“የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ፣
የህብረ ብሔር ቡቃያ፤
የሰላም ተምሳሌት ዓርማ፣
የቀለሞች ህብር ኢትዮጵያ፤” በሚል የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ህዝባዊ መዝሙር የሚገልጻት አገራችን ኢትዮጵያ፤ መላ ህዝቦቿ በደም አሻራ አትመው ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ ያሻገሯት፤ የገናና እና የህያው ታሪክና ስልጣኔ ባለቤት የሆነች አገር ናት፡፡
በገነነ ታሪኳ፣ በገዘፈ ስልጣኔዋ፣ በማይዋዥቅ የህዝቦቿ ጀብዱና የድል አውራነቷ፣ በነጻነትና አይበገሬነት ታጅባ በቆየችባቸው ሺህ ዓመታት፤ ከፍ ያለ ክብሯን የሚወክልና ከፍ አድርጋ በክብር የምታውለበልበው ሰንደቅ ዓላማም ባለቤት ናት።ይህ ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ዋጋ ተከፍሎባት ጸንታ በቆመች አገር ውስጥ ከፍ ብሎ የሚገለጽ የመስዋዕትነት እና የነጻነት ወካይ ህያው ምልክት ነው።
ባልተቆራረጠ የመንግስት አስተዳደር የምትታወቀው ኢትዮጵያ፤ በዘመናት የመንግስታት ቅይይሮሽ ሂደት ውስጥ ዘልቆ የተጓዘ ባለ “አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ” ቀለም ሰንደቅ ዓላማዋ፤ ለራሷ ብቻ ሳይሆን የነጻነቷን ዱካ ለተከተሉ በርካታ የአፍሪካ አገራት የእኔ ብለው ወካይ ሰንደቅ ዓላማቸው እንዲሆን በሚመቻቸው መልኩ የሚጠቀሙት የነጻነት ምልክት ሆኖ ያለ ነው፡፡
ይህ ከራስ አልፎ ለጭቁን ህዝቦች የነጻነት ምልክት ሆኖ ያለ ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ሊከበር እና ከፍ ብሎ ሊገለጽ የግድ ነው።በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ማክበር እና ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትውልዱ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተከብሯል፡፡
በዚህ መልኩ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ማክበር እና ትውልዱ ስለ ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውቅ መደረጉ ደግሞ፤ የኢትዮጵያን ታላቅነት እና የነጻነት ምድር መሆን እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው።ከዚህ በላይ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚታየውም፣ ከፍ ብሎ የሚከበረውም የአገር ክብር እና ልዕልና ከፍ ሲል መሆኑን እንዲረዳ ያደርገዋል።ይሄን የተረዳ ትውልድ ነው ስለ አገሩ ልዕልና የሚተጋው፤ የሰንደቅ ዓላማው ክብር በአንድነት የሚ ቆመውና የሚዘምረው፡፡
ሰንደቅ ዓላማን ቀን ሰጥተነው እናክብረው እንጂ፤ የሰንደቅ ዓላማ ክብር በጊዜ እና በቦታ ተወስኖ የሚገለጽና የሚከወን አይደለም።ስናከብረውም የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችን እና የነጻነታችን ልምክትም፣ ተምሳሌትም መሆኑን በማወቅ ከፍ ባለ ደረጃ እና ክብር ሊሆን ይገባል።ይህ ሲሆን ትውልዱ ሰንደቅ ዓላማው የአንዲት ኢትዮጵያ፣ ነገር ግን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦች መሰባሰቢያ ጥላና ወካይ ዓርማ መሆኑን ይገነዘባል፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የብሄራዊ አንድነትና የሀገር ፍቅርና ስሜት መገለጫ መሆኑን የተገነዘበ ትውልድ መፈጠሩ ደግሞ፤ ሰንደቅ ዓላማችን በተለይ ለኢትዮጵያውያን የነጻነት፣ የአትንኩኝ ባይነትና የአይበገሬነት አርማ መሆኑ አምኖ ለአገሩ ልዕልናና ለሰንደቅ ዓላማው ከፍታ የበለጠ እንዲተጋ ያደርገዋል። ከዚህም ባለፈ ሰንደቅ ዓላማውን የአገር ፍቅር ማሳያው አድርጎ አንዱ ለአንዱ ውግንናውን የሚገልጽበት መዋደድ፣ መተባበሩንና መደጋገፉን የሚያሳይበት መሰረትም ይሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያን ልዕልና በማግዘፍ፣ የሰንደቅ ዓላማውን ከፍታ ለማጽናት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን ሲባል፤ ሰንደቅ ዓላማችን የመልማት፣ የተስፋና የመስዋእትነት ምልክት መሆኑን አጉልቶ ማውጣት፤ ይሄንኑም ለትውልድ ማሳወቅ የሚያስፈልገው። ሰንደቅ ዓላማችንን ከፊታችን አድርገን ለአገር ልዕልና በአንድ ቆመን ስንሰራ፤ ኢትዮጵያ ትከብራለች፣ ኢትዮጵያ ስትከብር ደግሞ ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ይላል።ለአገራችን ልዕልናና ክብር በአንድ ቆመን ሰርተን የምናገኘው ውጤት እና የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ደግሞ ለአንድና ሁለት አካላት ተለይቶ የሚሰጥ ሳይሆን በሁላችን ጥረት እውን የሚሆን የሁላችን ከፍታ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014