አዳማ:- በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ስድስት ወራት በተሰሩ ስራዎች የህዝብ ሰላም እንዲመለስ መደረጉ ተገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ትናንት በአዳማ ከተማ በተጀመረው አምስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ አመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በሀገሪቷ የመጣውን ለውጥና የልማት ስራዎች ለማደናቀፍ ከፍተኛ ገንዘብ መድበውና መሳሪያ በገፍ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው ሁከት በማንሳት የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ የጥፋት ኃይሎችን የክልሉ መንግስት ለሴራቸው ቦታ ሳይሰጥ በትዕግስትና በብልሃት በመስራቱ የህዝብ ሰላም እንዲመለስ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የጥፋት ኃይሎቹ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ልማቱን እንዳያሳድግ፤ እርስ በርሱም እንዲጠላለፍ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ለማ፣ የክልሉ መንግስት እኩይ ተግባራቸውን ለማክሸፍ በሰራው ስራ የጥፋት ኃይሎቹ እንዲያፍሩ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በውስጥም በውጭም ሆነው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የጥፋት ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውንና የሰው ህይወትና ንብረትም መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡ በሰውና በሀገር ልማት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱትን የጥፋት ኃይሎች ለፍትህ ለማቅረብና የተፈናቀሉ ዜጎችንም ወደ የአካባቢያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በኢኮኖሚና በማህበራዊ አገልግሎቶች ባለፉት ስድስት ወራት በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በተለይም አርሶ አደሩ ከተበጣጠሰ የእርሻ ስራ ወጥቶ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እንዲጠቀም በተደረገው ጥረት በ284 ወረዳዎች አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉንና በዚህም ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በ2010/ 2011 የምርት ዘመንም ከ819 በላይ ሄክታር መሬት ታርሶ 9.1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አመልክተዋል፡፡ በማዕድን ልማት ዘርፍም 96 ቶን ታንታለም፣ 304 ኪሎ ግራም ኤመራድ እና ሌሎች ማዕድናትን ማምረት መቻሉንና ከዘርፉ ሰባት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ በውሃ አቅርቦትም የክልሉ የንጹህ የውሃ መጠጥ ሽፋን ከነበረበት 63 ነጥብ ስምንት በመቶ ባለፉት ስድስት ወራት በተሰሩ ስራዎች 64 ነጥብ አምስት በመቶ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ ፀጥታን ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተሰራው ስራ የተሻለ ቢሆንም፤ ከዚህ የበለጠ መከናወን እንዳለበትና በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የታዩት መዘግየቶች መስተካከል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው በህብረት ስራ ኤጀንሲ አዋጅ ላይና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ ይወያያል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በለምለም መንግስቱ