በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዓለም ሀብት ከግማሽ የሚበልጠውን በባለቤትነት የያዙት 85 ግለሰቦች ናቸው። በዓለማችን ውስጥ 85 እጅግ በጣም ሀብታም ግለሰቦች የ3.5 ቢሊዮን ድሆችን ሀብት ተቆጣጥረው ይዘዋል ማለት ነው (ፎርቢስ መጽኤት ጥር 20014)።
የሰው ልጅ የምቾት ረሀብተኛና ለእራሱ ምቾት ሲል ለብዙ ሰዎች የሚሆንን ሀብት ለማጋበስ እና ለመቆጣጠር የሚሮጥበትን አንዱ አንዱን የሚጥልበትን ፣አልፎም በሀገር ደረጃ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነት ለማሳየት የሚሻኮቱበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ተዘርግቷል። ሥርዓቱ ለፈርጣሞቹ የፈጠረላቸው እድል ደካማውን በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት እና ለመቀራመት የሚሩጡበት መሆኑንም በተጨባጭ እያየነው ነው።
የዚህ የኢኮኖሚ ሥርዓት ሃሳብ አመንጪ አዳም ስሚዝ ቢሆንም ፤ አሁን ያለው እውነታ ግን ካሰበውና ከገመተው ውጪ መረን ወጥቷል። በ16ኛው እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ምእራብ አውሮፓ በዋናነት በእንግሊዝ የታየው ካፒታሊዝም ወይም ግል መር (ገበያ መር) የሆነው የካፒታሊዝም ሥርዓት በእስኮቲሻዊው ፖለቲካል ኢኮኖሚስት አዳም ስሚዝ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። የኢንዱስትሪን መስፋፋት፣ የቴክኖሎጂ መፈልሰፍን በዚህም ከፍተኛ የስራ እድል ከቅናሽ የምርት ዋጋ ጋር በውድድር ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል እና በግለሰቦች ያልተገደበ ፍላጎተት እርካታ ውስጥ የህብረተሰብን እርካታ ማግኘት እንደሚቻል በዋናነት the wealth of nation በሚለው መጽሀፍ ውስጥ አትቷል።
የዚህ ሃሳብ ዓላማ በግርድፉ ማህበረሰባዊ ሀብትን በየግል ፍላጎት ውስጥ ከፍ ማድረግ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። እርግጥ ነው በአውሮፓም ይሁን በአሜሪካ ይሄ ሥርዓት ከሞላ ጎደል ዓላማውን አሳክቷል ማለት እንችላለን። ነገር ግን አሁን ላይ ሥርዓቱ ከአዳም ስሚዝ ግምት ውጪ አፈንግጦ ሀገራዊ ለውጥን ሳይሆን ግለሰባዊ (ሀያላዊ) ለሆነው አስተሳሰብ እጅ በመስጠቱ እና መረን በመልቀቁ የታሰበለትን ዓላማ እየሳተ ይገኛል።
በዋናነት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለግለሰቦች ትርፍ እና ጥቅምን በሚያሳድዱ አልጠግብ ባይ አጋሰሶች በግልጽ እንዲመራ እንዲወሰን በብዙሃኑ ላይ ይሾማቸዋል። በተለይም በአውሮፓ ሜዳ የተጀመረው ጨዋታ ወደ አፍሪካ ሲመጣ የአንዲትን ሀገር ሀብት የሆነውን መሬት፣ የሰው ሃይል እና መዋለ ነዋይን እነርሱ በሚፈልጉት ታክቲክ እና ቴክኒክ እንዲፈነጩበት እና የሀብታቸው ምንጭ ለሆኑት ለብዙሃኑ ቁራሽ እየጣሉ እነርሱ በሀብት ላይ ሀብት በንብረት ላይ ንብረትን ለማፍራት የሚያስችላቸውን ማሳለጫ መንገድ ሰርተውበታል።
እርግጥም ታላቅ ኢኮኖሚን በዚህ ሥርዓት መገንባት ችለዋል ፤ ማለትም ሥርዓቱ ሊያመጣ የሚችለውን ልዩነት መቶ በመቶ ባይሆንም ተቆጣጥውታል። ምክንያቱም የሥርዓቱ ዓላማ ቢያንስ መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ እንዲበዛና ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል እንዳይኖር የመካከሉም ወደ ላይኛው የሚመጣበትን የኢኮኖሚክስ ኢንጅነሪንግ ሰርተው ጨርሰዋል።
ምንአልባትም ሁሉም ዜጋ ውስጥ ለሀገር እና ለህዝብ ታላቅነት መስራትን በሚገባ ስላሰረጹም ይሆናል። ታዲያ ይሄንን የቤት ስራቸውን የጨረሱቱ አማላይ እና አብረቅራቂ በሆነው ኢኮኖሚያቸው አፍሪካውያንን እያታለሉ ያልተነካውን ሀብት መቀራመት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ከጀመሩ ቆይተዋል። ይሄም ቀድሞ በሀብቱ ላይ ለጥ ብሎ ለተኛው ለእንደኛ አይነቱ ሀገር ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ጥቂቶችንም ከእንቅልፋቸው አንቅተው የብዙሃን ሀብት ላይ እንዲራወጡ የሸፍጥ መንገዳቸውን ከፍተው የሄንን ሀብት ለማጋዝ ምቹሁኔታን ፈጥረዋል።
ታዲያ ያገሬ ሰው እኔ ሳልበላ ለወዳጄ ለጎረቤቴ የሚል እና በአንድ ተካፍሎ መብላትን ክብ እንጀራ ከቦ መጎራረስ የሚያውቀው በዚህም ለዘመናት የኖረውን ይሄ መጤ ሥርዓት ድንብርብሩን አውጥቶታል። በጥቅም ፈረስ እየጋለበ የመረጋገጥ፣ የመጠላለፍ፣ የመጠላላትን ክፉ ድርጊት አምጥቶበታል። ሰው መቼም እንደ ቤቱ እንጂ እንደጎረቤት እንዴት ይኖራል … ።
ሀገራችን የሚቀናባትን ማህበራዊ የትስስር እሴት ይሄ ሥርዓት እየገዘገዘው መሆኑን እናም በጣጥሶ ሊጥለው መቃረቡን ስንቶቻችን ልብ ብለነው ይሆን…. ወይስ ፊት ለፊት ስንጋፈጠው ለኖርነው የቅኝ ግዛት እጃችንን እየሰጠን ይሆን ? እኔ እጠቃለው…. በቅኝ ግዛት ዘመን እኮ አባቶቸችን በቀኝ ላለመገዛት አጥንታቸውን የከሰከሱት ደማቸውንም ያፈሰሱት ቅኝ ገዥው ጥርሱን ያገጠጠ ቀንዱን ያቆመ አውሬ ስለሆነ አይደለም፤ ክብራቸው አንዳይደፈር፣ ማንነታቸው እና ባህላቸው በሌላ እንዳይበረዝ፣ ሃይማኖታቸው አንዳይሻር፣ እነርሱ የመሰረቷት ያቆሟትን ሀገር ከነክብረዋ እና ከነባህሏ ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ ነው ።
ቀደምት የኪነ ህንጻ፣ የፍልስፍና፣ የንግድ ሥርዓት የነበራት ሀገሬ ዛሬ ላይ በሌሎች ጭንቅላት እንድታስብ ማነው ያስገደዳት? እዚህ ላይ መልካሙን ከሌሎች መውሰድን መማርን ለመንቀፍ እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳልኝ። ነገር ግን ከሌላ ያመጣነውን ከእኛነታችን ጋር አስማምቶ እና አዋድዶ መሄድን ለማመለከት እንጂ ፤ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዲሉ አበው ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና የካፒታሊዝም መርህ ለሁሉ የሚበቃ ምርትን የማምረት አቅም መፍጠር፣ ለብዙሃን የስራ እድል ማስገኘት የሚያስችል ሥርዓት መሆኑ እውን ሆኖ ሳለ ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ እንዴት ይህንን ውጤት ማየት ተሳነን? እኔ እጠይቃለሁ።
በሀገራችን ተመርተው ማለትም በሀገር ውስጥ በቂ ሀብት ያሉንን እንኳን በገዛ የሀገራችን ዜጋ ስግብግብነት እና ልላዊነት በፈጠረው የጥቅም መስመር ምክንያት ለገዛ የሀገራችን ዜጋ ሱሚ(የማይቀመስ) የሆነበት ምክንያት እና በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እየተበራከተ የመጣው ኢንቨስትመንት ተቀጣሪ ሰራተኞቹን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ሊያወጣቸው አለመቻሉ የሆነ ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ ያሳያል።
ካፒታሊዝም መንግስትን ከንግድ እና ሂደቱ ውጪ አድርጎ ታክስን እንዲሰበስብ እናም በታክስ ገቢ የሀገሪቱን መሰረተ ልማት እንዲገነባ ማለትም ከላይኞቹ ሰብስቦ የታችኞቹን መደጎም በግርድፉ ማለት እንችላለን የሚፈጸምበት ሥርዓት በመሆኑ በአውሮፓ ይሁን በአሜሪካ ይህንን እያንዳንዱ ዜጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ እንዲሁም የታክስ አከፋፈል ሥርዓቱ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ከፍተኛ ግብርን [progressive] የመሰብሰብ ሥርዓትን በሰለጠነ እና አግባብነት ባለው መልኩ ስለሚሰበሰብ አልፎ አልፎ ካልሆነ በምንም አግባብ ስህተት አይፈጸምም።
ግብርንም የሚከፍለው ዜጋ በኩራት የሚጣልበትን ግብር ያለ አንዳች ማቅማማት ይከፍላል፤ የሚከፍለውም ግብር ዋጋ ምን ያህል ለሀገሪቱ እድገት ለማህበረሰቡ ጥቅም እንዳለው ጠንቅቆ ያውቃል፤ የሚያሳዝነው በእኛ ሀገር ወይም እንደ አፍሪካ የግብር አሰባሰብን ብንመለከት ኋላ ቀር የአሰባሰብ ዘዴ ያለው እና በሙስና የተጨማለቀ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። አንዳንዱ ሁለት ጊዜ ታክስ ይከፍላል [double taxation] ያውም ደሞዝተኛ ሆኖ ሌላው ግን ያጭበረብራል። ዘመናዊ በምንለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ ሌሎች ባመጡልን የኢኮኖሚ ሥርዓት ስንመራ ቆይተናል። የዕዝ ቅይጡንም አራምደነዋል ።
አሁን ግን በግልጽ የየትኛው የኢኮኖሚ ሥርዓትን እየተከተልን ነው? እኔ እጠይቃለሁ። መቼም ዓለም ሁሉ የሚኖርበትን ሥርዓት መተግበሩ ባልከፋ፤ ነገርግን እነርሱ በተጠቀሙበት ደረጃ ተጠቅመንበታል የሚለውን ግምገማ መውሰድ ተገቢ ነው።
የሀገራችን ሁኔታ፣ የህዝባችን ለሥርዓቱ ያለው አመለካከት ከባህል፣ ከአኗኗራችን አንጻር ምን ያህል ተቀባይነት ወይም ውጤት አስገኝቷል? በመጨረሻም ይሄ ዓለም የሚያቀነቅነው እና ሃያላኑ በአፍሪካውያን ሜዳ ላይ የሚሽቀዳደሙበት ብሎም የሚፋለሙበት የኢኮኖሚ ጦርነት ለእኛ ከሜዳነት ያለፈ ምን ያተርፈናል? ይሄውም ጦርነት ከፍ ብሎ የጦር መሳሪያ አቅም ማሳያ እና የዝሆኖቹ መፋለሚያ አድርጎ የስንቱን ምስኪን ቤት ረጋገጠ? ስንቱንስ ከዬው አፈናቀለ? ቤት ይቁጠረው ።
ይህን መሰል ሥርዓት አመንጪ ኢኮኖሚስቶች በዓለም ያለው ሀብት ውስን መሆኑን እና የሰው ልጅ ፍላጎት ግን ያልተወሰነ በመሆኑ ያለውን ሀብት እና የሰውን ፍላጎት ለማመጣጠን የሚሰሩ ባለሙያዎች በመሆናቸው የሀገር ሀብት በተወሰኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር ሲውል ከኢኮኖሚያዊ እሳቤ ውጪ ስለሚሆን በየግላቸው የተሻለ የሚሉትን ሃሳብ (ፍልስፍና) ሲጽፉ፣ ሲናገሩ ሰምተናል። የካፒታሊዝም ሥርዓት እሳቤ አመንጪ የሆነው አዳም ስሚዝ ይሆናል ብሎ ከገመተው ውጪ ሥርዓቱ መረን መልቀቁን አጽንዖት ለመስጠት የወደድኩት የፈረጠሙቱ ካፒተሊስቶች ጥቅማቸውን በእኔ እና ባንተ ህይወት ስለሚያወራርዱ፤ አንዱ የሌላኛውን አቅም የሚፈጥንበት፤እኛም ቃላቸውን እንደ ወንጌል ከመቀበል ያለፈ ከእራሳችን አንጻር መቃኘት አልቻልንም።
ይህ እንደ ሀገር ተግዳሮት የሆነብን እውነታ ከሀገር መሪዎች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የማህበረሰበብ አንቂዎች ድረስ ሊያስቡበት የሚገባ ለመፍትሄውም የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። የለውጡ ሃይልም ይህንን እውነታ በአግባቡ ተገንዝቦ የሚያሻግረንን ሀገራዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ መቃኘትና በቁርጠንነት መተግበር ይጠበቅበታል።
ልጅ አብይ ተኮላ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014