ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ህዝቡ የሌሊት ቁርና ዝናብ ሳይበግረው በነቂስ በመውጣት ድምጹን ለመረጠው ፓርቲ ሰጥቷል። ለምርጫውም የተለያዩ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ተወዳድረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤትም የብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ አግኝቷል። ለቀጣዩ አምስት ዓመታትም ገዢውን ጨምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን አግኝተዋል።
በኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር የህዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው። ምክር ቤቱ ህጐችን የማውጣት የህግ አስፈጻሚው አካል የሚያወጣቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የማጽደቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የፌዴራሉ መንግስት ባለስልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የአስፈጻሚውን አካል አሰራር የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል። የፌዴራል መንግስት ፍርድ ቤት ዳኞችን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን፣ የኮሚሽነሮችን የዋናው ኦዲተርን የመሳሰሉ ኃላፊነቶችም የሚጸድቁት በዚሁ ምክር ቤት ነው።
ምክር ቤቱ አጠቃላይ በሚያወጣቸው ህጎች በኩል የአገሪቷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ አኗኗሮችን ዕጣ ፈንታም ይወስናል። ተመርጠው ምክር ቤቱን የሚቀላቀሉ አባላትም የህዝብ ወኪል እንደመሆናቸው በሃሳብ ሙግት የአገር እና የህዝብ ድምፅ ከፍ አድርገው ጥቅምና ፍላጎትን የሚያሰሙ ናቸው።
ቀደም ባሉት ዓመታት ስለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮ ምክር ቤት በተለምዶ ፓርላማ ድባብ በተለይም ስለ ቤቱ አባላቱ አቅምና አቃም ሲነሳ ሁለት አይነት አስተያየቶች ይደመጣል።አንዳንዶች ‹‹አባላቱ የሚፈለገው ያሕል ሰራተዋል ለማለት ባያስደፍርም የበኩላቸውን ተወጥተዋል››ይላሉ።
በርካቶች በአንፃሉ ከዚህ ቀደም በነበረው ፓርላማ ‹‹የትኛውም ሃሳብ ይቅረብ፣ የትኛውም ህግ ይርቀቅ የይስሙላ ተወካይ የሆነና እጅ ለማውጣት ብቻ የሚገቡ ብሎም እንቅልፋቸውን የሚተኙ የህዝብ ተወካዮች ያስመለከተን ነው›› ይላሉ።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ የፓርላማ አባላት ከቀናት በፊት ስራቸውን በይፋ ጀምረዋል። በገዢውም ሆነ በተፎካካሪ እንዲሁም በግል ለአገራቸውና ለወገናቸው በጎና ቀናኢ ራእይ ያላቸው ግለሰቦች ፓርላማውን ተቀላቅለው ተመልክተናል።
በርካቶችም በሚቀጥሉት ዓመታት የተሻለ የሚያስቡ፣ የተሻለ የሚናገሩ፣ የተሻለ የሚሰሩ ሊሂቃን ፓርላማ መግባታቸውን እየገለፁ ናቸው። በቆይታቸውም ባላቸው አቅምና ችሎታ ልክ አገራቸውን እንደሚያገለግሉ እርግጠኛ መሆናቸውን ሲገልፁ እየተደመጠ ነው።
በተለይ ፓርላማው የሃሳብ ሙግት የሚስተናገድበትና ሃሳብ አሸንፎ የሚወጣበት እንደሚሆን እምነታቸው እየገለፁ ናቸው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ልብ›› ያለው ፓርላማ እየተፈጠረ መምጣቱን መመልከታቸው ለዚህ እሳቤያቸው ማጠከሪያ አድርገው ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።
ለመሆኑ ቀደም ሲል የነበረውን የፓርላማ ድባብና አባላቱን አፈፃፀም እንዴት ይታወሳል? በአዲስ መንግስትስ ምን አይነት የፓርላማ ድባብ ይጠበቃል ?፣ አባላቱስ ሚናቸው እንዴት ሊሆን ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎች በማንሳት እንዲመልሱልን የተለያዩ ምሁራንን አናግረናል።
በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን እንዲያጋሩን ከጠየቅናቸውን ምሁራን መካከል የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ፀጋዬ ደመቀ አንዱ ናቸው። የህግ ምሁሩ እንደሚያስረዱት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻውን የአገሪቱን ስልጣን የያዘ ነው። አባላቱ ፓርላማ ገብተው የሚቀመጡት የመረጣቸውን አካባቢ፣ ፓርቲ ወይንም ህዝብ ሳይሆን ኢትዮጰያን ወክለው ነው። የአባላቱ ስራም የህዝብና የአገርን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ነው። አጠቃላይ የመንግስት አስተዳደሩንም የሚቆጣጠሩ ናቸው።
‹‹ሰው ሁሉ እኩል ነው አንዱ ግን ከአንዱ ይሻላል፣ በአስተሳሰብ በንግግር ተፅእኖ በመፍጥር ሁሉም አኩል አይደሉም። ሁሉንም ለማለት ባያስደፍርም፣ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች የተሻሉ አልነበሩም›› የሚሉት አቶ ፀጋዬ፣ ለእጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦችም ፍትሃዊ ተአማኒና በሆነ ምርጫ አቅምና ብቃታቸው መሰረት የእውነት ተወዳድረው የእውነት አሸንፈው የተመረጡ እንዳልነበሩም ያስታውሳሉ።
ይህ እንደመሆኑም እጅግ በጣም ደካማ፣ በርካታ ቀልዶች የሚስተዋልበት፣ የህዝብን ጥያቄ ከማስተጋባት ይቀልኑ ከሁሉም በላይ ደግሞ እጅግ በሚያስተዛዝብ መልኩ እንቅልፍ ሁሉ ሳይቀር ይተኙ እንደነበር የሚያስታውሱት የህግ ምሁሩ፣ በአብዛኛው የይስሙላ ህዝብ ተወካይ በመሆናቸው የትኛውም ሃሳብ ይቅረብ፣ የትኛውም ህግ ይርቀቅ እጅ ማውጣት እንጂ የወከላቸው ህዝብን ጥያቄ የሚያቀርቡ ብሎም መብቱንም የሚያስከብሩ አልነበሩም›› ይላሉ።
አዲስ የፓርላማ አባላት በቀጣይ አምስ ዓመትት ቆይታ በሁሉ ረገድ ፍፁም ሆነው ይታያሉ የሚል እምነት ባይኖራቸውም ከቀድሞ የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር የሌላቸው የህግ ምሁሩ፣ ከአዳዲሶቹ የፓርላማ አባላቱ መካከል የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና የግል እጩዎች መኖራቸውን ቀጣዩን የምክር ቤት ቆይታ የተለየ ድብብ እንደሚሰጠው ይጠቁማሉ። ‹‹ምክር ቤቱን የተቀላቀሉት አንዳንድ ግለሰቦች አቅምና ብቃት እንዲሁም ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው መሆናቸውም አዲሱን ፓርላማ ቀደም ሲል ከነበረው በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል ነው›› ያሉት።
የአዲስ ፓርላማ ድባብ ከወትሮ በተለየ ለህዝብ ጥያቄና መብት የሚቆም በዚህ ሂደትም፣ አስደማሚና የሞቀ ውይይት፣ የሃሳብ ሙግትና ፍጭት የሚታይበት ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁና ይሆናልም የሚል እምነት እንዳላቸው ነው የገለፁት።
በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን ያጋሩን ሌላኛው ምሁር፣በፈረንሳይ ፓሪስ ‹‹school of advanced studies in social sciences Paris –/EHESs/የፒኤች ዲ ተማሪ የሆኑት ጌታነህ ውድነህ ናቸው። አቶ ጌታሁን፣ ‹‹የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓርላማ የአገርና የህዝብ ጥያቄን ፍላጎት የሚወክልበት ነው። ምክር ቤት ውስጥ መግባትም ከባድ ሃላፊነት ነው። አንድ ዕጩ በቆይታው የወከለውን ህዝብ ፍላጎት በፓርላማ በሚወጡ ህጎች ደንብና መመሪያዎች በአግባቡ እንዲወከል ማድረግ የግድ ይለዋል››ይላሉ።
ቀደም ሲል የነበረው ፓርላማ እንቅልፋም የሆነበት ምክንያት ምን ይሆን? በሚል ለሚነሳው ጥያቄ፣ አቶ ጌታነህ በሰጡት መልስም፣ ጥያቄው በጥያቄ የሚመለስ መሆኑን ያብራራሉ፡
እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፣ የአንድ አገር ፓርላማ ጥንካሬና ድክመት የሚለካው በምርጫ ነው። ተአማኒነት ያለው እውቀትና ሃሳብ ሸጦ በፓርላማ መቀመጫ ያገኘ እጩ የተቀመጠበት ወንበር ዋጋው ይገባዋል። ይሁንና ምርጫ የእውነትም ምርጫ ካልሆነ ግለሰቦች ለምን ምክር ቤት እንደጠቀሙራሱ ጠንቅቀው አይረዱም።
አንድ አባል ትክለኛው መንገድ የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ ለመግለጽ የተወከለና የተቀመጠ ከሆነ ፓርላማ ውስጥ ላይተኛ እንደሚችል አፅእኖት የሚሠጡት አቶ ጌታነህ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም ፓርላማ ውስጥ ሲተኙ የተመለከትንበት ዋነኛ ምክንያት የእውነት የህዝብ ተወካይ ነበሩ? በሚል ሌላ ጥያቄን የሚመለስ ነው›› ይላሉ።
አሁንም የፓርላማ የተቀላቀሉ ግለሰቦች ከፓርቲ ይልቅአገርን ማስቀደም እንዳለባቸው ይህ ካልሆነም የቀድሞን መድገም መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ጌታነህ፣ የፓርላማ ክብር ከፓርቲ በላይ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት የግድ ይላቸዋልም ነው›› ያሉት።
በትክክል በህዝብ ተወክሎ ወደ ፓርላማ የገባ አባል መንግስት ሳይቀር ሊቃወም እንደሚችል የሚጠቁሙት ምሁሩ፣ ‹‹የህዝብን ጥያቄና ፍላጎት ለማስፈፀም እስከገቡ ድረስ መንግስትም መቃወም፣ መከራከል ሊኖርባቸው ይችላል፣ ከአዲስ ፓርላማ የምንጠብቀውም ይህን አይነት አቅምና አቋም ነው›› ይላሉ።
አዲሱ መንግስት የተሻሉና እውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ያለበት፣ አባላቱም ለህዝብ ጥቅምና ለመረጣቸው ህዝብ ፍላጎት ተግተው የሚሰሩ ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የሚገልጹት አቶ ጌታነህ፣ ይሁንና ሁሉም ነገሮች በአንድ ጊዜ ይለወጣሉ ብሎ ማሰብም ስህተት መሆኑንም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ የፓርላማ አባላት ከቀናት በፊት የስራ ትውውቅ ስልጠና ወስደዋል። በስልጠናው ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ ተመራጮች ተሳትፈዋል።
ስልጠናው በዋናነት የህዝብ ተወካዮች ሚና፣ የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ እና በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። የስልጠናው ዓላማ የምክር ቤቱ አባላት ስራዎቻቸውን ያለምንም የመረጃ እጥረት እንዲያከናውኑ ማገዝን ዓላማው ያደረገ እንደሆነም ታውቋል።
6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በተለየ መልኩ ነጻ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ያስታወሱት አዲስ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን በነጻነት መስጠታቸውም አገራቸው ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳያል ነው›› ያሉት።
ኢትዮጵያንና የመረጠንን ህዝብ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንና ህዝቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲሁም ሙስናና የህዝብ ሀብት ምዝበራን ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት። ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በፊት በነበረው የምክር ቤቱ አሰራር አባላቱ በሚያነሱት ሃሳብ ይገመገሙ እንደነበር አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ በምክር ቤቱ አሰራር የተሻለ ነጻነት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቅሰዋል። አባላቱምአግባብ በሆነ መንገድ የፈለጉትን ሃሳብ የማንሳት ነጻነት እንዳላቸውም ነው ያስታወቁት።
ምክር ቤቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተጀመሩ መልካም ስራዎችን በማስቀጠል ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ እንደሚያገለግልም አውስተው፣ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻለ ነጻነት ኖሮት ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም የትኛውም አይነት ሃሳብ የሚነሳበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
በርካቶችም ቀጣዩን አምስት ዓመታት የፓርላማ አባላት ቆይታ በሚመለከት ለሚነሳላቸው ጥያቄ ከሚሰጡት መልስ የፓርቲ ተመራጮች ከሚበዙብት ፓርላማ ከፓርቲ ውግንና የወጣ ነፃ የሆነ አቋም ይንጸባረቃል የሚል እምነት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል።
የአዲስ የፓርላማ አባላት በቀጣይ አምስት ዓመታት ቆይታቸው፣ ለህሊናቸው ፣ለመረጣቸው ህዝብና ለህገ መንግስቱ መገዛት ግድ ይላቸዋል። የፓርቲ ፕሮግራምን ለማስፈፀም ከመሽቀዳደም መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ከምንም በላይ ቅድሚያ ለፓርቲዬ የሚል አስተሳሰብን ማስወገድ የግድ ይላቸዋል።
አዲሱ መንግስት አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ከአጋጠማት የተለያዩ ፈተናዎች አንጻር ብዙ የቤት ስራዎች የተለያዩ ተግባራትና ሃላፊነቶች ይጠበቅበታል። የትኛውም መንግስት ቀዳሚ ተግባር የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ ሰላምን ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ በመሆኑ ቀዳሚ አጀንዳ በአገሪቱ ላይ ሰላም ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም ተሰምሮበታል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ አዲሱ የመንግስት ምስረታ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በደመቀ መልኩ ተካሂዷል። ከቀናት በፊትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባውን ማካሄዱ ይታወሳል።
በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቅርጽና ይዘት ያላቸው ቢሆንም የህዝብ ውክልና ሥርዓት የዘጠና ዓመት ልምድ ያላት መሆኑን አስታውሰዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃም፣ ፓርላማ ሥልጣኑንና ሉዓላዊነቱን የሚያገኘው በቀጥታ ከሚወክለው ህዝብ ነው። ከሥልጣኑም ቀዳሚ የሚሆነው የህዝብ ውክልና ነው። የህዝቡ ፍላጐት፣ ዓላማዎች፣ ችግሮች ወዘተ ድምጽ የሚያገኙት በተወካዮቹ አማካኝነት ነው። ለዚህም የፓርላማ አባል፣ የመረጠውና የሚወክለው ህዝብ መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖር መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
መንግሥት ለህዝቡ ተጠያቂ መሆንን ያጠናክራል። ተጠያቂነት ደግሞ ለዴሞክራሲ ግንባታ የማይታለፍ ጉዳይ ነው። ፓርላማ የህዝብን የልብ ትርታ ለማወቅ እድል ያለው ነው። በየጊዜው እያደጉ የሚመጡ የህዝቡ ፍላጎቶችን በጊዜ ለመለየት ይረዳል።
‹‹ምክር ቤቶቹ የህዝቡ ስሜት የሚንፀባረቅበት፣ የሚስተጋባበት የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የሚፋጩበት፣ ተከራክሮ የሚያሸንፍበት ቦታ መሆን ይጠበቅባቸዋል›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ። ጠንካራ ፓርላማ ለመልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ለዜጎች መብት መከበር ዋና መተማመኛ ስለመሆኑም አፅእኖት ሰጥተውታል።
‹‹ከተመዘገበው ህዝብ መካከል በብዛት ወጥተው ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱት ዜጎች ድምጼ ይቆጠርልኛል በማለት ነውና ተመራጮች ቃል የገቡትን መፈጸማቸውን በቅርብ እንደሚከታተሉ እሙን ነው። ፓርላማ በአንድነት የያዘን ሰንሰለት እንዳይናጋና እንዳይፈርስ ማድረግ ቀዳሚ ኃላፊነቱ ነው›› ነው ያሉት።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014