በኦሊምፒክ ማግስት ተወዳጆቹ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ታዋቂ አትሌቶችን እንዲሁም በርካታ ሯጮችን በማሳተፍ እየተካሄዱ ይገኛሉ። ትናንትም በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጣቸውን ጨምሮ በርካታ የማራቶን ውድድሮች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተደርገዋል። በተከታታይ ቀናት የሚደረጉት የአሜሪካዎቹ ቺካጎ እና ቦስተን ማራቶኖች ደግሞ በተለይ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ ውድድሮች ናቸው።
የ125 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው የቦስተን ማራቶን ትናንት የተካሄደውን የቺካጎ ማራቶን ተከትሎ ዛሬ ይደረጋል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ባለፈው ዓመት ያልተካሄደው ውድድሩ፤ ዘንድሮም ከተለመደው ወቅት ወራትን አሳልፎ ነው የሚካሄደው። የዘንድሮ ተወዳዳሪዎች ቁጥር ከቀድሞው የቀነሰ ሲሆን፤ እንዲያም ሆኖ 20ሺ ራጮች በውድድሩ ስፍራ ተገኝተው ሌሎች ደግሞ በኢንተርኔት (ቨርቹዋል) ታግዘው ውድድራቸውን ያደርጋሉ። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮናዎች እንዲሁም በርቀቱ ልምድ ያላቸው በርካታ ስኬታማ አትሌቶችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል።
ከርቀቱ ስኬታማ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊያንም የሚገኙበት ሲሆን፤ የተለመደውን ቀዳሚ የአሸናፊነት ግምትም ማግኘት ችለዋል።
በወንዶች በኩል የሁለት ጊዜ የቦታውን አሸናፊ ሌሊሳ ዴሲሳን ጨምሮ ስምንት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተካፋይ መሆናቸውን በውድድሩ ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ አረጋግጧል። በሩጫው ከሚሳተፉት አትሌቶች መካከልባላቸው ፈጣን ሰዓት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፉት ሶስት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ2ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች ያላቸው ናቸው። 2:04:06 በሆነው ምርጥ ሰዓቱ ከአጠቃላይ ተወዳዳሪዎች ፈጣኑ አትሌት የሆነው አሰፋ መንግስቱ ሲሆን፤ ይህንን ሰዓት እአአ የ2018 ዱባይ ማራቶን ነበር ያስመዘገበው። በመሆኑም ካለው ሰዓት አንጻር አትሌቱ የዚህ ውድድር አሸናፊ ሊሆን ይችላል በሚል እንዲጠበቅ አድርጎታል።
ሌላኛው ባለ ፈጣን ሰዓት አትሌት ለሚ ብርሃኑ ደግሞ 2:04:33 የሆነ ሰዓት አለው። በማራቶን ከፍተኛ ልምድ ያለው ለሚ ለቦስተን ማራቶን አዲስ አይደለም፤ ይልቁንም እአአ በ2016 አሸናፊ ነበር። የዱባይ ማራቶንን
ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሩጫዎች ላይ በመካፈል ስኬታማ የሆነው ለሚ በዚህ ውድድር ላይ የአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ሊሆን ችሏል።
በቦስተን ማራቶን የአራት ጊዜያት ተሳትፎ ታሪክ ያለው ሌሊሳ ዴሲሳ ያለው ፈጣን ሰዓት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠው እንጂ በጎዳና ላይ ሩጫዎች እጅግ ስኬታማ ከሆኑት አትሌቶች መካከል የሚነሳ ነው። እአአ በ2013 እና 2015 የቦስተን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው አትሌቱ፤ እአአ በ2016 እና 2019 ደግሞ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ነበር። ከቦስተን ውጪ በኒውዮርክ ማራቶንም በተደጋጋሚ ስኬታማ የሆነው አትሌቱ በዛሬው ውድድር የተለመደ ድሉን የማጣጣም ሰፊእድል እንዳለው ተገምቷል። በኢትዮጵያ በኩል ደጀኔ ደበላ፣ ከልክሌ ገዛኸኝ፣ ጽዳት አያና፣ ባየልኝ ተሻገር እንዲሁም ጀማል ይመር የሚሮጡ ሌሎች አትሌቶች ሲሆኑ፤ ከኬንያዊያን ከባድ ፉክክር እንደሚገጥማቸውም ይጠበቃል።
በሴቶች መካከል በሚደረገው ፉክክርም ፈጣን ሰዓታቸው ከ2ሰዓት ከ22 ደቂቃ በታች የሆኑ ዘጠኝ ታዋቂ ሴት አትሌቶች ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ታውቋል። በዚህ ውድድር ላይ 10 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሲሮጡ ዘጠኝ የሚሆኑት ከፈጣኞቹ መካከል ናቸው።
ባላት ፈጣን ሰዓት ቀዳሚውን የአሸናፊነት ግምት ያገኘችው የብርጓል መለሰ 2:19:36 የሆነ ሰዓት አላት። እአአ በ2015 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የነበረችው እንዲሁም በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ማሬ ዲባባ ሌላኛዋ ባለፈጣን ሰዓት አትሌት ናት። እአአ በ2012 ሶስተኛ በወጣችበት የዱባይ ማራቶን 2:19:52 የሆነ ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች።
ወርቅነሽ ኢዴሳ እና ሱቱሜ ከበደ ደግሞ 2:20:24 እና 2:20:30 የሆነ ምርጥ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ናቸው። በሱ ሳዶ፣ በዳቱ ሂርጳ፣ አጸደ ባይሳ፣ ብሩክታይት እሸቱ፣ ትዕግስት አባይቸው እና ነጻነት ጉደታ ሌላኛዎቹ አትሌቶች ሲሆኑ፤ ቺካጎ፣ ፍራንክፈርት፣ ቶሮንቶ፣ አምስተርዳም፣ ቶኪዮ ቫሌንሺያ እንዲሁም ዱባይ ማራቶኖች ተሳትፎ ልምድ ያላቸው በመሆናቸው ተከታትለው በመግባት ውጤታማነታቸውን ዳግም እንደሚያስመሰክሩም ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014