‹‹መተሐራ ፀሀይ የማይጠልቅባት የንግድ ከተማ ሆናለች››  – የመተሐራ ከተማ ከንቲባ አቶ አዲሱ ዋቆ

የዝግጅት ከፍላችን ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ፣ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ሰፊ ዘገባዎችን በሚሠራበት ወቅት ከዳሰሳቸው ጉዳዮች ውስጥ የመተሐራ ከተማ ሁለንተናዊ እድገት አንዱ ነበር።

የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ የመተሐራ ከተማ ከንቲባ ከሆኑት አቶ አዲሱ ዋቆ ጋር በነበረው ቆይታ በትምህርት፣ ጤና፣ ኢንቨስትመንት፣ ኮሪደር ልማት፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። በመሆኑም በዛሬው ወቅታዊ የእንግዳ ዓምድ ላይ የመተሐራ ከተማ አስተዳደር ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሠራቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እና ያመጣቸውን ውጤቶች እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፦ የመተሐራ ከተማ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ልዩ የሚያደርጋት መገለጫ ምን አንደሆነ ቢነግሩን?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ አመሰግናለሁ፡፡ መተሐራ ከተማ ምስራቅ ሸዋ ዞን ካሏት ከተሞች መካከል የመጀመሪያ ከተማ ነች። ከዋና ከተማችን ከአዲስ አበባ ወደ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። መተሐራ የሀገራችን ዋና መንገድ ተብሎ የሚጠራው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጅቡቲ የሚሄደው መንገድ የሚያቋርጣት ከተማ ስለሆነች እና በበርሃ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ከመሆኗ የተነሳ የተሰየመላት ሁለት ስሞች አላት። የመጀመሪያ ‹‹የፍቅር ከተማ›› ተብላ ትጠራለች። የፍቅር ከተማ ተብላ ስትጠራ ማንኛውም ሰው የትኛውም ብሄር ብሄረሰብ ሲመጣ እኩል የምታስተናግድ መሆኑን ነው።

መተሐራ በፍቅር የመጣን የትኛውንም እንግዳ ተቀብላ ብርቱካን፣ ማንጎ እያበላች በፍቅር ታስተናግዳለች። በዚህ ምክንያት በተለይ ከጅቡቲ ተነስተው ወደ መሀል ሀገር የሚሄዱ ዜጎች የፍቅር ከተማ ብለው ስያሜ ሰጥተዋታል።

ሁለተኛ መተሐራ ‹‹ፀሃይ የማይጠልቅባት ከተማ›› ተብላ ነው የምትታወቀው። ቅድም እንዳነሳነው የሀገሪቱ ዋና ኢኮኖሚን ይዞ የሚንቀሳቀሱ ከባድ መኪናዎች በዚሁ በመተሐራ ከተማ ውስጥ ነው የሚያልፉት። በከተማው ውለው አድረው ነው የሚሄዱት። ይህ ሲሆን እንግዶች ቀንም ሌሊትም የሚፈልጉትን አገልግሉት በመተሐራ ከተማ ውስጥ ያገኛሉ። የንግድ ዘርፉ ቀንም ሌሊትም ነው። አሁን ላይ ሙቀትም ስለሚጨምር ከቀን በላይ ሌሊት ነው መተሐራ ከተማ ውስጥ የሚሠራው። ስለዚህ መተሐራ ከተማ ፀሃይ የማይጠልቅባት ከተማ ተብላ ትታወቃለች።

አዲስ ዘመን፦ የከተማዋ ነዋሪ ዋና የኑሮ መሰረት ምንድን ነው?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ የከተማዋ ማኅበረሰብ ኑሮ የተመሰረተው በንግድ ዘርፍ ላይ ነው። እያንዳንዱ ሰው ንግድ ላይ ነው ተሰማርቶ የሚገኘው። ስለዚህ ይሄ የንግድ ዘርፍ እንዳይቀዘቅዝ ወደ ኋላ እንዳይመለስ እንደ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነት አለብን። ከኃላፊነቱም ውጪ ከንግድ ዘርፍ ላይ ገቢ ስለምናገኘው በጣም ነው የምንጠብቀው ። ከዚህ አንጻር ፀሃይ የማይጠልቅባት ከተማ ተብላ የምትጠራው መተሐራ ከተማ የበለጠ እንድትለማ እንደ ከተማ አስተዳደር የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ።

ይህንን እውን ለማድረግ ከነዋሪዎች ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን አካሂደናል። ካደረግናቸው ውይይቶች መካከል ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ከመንገድ ላይ ማንሳት አንዱ ነው። ድርጊቱን ያለምንም ግፊት እና ያለምንም ጫና ሰው በፍላጎቱ በሸራ እና በተለያየ ነገሮች የከተማውን ውበት ሊያጠፉ የሚችሉትን ነገሮች ከመንገድ ላይ አንስቷል። ሕገወጥ ግንባታው ከመንገድ ላይ ከተነሳ በኋላ ተደብቆ የነበረው ቤታቸው ሁሉ መታየት ጀመረ። አሁን ከንግዱ ጎን ለጎን ከተማዋም ውበት በግልፅ መታየት ጀምሯል።

አዲስ ዘመን፦ ከከተማ ውበት ጋር ተያይዞ ያነሱት ሀሳብ አለ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ በከተሞች የኮሪደር ልማት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ እሱን ማለቶት ይሆን?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ በትክክል። እንደ ፌዴራል መንግሥት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ከተሞች ላይ እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት በተመሳሳይ ፕሮፖዛል አቅርበን፣ ዲዛይን እና ስፔሲፊኬሽን አሰርተን ነበር። የከተማችን ኮሪደር ለመሥራት 70 ሚሊዮን ብር ጠይቆናል። እንደ መተሐራ ከተማ 70 ሚሊዮን አውጥተን ኮሪደር መሥራት ከባድ እንደሆነን ውሳኔ ላይ ከደረስን በኋላ መፍትሄው ምንድነው ወደሚለው መጣን።

መፍትሄው ከሕዝባችን ጋር መወያየት ነበር። ዲዛይኑን ለሕዝባችን እያሳየን ‹‹እናንተ ሕገ ወጡን ግንባታ ካነሳችሁ እኛ ደሞ ኮሪደር ልማት ለመሥራት እቅድ ይዘናል፤ ግን በዘንድሮ ዓመት ለመሥራት በጀት የለንም። ምንድነው ምታግዙን›› በማለት አወያየን። ሕዝቡም ‹‹ጀምሩና አሳዩን›› አለን። ካለን ትንሽ በጀት አውጥተን ፕሮጀክቱን ጀመርነው። ፕሮጀክቱ ውበት መታየት ሲጀምር ሕዝቡ ከጎናችን መቆም ጀመረ።

ባለው አቅም ጉዳዩ የሚመለከተው የማይመለከተው የከተማዬ ጉዳይ ይመለከተኛል በማለት ብቻ ገንዘብ እያወጣ ሕዝቡ አገዘን። እስካ ዛሬ ባለው ወደ አራት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ሠርተናል። በሠራነው ሥራ ሕዝባችን በጣም ደስተኛ እንደሆነ ተነሳሽነቱን ካየን በኋላ፤ አሁንም ወደ ውይይት ገብተን እያንዳንዱ ሰው ቤቱን በፍላጎቱ ቀለም እየቀባ የከተማዋን ውበት መግለፅ ችሏል።

በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ፣ በየዛፎቹ ላይ የዲም ላይት ወይንም ደሞ የኮሪደር መብራቶችን ገጥሟል። ከተማችን በእውነት ፀሃይ የማይጠልቅበት ከተማ መሆኗን በጉዞ እና በተለያየ ጉዳዮች መጥቶ ከተማችን ውስጥ ከሚያድረው ሰው የምናገኘው ግብረመልስ የሚያስደንቅ ነው።

አዲስ ዘመን፦ በከተማዋ ስንዘዋወር በአስተዳደሩ የተገነባ ዳቦ ቤት ተመልክተን ነበር። የዳቦ አቅርቦት እጥረት አለ ማለት ነው?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ ለሕዝባችን የምንሠራው ሌላው ጉዳይ ዳቦ ቤት ግንባታ ነው። በርግጥ በግለሰቦች ዳቦ ቤቶች አሉ። ነገር ግን የዳቦ አቅርቦት በቂ አይደለም። በተጨማሪ በግል የሚቀርበው ዳቦም በግራም ብዙ ግዜ የወረደ ይሆናል። አንዳንዴ ግዜ ደሞ ጥራቱም የወረደ ይሆናል። ይሄንን ሕገ ወጥነት እንዲታረም የንግድ ጽህፈት ቤት እየቀጣ እና እርምጃ እየወሰደ ነበር። ሆኖም እርምጃ መውሰድ ብቻ በቂ አይደለም። የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት የምንችለው፤ ዳቦ ቤትን በመሥራት ነው በሚል ድምድሜ ላይ ደረስን። በውሳኔውም ትልቅ ዳቦ ቤት ሠርተናል። በተገነባው ዳቦ ቤት ሥራ አጥ ወጣቶችን አደራጅተን ጥራት ያለው ዳቦ በማቅረብ፤ ሁለተኛ ደሞ ግራሙ ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ ችለናል። የዳቦ ዋጋውም ከሌላ የዳቦ ቤቶች የተሻለ ነው። የተደራጁት ወጣቶችም ሠርተው ሕይወታቸውን ለመቀየር ዝግጁ እንደሆኑ እያሳዩ ነው።

አዲስ ዘመን፦ የከተማዋን ነዋሪ ወጣቶች ለማሻሻል የምትወስዱት ሌሎች እርምጃዎችስ?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ የወጣቶችን ሕይወት ለማሻሻል እንደ መንግሥት የያዝነው እቅድ አለ። ከእቅዶቹ መካከል በዘንድሮ ዓመት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ የዶሮ እርባታ ሼዶች ሠርተናል። ከዚህ በፊት ለዶሮ እርባታ ተብሎ የሚሠሩ ሼዶች በቆርቆሮ ነው የሚገነቡት። በቆርቆሮ የተሠሩ የዶሮ እርባታዎች ቢኖሩም ነገር ግን ‹‹ውጤታማ ነው›› ብለን እራሳችንን ስንጠይቅ ያገኘነው መልስ ‹‹ውጤታማ አይደለም›› የሚለውን ነው።

ከተማችን በጣም ስለምትሞቅና የአየር ጸባዩ አስቸጋሪ በመሆኑ ዶሮዎቹ በቆርቆሮ ቤት ውስጥ ማርባት ትርፋማ አይደለም። ባለሙያ ጋር ባደረግነው ጥናት ሙቀቱ ባለበት ቆርቆሮ ቤት ላይ ማርባት ተገቢ አለመሆኑን ለይተናል። በዘንድሮ ዓመት በብሎኬት ሠርተን ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እያዘጋጀን ነው። ፕሮጀክቱን በቅርብ ግዜ የምንመርቀው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ የከተማን ሁለንተናዊ አድገት ለማረጋገጥ ትምህርት ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፤ የመተሐራ ከተማ ከዚህ አንጻር ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ መዋለሕፃናት ትምህርት ቤቶችን እየሠራን እንገኛለን። ግንባታውን ስናከናውን የትምህርት ስብራትን መጠገን አለብን በሚል እንደ ከተማችን ተወያይተንበት ነው። እንደ መንግሥትም ታቅዶ እየተሠራ ስለሆነ ያንን እውን ለማድረግ ከኦሮሚያ ልማት ማሕበር ጋር በመሆን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በ41 ቀኖች ሠርተን አጠናቀናል።

የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ይህንን ብቻ ማድረግ ተገቢ አልነበረም። በመሆኑም እንደ ከተማ ከምንሠራቸው ሥራዎች መካከል የተማሪ ምገባ አንዱ ነው። በትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ ተግባር ላይ አውለናል። ሆኖም ከዚህ ቀደም የተማሪ ምገባው የነበረው በመዋለ ሕፃናት ወይም ከአንድ እስከ አራት ላሉት ተማሪዎች ብቻ ነበር። የትምህርት ስብራትን የምንችለው ፕሮግራሙን ማሳደግ ስንቸል መሆኑን አምነንበት አሁን ከአንድ እስከ 12 እየመገብን እንገኛለን።

ምገባው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይቀሩ አድርጓል። የጠዋት ተማሪ ከሆኑ ወደ ትምህርት ገበታቸው ከመግባታቸው በፊት በልተው ይገባሉ፤ ጠዋት እስከ አንድ ሰዓት ምግብ ይበላሉ። በዚህ ምክንያት በሩጫ ነው ወደ ትምህርት ቤቶች የሚመጡት። ከሰዓት ከአምስት ሰዓት በኋላ እስከ ስድስት ሰዓት ምገባው ይከናወናል።

በሶስተኛ ደረጃ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን

እየሠራን ካለነው ሥራ መካከል ከአንድ እስከ አስር ደረጃ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ለይተን ማስተማር ነው። ከሰባት እስከ 12 ያሉትን ለብቻ ነው የምናስተምረው። ስፔሻል ክላስ ብለን በተመረጡ መምህራኖች ትምህርቱን እንሰጣለን። መምህራኖቹም የራሳቸው መለኪያ ያላቸው በዲሲፕሊንም በእውቀታቸውም ጥሩ የሆኑትን ለይተን ተማሪዎች እያስተማርን ነው። በውጤቱም እንደ እቅዳችን በ 2017 ዓ.ም የትምህርት ስብራትን እያሻሻልን እንገኛለን። በዘንድሮው ዓመት ከአምና በ20 በመቶ እናሻሽላለን የሚል እቅድ ይዘናል።

አዲስ ዘመን፦ የመተሐራ ከተማ የጤና ሽፋን እና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዴት ይገለፃል?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ በጤና ላይም ለውጥ ለማምጣት እየሠራን እንገኛለን። ከሥራዎቹ መካከል አንደኛ ጤና ጣቢያዎች ‹‹በሽታን መከላከል ብቻ ሳይሆን አክመው ማዳን አለባቸው›› የሚል የጤና ሚኒስትርን እሳቤ ይዘን እየሠራን ነወ። ይሄንን ግብ ለማድረስ ከጤና ጣብያ ሠራተኞች ጋር በተገቢው ሁኔታ ተቀምጠን ተወያይተናል። የከተማዋ ነዋሪ ወደ ጤና ጣቢያ ወይንም ደግሞ ወደ ሃኪም ቤት የሚሄደው ፈውስን ፈልጎ ነው። በመሆኑም ባለሙያዎች የተማሩትን አውቀት፣ የገቡትን ቃለ መሀላ በሚያስጠብቅ መልኩ ተገቢውን ሕክምና ለታካሚዎች መስጠት እንደሚኖርባቸው መግባባት ላይ ደርሰናል። በውይይታችን ላይ ዜጎች በሀይማኖታቸው አምላካቸው ምህረት አንደሚሰጣቸው አምነው ወደ ቤተክርስቲያን እና መስኪድ እንደሚሄዱት ሁሉ ሕክምና ቦታም ሲደርሱ ከፈጣሪ በታች ለሕክምና ባለሙያዎች ‹‹ለችግሬ መፍትሄ ያመጣልኛል›› ብለው እምነታቸውን ስለሚሰጡ ሀኪሞችም የተጣለባቸውን አደራ መወጣት እንዳለባቸው ተግባብተናል።

ስለዚህ በተማሩት፣ ባገኙት ልምድና እውቀት እንዲሁም ቃል በገቡት መሰረት ታካሚ ወደ ጤና ጣቢያዎቹ ሲመጣ በቂ የሆነ አገልግሎት ሰጥተው ማከም እንዳለባቸው ተነጋግረን ወደ አገልግሎት ገብተናል፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱንም አሻሽለነዋል። የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻልን ግብረ መልስ በመሰብሰብ አንዲሁም በየግዜው በምናደርገው ድንገታዊ ክትትል አረጋግጠናል።

ከዚህ ቀደም በቢሮ ውስጥ የማይገኙት ባለሙያዎች አሁን ከዚያም አልፎ መኖሪያ ቤት ተመቻችቶላቸው በዚያው አካባቢ እየኖሩ ሰዓታቸውን ጠብቀው ይገኛሉ። የሕክምና ባለሙያዎቹ አገልግሎት 24 ሰዓት በከተማዋ ጤና ጣቢያ እስከ ገጠር ድረስ ይሰጣል። በዚህም በየወሩ ከስድስት ሺ ታማሚ በላይ ያስተናግዳል። በሌላ መልኩ ሕክምና ለማድረግ በጤና ጣቢያ የሚገኙ ታማሚዎችን ምቾት እና ንፅህና ለመጠበቅ በማሰብ የግቢውን ከባቢ የማሳመር ሥራ ተሠርቷል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የጤና ጣቢያው የግቢ ውበት የሚስብ አልነበረም። ለታካሚዎች ራሱ በሽታ ነበረ። ‹‹የከተማ ኮሪደር የሚሠራ ከሆነ ጤና ጣቢያውም ከኮሪደሩ በላይ ማሳመር እንችላለን›› በሚል ተነጋግረን ጤና ጣቢያው እንዳያችሁት በጣም አምሮ ደምቆ ይታያል። የሕክምና ቦታ ሰው የሚሸሸው ሳይሆን፤ የእኛን ጤና ጣቢያ ሄዶ የሚያርፍበት፣ ጥላ ስር የሚቀመጥበት፣ መፅሃፍቶችን የሚያነብበት ሆኖ ተሰናድቷል። ግቢውን የማሳመር ሂደቱ በዋነኝነት በራሳቸው በሕክምና ባለሙያዎቹ ተነሳሽነት የተከናወነ በመሆኑ ባለቤቱ ራሳቸው ባለሟያዎቹ ናቸው። በጤና ጣቢያው ውስጥ የሚሠሩት ባለሞያዎች የእኛ ጥረት፣ የእኛ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ልማቱ እንዲፋጠንና በግዜ እንዲያልቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

አዲስ ዘመን፦ በተለያዩ ቦታዎች የመድሃኒት አቅርቦት ቸግር መኖሩን ነዋሪዎች ሲያነሱ ይደመጣሉ፤ ይህንን ቸግር ለመፍታት ምን እርምጃ እየወሰዳችሁ ነው?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ ሕዝባችን የሚያነሳው ቅሬታ ቢኖር ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ ነው። ያንን የመድሃኒት ችግር ለመፍታት አንደኛ የጤና መድህን በሚገባው ሁኔታ ሥራ ላይ እያዋልን ነው። በከተማዋ እስካሁን ቢያንስ ከስምንት ሺ ሰው በላይ የጤና መድህን አገልግሉት ያገኛል። በጤና መድህን ምክንያት አንድም ሰው ቢሆን ቅሬታ ሚያቀርብ ከሆነ እርምጃ እንወስዳለን። ሂደቱንም በሚገባ እንከታተላለን፤ እርምጃም እንወስዳለን።

ከሕዝባችን በጤና መድህን በምናገኘው ወይንም ከሰበሰብነው ገንዘብ የተለያዩ መድሃኒቶችን በመግዛት እንደ ከተማም በጀት መድበን ሁለት የሕዝብ መድሃኒት ቤቶች ከፍተናል። ሁለቱም የሕዝብ መድሃኒት ቤቶች በትንሹ 16 ሰዓት አገልግሉት ይሰጣሉ። በዚህም ከጤና ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙት መድሃኒት ቤቶች በተጨማሪ ሕዝቡ በራሱ በገነባው መድሀኒት ቤት ሄዶ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረግን ነው።

አፈፃፀሙን እንደ ከተማ አስተዳደር በየግዜው ከቀበሌ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ድንገታዊ የሆነ ክትትል በማድረግ እንገመግማለን። ታካሚዎች መድሀኒቱን እንዴት እንደሚያገኙ አንዲሁም በምን አይነት መልኩ አገልግሉት እንደሚሰጣቸው ለመለየት እንዲያስችለን በወረቀት ጥያቄ እናቀርብላቸዋለን። እነሱ የሚሰጡትን ግብረ መልስ አሊያም በመጠይቅ ከነሱ ላይ የምናገኘውን መልሶች አንድ ላይ ሰብስበን ወደ ሥራ እንቀይራለን።

በዚህ ምክንያት ዛሬ ላይ የተሻለ ጤና ጣቢያ መገንባት በጤና ጣቢያችን ውስጥም ደሞ የተሻለ አገልግሉት መስጠት የቻልን መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ። የግል ተቋማትን ወይንም ደግሞ ባለሃብቱም በጤና ዘርፍ ላይ እንዲሳተፍ አድርገናል። ከዚህ መካከል ወደ አስራ ስምንት ክሊኒኮች ከተማችን ላይ ይገኛሉ። በግል እነሱም ጥሩ የሆነ አገልግሎትን እየሰጡ የከተማዋን ነዋሪዎች እያገለገሉ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፦ ለወጣቶች መዝናኛ እና ማረፊያ የሚሆን ግዙፍ ፕሮጀክት አንደጀመራችሁ ይታወቃል፤ የፕሮጀክት አፈፃፀሙ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ እንደ ከተማችን ‹‹ችግር ነው›› ብለን ካየነው እና ‹‹ሰርተን መቀየር እንችላለን›› ብለን እቅድ ከያዝናቸው መካከል የወጣቶች መዋያ ወይንም ደሞ መዝናኛን መሥራት ነው። ከተማችን ሞቃታማ ከተማ ነች። በከፍተኛ ወበቅ እና ሞቃት አየር ፀባይ ትታወቃለች። ወይንም ደሞ በርሃ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነች። ነገር ግን ለወጣቶች ምቹ የሆነ እና ወጣቶች የሚውሉበት፤ የሚዝናኑበት በምቹ ከባቢ ውስጥ ሆነው ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት እንዲሁም የተለያየ ፕሮግራም እንኳን ቢኖራቸው የሚዝናኑበትና የሚያርፉበት ቦታ አልነበረም። የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ለመቀየር እንደ እቅድ በመያዝ ወደ ተግባር ገብቷል።

የወጣቶች መዋያ እና መዝናኘኛ ስፍራ ለመሥራት ስንነሳ መጀመሪያ ያደረግነው የቦታ ምርጫ ነበር። በዚህም በቅርብ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዚሁ በ2017 ዓመት ውስጥ በበሰቃ ሃይቅ ላይ ቤኑና የሚል ስያሜ ያለው ትልቅ የሆነ ፕሮጀክት ሠርተዋል። ቤኑና እንደ ስሙ የምድር ገነት ብለን ብንጠራው የሚያሳፍር ነገር አይደለም። በጣም በጣም ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ የሚያምር ፕሮጀክት ነው፤ የሚስብ የቱሪስት ቦታ ነው። ይሄንን ለከተማችን በጣም በቅርብ ቦታ ላይ ስለሚገኝ በተደጋጋሚ ሄደን አይተናል። በበሰቃ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነት እንደዚ አይነት ፕሮጀክት መሥራት የሚቻል ከሆነ እኛም ለወጣቶች መዋያ ይሆናል ብለን ያስብነውን ፕሮጀክት በተመሳሳይ በሃይቁ ዳር መሥራት አለብን ብለን ጀምረናል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ የመተሐራ ሕዝብ እና በሰቃ ሆድና ጀርባ ነበሩ ማለት ይቻላል። መጀመርያ ‹‹ለምንድነው በሰቃ በየ ግዜው እየሞላ ያለው›› የሚለውን አጥንተናል። በ2012 ዓ.ም በጣም ሞልቶ ብዙ ጉዳት አድርሷል። እዚህ ከተማ ላይ ብዙ ትምህርት ቤቶች (ሃይስኩልን ጨምሮ) ፈርሰዋል። ጤና ጣቢያዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። ብዙ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችና የተለያዪ ተቋማት በበሰቃ ተበልተዋል። ከዚህ የተነሳ ሕዝቡ ውሃን ቢፈልግም በሰቃ በሕዝቡ ላይ የደረሰው ቁስል በመኖሩ እምነት የለም። ሕዝቡን ‹‹በበሰቃ ዙሪያ የወጣቶች መዝናኛ እና ማረፊያ እንሠራለን›› ስንል አስቸጋሪ ነበር። ይሁን እንጂ እኛ እንደ አመራር እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን ብለን እንድናምን ያደረገን የጠቅላይ ሚኒስትራችን ሥራ ነው።

በመሆኑም የመተሐራ ከተማን ሕዝብ ተወካዮች ይዘን (ሕዝብን ይወክላሉ ያልነውን) ከሁሉም ማኅበረሰብ ክፍሎች በማቀናጀት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ የሆነውን ቤኑናን አስጎብኝተናል። በዚህም አስተዳደሩም ለወጣቱ የሚሆን በሀይቅ ዳርቻ ተመሳሳይ መዝናኛ እንደምንሠራ ስንነግራቸው አምነው ተቀብለውናል። ዛሬ እንደምታዩት ፕሮጀክቱ ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ተግባር ላይ ውሏል። ይህ ፕሮጀክት አሁን ላይ 75 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል።

በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ ላይ እየተሠራ ያለው የወጣቶች መዝናኛ እና ማረፊያ ፕሮጀክት ተሰርቶ ሲያልቅ በትንሹ ለመቶ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል። ይሄንን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን መታወቅ ያለበት ጉዳይ የመንግሥት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ነው። ሕዝቡ ልጆቹ የሚውሉበትና የሚዝናኑበት ስፍራ እንዲኖረው ይፈልጋል። እኛም የሕዝብ ጥያቄዎችን እየመለስን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፦ የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ አንጻር ምን ውጤት አስገኛችሁ? ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው የመግባት፤ ባለሀብቶችስ በልማት ላይ የመሳተፍ እድል አላቸው ትላላችሁ?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ ሰላምና ፀጥታ በጣም ወሳኝ ነው። ሰላምና ፀጥታ ከሌለ የምንሠራቸው ፕሮጀክቶች በሙሉ ዋጋ የላቸውም፤ አገልግሉት አይሰጡም። የከተማዋ ማኅበረሰብም በሰላም ወጥቶ ለመግባት ይቸገራል። በመሆኑም የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ከፀጥታ ዘርፍ ጋር በጥብቅ እየሠራን እንገኛለን።

እንደሚታወቀው ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን መንግሥት ብቻውን (በአንድ አካል ብቻ) ውጤታማ መሆን አይችልም። በመሆኑም ከፀጥታ ዘርፍ፣ ከሕዝብ ጋርም በቅርብ እየተወያየን እና በየግዜው እየተገናኘን እየሠራን ነው። ከዚህ የተነሳ እንደ ከተማ ያለውም ፖሊስ የነዋሪውንና የመተሐራን ሰላም ለመጠበቅ እየሠራ ይገኛል። የጸጥታ ኃይሉ በየግዜው እራሱን እያደራጀ እና እያቀናጀ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ እና የአሠራር ሥርዓት ጋር እያዋሀደ የከተማውን ፀጥታ እየጠበቀ ይገኛል።

በተመሳይ ሚሊሻም ከተሰጠን እቅድ በላይ (ከሁለት መቶ ሰባ ሁለት) በከተማችን ውስጥ በማደራጀት፣ አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት 24 ሰዓት ተዘጋጅቶ ሕዝቡን እየጠበቀ ይገኛል። በተጨማሪ ‹‹ጋቸና ሲርና›› በሌላ ቋንቋ የፀጥታው ጋሻ ብለን ልንጠራ የምንጠራውን አደራጅተናል። በዚህም ከ700 ባላይ ከሕብረተሰቡ የተውጣጡ የፀጥታ ጋሻ ወይንም አደራጅተን በመረጃ ልውውጥ እና በጥበቃ ቦታዎች በፍተሻ ኬላዎች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህን ኃይሎች በአንድ ላይ በማቀናጀት የከተማውን ማስከበር ተችሏል። ይሄ አሁን እንደምናወራው በቀልድ የመጣ ሳይሆን ብዙ መስዋዕትነቶች ከፍለናል። እንደምታውቁት አጠቃላይ እንደ ሀገር ችግር አለ፤ እንደ ክልላችንም እንደ ኦሮሚያም ችግር አለ፤ እንደ ከተማችንም ብንወስደው ደሞ የሰላምና ጸጥታ ችግር ተካፋይ ነበርን። ያንን ችግር የእኛ ሚሊሻ ሙሉ በሙሉ በመቋቋም መስዋዕትነት እየከፈሉ እየሞቱ ሕዝቡን ለማኖር የሚሠሩት ሥራዎች የሚያበረታታ ነው።

ፖሊስ ለራሱ እየሞተ ሕዝቡን ለማኖር ከሕብረተሰቡ የተውጣጡ የሥርዓት ጋሻዎች ቀንና ሌሊት እየሠሩ ነው። ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የመንግሥት ተቋማት ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው፤ የግል ተቋማት ወይንም ደሞ የግል ሃብቶች ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው እያደረገ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፦በመተሐራ ከተማ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎት ምን ይመስላል? አስተዳደሩስ ጥያቄዎቹን በምን መልኩ እያስተናገደ ነው?

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት እንደማይመጣ ይታወቃል። ከተማዋ ላይ ሰላም ስላለ በርካታ ኢንቨስተሮች ዛሬ ላይ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። ቢያንስ በከተማችን በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከአምስት እና ስድስት ኢንቨስተሮች በላይ መጥተው ለአስተዳደሩ ጥያቄ በማቅረብ በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲሠማሩ እያስተናገድናቸው ነው።

ከተማችን በሰላም ረገድ በዚህ ሰዓት ላይ ራሷን ችላ ያለች ነች። ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው ያለው። በኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ከተማዋን ማልማት የሚፈልጉ ከሆነ እኛ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ 24 ሰዓት አገልግሉት የምንሰጥ መሆኑን ለማሳወቅ አወዳለሁ። ወደ ከተማችን መጥቶ እንዲያለሙ እንደ መንግሥት ለሀብታቸው እና ለንብረታቸው ዋስትና የምንሰጥ ጥበቃ የምናደርግላቸው መሆኑንም ለመግለፅ እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፦ እናመሰግናለን !!

አቶ አዲሱ ዋቆ፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ!

ዳግም ከበደ

 

Recommended For You