ዓለማችን አሁን ከደረሰችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሂደቶችን አልፋለች። የሰው ልጅም ጥንት ከነበረበት የጋርዮሽ አኗኗር፣ በኋላም በኢንዱስትሪ አብዮት፤ አሁን ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘመን ያለው የርስ በርስ ግንኙነትና መስተጋብር እንደዘመኑ የተለያየ ነው።
የዓለም ሃገራትም አሁን የያዙትን ቅርጽ ከመያዛቸው በፊት የተለየ መልክ እንደነበራቸው የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ። ለምሳሌ የአንድ ምዕተ ዓመቱን እንኳን ብንመለከት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የነበሩ የዓለም ሃገራት ቁጥር ከሃምሳ የዘለለ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው በአራት እጥፍ አድጎ ከ200 በላይ ደርሷል። ይህ ታዲያ እንደሰው ልጅ እርስ በርስ እየተራቡ ሳይሆን የሰው ልጅ ራሱ በፈጠራቸው የመለያየት አጀንዳዎች የተነሳ ነው።
ከነዚህ ለውጦች ጀርባ የተለያዩ እውነታዎች ይኖራሉ። የተፈጥሮ ሃብትን ለመቀራመት ሲባል ሃገራትን የመከፋፈል እና የመለያየት እንዲሁም የርስ በርስ ስምምነት መታጣት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ለምሳሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓለም ሃያላን ሃገራት በሁለት ጎራ የተከፈሉ ነበሩ፤ ሶቭየት ህብረት እና አሜሪካ። ነገር ግን ሶቭየት ህብረት በድንገት በመፈረካከሷ ከአስር በላይ ሃገራት በአንድ ጊዜ ሊፈጠሩ ችለዋል። ከነዚህ ሃገራት መፈጠር መንስኤም ቀዝቃዛው ጦርነት እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል።
በአፍሪካም የሃገራት ቁጥር እንዲሁ በየጊዜው እያደገ መጥቷል። በቅርቡ እንኳን በዚህኛው ትውልድ ዘመን ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን አዲስ የተፈጠሩ ሃገራት ናቸው። ይሁን እንጂ ሃገራት በተከፋሉ ቁጥር ጥንካሬአቸውን ከማጣት በዘለለ የሚፈይዱት ነገር እንደማኖር እስካሁን ካየነው ተሞክሮ ማየት ይቻላል። በተለያዩ ወቅቶች የተከፋፈሉ ሃገራት በዓለም ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ እየቀነሰ እንደሚሄድ ከተበታተኑ ሃገራት ተሞክሮ ማየት ይቻላል።
ከነዚህ የዓለም ሃገራት መከፋፈል ጀርባ ደግሞ በአብዛኛው የበለፀጉና ዓለምን የመምራት ሃላፊነት የኛ ነው ብለው በራሳቸው ጊዜ በማንአለብኝነት ስልጣን የወሰዱ ሃያላን ሃገራት እጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዳለበት መገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም በአንድም ሆነ በሌላ እነዚህ ሃገራት ሲከፋፈሉ ከጀርባቸው የአሜሪካን አልያም የሸሪኮቿን እጅ እናገኛለን። ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት አሁን ካለው የሃራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማንሳት ፈልጌ ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ያላት ስም ገናና ነው። በተለይ ምዕራባውያን አፍሪካን ለመቆጣጠር በፈለጉባቸው በርካታ የቅኝ ግዛት ዘመናት ኢትዮጵያ የተባለችው አፍሪካዊት ሃገር ለዚህ ምቹ ሆና አለመገኘቷ ብዙዎቹን አበሳጭቷቸዋል። የዓለምን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብም አዛብቷል። ይህ ክስተት ለነዚህ በአፍሪካ ሃብት ለቋመጡ ሃገራት ትልቅ ተአምር ሆኖባቸው ነበር። ከዚህም አልፎ ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለመውረር መጥተው ባልታሰበ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተሸንፈው መውጣታቸው ከሽንፈቱም በላይ ያስተላለፈችው መልዕክት ከባድ በመሆኑ ምዕራባውያን ይህንን አስተሳሰብ ማስወገድ እንደሚገባ በማመን ቀስ በቀስ ስራቸውን ጀመሩ።
ይህንን አስተሳሰብ ለማጥፋት ደግሞ በመጀመሪያ የተጠቀሙት መልሶ መውረርና የኢትዮጵያውያንን ወኔ ማስተንፈስ ነበር። በዚህ የተነሳ ለአርባ ዓመት ተዘጋጅተው ዳግም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ አካሄዱ። ነገር ግን ይህ ሙከራቸውም ሊሳካ አልቻለም። ይልቁንም በዳግመኛው ሙከራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩባቸው አምስት ዓመታት በርካታ ዋጋ ከፍለዋል። ከዚህም አልፎ ዳግም በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማይቻል እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።
በዚህ ጊዜ ሌላ አማራጭ መጠቀም እንደሚገባ አማራጭ ወሰዱ። የመጀመሪያው ስትራቴጂያቸውም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሃገራት ጋር ዘላቂ ሰላም እንዳይኖራት የድንበር ጉዳዮችን አወሳስቦ ማለፍ ነበር። በዚህም መሰረት በወቅቱ በተለይ ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑን ስፍራዎች ሆን ተብሎ በተሰሩ ደባዎች ኢትዮጵያና ሱዳን ሲወዛገቡ የሚኖሩበት የድንበር የውዝግብ ምንጭ መሰረት ተጣለ። ይህ የሆነው ደግሞ በእንግሊዝ እና በጣልያን አማካኝነት ነው።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵውያን ለዘላለም ሲናቆሩ እንዲኖሩ ለማድረግ ኢትዮጵያን በብሄር መከፋፈል ሁለተኛው አማራጭ ነው። በዚህ የተነሳ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ተመሳሳይ ባህል ያላቸው በርካታ ዜጎች በተለያዩ ሃገራት ውስጥ ተካልለው እንዲኖሩ የተደረገበት መንገድ ማሳያ ነው። ለዚህም የአፋር፣ የሶማሌ፤ የትግርኛ እና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች በተለያዩ ሃገራት ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉ አንድ ማሳያ ነው። በአጠቃላይ ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የወረራ ሙከራ አድርጋ በተሸነፈችበት ወቅት በመካከሉ የነበሩት እንግሊዞች የኢትዮጵያ ክልሎችን በብሄር በማዋቀር እና የሚለያዩ አስተሳሰቦችን በህዝቡ ውስጥ በማስረፅ የመከፋፈል አጀንዳ ፈጥረው እንደነበር አባት አርበኞች ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ ይህ ጉዳይ ብዙም ፍሬ ባያፈራም ውስጥ ውስጡን ሲያቆጠቁጥ ቆይቶ በህወሓት አማካኝነት ዳግም ልደት አገኘ። ከዚያ በኋላም የህወሓት መርዘኛ የሴራ ፖለቲካ ታክሎበት ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጭጭ እና በምትኩ ፅንፈኛ ብሄርተኝነት እንዲጎመራ በማድረግ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ብዙ ጥረት ተደረገ።
ለምዕራባውያን የከፋፍለህ ግዛ ስርአት ምቹ የሆነው አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘራው የልዩነት ፍሬ በለውጡ ዘመን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። አሸባሪው ህወሓትም የጀመረው ሃገራችንን የመከፋፈል ሴራ በለውጡ አማካኝነት ሊከሽፍበት መሆኑን ሲረዳ ወደለመደው ጫካ በመግባት ኢትዮጵያን ዳግመኛ የማፍረስ አላማውን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ምዕራባውያን አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራቸውን ውስጥ ውስጡን ተያያዙት።
ለዚህ አንዱ ትልቁ ማሳያ በዚህ ወቅት ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚያደርጉት የአፍራሽነት ሚና ተጠቃሽ ነው። ለመሆኑ ምዕራባውኑ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ጠፍቷቸው ይሆን አሸባሪውን ህወሃት ቡድን በቀጥታ ከማውገዝ ይልቅ አንዴ ተደራደሩ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ መንግስትን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚጥሩት? ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ ደረጃ አስር ጊዜ ለውይይት አጀንዳ ያደረገው እውን ለኢትዮጵያ ሰላም አስቦ ነው? ለኢትዮጵያ ሰላም የሚያስብ ከሆነ ሰላምን ለማረጋገጥ ጥፋተኛውን ማውገዝ ለምን ተሳነው፤ መልካም ጎኖችንስ ለምን ማወደስ ከበደው?፤ ይህ ለማንም በግልፅ የሚታይ ኢትዮጵያን የማዳከም ስልት ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የገባችበት ጦርነት ፈልጋው ሳይሆን ተገዳ እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ቡድኑ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ከመንግስት ጎን በመቆም ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ እንዲሰራ በብዙ መንገድ ጥያቄ ቀርቦለታል። ከዚህም አልፎ ቢያንስ መንግስት ለጀመረው የልማት እና የብልጽግና ጎዳና እንቅፋት እንዳይሆን በብዙ መንገድ ተጠይቋል፤ ከዚህም አልፎ ተመክሯል። የዚያን ጊዜ ታዲያ አሁን የሚጮሁት ምዕራባውያን በዚህ ልክ ይህ ቡድን ወደጦርነት እንዳይገባ ለማድረግ አንዳችም ጥረት ሲያደርጉ አልታዩም ነበር።
ከዚያ በኋላ ቡድኑ ከመንግስት እያፈነገጠ ሲሄድና በኋላ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝን ሲወር የነዚህ የምዕራባውያን ምላሽ አሁንም ዝምታ ነበር። በተለይ ቡድኑ የሰሜን እዝን ወርሮ “በጥቂት ደቂቃ መብረቃዊ ጥቃት አደረስንባቸው” እያለ ሲፎክር ፍላጎታቸው የሰመረ መስሏቸው በደስታ ስሜት ውስጥ ቆይተዋል። ነገር ግን ይህ “መብረቃዊ ጥቃት” በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በክልል ልዩ ሃይሎች ተመትቶ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሲፍረከረክ ደነገጡ። እነዚያ ዝምታን መርጠው የነበሩ ሃይሎችም ከድንጋጤአቸው ሲወጡ የታያቸው ነገር እንዴት አድርገን ይህንን የተመታ ሃይል እናድን የሚል ነበር።
ስለዚህ በቅድሚያ ለዚህ ቡድን የግንኙነት መስመር እንዘርጋ በሚል የሳተላይት የግንኙነት መሳሪያ አቀበሉ። በቅርቡ ከሃገር እንዲባረሩ የተደረጉት እና በሰብአዊ እርዳታ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሃይሎች ሚናም ከሰብአዊነት ይልቅ ዋነኛ ዓላማቸው ይኸው ነበር። ከዚህ በኋላ እነሱ አሸባሪው ህወሓት ከጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የሚፈልገውን ከውጭ ወዳጆቹ ጋር እየተመካከረ እና ሲያስፈልግም ብስኩትና ሃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን በድብቅ ከነዚሁ ሃይሎች እየተቀበለ አንገቱን ቀና አደረገ። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ በአማራና አፋር ክልሎች ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ጭምር ያደረሰው።
ነገር ግን አሜሪካ አሸባሪ ከምትለው አንድ ቡድን ጋር ግንኙነት የፈጠረ አንድ ውጭ ሃገር ዜጋ ብታገኝ ምን ልታደርግ እንደምትችል ማሰብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታዘብነው ነው። አፍጋኒስታን እና ኢራቅ በዚህ ልክ የፈረሱት እና ህዝቡም አበሳውን ያየው አሜሪካ ጥቅሟ ስለተነካ እንደሆነም ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ እውነትስ ለምንድነው በዚህ መልኩ የሚጨፈለቀው ሲባል ከበስተጀርባው ሌላ እውነታ ስላለ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። እናንተ ድሆች ስለሆናችሁ እንደፈለጋችሁ ማድረግ እንችላለን ከሚል የእብሪት መንፈስ የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም።
ለአሸባሪው ህወሓት መሳሪያ ያቀበሉ ሰዎች ከሃገር ለቃችሁ ውጡ ሲባሉ የተባበሩት መንግስታት የተባለው ድርጅት ኃላፊ ፊት ለፊት ቀርበው ለምን ሲሉ ፈጽሞ ለማገናዘብ ሙከራ አላደረጉም። ለዓለም ሚዛናዊ ስራ ይሰራሉ ተብለው የሚታሰቡት አንቶንዮ ጉተሬዝ በበለፀጉት ሃገራት ላይ ሊናገሩ የማይችሉትን ወይም የማይደፍሩትን ንግግር በኢትዮጵያ ላይ ለመናገር ጊዜ አልወሰደባቸውም። በንግግራቸውም እነዚህ ሰዎች ከሃገራችሁ አይወጡም እስከማለት ደርሰው ነበር።
በዚህ ብቻ አላበቃም። የፀጥታው ምክር ቤት ጊዜ ወስዶ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምክክር አድርጓል። በእርግጥ ይህ ምክክር ሳይሆን የተወሰኑ የቡድኑ አባላት ያቀረቡትን ሃሳብ ተቀበሉ በሚል ለአባላቱ የቀረበ ረቂቅ ሃሳብ ነው ማለት ይቻላል። የሚገርመው ይህ ተቋም ሚዛናዊ አለመሆኑን የሚያሳየው ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የውሃ ጉዳይን ጭምር እስከማየት የሄደበት ርቀት ተቋሙ ምን ያህል ሚዛናዊ እንዳልሆነ ያሳያል።
ለመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን ያህል ጊዜ ወስዶ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲወያይ ለምንድነው የሚለው ጥያቄ አሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። በዚህ ዘመን በዓለም ላይ በርካታ ቀውሶች እንዳሉ ይታወቃል። ገና ዛሬም ያልሻረው የነሶርያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅም ሆነ የየመን ቁስል እንዲሁም በቅርቡ አሜሪካ ራሷ ለችግር የዳረገቻት አፍጋስታን ጉዳይ አለ። ከዚህም ባሻገር ፍልስጤማውያን ዛሬም ድረስ ያልተፈታ ችግር አለባቸው። በዚያ አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች ዛሬም በየጊዜው ሰው ልጅ ህይወትን ሲቀጥፉ ይታያል። ለኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ተቆርቋሪ መስሎ በተደጋጋሚ መሰብሰብ ታዲያ ምን የሚሉት አሳቢነት ይሆን?
ሰሞኑን ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤትም እንዲሁም በኢትዮጵያ እስከመጪው ጥቅምት ድረስ ሰላም ካልተረጋገጠ ማዕቀብ እጥላለሁ የሚል የዛቻ መልዕክት አስተላልፏል። ለነገሩ የፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ አውሮፓ ህብረት በአንድ ሳምባ የሚተነፍሱ፣ ለአንድ ወገን የሚሰሩ ተቋማት ለመሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው።
በነግብጽና ሱዳን መንደርም ቢሆን ህብረተሰቡ ስለዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በርካታ ናቸው። ግብጽ በየዓመቱ እንዲህ አድርጋችኋል፤ ተቃውሟኋል በሚል ሰበብ ብቻ የብዙ ባለስልጣናቷን እና ተቃዋሚዎችን ህይወት በአደባባይ ስትቀጥፍ ስለዴሞክራሲ የሚያቀነቅኑት ምዕራባውያን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሲያልፉ ይስተዋላል። በአጠቃላይ በዓለም ላይ የሚከሰቱ በርካታ ግጭቶች እኩል ድምጽ እንደሌላቸው እነዚህ ክስተቶች ማሳያ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጉዳይም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ሰባት ወይም ከዚያ በላይ ትንንሽ ሃገራት አደርጋለሁ እያለ በዛቻ ሲነሳ እሰየሁ ከማለት ውጭ ምዕራባውያኑ ትክክል አይደለም፤ ይህንን ጉዳይ አስተካክል ሲሉ አይሰማም። ከዚህም አልፎ ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የጅምላ፤ ጭፍጨፋ ሲያካሄድ፤ ለሰብአዊ እርዳታ የሄዱ ተሽከርካሪዎችን አፍኖ ሲያስቀር ዝምታን ይመርጣሉ። ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወርራ ስትይዝ የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን ድርጊት ለማውገዝ አልቻለም። ከዚህ ይልቅ የነሱ ጩኸት ሰብአዊ መብት ተጥሷል፤ ርሃብ ገብቷል፤ ወዘተ በማለት ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ነው። ለአንድ ችግር መፍትሄ ለመስጠት በቅድሚያ የችግሩን ምንነት በአግባቡ መረዳትና ለመፍትሄው መስራት ከእያንዳንዱ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል አካል ይጠበቃል። ይህ ካልሆነ ግን መቆርቆር ሳይሆን ጫና ይሆናል።
እንግዲህ አሁን ያለው የአሜሪካና የምዕራባውያን ሁኔታ አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማፍረስ ጥረት መሆኑን በርካታ ማሳያዎች አሉ። የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያ ቀና ለማለት ከጫፍ በደረሰችበት በአሁኑ ወቅት ቀና ያለውን አንገት ለመቀንጠስ አሰፍስፈዋል። የኛን እድገት የማይፈልጉ ሃይሎች እኛን በመከፋፈል ደካማ ሃገራትን ለመመስረትና እንደፈለጉ ለማሽከርከር ቋምጠው ተነስተዋል። ስለዚህ በዚህ ጊዜ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚጥሩ ሃይሎች ራስን ለመጠበቅ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል። መንቃት፣ አንድ መሆንና ጫናውን መመከት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014