ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአገሪቱ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ ተካሂዷል። በዚህም ህዝብ ይበጀኛል የሚለውን መርጦ ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት ወኪሉን ልኳል። ወኪሎቹም ከመስከረም አጋማሽ ጀምረው መንግስት መስርተዋል። በአሁኑ የመንግስት ምስረታ አብላጫ የህዝብ ድምፅ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ ከተፎካካሪዎቹ ጋር አብሮ ለመስራት ቃል ገብቷል። ቃል በገባው መሰረትም ከክልል ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግስት ኃላፊነት ላይ እንዲሳተፉ ተደርገዋል።
መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የካቢኔ ሹመት በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በካቢኔ አባልነት የተሾሙት አመራሮች ለሀገራቸው እንጂ ለመጡበት ክልል ጥብቅና መቆም እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ይህም ማለት የመንግስት ስራንና የፓርቲን ስራ ደባልቆ የማየት አተያይ መቆም እንዳለበት ነው። መንግስትን ለመፍጠር የግድ የፖለቲካ ፓርቲ ያስፈልጋል። እነዚሁ ሁለት ነገሮች የማይነጣጠሉ ቢሆንም ሁለቱንም በተለያየ መንገድ ማስኬድ ይቻላል። እንዴት ከተባለ ፓርቲን ከመንግስት ስራ ጣልቃ እንዳይገባ በማድረግ ነው። ምክንያቱም ፓርቲ መንግስትን መመስረት ቢችልም የመንግስት አሰራርን ግን ሊለውጥ አይችልም። የመንግስት ስራ አለም አቀፍ በሆኑ መርሆች የሚመራ በመሆኑ ነው።
የኢህአዴግ መንግስት አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የአስተዳደር ዘይቤዎችን ሲከተል ቆይቷል። ከዚህም ውስጥ በመንግስት መስርያቤቶቸ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን መመልመል ይገኝበታል። ይህ አሰራር ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የመጣ ነበር። በወቅቱ በመንግስት መስርያ ቤት ውስጥ የኢህአዴግ አባል መሆን እንደ ግዴታም ይቆጠር ነበር። በዚህ ወቅት ከኢህአዴግ አባልነት ውጪ የሚገኝ ሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው በሚል ውግዘት ይደረስበታል።
በመንግስት ስራ አመራር ላይ የሚገኙ ሰዎች በበታች የስራ ባልደረቦቻቸው ትችትና ዘለፋ አዘል ንግግር ግምገማ በተባለ መድረክ ላይ ይደርስባቸዋል። እዚህ ላይ ግን ልንረዳው የሚገባው በችሎታቸው አመራር ላይ የተቀመጡትን ብቻ ነበር በግምገማ ጥቃት ሲደርስባቸው የነበረው። በዚህም የስራ እንቅስቃሴዎች የተበላሹ እንዲሆኑ አድርጓል። በተጨማሪም ተገልጋዮች በሚመጡበት ወቅት ስራ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ስብሰባ ውስጥ ናቸው በሚል እንዲመለሱ ይደረጋል። ሰራተኛው በብሄር በተደራጁ ፓርቲዎች ውስጥ በመሰግሰግ እድገት ለማግኘት ስራ ሳይሆን የፓርቲ ታማኝነት በሚል ያልተፃፈ ህግ በመመራት እድገትና ዝውውር ሲያገኝ ቆይቷል።
የፓርቲ አባልነትን ለማጠናከር በሚል ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ በማድረግ ለመንግስት የስራ ማስፈፀሚያ ከተመደበ በጀት በማውጣት ማባከንም የተለመደ ተግባር ነው። ከዚህም ባለፈ ሰራተኛው በግድ የፓርቲ ምስረታ በዓላትን ከኪሱ እያዋጣ እንዲያከብር በማድረግ መማረር ፈጥሮም እንደነበርም አይዘነጋም። ከመስርያ ቤቶች ወጣ ስንልም በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃም ከመንግስት ስራ ይልቅ በፓርቲ ስብሰባዎች መወጠር የተለመደና ትልቅ ስራ እንደሰሩ ተደርጎም ይቆጠርላቸው ነበር።
ኢህአዴግ ሲመራው የነበረው መንግስት መሰረታዊ ለውጥ ያስልገዋል በሚል ከድርጅቱ በወጡ ለውጥ ፈላጊ አመራሮች 2010 ዓ.ም ላይ ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል። ለውጥ ከመጣ በኋላም መሰረታዊ የተባሉ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት ብዙ ርቀት ተጉዟል። ከኤርትራና በውጪ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሰላም በመፍጠር በቀጣናው መረጋጋት እንዲመጣ መሰረት አስቀምጧል። ዋናው ጉዳይ ግን የለውጥ ቡድኑ ብልፅግና ፓርቲ ከመሰረተ በኋላ ፓርቲውን ከመንግስት ስር አውጥቷል የሚለው ነው።
ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ፓርቲዎች በእኩልነት የመሰረቱት ፓርቲ ሲሆን ቀድሞ የነበረው የኢህአዴግ ህጋዊ ወራሽ ሆኖ ቀድሞ የነበሩ የፓርቲ ንብረቶችን እያስተዳደረ የሚገኝ ነው። በተጨማሪም ህጋዊነቱ ታውቆም በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብ ተደርጓል። ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ ይዟቸው የተጓዙ የቀድሞ የኢህአዴግ አባላት የመንግስትን ስራ ከፓርቲ ስራ ጋር ሲደባልቁ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይስተዋላል።
ሌላው በመንግስትና በህዝብ ትብብር የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ለፓርቲ ጥቅም እንዲውሉ ግብዓት ማድረግ ነው። አንድ የሚያስማማን ጉዳይ መንግስት የሚመሰረተው በአሸናፊ ፓርቲ ነው። ነገር ግን ፓርቲው የአገሪቱን ህግና ደንብ ተጠቅሞ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ሲገነባ ፓርቲ ሳይሆን በመንግስት ደረጃ የተሰራ እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል።
ሌላው ጉዳይ ቀደም ብሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ህዝብን ወክለው ይቀመጡ እንጂ በብሄራቸው የፖለቲካ ስብሰባና ግምገማ ያካሂዱ ነበር። ይህ ደግሞ አስፈፃሚ አካላትን በሚቆጣጠሩ ጊዜ እክል ፈጥሮባቸዋል። እንዴት ካላችሁ ደግሞ በምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙ
የህዝብ ተወካዮች አስፈፃሚ አካላትን ለመቆጣጠር በቋሚ ኮሚቴዎች ይደለደላሉ። ቋሚ ኮሚቴው ደግሞ በስሩ የተቀመጡለትን አስፈፃሚ አካል ወይም የፌደራል መስርያቤቶችን የስራ ሁኔታ ይገመግማል። በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የላላ ምልከታ በማድረግ ስራቸውን ያጠናቅቃሉ። ለምን ከተባለ የፌደራል መስርያ ቤቱ ኃላፊ በፓርቲ ግምገማ ልክ ስለሚያስገባቸው ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡ አባላት ጠንካራ ትችት እንዲሰነዝሩና አስፈፃሚ አካላትን በአግባቡ እንዲገመግሙ አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል። ዋናው ጉዳይ አባላቱ የተሰጣቸውን ስልጣን በአግባቡ ይጠቀማሉ ወይ ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፓርቲን ወክለው ይምጡ እንጂ ለአንድ አገር እድገት የተሰባሰቡ ናቸው። ይህ ሀሳብ ተረድተው ከብሄርና ከጎጥ አስተሳሰብ የወጡ እንዲሁም የፓርቲን ስራ ከመንግስት ስራ ነጥለው የሚያዩ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ሌላው ጉዳይ በፓርቲ ስም በመንግስት ስልጣንም ላይ አቅም የሌላቸውን ሰዎች መሾም ነው። ይህ በቀደመው የአገዛዝ ዘመን ምን ያክል ኪሳራ አምጥቶ እንደነበር አንዘነጋውም። በፓርቲ አሰራር መሰረት ማንኛውም የፓርቲው አባል የተቀመጠለትን ተልዕኮ መፈፀም ከተቻለ የትኛውም ቦታ መሾም ይችላል። ይህ አሰራር ግን ሊተገበር የሚችለው በፓርቲው ስራ ላይ ብቻ ነው።
ነገር ግን በኢህአዴግ ዘመን በመንግስት መስርያ ቤቶች ላይ ተሹመው የሚመጡ ሰዎች በትምህርት ደረጃም ሆነ በስራ ልምድ ብቁ ያልሆኑ ሰዎች በመሆናቸው አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል። እዚህ ጋር ልንረዳው የሚያስፈልገው ነገር ማንኛውም ብቃት ያለው ሰው በመንግስት ስራ ላይ ተሹሞ መስራት ይችላል። የሚሾመው ሰው የፓርቲ አባል ከሆነ ቢያንስ ስለሚሾምበት ቦታ እውቀት ሊኖረው ይገባል። በፓርቲ ስም ብቃትም ክህሎትም የሌለውን ሰው እያግበሰበሱና እየሰበሰቡ መሾም ሊገታ የሚገባ ጉዳይ ነው።
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሸንፎ መንግስት የመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ በክልልም ይሁን በፌደራል ደረጃ ካቢኔ ሲያዋቅር በስራና ብቃት እንዲሁም በሰሩበት ኃላፊነት ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን ሹመት ሰጥቷል። የተሾሙት ሰዎች ከፓርቲ አተያይ ወጥተው ከአገር መስራት አለመስራታቸው እንዲሁም በክልልና በፌደራል ካቢኔ ውስጥ የተካተቱት ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ልዩነታቸውን ወደ ጎን አድርገው ለሀገር ይሰራሉ ወይ የሚለው በቀጣይ የሚታይ ነው።
እስከዛው ቸር እንሰንብት።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014