ዓለማችን የጉልበተኞች መሆን ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። በተለይ ከ15ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የአንድ ሃገር ህዝቦች የሌላውን ሃገር ህዝቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ግዛትን ለማስፋፋት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ድረስ የአውሮፓ ሀገሮች የአፍሪካን፣ ሰሜን አሜሪካን እና የእስያ ሃገሮችን የተቆጣጠሩበት ዘመን ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው። በነዚህ ዘመናት ቅኝ ገዢዎቹ ቅኝ የገዙት ታዲያ የተፈጥሮ ሃብቱን ወይም ንብረቱን ብቻ አልነበረም፤ ከዚያም አልፎ የሰዎችን ስነልቦናም ጭምር የአተሳሰባቸው ምርኮኛ አድርገዋቸው ቆይተዋል።
አዴሌ የተባሉ አንድ የናይጄርያ ምሁር ስለቅኝ ግዛት በፃፉት መፅሃፍ እንደጠቀሱት በአፍሪካ የቅኝ ግዛት አገዛዝ በይፋ ካበቃ ከ60 ዓመታት በኋላም በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች አሁን ድረስ በታሪክ ክፍለ ጊዜ ስለ ቅኝ ግዛት ትምህርት ይሰጣል። በትምህርት መርኃግብሮቹም ልጆችን ሌሎች ሀገራትን ቅኝ ስለመግዛት ያስተምሯቸው ነበር። ለብሪታንያ ህዝብ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን በባርነት መግዛት ጥሩ ነገር እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። በበርካታ የአፍሪካ ሃገራትም የታሪክ ትምህርት መምህራን ነጮች ነበሩ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በአብዛኛው ተቀይሮ በሌላ እንዲተካ ተደርጓል። ለዚህ ኢትዮጵያ ጣልያንን ለመጀመርያ ጊዜ ያዋረደችበት እና ጥቁር ህዝብ መብቱን ማስከበር እንደሚችል ያሳዩበት አድዋ ድል መሰረት እንደነበር ይታወቃል።
ሃያላኑ ሃገራት ከሁለተኛው የዓም ጦርነት በኋላ ፈትለፊት ገጥሞ መዋጋት ያለውን ጣጣ ሲረዱ የጀመሩት አዲሱ ስልት የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ነው። በዚህ የተነሳ አንዱ ሌላውን መወንጀል፤ በስነልቦና የበላይነት መያዝ እና በሌሎች የሰብአዊ ድጋፍና እርዳታ ስም የድሃ አገራትን ተፈጥሮ መበዝበዝ አዲሱ ስልታቸው ነው።
በዚህ ወቅት ታዲያ የሚገዳደራቸው አልያም ወደስልጣኔ ሊገባ ነው ብለው የሚያስቧቸውን ሃገራት የማዳከም እና ባስ ሲልም እስከ በሃይል ለማንበርከክ የዘመናዊ ጦር መሳርያዎቻቸው መፈተሻ እስከማድረግና ሃገርን እስከማፍረስ የሄዱበት ርቀት የዚህ ዘመን ትውልድ ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው።
በተለያዩ መንገዶች ትብብራቸውን በማጠናከር በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱት አሜሪካና ጥቂት የአውሮፓ ሃገራት ከነሱ በተቃራኒ የቆሙ ሃገራትን ሁሉ በተለያዩ መንገዶች በማዳከም እና በማፍረስ በርካታ ሃገራትን ለድህነት፤ ዜጎቻቸውን ደግሞ ለከፋ ችግር ዳርገዋል። ከዚህ አንጻር በተለይ በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉትና የቀደመ ስልጣኔ የነበራቸው እንደነ ሶርያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ እና ሊቢያን የመሳሰሉ ሃገራት የዚህ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሃገራት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
ከቅርብ ጊዜ ደግሞ አሜሪካ ዋነኛዋ ሃያል ሃገር መሆኗን ተከትሎ የዓለም ሃገራት ሁሉ ፖሊስና ጠባቂ እኔ ነኝ በሚል በእያንዳንዱ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጭምር ጣልቃ በመግባት በዚህ መንገድ ካልሄዳችሁ ከፊታችሁ ገደል አኖራለሁ በሚል ከፍተኛ የሃይል እርምጃ ውስጥ መግባት ጀምራለች። ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሽብርተኝነት በሚል ሽፋን ብዙ ሃገራትን አፍርሳለች፤ ለዚህ አፍጋኒስታን የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ናት።
በአሁኑ ወቅትም ፊቷን በሰበብ በአስባቡ ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ለማዳከም እየሰራች ነው። በዚህም መሰረት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጀምሮ በትግራይ በሚካሄደው ጦርነት በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ሚዛን የሳተ አቋም በመያዝ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሰራች ነው። ለዚህ ደግሞ በአሜሪካ ሳንባ የሚተነፍሱት የተባበሩት መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም በግብፅ የሚሽከረከሩት የአረብ ሊግ ከጎኗ ተሰልፈዋል።
በዚህ የተነሳ የፀጥታው ምክር ቤት ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ ጉዳይ አስር ጊዜ ስብሰባ አካሂዷል። የአውሮፓ ህብረትም ሰሞኑን ተሰብስቦ ኢትዮጵያ በሰብአዊ ድጋፍ ስም ከአሸባሪው ቡድን ጋር ሲሰሩ የነበሩ የእርዳታ ድርጅት ኃላፊዎችን ከሃገሯ ማስወጣቷን ኮንኗል። ከዚህም አልፎ እስከመጪው ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ሰላም ካላሰፈኑ ማዕቀብ እጥላለሁ የሚለውን ማስፈራያ አክሏል።
እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ያካሄደችውን ዴሞክራሲዊ ምርጫ ተከትሎ መንግስት መመስረቷ ከዚህም አልፎ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ የካቢኔ ኣባላቷን ማዋቀሯ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተነቃቃ የህዝብ አንድነትና ህብረት እየተገነባ መሆኑ ያስከፋቸው ይመስላል።
ኢትዮጵያ ግን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በይፋ ጀምራለች። ከዚህ በኋላ ከዚህ የዕድገት ጎዳና የሚመልሳት ሃይል አይኖርም። አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ከድህነት እድንትወጣና ከልመና ተላቃ በሁሉ ዘርፍ ራሷን የቻለች ሃገር እንድትሆን የበኩላቸውን ድጋፍ ቢያደርጉ ለዓለም ሰላም ወሳኝ ነው። ይህም ባይሆን ደግሞ ልክ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰላማችንንም ሆነ ልማታችንን ሁሉ በራሳችን እንድናከናውን ጫና ባያደርጉ መልካም ነው። ለማንም ግልጽ መሆን የሚገባው ግን ኢትዮጵያ በማንኛውም መልኩ ወደልማትና ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ለአፍታም ቢሆን የማታቆም መሆኑን ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም