በዓለም የስፖርት ማህደር ገጾች ከተሰነዱ ታሪኮች መካከል በቀልድ ተጀምሮ በአሳዛኝ ሁኔታ የተጠናቀቀን አንድ ታሪክ ይጠቀሳል፡፡ በእግር ኳስ ስፖርት ታሪክ ምናልባትም ይህ መራር ቀልድ ተብሎ ሊባልም ይችላል፡፡
ባለታሪኩ ሉሲያኖ ረ ሴሶኒ የተባለ ጣሊያናዊ ባለ ወርቅማ ጸጉር እግር ኳስ ተጫዋች ሲሆን፤ ከጓደኛው ጋር ሆነው የፈጠሩት ቀልድ ከሚወደው ስፖርትና ቤተሰቦቹ ለዘለዓለም የነጠለውን ክስተት አስከትሎበት ታሪክ አድርጎታል፡፡
ይህ ተጫዋች እአአ 1948 ከሚላን አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ከአርሶ አደር ቤተሰቦች ተገኘ፡፡ የእግር ኳስ ችሎታው በክለቦች ዓይን ስላስገባውም በቅድሚያ በሴሪ ሲ ለሚጫወተው የሃገሩ ክለብ ፕሮ ፓትሪያ ቀጥሎ ለሴሪ ኤ ለሚጫወተው ፎጊያ (ከሴሪ ቢ ቡድን ወደ ኤ በማደግ) ክለቦች ተሰልፎ ለመጫወት ችሏል፡፡ እአአ ከ1972 ጀምሮ ደግሞ ዝናን ወዳተረፈበት ላዚዮ ተዘዋውሮ ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል፡፡
የብቃቱ ጥግ ላይ በደረሰበት ላዚዮ ‹‹ባለ ወርቃማ ጸጉሩ መልአክ›› እየተባለ እስከመጠራት የደረሰው ሴሶኒ፤ በጥንካሬውና በፍጥነቱ ይታወቃል፡፡ ከሜዳው አንድ ጥግ እስከ ሌላኛው ጥግ ደርሶ የሚጫወት መሆኑ ክለቡን በተቀላቀለ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የቡድኑ ቂልፍ ተጫዋች ለመሆን በቃ፡፡ ወደ ላዚዮ ባመራበት ዓመት ከክለቡ ጋር ዋንጫ ማንሳት ባይችልም በቀጣዩ የውድድር ዓመት ግን ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል፡፡ ከኳስ ጋር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለፈ ላዚዮ ዋንጫውን ባነሳበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠርም ወሳኝ ተጫዋችነቱን አስመስክሯል፡፡
ከክለቡ ባለፈም ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም ለጣሊያን ዋናው ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ በመጫወት ሁለት ዋንጫዎችንም አሳክቷል፡፡ ሴሶኒ ከምርጥ ተጫዋችነቱ ባለፈ በቀልደኛነቱ እና ተጫዋችነቱ በተለይ በቡድኑ አባላት የሚታወቅና የሚወደድ ተጫዋች በመሆኑ ስኬታማ የተጫዋችነት ህይወቱን እአአ እስከ 1977 ድረስ እያጣጣመ ቆይቷል፡፡ በዚያው ዓመት አንድ ዕለትም ፔትሮ ጌዲን ከተባለው የቡድን አጋሩ ጋር በመሆን በሮም ጎዳናዎች ሲዘዋወሩ ወደተመለከቱት የጌጣጌጥ መሸጫ መደብር ይገባሉ፡፡ በመደብሩ ጌጣጌጦችን እየተመለከቱ ሳለም ሌሎች ሁለት የክለብ አጋሮቻቸው ወደ መደብሩ ሲመጡ ይመለከቷቸዋል፡፡
እግር ኳስ ተጫዋቾች በተለይ ከጨዋታ በኋላ እንዲሁም በመልበሻ ክፍሎቻቸው መጨዋወታቸው የተለመደ ነው፡፡ እነ ሴሶኒም ከተቀሩት የክለቡ አባላት ጋር በመወዳጀታቸው እርስ በእርሳቸው በመበሻሸቅና በመቀላለድ ሳቅና ደስታን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ የተለመደ ነውና ጓደኞቻቸው ወደ መደብሩ ሲገቡ አንዳች አስቂኝ ጨዋታ ፈጠሩ፤ እንዳያዩዋቸው ሆነውም ጠበቋቸው፡ ፡ ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ሲገቡ ሲሶኒ እና ጌዲን ፊታቸውን በለበሱት ልብስ ሸፍነው ከኋላቸው ያዟቸው፡፡ በሁኔታው በተደናገጡ ጓደኞቻቸው ለመሳለቅ ናፍቀውም ድምጻቸውን አጉልተው ‹‹እጃችሁን ወደላይ አንሱ፤ ዘራፊዎች ነን›› እያሉ ያዋክቧቸው ያዙ፡፡
ይሁን እንጂ የነገሩ ቀልድነት ለሁለቱ ተጫዋቾች እንጂ ለጌጣጌጥ መደብሩ ሰራተኞች አልነበረምና በቅጽበት ነገሮች ወዳልሆነ አቅጣጫ ተቀየሩ፡፡ መገጣጠም ሆነና መደብሩ ከአንድ ሳምንት በፊት በተመሳሳይ ዘራፊዎች ጥቃት ደርሶበት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በጣሊያን ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚችልበት በመሆኑ ብዙዎች መሳሪያ ነበራቸው፡፡ በሃገሪቷ ስርዓት አልበኝነት በመንገሱም እግር ኳስ ተጫዋቾችም ጭምር የጦር መሳሪያ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በመደብሩ የተገኙት የአንድ ክለብ አራት ተጫዋቾች ምንም ዓይነት መሳሪያ አልያዙም፡፡
ከደረሰባቸው ዘረፋ በኋላ ራሳቸውን ከዝርፊያ ለመከላከል የተዘጋጁት የመደብሩ ሰራተኞች ግን ታጥቀው ነበርና፤ ድርጊቱ ቀልድ መሆኑን ሳያውቁ አረር የሚተፋውን መሳሪያ ደቀኑባቸው፡፡ ተጫዋቾቹ በድንጋጤ የያዟቸውን ተጫዋቾች ለቀው እጃቸውን ወደላይ ቢያነሱም ነገሩ ዘግይቶ ነበርና፤ ከሲሶኒ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ሻጭ የተኮሰው ጥይት ከባለ ወርቅማ ጸጉሩ ተጫዋች ደረት ተመሰገ፡፡
ሁኔታው ሲታወቅም ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ሆስፒታል ይዘውት ከነፉ፤ ተጫዋቹ ግን ከ30 ደቂቃ በላይ በህይወት ሊቆይ አልቻለም፡፡ በ28 ዓመቱ የሚወደውን ስፖርት፣ ባለቤቱንና ሁለት ልጆቹን ትቶ ላይመለስ አሸለበ፤ ህይወቱ እስክታልፍ ድረስም ‹‹ጨዋታ ነበር፤ ቀልድ ነበር›› ይል እንደነበር በአሳዛኙ የህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሯል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም