የመንግስት ምስረታ ድግሱ ተጠናቅቋል። የሚሾሙም ተሹመው ወደ ስራ ገብተዋል። የመንግስት ምስረታ በአሉ ትውስታ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚለቀን አይመስልም።
ባለፉት ዘመናት በእኛ ሀገር የመንግስት ምስረታ ሂደት በፓርላማ ብቻ የሚያልቅ ጉዳይ ነበር። የዘንድሮው ግን ይለያል። በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ በታደመበት፤ የሀገሮች መሪዎች፣ ተወካዮች፣ አምባሳደሮች በተገኙበት፤ ለቀጣይ 5 ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራት መሪ እና መንግስት በአለ ሲመት ተደርጓል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በአለም ፊት ሀገሪቱንና ህዝቧን በቅንነት ሊያገለግል ቃልም ገብቷል።
ጠቅላላ ስርዓቱ ውብ ነበር። በዚህ ውብ ስርዓት ላይ ታዲያ ነገሩን የበለጠ ውብ ያደረገው ስለ ኢትዮጵያ የተነገረው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደተለመደው በጣም በሚመጥናት መልኩ ኢትዮጵያን አሳ ምረው ገልጸዋታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እንዲያ ማሽሞንሞን እና አቀማጥሎ መጥራትስ መቼም የተለመደ እና የሚጠበቅባቸው ነውና አንገረምበት ይሆናል። ነገር ግን የእለቱ እንግዶች ኢትዮጵያን በትክክለኛ ስሟ እና ክብሯ ሲገልጧት መስማት የነፍስ ሀሴት ነበር። የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ፤-“ኢትዮጵያ ትልቅ የሚያኮራ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ወደኋላ መለስ ብለን ታላቋን አቢሲኒያ ስናያትም ኢትዮጵያ የብዙ አፍሪካ ሀገራት እናት ከመሆኗም በላይ የብዙ አፍሪካ ሀገራትን ችግሮች ይዛ የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል የሆነች፤ ከዚያም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ብዙ ሚና የተጫወተች ናት። ” ሲሉ ኢትዮጵያን ገልጸዋታል። ልብ አድርጉ ይህን ያሉት የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ናቸው። የኛዎቹስ ምን ይላሉ? የኛዎቹማ የዚህን ተቃራኒ ነው የሚሉት። አንድ በጣም ታዋቂ የፖለቲካ ሰው እና የህዝብ ትግል መሪ ነኝ የሚል ግለሰብ እንግዳው ፕሬዚዳንት “የሚያኮራ ታሪክ ያላት ናት” ያሏትን ሀገሩን “እንደ ህዝብ የጋራ የሆነ የጀግነነት ታሪክ የለንም” ብሎ በድፍረት አቃልሏታል። ዛሬ ጁንታ ሆነው ሀገር የሚያምሱት የቀድሞ መሪዎቿ ደግሞ ይቺን ባለ ብዙ ታሪክ ሀገር “የ100 አመት ታሪክ ብቻ ነው ያላት” ብለዋል። ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ብዙ መስዋዕት የከፈለችውን ሀገር ቅኝ ግዛት ይዛናለች የሚሉ ጉደኞችም አሉ። ይገርማል። ሌላው ያደንቀናል እኛ ራሳችንን ለማዋረድ እንተጋለን።
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ደግሞ፤ “ኢትዮጵያ እናታችን ናት፤ ታላቅ እናታችን። ኢትዮጵያ ባትኖር ኖሮ ደቡብ ሱዳን አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ አትደርስም ነበር። ” ሲሉ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል። በበአለ ሲመቱ ወቅት ነው፤ ሩቅም አይደለም። የጎረቤት ሀገር መሪ ናቸው እንግዲህ ኢትዮጵያን እናቴ ብለው የሚጠሯት። አስደናቂ ነው።
ይህ ከንቱ ሙገሳም አይደለም። በእውነትም ኢትዮጵያ ለማንም ቢሆን እናት ናት። ነገር ግን ይህ እውነታ ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ይልቅ ጎልቶ ሊሰማ ይገባ የነበረው ለእኛ ነበር። የሆነው ግን እንደዛ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ እናታቸውን የሚወቅጡ የሙቀጫ ልጆች ተወልደዋል። ኢትዮጵያን እናቴ ማለት ቀርቶ ኢትዮጵያ ማለት ራሱ ነውር ሆኖባቸው “ሀገሪቱ” እያሉ ሲጠሯት የኖሩ ገዢዎችም ነበሩ። ”እናት ሀገር ኢትዮጵያ” ማለት ያለፈውን ስርአት መናፈቅ ነው። ነፍጠኝነት ነው፣ ወዘተ እያሉ ህዝብን ሲያሸማቅቁ የኖሩ ሀይሎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ያሳዝናል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደግሞ እንዲህ አሉ፤- “ኢትዮጵያ የሁላችንም አፍሪካውያን እናት ነች። እናት ሰላም ካልሆነች ደግሞ መላው ቤተሰብ ሰላም እንደማይሆን ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ሰላም ነው። ”ግሩም ንግግር ነው። ግሩም ንግግር ብቻ ሳይሆን እውነትም ነው። ያለ ኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ሰላም አይኖርም። ነገር ግን የኛው ጉዶች የሚያስቡት ከዚህ በተቃራኒ ነው። ኢትዮጵያን አፍርሰው እነሱ በሰላም ሀገር ሆነው እንደሚቀጥሉ ያስባሉ። ሌሎች የእኛ ሰላም የእነሱም ሰላም እንደሆነ ሲናገሩ፣ የእኛ ጁንታዎች ግን የኢትዮጵያ መበጥበጥ እና መፍረስ የሰላማቸው ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስም ቢሆን እንደሚወርዱ ይምላሉ፤ ይገዘታሉ። አስደንጋጭ ነው።
የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ፤- “ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ያህል የአፍሪካ የፖለቲካ ትእይንትን እየተመለከትኩ እና እየተሳተፍኩ ቆይቻለሁ። በዚህ ሰላሳ ዓመት ውስጥ ያስተዋልኳቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። በኡጋንዳ ካጋጠሙን ችግሮች አንዱ የማንነት ፖለቲካ ነበር። እኔ ከዚህ ጎሳ ነኝ፤ እኔ ከዚያ ነገድ ነኝ፤ እኔ የዚህ ሀይማኖት ተከታይ ነኝ፤ እኔ የዚያ ሀይማኖት ተከታይ ነኝ የሚሉ ነገሮች ብዙ ችግር ፈጥረውብናል። ዩጋንዳ ወደ አንድ መምጣት የጀመረችው የማንነት ፖለቲካ ጉዳይን መስመር በማስያዝ ወደ የፍላጎት ፖለቲካ ማራመድ ስንጀመር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የፍላጎት ፖለቲካ ወይስ የማንነት ፖለቲካ ይሻላል የሚለውን በትኩረት እንዲያሰላስል እመኛለሁ። ” ሲሉ ገልጸዋል።
መቼም ይህ የሙሴቪኒ ንግግር አንድም የሚጣል ነገር የለውም። ሀገራችን እንዲህ እየታመሰች ያለችው በማንነት ፖለቲካ ነው። ይህን ማንም ሊክድ አይችልም። ታዲያ እንግዳው ሰው እንኳ ይህ ታይቷቸው ተው የያዛችሁትን መንገድ እኛም ሄደንበት ወድቀናል ሲሉ የኛ ጽንፈኞች ግን በተቃራኒው የማንነት ፖለቲካ ከተነካ ሀገር ይፈርሳል፤ በኛ መቃብር ላይ ካልሆነ ይህ የስህተት መንገድ ሊቃና አይገባም እያሉ ይፎክራሉ። አሳፋሪ ነው።
በጥቅሉ ይህ የመንግስት ምስረታ በዓል እና በበዓሉ ላይ በጎረቤት ሀገራት መሪዎች የቀረበው ንግግር ያመለከተን በእጃችን ያለችውን ወርቅ ኢትዮጵያችንን በአግባቡ እንዳልወደድናት እና እንዳላከበርናት ነው። በእኛ አይን ሟሽሻ እና ደብዝዛ የምትታየው ሀገራችን በሌሎች አይን ግን ግዙፍ እና ደማቅ እንደሆነች ተገንዝበናል።
እርግጥ የሀገራችንን ታላቅነት እና ውድነት ለማወቅ የጎረቤት ምስክርነት አያስፈልገንም ነበር። ግን እንደዚያ ሆነ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረትም እንዳንዶች ተራ የቃላት ጨዋታ እና ከንቱ ውዳሴ ቢመስላቸውም እውነታው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራችን ትልቅ እንደሆነች ለማሳየት ነው ጥረታቸው። ምክንያቱም ትውልዱ የኢትዮጵያን ታላቅነት ረስቷል። ስለረሳም ነው የኢትዮጵያን ታላቅነት በሰማ ጊዜ እንደ አዲስ የሚገረመው።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን፤ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ናት፤ ኢትዮጵያውያን የጋራ የድል ታሪክ የላቸውም፤ እኔ ምንትስ ፈርስት ነኝ፤ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት ያለፈውን ስርዓት መናፈቅ ነው ወዘተ…የሚሉ እሳቤዎች እና ንግግሮች አንድም ታሪክን ያለማወቅ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት ለረዥም ጊዜ ካለመስማት የተነሳ ኢትዮጵያን እንደ ተራ ጎጆ የማየት ውጤት ናቸው።
የኢትዮጵያን ትልቅነት እና ውብነት መረዳት ደግሞ ልክ መሪዎቹ እንዳደረጉት ኢትዮጵያን እናት፤ የአፍሪካ የነጻነት ፋና ወጊ፤ የጥቁር ህዝብ ኩራት፤ የጀግንነት ተምሳሌት፤ የወዳጅነትን ጥግ፤ የብዝሀነት ውበት ማሳያ፤ የአንድነት ጉልበት ማስተማሪያ እያሉ ለማሞካሸት ምክንያት ይሆናል።
ጓዶች፤ ሁላችንም እንረዳ፤ ኢትዮጵያ ከኛ እይታ እና ትውስታ በላይ በጣም ትልቅ እና ውብ ናት። ወዳጆቻችን ይህን ስለሚያውቁ በሚገባ ያሞግሷታል። ጠላቶቻችንም ታላቅነቷን ስለሚያውቁ ይህን ታላቅነት የሚረዳ ትውልድ እንዳይፈጠር ከተቻለም ደግሞ እንደ ጁንታው አይነት አደገኛ ጠላት እንዲፈጠርባት የቻሉትን ያህል ይሞክሩባታል። ስለዚህም ይህን ተረድተን ወዳጆቻችን ከሚያከብሯት በላይ እንድናከብራት ጠላቶቻችን ከሚፈሯትም በላይ እንድንፈራት ያስፈልጋል። የኛዋን ጨው፤ ኢትዮጵያን እኛ ባለ አሞሌዎቹ እንውደዳት። ይህን ማድረግ የማንችል ከሆነ ሌላው ወስዶ እየላሰ ያጣጥማታል።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም