በስድስተኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ አመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ‹‹ከመንግስት የጤናው ዘርፍ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ የማይበገር የጤና ስርዓት በመገንባት የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻልና ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማድረግ ነው›› ብለዋል።
መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ምክንያት የሚደርሱ የእናቶችና ህፃናት ሞትን መግታት፤ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ የሚደርስ ህመምና ሞትን መከላከልና መቀነስ ብሎም ዜጎችን ከድንገተኛ የጤና አደጋዎች መጠበቅ በቀጣይ በጤናው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል። የወረዳ ትራንስፎርሜሽንን ማምጣት እና ተገልጋይ ተኮር እንዲሁም ተአማኒነት ያለው የጤና ሥርዓትን መዘርጋት በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ ተካተው የሚሰሩ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ለመሆኑ በሽታ መከላከል ላይ ያተኮረና የማይበገር የጤና ስርዓት እንዴት መገንባት ይቻላል? ይህን የጤና ስርዓትስ እንዴት ነው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ማድረግ የሚቻለው?
በተመሳሳይ ይህን የጤና ስርዓት በመጠቀም እንዴት የእናቶችና ህፃናትን ሞት መግታት፣ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚደርሰውን ሞት መቀነስ እንዲሁም ዜጎችን ከድንገተኛ የጤና አደጋዎች መጠበቅ ይቻላል?
ዶክተር ሙሉቀን ዮሃንስ በጤና ሚኒስቴር የሚንስትሯ ከፍተኛ አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረና የማይበገር የጤና ስርዓት ሲባል በየግዜው የሚከሰቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ የጤና ችግሮችን የሚቋቋም ስርዓት ማበጀት ነው። ይህም ለማህበረሰቡ የሚገባውን የጤና አገልግሎት በተሟላና በበቂ መልኩ በመስጠት ለሀገራዊ እድገትና ብልፅግና ከዚህም ባለፈ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ጤናማ የሆነ ዜጋ ማፍራትን ያካትታል።
የጤና ስርዓቱ በብዙ መልኩ ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል የሚሉት ዶክተር ሙሉቀን፤ ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የጤና ስርዓቱ በራሱ ጠንካራ፤ በሀገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና ችግሮች የማይበገር ሲሆን ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ይህም ጤናማ ዜጋ ከማፍራት አንፃር የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትና ከዚህም ጋር ተያይዞ ጤናው የተጠበቀ፣ ንቁና ብቁ ዜጋ ሲፈጠር ለሀገር ብልፅግናና ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራና የማይበገር የጤና ስርዓት በሀገሪቱ ካለ ጤናው የተጠበቀ፣ ንቁና ብቁ ዜጋ ስለሚፈጠር በጤናው ዘርፍ በሽታ ለመከላከል፣ ለህክምናና ለመድሃኒት ግዢ ሊወጡ የሚችሉ የውጪ ምንዛሬዎችን በመቀነስ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሚሆንም ዶክተር ሙሉቀን ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ በማይበገር የጤና ስርዓት ውስጥ የተለያዩ ፓኬጆች ያሉ ሲሆን ጤናን ከማበልፀግና በሽታን ከመከላከል አንፃር የሚሰሩ በርካታ ስራዎች ይኖራሉ። ይህም አጠቃላይ ህክምናን በሚመለከትም በሆስፒታሎች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በሶስተኛ ደረጃ ጤና ተቋማት እንዲሁም በሪፈራል ሆስፒታሎች ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ያጠቃልላል። እነዚህ የጤና ፓኬጆች ጠንካራ ሊሆኑ የሚችሉትም ጠንካራ የጤና ስርአት ሲዘረጋ ነው።
ከጥቂት ወራቶች በፊት የአስር ዓመት የጤናው ዘርፍ መሪ እቅድ ተዘጋጅቷል። የዚህ እቅድ ዋና ዋና ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥም አንዱ ፍትሃዊና ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ መስጠት ነው። በሽታ መከላከል፣ ጤና ማበልፀግና ህክምናና የጤና አገልግሎት ጠንካራ ሊሆን የሚችለውም ጠንካራና የማይበገር የጤና ስርዓት ሲኖር ነው።
በቅርቡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በጤና አገልግሎት ዘርፍ ላይ በተወሰነ መልኩ መቆራረጥ መታየቱን ለአብነት የሚያነሱት ዶክተር ሙሉቀን፤ ከዚህ አንፃር ለእንዲህ አይነቱ ዓለም አቀፍ የጤና ችግር የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ጠቋሚ ምልክት መሆኑን ያብራራሉ።
ወረርሽኝ በመጣ ቁጥር ሁሉም ነገር ወደ ወረርሽኝ የሚዞርበት ምክንያት ስለማይኖር ወረርሽኙን በበቂ ሁኔታ እየተከላከሉ መደበኛው የጤና አገልግሎት ሳይቋረጥ ለዜጎች እንዲሰጥ የሚያስችል ጠንካራ የጤና ስርዓት ማበጀት እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ጤና ማበልፀግን፣ በሽታ መከላከልንና የጤና አገልግሎቶችን ከታችኛው የጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡ አጠቃላይ የጤና አገልግሎቶችን ደረጃቸውንና ጥራታቸውን በጠበቁ መልኩ በመስጠት ረገድ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ዶክተር ሙሉቀን እንደሚያብራሩት የዛሬ አስር ዓመት የነበረው የጤና ስርዓት ሲታይ በዋናነት በሽታ መከላከል ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ የጤና ስርዓትም በተለይ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን በአስተማማኝና ጉልህ በሆነ መልኩ መቀነስ ተችሏል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ ነገር ግን ማህበረሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቁ የመጡ በሽታዎች እየጨመሩ መጥተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድን ጨምሮ የዓስር ዓመቱን መሪ እቅድ በመደመር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከተላላፊ በሽታዎች እኩል ትኩረት በመስጠት የሚሰራባቸው ይሆናል። በዚህም ትርጉም ያላቸው ለውጦች መጥተዋል።
ይሁንና አሁንም ገና መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ። በተለይ ደግሞ ባጠቃላይ በሆስፒታሎች አካባቢ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከማዘመን፣ ደረጃቸውንና ጥራታቸውን ከማሳደግ አኳያ ጤና ሴክተሩ በስፋት የሚሰራበት ይሆናል።
ኢትዮጵያ በምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች በተለይ የህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ከአራት ዓመታት በፊት ቀድማ እንዳሳካች የሚገልፁት ዶክተር ሙሉቀን፤ ይህ የዘላቂ የልማት ግብ ተብሎ መቀጠሉን ይጠቁማሉ። የእናቶች ሞትን ከመቀነስ አኳያ ግን ኢትዮጵያ አሁንም ትኩረት ሰጥታ ከምትሰራቸው ስራዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ይናገራሉ።
የእናቶችን ሞት ለመቀነስም ከተቀመጡት ዘላቂ የምዕተ ዓመት ግቦች ጋር በማስተሳሰር በሁሉም አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ያብራራሉ። ከዚህ አኳያም ለልዩ ልዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የጤና ችግሮች የማይበገር ጠንካራ የጤና ስርዓት በመዘርጋት የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ በቀጣዮቹ አምስት አመታት በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ እንደሚሆንም ይገልፃሉ።
ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ዜጎችን ድንገተኛ የጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንዳሉም የሚናገሩት ዶክተር ሙሉቀን፤ በተለይ አሁን ባላው ሁኔታ እነዚህ ችግሮች እየሰፉ መምጣታቸውን ይጠቁማሉ። ለአብነትም ኮቪድን ጨምሮ በየግዜው እየተከሰቱ ያሉ ወረርሽኞች የዜጎችን ህይወት በድንገተኛ መልኩ አደጋ ላይ እየጣሉ ስለመምጣታቸው ይጠቁማሉ። ከዚህ አንፃር በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ማንኛውንም ሀገራዊም ሆኑ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በማድረግ ህይወትን በድንገት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሀኔታዎችን ለመከላከል የሚሰራ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከዚህ ጎን ለጎን በበርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ በመሆኑ ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በመተባበር በድንገት ተከስተው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ተፍጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ከማስቀረት አንፃር ሰፊ ስራ እንደሚሰራም ይገልፃሉ። በተመሳሳይ የትራፊክ አደጋን በሚመለከትም አንዱና ዋነኛው ችግር በመሆኑ የጤና ስርዓቱ የሚመልሰው ሌላው የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ።
ዶክተር ሙሉቀን እንደሚሉት በጤናው ዘርፍ አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ አንዱና ቁልፉ ጉዳይ ተገልጋዩን መሰረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ይህም እንደ አንድ የጥራት መመዘኛ መስፈርት ይቆጠራል። ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተሰጠ የሚባለውም የተገልጋዩን ችግር ሊፈታ የሚችል የጤና አገልግሎት መስጠት ሲቻል ነው። ይህም እንደ አንድ የጤናው ዘርፍ መርህ የተቀመጠ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ግልፀኝነት በጤናው ስርዓት ውስጥ በሰፊው መተግበር የሚገባው ጉዳይ ሲሆን ግልፀኝነት ሲኖር ማህበረሰቡና አጠቃላይ የጤናው ሴክተር ተናበው የሚሰሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ማነቆዎችንና ክፍተቶችን የማስተካከል ሁኔታዎችም ይፈጠራሉ። ከዚህ አኳያ ተገልጋይ ተኮርና ተአማኒነት ያለው የጤና ስርዓት መዘርጋት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው ዐብይ ጉዳዮች ውስጥ አንዱና በጤና ስርዓቱ ውስጥ የተካተተ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014