ኢትዮጵያ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን አብሪት እና በመከላካያ ሰራዊቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች። ይህ ሲሆን የዓለም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና አርአያ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቀምጡት ምእራባውያንና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በአንፃሩ የሽብር ቡድኑ የእብደት ተግባር እና ጥፋት አልታያቸውም።
ይልቁንስ ከህግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ ምእራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ፍጹም ሀሰተኛ መረጃዎች በማስተጋባት ተጠምደዋል፤ ከተለያየ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ማስጨነቅ፣ መክሰስ፣ ማሸማቀቅና መወንጀልን ተያይዘውታል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈዋል። በውክልና ጦርነት ሳይቀር እጃቸውን እያስረዘሙ ሊያዳክሟት ተነስተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየፈርጁ የተለያዩ አሉታዊ ሪፖርቶች እያቀረቡባት ነው።
ለዚህ ዓላማቸው ማስፈፀሚም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ደጀን አድርገዋል። በመገናኛ ብዙሃን ‹‹ፕሮፓጋንዳ›› ዘመቻም ጥይት የጣለውን አሸባሪ ቡድን ህይወት ለማዘራት፣ የኢትዮጵያን እጅም ለመጠምዘዝ እየተጉ፤ እየታተሩ ናቸው።
ስለ ፕሮፓጋንዳ የተለያዩ ጸሃፍት አያሌ ማብራሪያዎችን መስጠታቸው ይነሳል። ከእነዚህ ምሁራን መካከልም፣ ፕሮፌሰር ጋሬዝ ጃውትና ፕሮፌሰር ቪክቶሪያ ኦዶኔል ተጠቃሽ ናቸው። ምሁራኑ እኤአ በ2011 ‹‹Propaganda and Persuasion››በሚል ርእስ አንድ መፅሃፍ ለንባብ አብቅተዋል።
በመፅሃፋቸውም፣ ፕሮፓጋንዳ መረጃዎችንና ሃሳቦችን ሆን ብሎ በስፋት በማሰራጨት አንድን ግለሰብ፣ ቡድን፣ ተቋም፣ድርጅትና አገር ለመደገፍ ወይም ለመቃወምና ለማጥላላት በድግግሞሽ የሚሰራጭ የመረጃ ቅስቀሳ ዘዴ እንደሆነ በስፋት አትተዋል።
ሌሎች ስመጥር የኮሚኒኬሽንና ፖለቲካ ፀሃፍትና ምሁራንም፣ ፕሮፓጋንዳን በአይነትና በዓላማው በመከፋፈል በሶስት ይመድቡታል። ከሶስቱ ፕሮፓጋንዳ አይነቶች አንዱና እጅግ አደገኛው ደግሞ ‹‹ጥቁር ፕሮፓጋንዳ ‹‹Black propaganda›› የሚባለው ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
‹‹ትልቁ ውሸት›› በሚል ሌላ ቅፅላው የሚታወቀው፣ ይህ አይነቱ የፕሮፓጋንዳ ዘዴ መረጃ ምንጩ የማይታወቅና በሬ ወለደ የፈጠራ ውሸት፣ ወሬ፣ ሀሜትና አሉባልታዎች እውነት አስመስሎ የማናፈስና የማሰራጨት ዘዴ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
የወቅቱ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃንም ስለ ኢትዮጵያ ሲያነሱ በዚህ ‹‹ትልቅ ውሸት›› ተለክፈዋል። የተለያዩ ምሁራን እንደሚያስገነዝቡት ከሆነ ግን፣ መገናኛ ብዙሃንና ‹‹ጥቁር ፕሮፓጋንዳ›› መቼም መቀራረብ የማይገባቸው እሳትና ጭድ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው።
በጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ተሸላሚ የሆነችው (Linda Rey) እንደምትለው፣ የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች የግል ሃሳብና ፍላጎትን የሚያስተጋቡ አይደሉም። ሙያውን የሚያከብር፣ ለዘርፉ ክብር ያለውና በስራው ሃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኛም የራሱን አስተሳሰብ ከሚያስተላልፈው ዘገባ ነጥሎ የሚያቀርብ ነው።
አንድ ጋዜጠኛ ዜና ሲያዘጋጅ መረጃ እና ማስረጃ የግድ ይለዋል። ዘገባውም 5ቱን “W’s” and “H” ማለትም (who, what, when, where, why, how) ማካተትና መመለስ ይኖርበታል። ሚዛናዊነት ደግሞ የስራው ሁሉ ማጠንጠኛ መሆን አለበት።
ከሁሉ የበላይ ነን የሚሉት ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን በአንፃሩ ይህን መርህ እርግፍ አድርገው ትተውታል። በተለይ CNN የተባለ ድርጅት አጭበርባሪ የሆኑ ዜናዎችን በመስራት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማጠልሸት ቆርጦ የተነሳ መስሏል።
ከቀናት በፊትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያ አጓጉዟል ሲል የሀሰት ዘገባን ሰርቷል። ሱዳናዊቷ ዘጋቢም ኒማ ኤልባገር በአየር መንገዳችን ላይ ምናብ -ወለድ የፈጠራ ታሪክ ሰርታለች።
ይሁንና ላለፉት 75 ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተዛማጅ ደንቦችን እና መስፈርቶችን በጥብቅ የሚያከብር ፣በሁሉም የሥራ ክንውኖች ውስጥ ከማንኛውም የሲቪል አቪዬሽን ደንቦች የማይወጣ፣ በጦር መሣሪያ ማጓጓዝ ተግባር ውስጥ ተሰማርቶ የማያውቅ መሆኑን ዓለም የሚያውቀው ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው መግለጫም ይህን በአግባቡ አረጋግጧል።
ይሁንና ሲ ኤን ኤን ኢትዮጵያ ላይ የሚሰራውን ለተመለከተም፣ Jerry B. Blackburn የተሠኘው ግለሰብ ‹‹CNN is no news and simple propaganda›› ሲ ኤን ኤን የዜና ሳይሆን የፕሮፓጋንዳ ምንጭ ሆኗል። ያለው ትክክል መሆኑን በግልፅ ያሳያል።
በበሀገሪቱ ላይ የመገናኛ ብዙሃኑ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በስፋት መከፈቱን አመላካች ነው። ለመሆኑ ይህ ሁሉ ትግልና ድካም ለምንድ ነው? ኢትዮጵያንስ ለምን ማጨለም ፈለጉ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳቱ ተገቢ ነው። መልሱም አጭር እና ግልጽ ይመስለኛል። ዋና ዓላማው አሸባሪውን ቡድን ከሞቱ ለመታደግ ነው።
የተንሸዋረረ እይታቸውም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማሳነስ ባለፈ ምንጊዜም ለአፍሪካውያን የሚቆም ብሎም ነፃነቱን የሚያስጠብቅ መሪና መንግስት ሲፈጠር ማየት እንደማይፈልጉ በአደባባይ የመሰከረ ነው። ኢትዮጵያውያንም ይህንን የሴራ ጥልፍልፎሽ በአግባቡ እየተገነዘቡት መጥተዋል። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አብጠርጥረው እያወቁት ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም ሲ ኤን ኤን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሰራው ዘገባ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭራሽ እንከኑ እየበዛ እና ስውር ፍላጎታቸው እየተገለጠ ያምኑት የነበሩት ሳይቀሩ እየሸሹት ይገኛሉ። በተለያዩመገናኛ ብዙሃን ዘገባ እንደተመላከተውም፣ ባሳለፍነው ዓመት የተቋሙ አማካኝ የቀን ተመልካቾች ቁጥር 950 ሺ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ይህ አሃዝ ወደ 557 ሺ አዘቅዝቋል። ይህም 41 በመቶ እንደማለት ነው። ለተመልካች ምቹ በሚባሉ ሰአታት የሚከታተላቸው ደንበኞች ቁጥርም በአማካኝ ከነበረበት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወደ 770 ሺ አሽቆልቁሏል።
ከዚህ ባሻገር ኒክ አዳምስ የተባለው የፋውንዴሽን ፎር ሊበርቲ ኤንድ አሜሪካን ግሬትነስ መስራችና ፕሬዝዳንት፣ ሲኤንኤን በከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ መግባቱን አጋልጧል። ይህን ተከትሎም ከቀውሱ በተወሰነ ለማገገም ከጁንታው ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለው የሃሰት ዘገባ እንደሚያሰራጭም የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።
ምክንያታቸውም ምንም ይሆን በአሁኑ ወቅት መታወቅ ያለበት አብይ ጉዳይ ቢኖር ‹‹ፕሮፖጋንዳ›› ዘመቻ የምትሸነፍ ኢትዮጵያ ፈፅሞ አትኖርም። ልጆቿም ለውጭ ኃይሎች ግፊያና ጉሽሚያ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በሁሉም ግንባር ንቁና ብቁ ሆነዋል።
መላው ኢትዮጵያውያንም አሻባሪውን ህወሓት ዳግም ፈፅሞ ማየት እንደማይፈልጉ በግልፅ እያስመሰክሩ ናቸው። አሸባሪ ቡድን አሁን ላይ ከመኖር ወደ አለመኖር ተሸጋግራል፤ ጠውልጎ ከስሟል። የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ ቡድን በመጨረሻ የሚፈራው ለውጥ እራት ሊሆኑ ተቃርቧል ይህንን ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም ምእራቡ ዓለም በአግባቡ ሊረዳው ይገባል ።
በአሁኑ ወቅት የሽብር ቡድኑ ፖለቲካዊ ሞቱ ተፈጽሟል። መላ ኢትዮጵያውያንም የቡድኑን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት ከሰራዊቱ ጎንና ከሰንደቅ ዓላማ አጠገብ ቆመዋል። በ‹‹ፕሮፓጋንዳ›› ዘመቻ ሊሸነፉ የሚችሉበት እውነታ ያለው ፤እውነቱን ዋጋ እየከፈሉ ተረድተውታል።
በየዘመናቱ የተነሱ ጠላቶቿን በህዝቦቿ አንድነት እና የጋራ ክንድ እያሳፈረች ዘመናትን የተሻገረችውና ለጥቁሮች የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በልጆቿ የጋራ ብቃት የመወጣት ጉዞ ላይ ነች።
በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ በተለይም የለውጡን ጎዞ ለማሰናከል ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ስለ ኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ለመሆን ባልተገባ መንገድ እየተጓዛችሁ ያላችሁ ሃይሎች ከድርጊታችሁ ልትቆጠቡ ይገባል። የራሳችንን ጉዳይ ለራሳችን ተዉልን ። ለችግሮቻችን በቂ ነን።
ከሁሉም በላይ ከአንድ ወገን እይታ ይልቅ እውነታውን በጥልቀት በመገንዘብ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ሊያጠናክር የሚችል ገንቢ ድጋፍ መስጠት ይጠበቅባችኋል። ይህንን የማድረግም የሞራል ግዴታ አለባችሁ።
ከዚህ ውጪ በፈጠራ ታሪኮችና በጥቁር ፕሮፓጋንዳ ኢትዮጵያን ለማስጨነቅ፣ ለማሸማቀቅ እና ስሟን ለማጠልሸት የሚደረገው ጥረቶች በየትኛውም ሁኔታ እና መመዘኛ የህዝቦቿን የለውጥ ፍላጎት ሆነ የለውጥ ጉዞ ሊያደናቅፈው አይችልም፤ መቼም ቢሆን !
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014