የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በባህር ዳር ያደርጋል። በቀጣዩ ዓመት (እአአ 2022) በኳታር በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችለውን እድል ለማግኘት በምድብ ሰባት የሚገኙት ቡድኖች ዛሬ በባህርዳር እና በጋናዋ ኬፕ ኮስት ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው የእግር ኳስ ስፖርት ትልቁ ውድድር ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስር የሚገኙ ሃገራትም ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን በ10 ምድብ ተከፍለው ማጣሪያ በማድረግ ላይ ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነው። በመሆኑም ዛሬ ብቸኛ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የማስተናገድ ፈቃድ ባለው የባህር ዳር ስታዲየም ዋሊያዎቹ ባፋና ባፋናዎቹን ያስተናግዳሉ። ከቀኑ 10ሰዓት ላይ በሚደረገው በዚህ ጨዋታ ተመልካቾች በስታዲየም ተገኝተው ለቡድናቸው ድጋፍ መስጠት የማይችሉ ሲሆን፤ በፊፋ ቲቪ (ዩቲዩብ) አማራጭ የስፖርት ቤተሰቡ ጨዋታውን መመልከት ይችላል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ሁለት ሳምንታትን አስቀድመው ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። 25 ተጫዋቾችን ያቀፈው ቡድኑ ዝግጅቱን ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሯል። የቡድኑ የመሀል ሜዳ ሞተር ሽመልስ በቀለም ከቀናት በኋላ በባህርዳር ዋልያዎቹን ተቀላቅሏል። በዝግጅቱም የእርስ በእርስ ግጥሚያ ከማድረግ ባለፈ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተመልክቶ በመወያየት እንዲሁም በባለሙያዎች የታገዘ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቆይተዋል። ከጉዳት ጋር በተያያዘም በቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ያጋጠመው የመስመር ተጫዋቹ ሽመክት ጉግሳ ባለማገገሙ ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል።
ዋሊያዎቹ በዛሬው ጨዋታ ጠንካራዋን ደቡብ አፍሪካን በሜዳቸው ረተው ሶስት ነጥብ ለማስመዝገብ ነው የሚጫወቱት። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም ከደቡብ አፍሪካ ጋር በተገናኘባቸው መድረኮች አቻ እንዲሁም ብልጫ ይዞ በመውጣት ይታወቃል።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ባፋና ባፋናዎቹ ለዚህ ጨዋታ ለሚሰለፉ የቡድኑ አባላት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር ጥሪ የተደረገላቸው። የቡድኑ አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ ለወሳኙ ፍልሚያ ጥሪውን ያስተላለፉት ለ34 ተጫዋቾቻቸው ነው። ቡድኑ በተመሳሳይ አንድ ጉዳት ያስመዘገበ ሲሆን፤ ፔርሲ ታኡ የተባለው ተጫዋች ከስብስቡ ውጪ ሆኗል።
በዓለም ዋንጫው አምስት ሃገራትን የምታሳትፈው አህጉረ አፍሪካ የኮንፌዴሬሽኑ አባል ብሄራዊ ቡድኖችን በአስር ምድብ በመከፋፈል የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያካሄደች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምቧቡዌ ጋር ተደልድሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ከጋና ጋር እንዲሁም በሜዳው ከዚምቧቡዌ አቻዎቹ ጋር ማድረጉ የሚታወስ ነው። ጋና ላይ በጥቁር ከዋክብቱ 1 ለ 0 የተሸነፈችው ኢትዮጵያ ከቀናት በኋላ ደግሞ ዚምቧቡዌን በባህርዳር ስታዲየም አስተናግዳ 1ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፏ ይታወቃል።
የምድቡ ሶስተኛው ጨዋታም ባላት ነጥብ ቀዳሚ ከሆነችው ደቡብ አፍሪካ ጋር የምትጫወት ይሆናል። ትናንት ማለዳ 39 የቡድኑን አባላት ይዞ በባህርዳር የተገኘው የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው ከዚምቧቡዌ ጋር ተገናኝቶ ያለምንም ግብ ነበር የተለያየው። በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ጋናን 1ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። በዚህም ቡድኑ በ4 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጀመሪያው ስፍራ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ እና ጋና አንድ አንድ ጨዋታ በማሸነፍ እኩል ሶስት ነጥብ ሲኖራቸው ዜምቧቡዌ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ትይዛለች።
በምድቡ ዛሬ በሚካሄደው የሶስተኛ ዙር ሌላኛው ጨዋታ ጋናና ዚምቧቡዌ በኬፕ ኮስት ሁለገብ ስታዲየም ይገናኛሉ። ከአራት ቀናት በኋላ ጥቅምት 02 ቀን 2014 ዓም ደግሞ ዋሊያዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጪ ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጋር በጆሃንስበርግ የሚያደርጉ ይሆናል። በዚሁ ዕለት የዜምቧቡዌ ብሄራዊ ቡድን ገናዎችን /ጥቋቁር ከዋክብቱን/ በሃራሬ የሚገጥሙ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014