ። እንዲህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ በየደረጃው በሚኖሩት የተቋም ኃላፊነት ቦታዎች የሴቶችና የወንዶች ቁጥር እንዲመጣጠን እንደሚያደርጉም ይጠቅሳሉ።
‹‹ሴቶች ከወንዶች የሚያንሱበት የለም›› ሲሉም በባህርያቸው ተደራራቢ ኃላፊነቶችን ይዘውም መሻገር እንደሚችሉም እሳቸው ወደ አመራርነት ሲመጡ መንትያ ልጆች ይዘው እንደነበርና ከሥራቸው ስኬታማነት ጎንም ልጆቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት ማብቃታቸውን አብነት ያደርጋሉ። ሴቶች ተደራራቢ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይተጋሉ ይፈራሉ። ሥራውን ፈርተው ነው የሚሰሩትም ሲሉ ሃሳባቸውን ያሳርጋሉ።
እኛም ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› እንዲሉት በየትኛውም መንገድ ቢሆን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው እንመክራለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014