አይንዎ አንዱና ወሳኙ የሰውነትዎ አካል ነው። በሰውነትዎ ውስጥ ያለው ልዩ ተግባርም በጣም አስፈላጊ የአካል ክፍል ያደርገዋል። ልክ እንደተቀሩት የሰውነት ክፍልዎ ታዲያ አይንዎም የሚፈልገውና የሚጠላው ነገር አለ። ከዚህ አንፃር የአይንዎ ጤና እንደሚያሳስብዎ ምንም አያጠያይቅም።
ለአይንዎ ጤና የሚስማሙ የተለያዩ ምግቦችና መጠጦች እንዳሉ ሆኖ የማይስማሙም ይኖራሉ። ይሁንና የአይንዎን ጤና በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አምስት የተፈጥሮ መጠጦች አሉ።
እናም ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮሀ›› እንዲሉ አንዴ የአይንዎ ጤና ከተቃወሰ በኋላ ዳግም ለመመለስ ችግር ውስጥ ከሚገቡና ለከፍተኛ የህክምና ወጪም ከሚዳረጉ በቀላል ወጪ የሚከተሉትን ተፈጥሯዊ መጠጦች ይሞክሯቸው።
1ኛ፡- የብርቱካን ጭማቂ፡-
የብርቱካን ጭማቂ ስልዎ እንደው በፋብሪካ ተመርተውና ታሽገው ለገበያ የሚቀርቡትን አይደለም። እነዚህኞቹ የብርቱካን ጭማቂዎች በውስጣቸው ብዛት ያለው ስኳርና ጭማቂው ሳይበላሽ ለረጅም ግዜ ለማቆየት የሚያስችል ኬሚካል በመሆናቸው ለአይንዎ ጤና መልካም ናቸው ተብሎ አይመከርም። ስለዚህ ይህ ይቀርብዎና ራሱ ብርቱካኑን ከፍራፍሬ መደብር ይግዙና በቤትዎ ጭማቂውን አዘጋጅተው ዘወትር ይጎንጩ። በአጭር ግዜ በአይንዎ ጤንነት ላይ ለውጥ ይመለከታሉ።
2ኛ፡- የካሮት፣ ቀይስርና ፖም ጭማቂ
ካሮት በርከት ያሉና ወደ ቪታሚን ኤ የሚቀይሩ ‹‹ቤታ ካሮቲን›› የተሰኙ ቀለማትን ይዟል። ይህ ቪታሚን ኤ ደግሞ ለሁንተናዊ የአይንዎ ጤንነት እጅግ አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀይስር ‹‹ማኩላርና ሬቲና›› የተሰኙ የአይን ክፍሎች ጤንነትን የሚጠበቁ ‹‹ሉቲን እና ዚያዛንቲን›› የተባሉ ንጥረ ነገሮችን አቅፏል።
ከዚህ ውጪ ፖም የአይን እይታን ከፍ በሚያደርጉና የአይን ጤናን በሚያሻሽሉ ‹‹ባዮፍሌቨኖይድ›› በተሰኙ ንጥረ ነገሮች የበለፀገ ነው። ከዚህ አንፃር እነዚህን ፍራፍሬዎች ደባልቀው አልያም ለየብቻቸው ጨምቀው ቢጠጧቸው የአይንዎን ጤና በዘላቂነት መጠበቅ ይችላሉ።
3ኛ፡- የእንጆሪ ጭማቂ
የእንጆሪ ፍሬ ‹‹አንቲኦክሲደንትስ›› የተባሉ ንጥረ ነገሮችን በከፍተኛ መጠን ይይዛሉ። በአጠቃላይ የእንጆሪ ፍሬዎች በሰውነት ውስጥ ‹‹የኦክሳይድ›› ውጥረትን ለመዋጋት የሚረዳ የበለፀገ ምግብ ተደርገውም ይቆጠራሉ። ለተሻለ የዓይን ጤናም አስፈላጊ ናቸው ተብለው ይታሰባሉ።
ከሁሉ በላይ ደግሞ እርጅናን ተከትሎ የሚመጡ የአይን ችግሮችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ የእንጆሬ ፍሬ ጭማቂ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ስለሆነም ለአይንዎ ጤንነት ሲሉ የእንጆሬ ጭማቂን ከመጠጣት ወደኋላ እንደማይሉ ጥርጥር የለውም።
4ኛ፡- የሙዝ ጭማቂ
የሙዝ ጭማቂ ‹‹አልፋና ቤታ ካሮቲን›› የተሰኙ ንጥረ ነገሮችን ያሟላ ነው። የሙዝ ጭማቂ የአይን ጤናን በማሳደግ ረገድም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። እናም ሙዝ በአቅራቢያዎ እንደልብ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ ጭማቂውን የዘወትር መጠጥዎ ያድርጉ።
5ኛ፡- የቲማቲም ጭማቂ
ቲማቲም ከፍተኛ ጥራት ያለውና ‹‹ላይኮፒን›› የተሰኘ ንጥረ ነገርን የያዘ ነው። ይህ ንጥረ ነገር በተለይ ከአይን እይታ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥምዎትን ችግሮች አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዳና የአይንዎን ጤናንም በእጅጉ የሚጠብቅልዎ ነው።ምንም እንኳን የቲማቲም ጭማቂ የመጠጣት ልምድዎ እምብዛም ቢሆንም ጭማቂው የአይንዎን ጤና ከመጠበቅ አኳያ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለመጠጣት አያመንቱ።
ምንጭ፡- ኦፔራ ኒውስ
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014