አዲስ ምእራፍ ተጀምሯል። ይህን ብሩህ ተስፋ አብሳሪ እለት ደግሞ ኢትዮጵያውያን (ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች) በጋራ አድምቀውታል። ዜጎች አዲስ የተመሰረተውን መንግስት ስልጣኑን የሰጡት ይሁንታ የሰጡት በምርጫ ድምፅ ብቻ ሳይሆን በምስረታው ስነ ስርአት ላይ የባህል አምባሳደሮቻቸውን ወክለው “በወግ ማእረግ፣ በባህልና ውብ ስርዓት” በቀጥታ ትርኢት በማቅረብና በማክበር ነበር።
ዓለም ከሶስት ሺ ዘመናት በላይ የዘለለውን የስርዓተ መንግስት ምስረታ በዓል አንዱ አካል የሆነውን “የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ” በዓለ ሲመት እንዲሁም የመንግስት ምስረታ ያሳለፍነው ሰኞ ዕለት ህዝቡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መከታተሉ ይታወሳል። ወዳጆቻችን አብረውን ሲደሰቱ ጠላቶቻችን እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅ በዝምታ ተውጠውና ተሸሽገው ሃቁ እየተናነቃቸው ውጠውታል።
በዚህ ዝግጅት ላይ ታዲያ ወዳጅ መንግስታት በቀጥታ በፕሬዚዳንቶቻቸው ተወክለው ስነ ስርዓቱን አድምቀውት አልፈዋል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ መንግስታቸውን ብቻ አልነበረም በእለቱ የመሰረቱት “ሚሊዮኖች” በቀጥታ በተከታተሉት ዝግጅት ላይ የባህል እሴቶቻቸውን፣ የቱሪዝም ሃብቶቻቸው የሆነውን የማንነት መገለጫቸውን በአንድነት ማሳየት ችለዋል።
ኢትዮጵያውያን በልዩነት ውስጥ የደመቁ ድብልቅ ማንነት ያላቸው መሆናቸውን በታላቁ መድረክ ላይ አንፀባርቀዋል። አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው በአጠቃላይ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ታላላቅ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ደማቅ ስነስርዓቶች በሚዘጋጁበት “መስቀል አደባባይ” በመገኘት በዓለ ሲመቱ እንዲያሸበርቅ አድርገዋል። ከዚህ በላይ አባቶች ምርቃቶቻቸውን “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ” ሰጥተውታል። ይህን ሲያደርጉ ኢትዮጵያዊ በሆነው በባህላዊ ስርዓት አጅበው በወግና ማእረግ ነበር።
ስነ ስርዓቱ “በዓለ ሲመት ብቻ አልነበረም” ከተለያየ አገራት የተወከሉ ዲፕሎማቶች የዓለም አቀፍ ማህበረሰቦች የኢትዮጵያውያንን ወግ፣ ባህል፣ እምነት እንዲሁም የቱሪዝም እሴቶች እጥር ምጥን ባለ ውብ ዝግጅት ቀርቧል። እሴቶቻችንን የማያውቁት ታዳሚዎች እንደ አዲስ ተደንቀው ብዙ መረጃዎችን ይዘው ወደ መጡበት ተመልሰዋል። ከዚህ ቀደም የሚያውቁት ደግሞ ደግመው ደጋግመው ቢያዩትና ቢያዳምጡት የማይሰለቸውን ባህላዊ እንቅስቃሴ፣ ስርአት፣ ዜማና ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን በድጋሚ የመመልከት አጋጣሚውን አግኝተዋል።
መሰናዶው ላይ ሌላው ልዩ የሚያደርገውና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የተላበሰ መሆኑን የሚያሳየው ልዩ የአቀባበል ስርዓት ነው። ከተለያዩ ዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ታላላቅ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና በርካታ ተቋማትና አገራትን የወከሉት ግለሰቦች በመስከረም ወቅት በሚፈካው የብሩህ ተስፋ “የአደይ አበባ” ምንጣፍ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከሌላው ዓለም የተለየ ማንነት፣ የራሳችን መገለጫ፣ የቱሪዝም እሴት “የ13 ወራት ፀጋ” እንዲሁም “ምድረ ቀደምት” መሆናችንን የሚያመላክት፣ ባህላዊ ማንነት እንዳለን እንዲመለከቱ ሆነዋል። ከምንም በላይ ተፈጥሮ አድልታ ዳመናው ሲገልጥ በዐደይ እንደምንፈካ፣ በቢጫ ቀለም በተስፋ እንደምናብብ የተመለከቱበት ጭምር ነው። ምንም እንኳን ከጥቂት ወዳጆቻችን በስተቀር “ውብ እኛነታችንን” በአደባባይ የሚመሰክሩልን ባይሆንም ደጃፋችንን የረገጠ በክብር ተቀብለን ውበታችንን ገልጠን የምናሳይ “ፈጣሪ የሚወደን ህዝቦች” መሆናችንን ግን በአጭር ዝግጅት ብቻ እንዳዩ እንደማይዘነጉት ግን እርግጠኞች ነን። ጥንታዊ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያን በአንድ መድረክ ላይ ቅልብጭ ብላ አይተዋታል። የሺህ ዘመን የስርአተ መንግስት ምስረታ፣ የአልገዛም ባይነት፣ የሉዓላዊነትና የነፃነት ተምሳሌት፣ የታሪክ፣ ባህል፣ ታላላቅ ቅርስ ባለቤት ከመሆኗም በላይ ህዝቦቿ መሪያቸውን የሚያከብሩ፣ መሪውም ዜጋውን የሚወድ የተሳሰረ ማንነት ያለን መሆናችንን መመስከር ችለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም “ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ድንቅ ማንነት” ከዚህ እንደሚከተለው በዚህ ውብ መድረክ ላይ አውስተውታል።
ኢትዮጵያዊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት
“ኢትዮጵያ በአቃፊነቷና በቀደመና ገናና ታሪኳ በመርከብ ትመሰላለችⵆ በታላላቆቹ ቅዱሳን መጽሐፍት እንደተነገረው መርከቧ ኢትዮጵያ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነጻነትና የላቀ ስብዕና አገር ናት” በማለት በበዓለ ሲመታቸውና በመንግስት ምስረታ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓለም ህዝቦች ተገልጦ የማያልቅ፣ ተዳስሶ ግዜ የማይበቃው፣ ተፈትቶ የማይቻል ሚስጢራት ባለቤት እንደሆንን መስክረዋል። ለዚህ ነው እርሳቸውም “ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ነብርም ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም፤ የተባለላትና ከቀደምት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባን ያፈራች አገር ነች። ነብዩ መሐመድ አሊ ወሰላት ወሰላም የተከታዮቻቸው ማረፊያ አድርገው የመረጧት የእውነትና ርትህ አገር ብለው ያወደሷትና የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላል መነሻ የሆነች አገር ናት፤ ኢትዮጵያ” በማለት ጠንካራ ምሳሌን በማንሳት ከሌላው የዓለም ክፍል እኛን ለማየት የሚመጣ እጅግ ብዙ የሚደንቁ ነገሮችን ማግኘት እንደሚችል ያስገነዘቡት።
“እኛ ማለት” አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ማንነታችንን አይናቸውን አጉልተው፣ ትኩረታቸውን ሰብስበው ለሚያዳምጡ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም ህዝቦች “እኛ ማለት! የመካከለኛው ዘመን ፖርቱጋላዊ አሳሽና ፀሐፊ ፔድሮ አልቫሌዝ ኢትዮጵያውያን ፍትህና ዳኝነትን የሚያውቁ፤ ኪነ ህንፃና ስዕሎቻቸው በጥበብ የደመቁ ሲል የመሰከረልን ድንቅ ህዝቦች ነን። ኢትዮጵያ በኤዞጵ ተረቶችና በሜናንደር ተውኔቶች የተወደሰች፤ ግሪካዊ የታሪክ አባት ሔሮዳተስ የወርቃማ ባህልና ስነምግባር ባለቤት የሆኑ ብልህ ህዝቦች ብሎ የፃፉላት ድንቅ አገር ናት፤ ኢትዮጵያ” በማለት ቀደምት አገር፣ ባለታሪክ አገር፣ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ መሆናችንን በታላቅ ኩራት በአደባባይ መስክረዋል።
ቀጠል አድርገውም የታሪክ አጥኚዎች፣ ጎብኚዎችና መሰል ተመራማሪዎች ጆሯቸውን እንዲከፍቱ የሚያደርግ ንግግር ያስከትላሉ “የዘመናችን አርኪዮሎጂስቶች ምድረ ቀደምትነቷን ያረጋገጡላት ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ ግዛትና በፀረ አፓርታይድ ትግል ወቅት ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ነፃነት ከውስን ሃብቷ ሳትሰስት ቀንሳ የሰጠች፣ በጥቁር ህዝቦች መብት ትግል ውስጥ ትልቅ ቦታ በነበራቸው ማርክስ ጋርቬና ዱቦ ይስ ልቦና ውስጥ ጎልታ የተሳለች ‘አፍሪካዊ ማንነቴን የገለጠችልኝ’ ተብላ የተወደሰች የእውነትና የአፍሪካዊነት ሞገስና ፈርጥ የሆነች ናት ኢትዮጵያ። አንዳንዶች ዛሬ አትችሉም ሲሉን አንድም ከታሪክ መዝገብ ገልጠን የአባቶቻችንን ገድል በማጣቀስ፣ ሁለትም የእኛ ትውልድ ለኢትዮጵያ ብልፅግና የወጠነውን አይቀሬ ተግባር ጉዞ ወደ ውጤት በመቀየር መቻላችንንና ኢትዮጵያ መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል። በቀደሙ ድሎቻችን ከሚሰማን የኩራት ስሜት ጋር ሲነፃፃፀር የነገ ተስፋ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ዋናው ጥያቄ ተስፋ ተስፋውን አይተን እውን ለማድረግ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን ራሳችንን መጠየቅ ነው። ኢትዮጵያ የምትበለጽገው እኛ አገራችንን ለመለወጥ በፈለግንበት መጠንና የጋራ ራእይ በሰነቅንበት ልክ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው። ይህን ለማሳካት የዛሬ ህያው ኢትዮጵያዊያን ታላቅ አደራ ተጥሎብናል። ይህንን አደራ ጠብቀን የዘመናት በጎ ድምር ውጤቶችን አጎልብተን፣ ኢትዮጵያ የተባለችውን መርከብ ሞተሯን አድሰን ማዕበል ወጀቡ ፈፅሞ ሳያናውጣት እንድትጓዝ ማድረግ ደግሞ የየትውልዱ የኢትዮጵያ ልጆች አደራ ይሆናል።
ከባህላዊ ትርኢቶቹ መካከል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከበዓለ ሲመታቸው መልስ በፓርላማ ካቢኔያቸውን ሲሰይሙና ንግግር ሲያደርጉ በዝግጅቱ ወቅት ስለነበረው ባህላዊ ትእይንትም አንስተው ነበር በዚህም “በመሰናዶው ላይ ተጋባዥ የነበሩ አፍሪካውያን ባህላዊ ትዕይንቱን ሲታደሙ ሁሉም በእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ውስጥ እራሳቸውን እየተመለከቱ ነበር። ይህ ማለት አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን መላው አፍሪካውያን በደምና በባህል የተሳሰርን ሕዝቦች መሆናችን ምስክር ነው” የሚል መልእክት አስተላልፈው ነበር። ዝግጅቱም ከመንግስት ምስረታ ባሻገር የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሃሳብ የሰበከና ትስስር ለመፍጠር ያለመ ጭምር መሆኑን አመላክተዋል።
በበዓለ ሲመቱ እለት ከታዩ ድንቅ ባህላዊ ክንዋኔዎች መካከል ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ አንድ ሁነት ነበር። ይህም የሲዳማ ክልል አባቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹመት ተከትሎ የምርቃት ስነስርዓት ማካሄዳቸውና እርሳቸውም ባህልና ስርዓቱን ተቀብለው ከተቀመጡበት ወንበር ተነስተው በእግራቸው መሬት ላይ “ቁጢጥ” በማለት ምርቃቱን መቀበላቸው ነበር። ይህን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የሲዳማ የአገር ሽማግሌ አርጋታ ሪቄ የስነ ስርዓቱን ትርጉምና በእለቱ የታየውን ሁነት እንደሚከተለው አብራርተውልናል።
የሲዳማ አባቶች “ኤጀቶና አያንቱ” የሚል ስያሜ አላቸው። እነዚህ የአገር ሽማግሌዎች በምርቃታቸው “ የተሾምክበት ቦታ ይስመርልህ” የሚል መልክት ያለው ምርቃት ያቀርባሉ። ከዚህ ባለፈ “እውነት በተሿሚው ውስጥ ነው ያለው። ሃቀኝነትም ጭምር” በማለት ለመንግስትና ለተሾመው ሰው አደራ የመስጠት ስነ ስርዓትን የያዘ ስነ ስርዓትን “በመስቀል አደባባይ አድርገዋል። ከዚህ ባለፈ አባቶቹ ተንበርክከው በአማረኛ ትርጉሙ “ኖር” በማለት የማክበር ስርዓት ያደርጋሉ። ይህን የአባቶቹን ባህላዊ የሹመትና የምርቃት ስነ ስርዓት ደግሞ ስልጣኑን የሚረከበው ሰው “ከዙፋኑ” ተነስቶ በመሬት ላይ ቁጢጥ በማለት የማክበር ስነስርዓት ያደርጋል። የፈለገ ስልጣን ቢኖረውም በዚህ ስነ ስርዓት ላይ በዚህ መንገድ ስነ ምግባሩንና ባህላዊ ስርዓቱን ማክበሩን ማሳየት ይኖርበታል። ለዚህ ነበር በዓለ ሲመቱ ላይ ብሄር ብሄረሰቦች በየራሳቸው ባህልና ወግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን “ሹመት ያዳብር” በማለት ሲመርቁ ዶክተር ዐቢይም በባህላዊው መንገድ መቀበላቸውን የገለፁት።
ለማጠቃለል
የመንግስት ምስረታ ስነ ስርዓቱ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸውን ታላቅ ፍቅር ያሳዩበት ሆኖ አልፏል። ይህ ብቻ አይደለም ወዳጅ አገራቶችን አቀራርቦና ቀጠናዊ ትስስር ፈጥሮ በጋራ ለብልፅግና መትጋት እንደሚገባም “በፓን አፍሪካን” ቅኝት ታላላቅ መልክቶች ተላልፈውበታል። ከሁሉም በላይ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን የስልጣኔ መሰረት የነበርን አገራችን “ምድረ ቀደምት” የሰው ልጆች ጥንስስ ስፍራ እንደሆነች በታላቅ ስነ ስርዓት ለመላው ዓለም አሳይተናል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም