የምዕራቡ ዓለም ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፤ ስለ መልካም አስተዳደር፤ ስለ ሰብአዊ መብቶችና ለሌሎችም ሰው ሰው ስለሚሸቱ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ላለፉት ሁለት መቶ አመታት ከፍ ባለ ድምፅ ሲጮህ እንደነበር ይታወሳል። አሁን ይህ ዘመናት ያስቆጠረው ጩኸቱም ላይ ትርጉም አልባ እየሆኑ መምጣቱም የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል።
ሰብአዊ እሴቶችን የብሄራዊ ጥቅሙ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የምዕራቡ ዓለም ይህንን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ሀገርን እስከማፍረስ የሚዘልቅ እንደሆነም እየታየ ነው። ይህም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ዓለምን እየተፈታተነ ያለ ትልቁ ተግዳሮት ሆኗል።
ምዕራቡ ዓለም ቀደም ሲል ጥቅሙን ለማስከበር ይከተለው የነበረውን የቅኝ አገዛዝ ስርዓት መልኩንና የአገዛዝ መሰረቱን ወደ ቀጥተኛ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በመለወጥ በቅኝ አገዛዙ ዘመን ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው መወሰን ያልቻሉ የዓለም ሀገራት ህዝቦች ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የራሳቸውን እጣ ፈንታ መወሰን እንዳይችሉ እያደረጋቸው ነው።
እነዚህ ህዝቦች ከትናንት ተጨባጭ ተሞክሯቸው እና ከከፈሉት ዋጋ በመነሳት የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን በሚያደርጉት ጥረት እንዳይሳካ የምዕራቡ ዓለም ዋነኛ ተግዳሮት ሆኗል። ከዚህም ባለፈ ጥረታቸው ፍሬ እንዳያፈራ፤ ከዛም በላይ እንደ ሀገር የመቀጠል እጣ ፈንታቸው በስጋትና በፈተናዎች እንዲሞሉ እያደረገ ይገኛል።
በቀደመው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተቃኘው ይህ አዲሱ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እሳቤ የሀገራቱን ህዝቦች በመከፋፈል አለመግባባቶችን ከመፍጠር የሚነሳ፤ አለመግባባቶችን ወደ ግጭቶች በመለወጥ፤ ከግጭቶች ማትረፍን መሰረት ያደረገ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ግጭቶች ወደ ከፋ ብሄራዊ አደጋ እንዲሻገሩ ማድረግንም ያካተተ ነው።
ለዚህ ደግሞ የምዕራቡ ዓለም በተለይ በአሜሪካ የሚመሩት የአውሮፓ አገራት በተናጠል ሆነ በግዙፉ ወታደራዊ አቅማቸው /ኔቶ/በኩል ስላፈረሷቸው ሀገሮች፤ ስለ የበተኗቸው ህዝቦች መናገር ብዙ የሚከብድ አይደለም። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ለምዕራቡ ዓለም ያልተገባ ብሄራዊ ጥቅም ሲባል ከፍ ያለ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ህዝቦች ብዙ ናቸው።
ከዚህም በላይ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ስም በተፈጠሩ ጫናዎች በአዲሱ የምዕራብ ዓለም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር ሆነው እጣ ፈንታቸውን ለመኖር ያልቻሉ፤ ከብዙ የመስዋዕትነት ትግል በኋላ ያገኙት ነጻነት ትርጉም አልባ የሆነባቸው ህዝቦችም ጥቂት አይደሉም።
ይህ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማግስት ህይወት ዘርቶ ዛሬ ላይ የዕድገት ደረጃውን ጨርሶ የዓለምን አደባባዮች የሞላው የምዕራቡ ዓለም ተግዳሮት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን ለመሆን፤ የራሳችንን እጣ ፈንታ ለመወሰን ለጀመርነው አዲስ የታሪክ ጉዞ ተግዳሮት ሆኖ ከተገለጠ ውሎ አድሯል።
በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጡ መንግስት ስለ ብሄራዊ ጥቅምና ብሄራዊ ክብር ከፍ ባለ ድምጽ መናገሩ እንዲሁም ለቃሉ መፈጸም ቁርጠኛ መሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ይህን እውነታ መረዳቱና ለለውጡ ኃይል ያሳየው ድጋፍ የምዕራቡ ዓለም ለጥቅሙ ተግዳሮት አድርጎ ወስዶታል።
ከዚህም የተነሳ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የለውጡ መንግስት ኃይሉን በሙሉ አቅሙ እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ ጀምሮ፤ ከተነሳበት የለውጥ አስተሳሰብ ወጥቶ ለስልጣኑ ሲል በሀገሪቱ እና በህዝቦቿዋ ጥቅም ወደ መደራደር እንዲመጣ ሁለንተናዊ ጫና እየፈጠሩ ነው።
ተልዕኳቸውን ለማስፈጸምም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀንን አሰልፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። በዚህም የለውጡን ኃይል ከማጠልሸት አንስቶ አሸባሪ ተብለው ለተሰየሙ ቡድኖች ጠበቃ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ባልተገባ መንገድ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እያደረጓት ይገኛሉ ።
ህዝባችን ለዘመናት ብዙ ዋጋ የከፈለበትን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት፤ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና፤ ሰብአዊ መብቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰብአዊ እሴቶችን ለመጠበቅና ለማስቀጠል የሚንቀሳቀሰውን የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር ከጉዞው እንዲደናቀፍ እየሰሩ ነው።
የዓለምን አደባባይ የሞላው ይህ የምዕራቡ ዓለም ተግባር በርግጥ የምዕራቡ ዓለም ራሱን የዴሞክራሲ፤ የመልካም አስተዳደር እና የሰብአዊ መብቶች ጠባቂና አስጠባቂ አድርጎ የሚጮኸውን ጩኸት ደጋግመን እንድንመረምረው የሚያስገድደን ነው። ዓለምም ስለ አዲስ የዓለም የፖለቲካ ስርአት እንዲያስብ የሚያስገድደው ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014