ህይወት ለጠቢባን ህልም፣ ለሰነፎች ጨዋታ፣ ለሀብታሞች ፌሽታና ለድሆች ፈተና ነች ይባላል። ምክንያቱም በቆየንበት ዘመንና እድሜ ጥበቡን መረዳትና በዚያ መኖር ካልቻልን ስንፍናው ቤታችን ይሆንና መቀለጃ ያደርገናል። ዘላለም አስር ሞልቶ አያውቅም የሚለውን አባባል እንድንኖረውም ያደርገናል። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው ከሆንን ህልማችን ብቻ ሳይሆን ነጋችን ይበራል። ለሌሎችም ብርሃንን ሰጪ እንሆናለን። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ሰዎችን እንዳሉ ግልጽ ነው። ለዛሬ የህይወት ገጽታ አምድ እንግዳ ያደረግናቸው መምህር በቀለ ወርቁም ለዚህ አንዱ ማሳያ ናቸው። በህይወት ቢፈተኑም ለስኬት የበቁና ለሌሎች ብርሃን መሆን የቻሉ ናቸው።
በደርግ ጊዜ የመከላከያ ሰራዊት በመሆን ከ14 ዓመት በላይ አገልግለዋል። በኢህአዴግ ሲባረሩ ደግሞ ዝቅተኛ የሚባል ሥራን በመስራት ኑሮን ተፋልመው ከስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ጀምረው ሁለተኛ ድግሪያቸውን መያዝ ችለዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ልጃቸውን ጭምር በምህንድስና አስተምረው አብረውት በመመረቅ ነው። እናም ከዚህና መሰል ህይወታቸው ትማሩ ዘንድ ለዛሬ ይዘንላችሁ ቀርበናልና መልካም ቃርሚያ ተመኘን።
የአጎት ቤት እንጀራ እናት
የእንግዳችን ወላጅ አባት አቶ ሀይለየሱስ ሚዴክሳ ይባላሉ። ለሥራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ በሚመላለሱበት ጊዜ ነው የወለዷቸው። ቋሚ ኑሯቸው ግን አምቦ ነው። በዚህም ከወላጅ አባታቸው ጋር ማደግ አልቻሉም። እናታቸውም ቢሆኑ እርሳቸው በተወለዱበት ማለትም በአዲስ አበባ በቀድሞ አጠራር ከፍተኛ 23 ቀበሌ 23 ወይም በአሁኑ ሳርቤት አካባቢ ሰፈረ ሰላም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከእርሳቸው ጋር አልቆዩም። ምክንያቱም ከባለቤታቸው ጋር መኖር ባለመቻላቸው ኑሯቸውን ከአዲስ አበባ ውጪ አደረጉ። ስለዚህም የዛን ጊዜ ሕፃኑ በቀለ አጎት ጋር እንዲያድጉ ግዴታ ተጣለባቸው። በዚህም ወላጅ አባታቸው ታናሽ ወንድማቸው ጋር አስር አለቃ ወርቁ ሀይለማርያም ቤት እንዲኖሩ አደረጓቸው። በጊዜው ምንም ሳይጎልባቸው ነበር ያደጉት። ነገር ግን አጎታቸው በህግ ከአገቧቸው ባለቤታቸው ጋር ሲለያዩ ለባለታሪካችንም ቀን ጎደለባቸው።
አስር አለቃ ወርቁ ኑሮውን ብቻቸውን መግፋት ስላልቻሉ ሰራተኛ ቀጠሩ። ሆኖም ይህቺ ሴት በብዙ ነገር ተመችታቸው ነበርና የትዳር አጋራቸው አደረጓት። ይህ ደግሞ ከአባወራው በስተቀር ለሚኖሩት ልጆች ሰላም የሚነሳ ኑሮን እንዲኖሩት አደረጋቸው። ምክንያቱም እርሷ ሀብትና ንብረታቸውን እንጂ እርሳቸውን አትፈልጋቸውም ነበር። ስለዚህም ሰበብ እየፈለገች በልጆቹ በኩል እንዲጣሏት ትገፋፋቸዋለች። ባለታሪካችን ደግሞ በዚህ ቤት ማደግ ብቻ ሳይሆን የልጅነት እድሜያቸውን በአብዛኛው አሳልፈዋልና ማንንም ከማንም ማጣላት አይፈልጉም። ስለዚህም ስቃዩን ቻል አድርገው ኖረዋል።
በአጎታቸው ዘንድ ለትናንቱ ህጻን ለአሁኑ ጎልማሳ መምህር በቀለ ልዩ ልባዊ ፍቅር አለ። ለዚህም ነው በስማቸው ያስጠሯቸውም። ነገር ግን ዳግመኛ ለቤቴ መስታወት ትሆናለች ብለው ያገቧት ባለቤታቸው ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደችላቸውም። ደስተኝነታቸውንም ነጥቃቸው ነው የኖረችው። እንዲያውም እንግዳችን የእርሷ መረማመጃና ከአጎትዬው ጋር ጸብ መፍጠሪያ መንገድ ለማድረግ ብዙ ነገሮችን ትፈጥር እንደነበር አይረሱትም። ይህ ደግሞ የአጎታቸው ባለቤት በአጎትም ቤት እንጀራ እናት አለ እንዴ ያሰኛቸውም እንደነበር ያስታውሳሉ።
አስር አለቃ ወርቁ እርሳቸውና አንድ ልጅ ብቻ ነው ያላቸው። በዚህም በአላቸው ሁሉ ልጆቹ ተደስተው እንዲኖሩ ይፈልጋሉ፤ ያደርጉታልም። ይሁን እንጂ የአጎት ሚስት ይህንን አትፈቅድም። እነርሱን ማንም እንዲነካባቸውም እንደማይፈልጉም ስለምታውቅ ወጣ ሲሉ እንዲመራቸው ታደርጋለች። ይህ እንዳይሆን ባለታሪካችን እየተጨቆኑ ሳይቀር ዝም ቢሉም አባቴ የሚሏቸው አጎታቸው ግን በአጋጣሚ ያዩ ነበር። የዚያን ጊዜም መናገር ያለባቸውን ይናገራሉ፤ ተጣልተውም ያውቃሉ። ነገር ግን አጋጣሚ እየጠበቀች የፈለገችውን የምታደርገው ሚስት ይህንን ተግባሯን ማቆም አልቻለችም። ይህ ሁኔታም የልጅነት ጊዜያቸው ምሬት የተሞላበት እንዲሆንባቸው አድርጓቸዋል።
መምህር በቀለ በአጎታቸው ሚስት ጫና እንደልጅ ተጫውተው እንዳያድጉ ከማድረጉም በላይ ከአዲስ አበባ እንዲወጡና ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ውትድርና እንዲገቡ ያስገደዳቸው፤ በደስታ ተምረው የሚፈልጉት ህልም ላይ እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘም አንድ ጊዜ የሆነውን አጫውተውናል። ነገሩ እንዲህ ነው። ልጅ ናቸውና ለመጫወት እርሷ በወጣችበት ሰዓት ከቤት ወጡ። ቶሎ ግን መመለስ አልቻሉም። ከጓደኞቻቸው ጋር ያሻቸውን ጨዋታ ተጫውተውና ቦርቀው ሲመለሱ የጠበቃቸው ያላሰቡት ነበር። ለምን ወጣህ በሚል መቼም የማይረሱት ቅጣት ተጣለባቸው። ይህም በጨቅላ ጉልበታቸው የወፍጮ መጅ በአንሶላ አሳዝላ እንዲሮጡ ያደረገቻቸው ነው። ሁኔታው በሁለት መልኩ እርሳቸውን ቀጥቷቸዋል።
የመጀመሪያው የአቅም ጉዳይ ሲሆን፤ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን የወፍጮ መጅ ተሸክመው እንዲጫወቱ ማራወጧ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በጓደኞቻቸው ፊት እንዲሳለቁባቸው ማድረጓ ሲሆን፤ ተግባራቱ የሥነልቦና ጫና አሳርፎባቸዋል። መደብደቡ፣ ለጨዋታ ሲባል መሳቀቁ በህይወታቸው ውስጥ በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው ያደረገ እንደነበር አይረሱትም። ቁጡ የመሆናቸው ምስጢርም ይህ ጫና ያመጣው እንደነበር ይናገራሉ። እንዲያውም ከዚያ መገረፍ በኋላ ጨዋታ የሚባል ነገር አስበው አያውቁምም። ይህ መሆኑ ደግሞ አብዛኛ ጊዜያቸው የሚያልፈው በቤት ውስጥ ብቻ እንዲሆን አድርጓቸዋል።
እንግዳችን በቤት ውስጥ መዋላቸው ሌላ እድልን እንደሰጣቸው ያምናሉ። በተለይም አባቴ የሚሏቸውና በስማቸው የሚጠሩት አጎታቸው ካሉ ጊዜውን የሚያሳልፉት ታሪክ በመስማትና በማንበብ ስለሆነ ደስተኛ ናቸው። ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጡ በመሆናቸው አሉ የሚባሉ መፅሐፍትን ስለሚያመጡላቸው ጥሩ አንባቢ መሆን አስችሏቸዋልና በቤት መዋላቸውን ወደውት ኖረዋል። አጎታቸው አስር አለቃ ወርቁ የክቡር ዘበኛ አባል፣ የኮንጎና የኮርያ ዘማች እንዲሁም ታዋቂና አዋቂ ወታደር በመሆናቸው ለሥራ ከወጡ ግን ቤት መዋሉን አጥብቀው ይጠሉታል። ምክንያቱም ድብደባውና የሥራ ጫናው ቀላል አይሆንላቸውም።
እንግዳችን ከአዲስ አበባ የመውጣታቸው ምክንያት ይህቺው የአጎት ቤት እንጀራ እናት ስትሆን፤ አጎት ለዳግም ዘመቻ በተጠሩበት ወቅት ከሚችሉት በላይ ታሰቃያቸዋለች። ስለዚህም በቤት መቆየት ከበዳቸው። ይሁንና በመሀል አስር አለቃ ወርቁ መጥተው ነበርና ሁኔታው ስላልጣማቸው የዛን ጊዜ ኤጄሬ በአሁኑ አዲስ ዓለም ከሚባል ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ስፍራ አባታቸው ጋር ወስደው አስቀመጧቸው። ይሁን እንጂ እዚህም የተለየ ነገር አልገጠማቸውም። ሁኔታው ከበዳቸው። ስለዚህም ራሳቸውን ለማኖር ፓራ ኮማንዶ የሚባል ይቀጠር ነበርና አልመዘግብም ብለዋቸው በትግል በአራተኛው አባት እናት የለኝም ብለው መቀጠር ቻሉ። የልጅነት ሁኔታቸውም እዚህ ላይ አብቅቶ ወደራሳቸው ህይወትና ራስን ማስተዳደር ውስጥ ገቡ።
ተስፋን በትምህርት
መምህር በቀለ እንደማንኛውም ልጅ በአንድ ቦታ ተረጋግተው አይደለም ትምህርታቸውን የተከታተሉት። ከአራትና አምስት በላይ ትምህርትቤቶችን ረግጠዋል። ለአብነት ሀረር ጎዴ ላይ፤ አዲስ አበባ፣ ኤርትራና ጉደር በዋናነት ለትምህርት የረገጧቸው ቦታዎች ናቸው። መጀመሪያ ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት ግን በአጎታቸው ቤት በአዲስ አበባ እያሉ ሲሆን፤ በተለምዶ ሳር ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ባለው አባይ ምንጭ አንደኛ ደረጃ የግል ትምህርትቤት ነው። እንደየክፍሉ ብዛት ብር እየተከፈለም ነው የተማሩት። እስከ ስድስተኛ ክፍልም በትምህርትቤቱ ቆይተዋል።
ኑሮው አልደላደል ሲላቸው ደግሞ ተከታታይ ትምህርቱን አቋርጠው ፓራ ኮማንዶ እናት አባት የለኝም ብለው ተቀጥረው በለገዳዴ ስልጠና ወስደዋል። ለግዳጅ በሄዱበት ወቅትም ብዙም በውትድርናው ሳያገለግሉ መሰረተ ትምህርት ይመጣል። እንደእርሳቸው ያሉ እስከስድስተኛ ክፍል ፊደል የቆጠሩ ሰዎች ይፈለጉ ነበርና እንዲያስተምሩ እድል ይሰጣቸዋል። አጋጣሚው ደግሞ ለእርሳቸው የማስተማር ብቻ ሳይሆን የመማሩንም እድልን የሚያቀዳጅ ነበርና ጊዜ ሳይሰጡ በጎዴ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀን እየተማሩ ማታ ማስተማራቸውን ቀጠሉ። ሰባትን ጨርሰው ስምንተኛ ክፍልን ጀመሩ። ይሁን እንጂ ወቅቱ ጦርነት ስለነበርና እርሳቸውም ወደግዳጅ መግባት ነበረባቸውና ስምንተኛ ክፍልን ማጠናቀቅ አልቻሉም።
ግዳጃቸው ኤርትራ ላይ አስመራ ከተማ የሆነው ባለታሪካችን፤ ሁኔታው መረጋጋት ሲጀምር አስመራ ቀይ ባህር ትምህርትቤት በመግባት ያቋረጡትን ትምህርት ቀጥለው ነበር። ይሁንና እዚህም ቢሆን ስምንተኛ ክፍሉ መጠናቀቅ አልቻለም። ምክንያቱም ከእርሳቸው ጋር የሚሰሩ አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ምልከታ አልነበራቸውም። እንዲያውም ሊያስቀጧቸው ሰበብ ይፈልጉ ነበር። በዚህም አንድ ጊዜ ያሰቡት ነገር ተሳካላቸውና ለእስር ዳረጓቸው። ሁኔታው የተፈጠረው ለሥራ ወደ አዲስ አበባ በተላኩበት ወቅት ሲሆን፤ የርቀት ትምህርት መስጠት የሚፈልግ ትምህርት ቤት እንዳለ ሰሙ። ለመመዝገብ አድራሻውን ይዘው ወደ አስመራ ተመለሱም። ብዙም ሳይቆዩ በአድራሻው ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤያቸው ግን አዲስ አበባ ሳይሆን ኬኒያ ነበር የተላከው። ምክንያቱም አዲስ አበባ ያለው መስሪያ ቤት ፕሮግራም ፋሲሊቴተር እንጂ ትምህርት ሰጪ አይደለም። በዚህም በአድራሻቸው ከኬኒያም ምላሹ ይመጣላቸዋል።
ለማንኛውም ወታደር የሚመጣ ደብዳቤ በደንብ ይታያል። ከኬኒያ ሲሆን ደግሞ ደብዳቤው ሁሉንም ትኩረት ይስባል። ምክንያቱም በወቅቱ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚባል የፖለቲካ ቡድን በኬኒያ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ ሰራዊቱ ከጠላት ጋር ግንኙነት አለው ያስብላል። እናም የእንግዳችን ደብዳቤ በሦስት ምክንያቶች እርሳቸውን ተጠያቂ አድርጓቸው ነበር። የመጀመሪያው የመጣበት ቦታ ሲሆን፤ ሁለተኛው የተጻፈው በእንግሊዝኛ በመሆኑ የገባው አለመኖሩ ነው። ሊረዳቸውም የሚፈልግ አልነበረም። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ማህተም ቀይ ነበርና ከፖለቲካ ቡድን ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ስለዚህም አንብቦ የተረዳ ባለመኖሩ ወህኒ ወረዱ።
በወቅቱ አዛዥ የነበሩት ሻለቃ ጌታቸው ተክሌ ከሄዱበት ሥራ ሲመለሱ ግን ይህ ነገር መፍትሄ አገኘ። በሰራዊታችን ውስጥ ተቀምጦ ከጠላት ጋር ይገናኛሉ የተባሉትም ባለታሪካችን በነጻ ተለቀቁ። እንደውም በእስር ወደ ሰሜን እዝ ዋጠው የሚባል ማረሚያ ቤት በመግባታቸውና ከፍተኛ ስቃይን በማሳለፋቸው በጣም እንደተቆጧቸው ያስታውሳሉ። ምክንያቱም ዋጠው የሚባለው ማረሚያ ቤት እንደ ልብስ ሳጥን በቁልፍ የሚከፈት ሲሆን፤ ቀኑንና ምሽቱን ሳያውቁት ነው ወራቱ ያለፉት። በዚያ ላይ ምግብ በቀን ሁለት ጊዜ የሚሰጣቸው ሲሆን፤ እርሱም አንድ ደረቅ ዳቦ ነው። እናም በማያውቁት ነገር መሰቃየታቸው አዛዡን በጣም አናዷቸው እንደነበር አይረሱትም። በእናንተ መሀይምነት የልጁን አዕምሮ አበላሻችሁ ብለው የተቆጧቸውንም አይዘነጉትም።
መምህር በቀለ በወቅቱ ለመማር ብለው ብዙ መስዋዕትነትን ቢከፍሉም የመማር እድሉ በክፍያ ስለነበር አልተሳካላቸውም። በዚያ ላይ ለዘመቻ የሚሄዱበት ጊዜ ነበርና በአስመራ በኩል ዘመቻውን መቀላቀል ግድ ነው። ስለዚህም ግዳጅ ላይ እያሉ እግራቸውን በመመታታቸው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ ነው ዳግም ወደመማር የተመለሱት። ይህም ብዙዎቹ ጓደኞቻቸው ይወዷቸው ነበርና ረጅም ፈቃድ ጭምር እየሰጧቸው ነው ጉደር ላይ እየተመላለሱ ስምንተኛ ክፍላቸውን የቀጠሉት።
ወጣትነታቸው መጥፎ የሆኑ አሰራሮችን እንዲቃረኑና አይሆንም እንዲሉ ስላደረጋቸው እየሰሩ ሲማሩ ከቀበሌው አመራሮች ጋር መስማማት አልቻሉም ነበር። በዚህም ብሔራዊ ውትድርና ተይዘው ዳግመኛ እንዲሄዱ አደረጓቸው። ደዴሳ ማሰልጠኛ ገብተውም ከሰለጠኑ በኋላ ባሌ ውስጥ የምትገኘው መስኖ የምትባል ማሰልጠኛ ገብተው ግዳጃቸውን ጨረሱ። አሁንም ስምንተኛ ክፍልን እየተማሩ ሳለ ለሦስተኛ ጊዜ የዘመቻ ጥሪ ተደረገ። መልሶ ኤርትራም ደረሳቸውና ወደዚያ አመሩ። ከዓመታት ቆይታ በኋላም ያለውን ሁኔታ ሪፖርት እንዲያደርጉ አዲስ አበባ በተላኩበት ጊዜ የእነርሱ ክፍለጦር በመቀልበሱ ወደዘመቻው ተመልሰው ሳይሄዱ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ሆኑ።
በእርሳቸው እምነት ያልተማረ የትም አይደርስም ነውና ሁልጊዜ መማርን ያስባሉ። አንድ ቀን የተፈጠረው አጋጣሚ ደግሞ ግፊታቸውን እውን እንዳደረገው ይናገራሉ። ይህም በቤታቸው በነበረቺው ብላክ ኤንድ ኋይት ቴሌቪዥን ያዩት ነገር ሲሆን፤ በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያስመርቃል። ከተመራቂዎቹ መካከል ደግሞ አባትና ልጅ ሁሉንም የሳባቸው ነበር። በተለይ የልጁ እናት አበባ ይዘው ቆመው አበባውን ለማን ነው የምትሰጡት ተብለው ሲጠየቁ ለጋዜጠኛው የመለሱለት መልስ የእርሳቸውን ልብ ወዲያው የነካ ነበር። ይህም ‹‹እኔ መጀመሪያ ያገኘሁት ባለቤቴን ነው። አበባውም የሚገባው ለእርሱ ነው። ከፈለገ እርሱ ለልጁ መስጠት ይችላል›› ያሉት ነገር በእርሳቸው ጥረት መማር አለመቻላቸው ውስጣቸውን አስከፋው። አምላካቸውንም ‹‹እኔም ከልጄ ጋር ብመረቅ ምን አለበት›› ብለው ስቅስቅ ብለው እንዳለቀሱ የማይረሱት ንግግር ነው።
በወቅቱ ማልቀሳቸውን ያየች ባለቤታቸው ተስፋ ሰጥታቸው ነበር። ‹‹ያሰብከው ይሳካል›› ስትልም አጽናንታቸዋለች። ከዚያም አልፋ ህልማቸውን እውን ለማድረግ አረቄና ጠላ ሸጣ ካጠራቀመችው ገንዘብ ደርዘን ደብተር ገዝታ ለአዲስ ዓመት በስጦታ መልኩ አበርክታላቸዋለች። በጊዜው የሆነውን ማመን አልቻሉም። ምን እንደሚሏትና እንዴት እንደሚያመሰግኗትም ግራ ተጋብተው ነበር። ሆኖም ማድረግ ነበረባቸውና ራሳቸውን አረጋግተው ደስታቸውን ገልጸውላታል። ህልማቸውን ለማሳካት ላበረከተችላቸው ገጸበረከትም አመስግነዋታል። ከዚያ የህልማቸው መሪ የሆነችውን ሚስታቸውን ይዘውም የመማር ጉዟቸውን ጀምረዋል።
እንግዳችን ለመማር ሲነሱ በቤት ውስጥ ምንም ገንዘብ አልነበረም። በዚያ ላይ አራት ልጆች ተወልደዋል። ቤቱ እንዳይጎድል ሁለቱም መፍጨርጨር ነበረባቸው። በዚህም የመማሪያ ጊዜያቸውን መወሰን ግድ ነው። እናም ቀን እየሰሩ ማታ ለመማር ወሰኑ። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ፈተናን ማለፍ ይኖርባቸዋል። ይህም የማታ ትምህርት ቤት በጉደር ስለሌለ አምቦ ሄደው ለመማር በቀን 24 ኪሎሜትር መጓዝ አለባቸው። እርሱንም አድርገው ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን አንዱን ክፍል ዓመት ከመንፈቅ እየተማሩ በሦስት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል።
ወደ 11ኛ ክፍል ሲዛወሩ ደግሞ ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው በሚኖሩበት አካባቢ የመማር እድል አገኙ። ስለዚህም በጉደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ሆኑ። ነገር ግን ከዚህ በኋላም ቢሆን ሌላ ጭንቀት ነበረባቸው። የምድባቸው ጉዳይ። ርቀት ቢመደቡ ትምህርታቸው እንደሚቋረጥ ያስቡ ነበር። ሆኖም እድል ቀናቸውና አምቦ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በዚህም ገብተው ቢሆን የተለያየ ፈተና ገጥሟቸዋል። በዋናነት ግን የኢኮኖሚ ጉዳይ የራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር። በተለይም የመጀመሪያ ዓመትን እንዳጠናቀቁ የልጃቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ባለቤታቸውን የሚያግዛቸው እንዳይኖር ያደረገ ነበርና በእርሷ እገዛ ብቻ መኖሩ ከበዳቸው። በዚህም ለማቋረጥ ወስነው እንደነበር ይናገራሉ።
ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ከማህበረሰቡም ሆነ ከመምህራኑ እንዲሁም ከተማሪዎች የሚደርስባቸው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ በእልህ በመስራታቸው 3 ነጥብ 9 በማምጣት የግቢው ሰቃይ መሆን ችለዋል። ነገር ግን ቀጣዩን ዓመት ለማማር ደግሞ የቤተሰብ ጉዳይ ፈትኗቸዋል። በዚህም ዊዝድሮ እንዲጠይቁ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው ሀሳባቸውን ሊለቃቸው አልቻለም። ከፍተኛ ውጤትና አርአያ የሆኑ ሰውን አለማገዝ ውድቀት እንደሆነ ስለተሰማውም ፍላጎታቸውን በመግታት በቤተመጽሐፍ በቀን 20 ብር እየከፈሏቸው እንዲማሩ አደረጓቸው። ይህም ቢሆን ቤተሰቡን በሚፈልጉት ደረጃ የሚደጉም አልነበረምና ደስተኛ ሆነው መማር አልቻሉም። በዚህም ሌላ ያማትሩ ነበር። ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆነናም ከግቢው ሳይወጡ ሌላ የሥራ አጋጣሚ ተፈጠረላቸው። ይህም ዮቴክ የሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት ሀላፊ ስለዝናቸው ሰምቶ ነበርና በምን መልኩ እንደሚደግፋቸው ሲያስብ ቆይቶ በመጨረሻ አናገራቸው። የድርጅቱ ጥበቃ ሀላፊ አድርጎም በቀን 45 ብር እየታሰበላቸው እንዲሰሩ ቀጠራቸው። ይህ እድልም ቤተሰቡን ከመደገፍ ባለፈ በውጤት የተሻሉ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ አገዛቸው።
የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ ቀጥታ የተቀጠሩት መምህር በቀለ፤ የተማሩት ትምህርት አፕላይድ በመሆኑ ለማስተማርና ሁለተኛ ድግሪያቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ትምህርት መውሰድ ነበረባቸው። በዚህም ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የሁለት ዓመታት ትምህርትን ተከታትለዋል። ከዚያ እንደተመለሱ ብዙም ሳይቆዩ ለሁለተኛ ድግሪ ተወዳደሩ። የሥራ አፈጻጸማቸውም ሆነ ውጤታቸው ጥሩ ስለነበር አልፈው ዳግም አምቦ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀል ችለዋል። ዩኒቨርሲቲው በኮሮና ምክንያት የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን በአንድነት ላይ ማስመረቁ ደግሞ ከልጃቸው ጋር ለመመረቅ አብቅቷቸዋል። ምክንያቱም እርሱ የተማረው ምህንድስና በመሆኑ አምስት ዓመታትን በዚያ አሳልፏልና ነው።
እንግዳችን ዛሬም ቢሆን መማርን ይፈልጋሉ። ለዚህ ግን እድሉን የሚሰጣቸው ካላገኙ በእርሳቸው አቅም አይችሉም። ስለዚህም ‹‹ለሌሎች አርአያነቴ እንዲቀጥልና ማስተማር እንድችል አምቦ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌሎች ሦስተኛ ድግሪዬን እንድሰራ እድሉን እንዲሰጡኝ እማጸናለሁ። ለዚህ ደግሞ ጥሩ ውጤት ስላለኝ ያግዘኛልና አያፍሩብኝም›› ብለዋልም።
ወታደሩ ሰራተኛ
መምህር በቀለ ሥራን ሀ ያሉት በውትድርና ህይወት ነው። ይህም የሆነው ኑሮን ለማሸነፍ በሚሯሯጡበት ወቅት ነው። በዚህም ከአጎታቸው ቤት ሲወጡ አባትም እናትም የለኝም ብለው ሥራ ጀምረዋል። በእርግጥ መጀመሪያ ስልጠና ነው የወሰዱት ከዚያም በቀጥታ ወደ ውትድርናው ሥራ ገብተዋል። የመጀመሪያ ግዳጃቸውም በምስራቅ ጦር ግንባር ሰዲስና ሚዳጋሌ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ከሱማሌ ሰራዊት ጋር ውጊያ ያደረጉበት ነበር። ከዚያ በባቢሌ በኩል ወርደው ያሉ እንደ ደጋህአመዶ፣ ፊቅ፣ ቀብሪድሀርና ጎዴ እያሉም መዋጋት ችለዋል። ስለዚህም በውትድርናው አምስት ዓመታትን ማገልገል የቻሉ ሲሆን፤ በመሳሪያ ተኳሽና በባትሪ መሪነት የመሳሰሉት ላይ በመሳተፍ ዓመታቱን አሳልፈዋል። በስልጠናው ደግሞ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ቆይተዋል።
እንግዳችን በደርግ ጊዜ የመከላከያ አባል በመሆናቸው አገራቸውን እንዳገለገሉ ሰራዊት ሳይሆን አገራቸውን እንደሸጠ ባንዳ ተደርገው ነበር ሰራዊቱ ከተደመሰሰ በኋላ የሚታዩት። በዚያ ላይ ራሳቸውን ሰርተው እንዳያስተዳድሩ እንኳን ከመንግስት ጭምር ጫና ይደረግባቸው ነበር። በዚህም ኑሮን ማሸነፍ ከብዷቸው ቆይተዋል። ጉደር ከተማ ውስጥ መቀጠር ባለመቻላቸው ዘንቢል እስከመሸከም የደረሰ ሥራ ይሰሩ ነበር። በተመሳሳይ በአካባቢያቸው ሮድ ኮንስትራክሽን የሚባል ድርጅትም ስለነበረ በዚያ ባሬላ ተሸክመው የዕለት ጉርሳቸውን ይሞሉም እንደነበር አይረሳቸውም።
አምቦ ወረዳ ፍርድቤት አካባቢም ቢሆን ራፖር እየጻፉ የልጆቻቸውን ጉሮሮ ይደፍናሉ። ከዚያ ሲያልፍም ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ የማይሰሩት የቀን ስራ አልነበረም። ከኩትኳቶ ጀምሮ ያሉ ለእርሳቸው የማይመጥን፣ በማህበረሰቡ ዝቅተኛ የተባሉ ሥራዎችን ሰርተው ክፉ ቀኖችን አልፈዋልም።
እንደእርሳቸው አገላለጽ ‹‹ እኛ የደርግ ወታደር አይደለንም። ደርግ በነበረበት ጊዜ አገሪቱን ስንጠብቅ የቆየን ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት እንጂ። አገርን መጠበቅ ደግሞ የአንድ ፓርቲ ወገንተኝነትን አያሳይም። ነገር ግን ኢህአዴግ የአንድ ፓርቲ ደጋፊ ናችሁ ሲል አሰቃይቶናል፤ እኛን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባችንንም ጭምር ፈተና ውስጥ ከቷል። እኔን መሰል በእሳት የተፈጠነና በድል የተሻገረ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎች በህይወት እንኳን መቆየት አልቻሉም። ስለዚህም በእርሱ ሥራ ብዙዎች ነብሳቸውን ተነጥቀዋል። ለዓመታትም ከቤተሰቦቻችን፣ ከአገራችንና ከማህበረሰቡ ጋር ሊያጣሉን ብዙ ለፍተዋል። ግን አልተሳካላቸውም። ምክንያቱም እኛ አገራችንን በመውደድ እነርሱ ደግሞ አገራቸውን በመሸጥ ተለያይተናል። ዝቅ ብለን ሰርተን ለራሳችን በማሳለፋችን አሸንፈናልም›› ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ጉደር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በመምህርነት የሚያገለግሉት ባለታሪካችን፤ ይህንን ማድረግ የጀመሩትም የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እንደያዙ በ2007 ዓ.ም ነው። በኦሮምያ ደረጃ ሲወዳደሩ እድል ቀናቸውና ሌሎቹ መምህራን በርቀት ሲመደቡ እርሳቸው ቤተሰብ ስላላቸው በሚፈልጉት ቦታ ይመደቡ ተብሎ ጉደር ከተማ ላይ ከባለቤታቸው ጋር እንዲኖሩና እንዲሰሩ ሆኑ።
የዩኒቨርሲቲው ገጠመኞች
አምቦ እየተመላለሱ ሲማሩ ዩኒቨርሲቲን ሲናፍቁ እንደነበር ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በሩን እስማለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር። ቃል የእምነት እዳ ነውና ጊዜው ደረሰ። ማድረግም ግዴታ ሆነባቸው። በዚህም የወደቁ መስለው ተደፍተው የተሳለሙበት ገጠመኝ የመጀመሪያው ነው። ሌላው የማይረሳቸው ነገርና የገጠማቸው የትምህርት ማስረጃቸውን ይዘው ለመመዝገብ ከተማሪዎቹ ጋር ሪጅስትራል አካባቢ ሲጋፉ የሆነው ነው። በጊዜው ‹‹ አባት ለምንድነው የሚጋፉት፣ ለማን ነው የሚጋፉት፣ የታለ ልጁ፣ ልጁን አሳዩኝ›› ተብለዋልም። በወቅቱ ‹‹ ለልጅ አይደለም ራሴ ነኝ ተማሪው›› ሲሉት አላመናቸውም ነበርም። በዚያ ደረጃ ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰውም አስገርሞት ነበር። በዚህም ተቀብሎ ሲመዘግብ ማረጋገጡንና እንደሚያገብራቸው የገለጸላቸውን መቼም አይዘነጉትም።
በሦስተኝነት ደረጃ የገጠማቸው የውጪ ዜጋ የሆነው መምህራቸው ሊያስተምራቸው ሲገባ ያላቸውን ነው። እርሳቸው የዓይን ችግር ስላለባቸው የሚቀመጡት ፊት ወንበር ላይ በመሆኑ ከሁሉም በላይ እርሳቸው ላይ ዓይኑ አርፏል። በዚህም ተሳስተው ነው በሚል ‹‹ ይህ የመጀመሪያ ድግሪ ወይስ የሁለተኛ ድግሪ ክፍል ነው›› ሲል ጠየቃቸው። እርሳቸውም ‹‹የመጀመሪያ ›› አሉት። ‹‹ እርግጠኛ ነህ፤ የዚህ ክፍል ተማሪ ነህ›› አላቸው ዳግም ተገርሞ በጥርጣሬ እያያቸው። ልባቸው ቢሰበርም መመለስ ነበረባቸውና ‹‹ አዎን›› አሉት። እርሱም ሁኔታው ከሚያስበው በላይ ሆኖበት ማስተማሩን ቀጠለ። በተከታታይ ሲያገኛቸውም ወደማድነቁ እንደገባ አይረሱትም።
ቤተሰብ
ባለቤታቸው ወይዘሮ ሽብሬ ትባላለች። ለዛሬ ህይወታቸው መሰረት ብቻ ሳይሆን ህይወት የሆነቻቸው ነች። ምክንያቱም ዛሬን ያዩት አረቄና ጠላ እየሸጠች ህልማቸውን ስላሟላችላቸው ነው። በእርግጥ የተገናኙበት ሁኔታም በፈተና ውስጥ እያሉና ኑሮው ስለከበዳቸው የሚያግዛቸው ሲፈልጉ ነው። በዚህም ሚስት የባልና ሚስት መሰረታዊ የጋብቻ አስፈላጊነትን በሚገባ አሳይታቸዋለች። መረዳዳት ምን ያህል ለስኬት እንደሚያበቃ አረጋግጣላቸዋለችም። በዚህም የህይወቴ ቤዛ ናት ይሏታል።
ጥንዶቹ ለረጅም ዓመታት በፍቅር ቆይተዋል። አምስት ልጆችን አፍርተዋል። ሆኖም የማይሱት የጸብ ጊዜ ነበራቸው። ይህም በሰዎች ምክር ከዩኒቨርሲቲ ድረስ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሆኑበት ነው። ነገሩ የተከሰተው የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በሚማሩበት ጊዜ ሲሆን፤ አንቺ እንዲህ እየለፋሽ ታስተምሪዋለሽ እርሱ ግን ትቶሽ ለመሄድ ራሱን እያመቻቸ ነው በማለት በተደጋጋሚ ይነግሯቸው ነበር። እውነት የመሰላት ባለቤታቸውም ከልባቸው የሚሳሱላቸውን ባለቤታቸውን ከሰሱ። በፍርድቤትም ገተሯቸው። ነገር ግን በሁኔታው የተገረሙት ባለቤታቸው እንደማይሆን አሳመኗቸው። ተማምነው ችግራቸውን ፈቱ። ከዚህ ተሞክሯቸውም ባልና ሚስት ጠላትን የሚያሸንፉት መተጋገዝና መወያየት ሲኖር ብቻ ነውም ብለዋል።
መልዕክተ በቀለ
በኦሮምኛ ‹‹ብዴን ጋሪን ዱባ አቢዳቲ ›› በአማርኛ ደግሞ መልካም እንጀራ ከእሳት በስተጀርባ ነው እንደሚባለው የእርሳቸው ህይወት ይህንን መርህ ይይዛል። ምክንያቱም እሳትን በጎን ወይም በላይ፣ በስተቀኝ አለያም በስተግራው ማለፍ አይቻልም። ለማለፍ እሳቱን መሰንጠቅን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ብዙ ስቃይ አለበት። ጥንካሬንና ነገን ማለምን ይፈልጋል። እርሳቸው ደግሞ ይህንን ያምናሉ፤ ያደርጋሉም። በዚህም ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በምናውቅበት ልክ፤ ልናደርጋቸው በምንጓጓበት መጠን መጥፎ ነገሮችን መጋፈጥም ልምድ ልናደርግ ይገባል ይላሉ። መጥፎውን መጋፈጥ ካልተቻለ በምንም መልኩ ጥሩው አይገኝም ባይም ናቸው። እኔንም ከብዙዎች ለየት ያደርገኛል የሚሉትም ማስተማርና መማር አዲስ ሆኖ ሳይሆን በእስተርጅና ተምሮ በከባድ ስቃይ ውስጥ አልፎ ለዚህ መብቃት በመቻላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹እንደ እኔ ስቃይ አሳልፈው ለስኬት ለበቁ ሰዎች የምመክረው አሁንም ቀኑ አልመሸም በርቱ፤ ስማችሁን የሚቀይርና አለቃ የሚቀንስ ተግባር ላይ ተሰማሩ። መማርን የልባችሁ መሪ አድርጉት ነው። ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ለቀጣዩ ትውልድም የሚሉት አላቸው። ይህም የማያልፍ ነገር የለም ብላችሁ ለህልማችሁ ታገሉ። እውነተኛ ተግባር ይኑራችሁ። በእውቀትና በትምህርት ሁልጊዜ ራሳችሁን አሸንፉ። ምክንያቱም ለአብነት በእኛ ቤት ሁለተኛ ድግሪ ብርቅ አይሆንም። የቤቱ ሽማግሌ ይዞታልና። ብርቅ የሚሆነው ሦስተኛ ድግሪ ነው። ያም ቢሆን ላለመቀደም እጥራለሁ። ወጣቱም ይህንን ያድርግ የሚል ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደሃገር የዛሬዋ ቀን ላይ ለመድረስ የቻለችው የተባበረ ህዝብ ባለቤት፣ የተከባበሩ የህዝቦች ምድርና ጠንካራ ሀገራዊ ስሜትን መፍጠር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ባህሎች መገኛ በመሆኗ እንደሆነ የሚናገሩት መምህር በቀለ፤ የሀገር ፍቅር የተሟሸ ማህፀኗ ዘወትር ጀግኖችን ማፍራት አይሳነውም። ነገር ግን እንደ ህወሓት አይነቱ ይህንን ለማፍረስ ይሰራል። በእርግጥ ይህ ተግባራቸው እኛ በወታደርንት ባለንበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው። አሁን እየሆነ ያለውም አዲስም አይደለም። ምክንያቱም ህወሓት ከሱማሌ ጋር ስንዋጋ ሰራዊቱን በሞቃድሾ በኩል እየላከ የአገሪቱን መከላከያ ሰራዊት ይደበድብ ነበር። በተመሳሳይ በወቅቱ ጠላት ተብሎ ከተፈረጀው ሻቢያ ጋርም ገጥሞ መከላከያን ሲወጋ የነበረ ነው። ስልጣን ሲይዙ ቢሆን ለአፍሪካ ጭምር ግርማ ሞገስ የነበረን ሰራዊት የራሳቸውን ስልጣን ለማደላደል ሲሉ በትነውታል። ሀገር ማፍረስንም የተለማመዱት አሁን ሳይሆን ድሮ ጀምሮ እንደሆነም ይናገራሉ።
በደርግ ጊዜ የነበረ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሀብት ንብረት በደንብ ይጠነቀቃል፤ ጥይት ተኩሶ የመታው አንድም ንጹህ ሰው የለም። እንዲያውም ምግብ ሳይቀር እየለመነ ነበር ሲዋጋ የቆየው። ይህ ደግሞ ህዝባዊነቱን እንጂ ደርጋዊነቱን የሚያሳይ እንዳልሆነ በደንብ ያሳያል። ህወሓት ግን ዛሬ ጭምር ምን እያደረገ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። ስለሆነም ይህንን ባንዳ ድባቅ መምታት የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነውም ሌላው መልዕክታቸው ነው። በምክንያትነት ያነሱትም አሁን ባለው ሁኔታ ሳናቋርጥ ከተንቀሳቀስን ለእነዚህ አካላት ኢትዮጵያ መቃብር፣ ለወዳጆቿ የመንፈሳዊ ገነት ትሆናለች የሚል እምነት ስላላቸው ነው።
የመጨረሻ በማንነት ዙሪያ ያነሱት ሲሆን፤ እኛ የቤተሰብ፣ የአካባቢ፣ የጓደኛ፣ የምንከተለው ሃይማኖትና የተማርነው ሳይንሳዊ ትምህርት ድምር ውጤት ነን። በዚህም ማንነታችንን ለማሳየት ዛሬ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን የማንሳትና ወደነበሩበት ቀዬ የመመለስ ግዴታ የሁሉም መሆን አለበት ብለዋል። ለእኛ እነዚህ ሰዎች ቤተሰቦቻችን፣ በዜግነታቸው የምንመስላቸው ወገኖቻችን፣ ያም ባይሆን በሀይማኖት ሰው በመሆናቸው የምንዛመዳቸው ናቸው። ስለሆነም መረዳዳት ጥሩ ሰው ስለሆንን ወይም መጥፎ ስለሆንን የምናደርገው ሳይሆን ሰው ስለሆንን ብቻ የምንፈጽመው ነውና እነርሱን በማገዝ ለነፍሳችን ስንቅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል መልዕክታቸው ነው። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም