ሌብነት እና ልመና በብዙ መልኩ የሰዎች ስንፍናን፣ የራስን ትቶ የሰው መመኘትን፣ በሌሎች ላይ ተንጠልጥሎና ተጠግቶ የራስ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ የማያዋጣ ጉዞ መገለጫዎች ከመሆናቸውም በላይ ክብርን የሚያሳጡ ነገሮችም ናቸው።ሌብነት እና ልመና በሁሉም እምነቶች የማይደገፉና እንዳይኖሩ የሚፈለጉ ድርጊቶችም ናቸው። አለፍ ሲልም ሌብነት እና ልመና የህሊና ክስን የሚፈጥሩ እርካታን የማያመጡ ተግባራት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም የቀደምት የስልጣኔ ባለቤት እና የነጻነት ምድር ሆና ሳለ፤ በተለይ ከሶስት አስርት ዓመታት ወዲህ ሌብነት እንደ መበልጸጊያ፣ ልመና ደግሞ ከድህነት መውጫ ተደርጎ ከፍ ባለ መልኩ ተስተውሏል።ይሁን እንጂ ሌብነት በፈጣሪም የሚያስኮንን፤ በምድራዊ ሕግም የሚያስጠይቅ፤ በሞራል ልኬት ሰብዕናን እጅጉን ዝቅ የሚያደርግ ነውር ተግባር ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም የአገርን ኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ ከፍ ያለ ችግር የሚፈጥር፤ በሰላም እና ደህንነት ላይ አደጋ የሚጋብዝ እኩይ ድርጊት ነው።እንደ ሌብነት ሁሉ ልመና ሰርቶ በላብ የማደር የፈጣሪን ትዕዛዝ የሚጥስ፤ በሰው ዘንድም ክብርን የሚያዋርድ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ለትልቅ አገር የማይመጥን፤ የግለሰብንም ሆነ የአገርን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባር ነው፡፡
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ሌብነት የመንግስት እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት ዘንድ ዋና መገለጫ ከፍተኛ ችግር ሆኖ ዘልቋል።ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ በርካታ ዶላሮችን በልመና ከውጭ አገራትና ተቋማት ታገኛለች፤ በአንጻሩ ለምና ካገኘቻቸው ዶላሮች የላቁ የውጭ ምንዛሬ ገንዘቦች በሌቦች ምክንያት በውጭ አገራት ባሉ ባንኮች ተሸሽገው ይገኛሉ፡፡
በዚህ መልኩ በመንግስት እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው የሌብነት ሁኔታም ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ህዝብ ለበርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓል። በአንጻሩ ጥቂቶች ያልለፉበትን ሃብት እንዲያካብቱ እድል ፈጥሮላቸዋል።ሆኖም ድምር ውጤቱ ለአገር አደጋ፣ ለህዝብም ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በልመናም በኩል ድጋፍ ለማግኘት ሲባል በርካታ ድጋፎች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም ለኢትዮጵያውያን ግን ጠብ የሚል ነገር አላስገኙም።በዚህ ድጋፍ ኢትዮጵያንም ከድህነቷ ማላቀቅና ለልመና የተዘረጋ እጇን ማሳጠፍ አላስቻለም።
ይልቁንም የአገርን ክብር ዝቅ እያደረገ ድጋፍና እርዳታን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአገራችን ውስጣዊ ጉዳይ እጃቸውን ለማስገባት ለሚሞክሩ ኃይሎች አገራችንን ተጋላጭ አድርጓታል።ይህን ጉዳይ አሁን በቅርቡ በአገራችን ከተከሰተው ሁኔታ ጋር አስተሳስረን ለማየት ብንሞክር እንኳን አንዳንድ አገራት የአገራችንን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ተግባር ለመፈጸም የሚሰጡንን እርዳታ እንደማስፈራሪያ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ አስተውለናል።
ዛሬ ላይ ግን በለውጡ ሂደት በተከፈተው አዲስ ምዕራፍ እውን የሆነው አዲስ መንግስት ይሄንን ታሪክ የመቀየር ኃላፊነት ተጥሎበታል።ለዚህ ደግሞ ልመናን እና ሌብነትን የሚጠየፍ፤ እነዚህንም ለማጥፋት ተግቶ የሚሰራ አመራር እንዲኖረው ይጠበቃል።በዚህ ረገድ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ባወቀሩበት ወቅት እንዳሉትም፤ አዲሱ ካቢኔ ወይም ተሿሚ ሚኒስትሮች ዋናው ተልዕኮና ተግባራቸው ሌብነትን እና ልመናን ማጥፋት ነው።ምክንያቱም ሌብነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከፍ ላለ አደጋ ጋብዟል፤ ልመናም ከችግር ላያላቅቅ ክብራቸውን ዝቅ አድርጓልና፡፡
ይህ የሆነው ደግሞ አንድም የሞራል ልዕልናቸውን ባጡ የመንግስት ሹማምንት በሚፈጸም ሌብነት ሲሆን፤ ሁለተኛም ያላቸውን ሃብት አውቀው በራሳቸው ሰርተው ማደግና መበልጸግ እንደሚችሉ ባልተገነዘቡ መሪዎች ምክንያት የመጣ ችግር ነው።በመሆኑም በአንድ በኩል ፈጣሪንና ህዝብን በመፍራት የሞራል ልዕልናን በመላበስ ሌብነትን በመጠየፍና ለሌብነት የተከፈቱ በሮችን በመዝጋት ሌብነትን ማጥፋት የአዲሱ ካቢኔ ኃላፊነት መሆኑን አውቆ መስራት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ያላት ሃብት በአግባቡ መልማት ከቻለ ከራሷ አልፎ ለቀጠናው በቂ መሆኑን በመገንዘብ፤ ብልጽግና የሚረጋገጠው በልመና ሳይሆን ያለንን አቅም ለይቶ ተግቶ በመስራት መሆኑን አውቆ በዛው አግባብ ሰርቶ የማሰራት ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል።ይህ ሲሆን ነው ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆና ክብሯ ተመልሶ ወደ ብልጽግናዋ ማማ የምትገሰግሰው።እናም አዲሱ ካቢኔ ልመናን እና “ሙስና” በሚል የዳቦ ስም የሚታወቀውን ሌብነት በማስወገድ ረገድ የማይተካ ሚናውን ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም