አዲስ አበባ፡- አዲስ የተቋቋመው የኢት ዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በእውቀታቸው ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ። ኤጀንሲው ስራውን ጀምሯል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኤጀንሲውን መቋቋም አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ኤጀንሲው ዳያስፖራው በእውቀቱ ለአገሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ፣መብትና ተሳታፊነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ከኤጀንሲው መቋቋም በኋላ ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮችና ሳይንቲስት ኢትዮጵያውያን ለማገዝ ፍቃደኛ ናቸው። የእነርሱን ሃሳብ ማዳመጥ፣ መቀበልና ማሳተፍ ይገባል።
ሆስፒታሎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የባለሙያ ክፍተት አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ለእረፍት ወደአገር ቤት ሲመጡ በፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ የሚደረግበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል። በኢንቨስትመንትና በንግድ ስራ ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበት አሰራር እንደሚዘረጋም አመልክተዋል።
ኤጀንሲው መንግስት ባወጣው መስፈርት መሰረት የውጭ ግንኙነትንና የአስተዳደር ስራዎችን የሚሰሩ 53 ባለሙያዎችና ሰራተኞች መቅጠሩን፣ በውጭ አገር በሚገኙ 60 ሚሲዮኖች ውስጥ ቅርንጫፎች እንዳሉትና በጀት ተመድቦለት ራሱን ችሎ መመስረቱንም ጠቁመዋል። አሁን ጽህፈት ቤቱን ካዛንቺስ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማድረጉን በመጠቆምም፤ በቀጣይ የራሱ ህንጻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኤጀንሲው ‹‹እኔ ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ለኔ›› የሚል መርህ እንዳለው ጠቁመው፤ አገሪቱ ለዳያስፖራው የምትሰጠው ነገር እንዳለ ሁሉ፤ ዳያስፖራውም ለሀገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ስላለ ግንኙነቱ የሁለትዮሽ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። ዳያስፖራው ሃሳቡን የሚገልጽበት የመረጃ መለዋወጫ መስመር እንደሚዘረጋም አመልክተዋል።
ዳያስፖራው ወደ አገሩ ሲመጣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎቹም ዘርፎች የሚያገኘውን ጥቅምና አሰራሩን እንዲያውቅ በየሚሲዮኑ ያሉ ባለሙያዎች መረጃ የሚሰጡበት ስርዓት እንደሚኖርም ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከአገሩ ውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋን ያለምንም ልዮነት ያስተናግዳል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ለአውሮፖ፣ ለአሜሪካ ለምዕራብ አገራት ወይንም በአረብ አገራት ለሚኖሩ ዳያስፖራዎች የተለየ አገልግሎት የሚቀርብበት ወይንም የተለየ ክብር የሚሰጥበት አሰራር አይኖርም፤ ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ እኩል የሚስተናገድበት ቤቱ ይሆናል ብለዋል።
ለዳያስፖራው ልናስብለት ልንቆረቆርለትና ችግር ሲደርስበትም ለመድረስ ያለበትን የምናውቅበት ስርዓት እንዘረጋለን ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃ የሚያዝበት የመረጃ ቋት ለማዘጋጀት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ኤጀንሲው በመቋቋሙ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋና የዳያስፖራውን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋም ተናግረዋል።
በዳያስፖራው ይነሱ የነበሩትን ቅሬታዎች በጥናት ለመለየትና የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለመቀመር ታስቦ ኤጀንሲው ወደ ትግበራ ሳይገባ መዘግየቱን አስታውሰው፤ የውጭ አገር ተሞክሮ፣ በህግ፣ በአሰራርና በመመሪያ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመመርመር ሊያሰራ የሚችል መዋቅርና አሰራር ተዘጋጅቶ መጽደቁን ተናግረዋል። የተለዩ ውጤታማ አሰራሮች እንደሚቀጥሉና ክፍተቶች የሚታረሙበት አካሄድ እንደሚከተልም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሆን እንደ አንድ ፌዴራል መስሪያ ቤት መቋቋሙ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በዘላለም ግዛው