የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሰላፊ ክለብ አሰልጣኞች የአቅም እና እውቀት ማሻሻያ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።የካፍ የ‹‹ዲ›› ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንአስታውቋል።
አሰልጣኞች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በየጊዜው የሙያ ማሻሻያ ሰልጠናዎችን መውሰዳቸው ተገቢ መሆኑ ይታወቃል።በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ሊግ ካምፓኒ ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ጋር አስቀድሞ በገባው ስምምነት መሠረት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ለሆኑ የክለብ አሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።የ16ቱ ክለብ አሰልጣኞች የተሳተፉበት ስልጠና አቅም እና እውቀትን ለማሳደግ እንደሚያስችልም የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ አመላክቷል።
ከመልቲቾይዝ እና ከሆላንድ እግርኳስ ማህበር በተወጣጡ ሶስት አሰልጣኞች እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠናው የንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ውስጥ የሚሰጥ የተግባር ስልጠናን ያጠቃለለ መሆኑም ታውቋል።ስልጠናው ከመስከረም 24/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ነው የተሰጠው።በቀጣይ ደግሞ 36 የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ምክትል አሰልጣኞች ከጥቅምት 02/2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስልጠናው የሚገቡ ይሆናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በስልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ማስተላለፋቸውን በዘገባው ተመላክቷል።በንግግራቸውም የሊግ መመስረት ውጤት እንዲህ ያሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት ስለሚያስችል ነው። እግርኳሱ እንዲያድግ ከተፈለገ በእውቀት የሚያሰለጥንና የሚመራ ሰው ያስፈልጋል። ስለዚህም ስልጠናው ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ‹‹ትርጉም ወዳለው ስልጠና ለመግባት እዚህ ቁጥራችሁ አነስተኛ የሆነ ነገር ግን የስራው ባለቤት የሆናችሁ አሰልጣኞች ናችሁ ያላችሁት። የሀገሪቱ እግርኳስ በእናንተ እጅ ላይ ነው ያለው። እግርኳሱን መለወጥ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ። ስለዚህ ይህ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባችሁ አውቃችሁ ስልጠናውን በትኩረት እንድትከታተሉ አደራ እላለሁ›› ብለዋል።አያይዘውም መሰል ስልጠናዎች በቀጣይም ተጠናክረው የሚቀጥሉ እንደሚሆንም ነው የጠቆሙት፡፡
በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ሌላኛው የካፍ ‹‹ዲ›› ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠናም ተጠናቋል።ስልጠናው በክልሎች ጥያቄ የሚቀርብ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ እና ልማት ዳይሬክቶሬት ካፍ በሰጠው መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ የካፍ ኢንስትራክተሮች የሚሰጥ ነው።ይህም በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና ኢንስራክተር ሰላም ዘርዓይ ጋር በመሆን በተግባር እና በንድፈ ሃሳብ የተደገፈ ስልጠና ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት የትምህርትና ሥልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደረሰ እሸቱ እና የባህር ዳር ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ሃብታሙም ስልጠናው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ የማስተባበሩን ስራ አከናውነዋል።
በስልጠናው ላይም 1 ሴት እና 29 ወንዶች በጥቅሉ 30 አሰልጣኞች ተሳትፈው የምስክር ወረቀታቸውን ከፌዴሬሽኑ አመራሮች የተቀበሉ መሆኑንም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በስልጠናው ማብቂያ ላይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ የፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክና ልማት ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ፍራንኮ እንዲሁም የባህር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊና የባህር ዳር እግር ኳስ ክለብ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አሰፋ ተገኝተዋል።
ይህንን ስልጠና የተለየ የሚያደርገው ለሰልጣኞች በካፍ የሚመዘገብ የማሰልጠኛ ፈቃድ ቁጥር የተሰጣቸው በመሆኑ ነው።ይህም ፈቃድ የመለያ ቁጥር የያዘና እስከ መጨረሻው የአሰልጣኝነት እርከን ድረስ የሚያገለግል እንዲሁም በካፍ የሚመዘገብበት እና ሰልጣኙን እንዲወክል ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑም ነው።
ስልጠናው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ከተማ ክለብ ጋር በመተባበር የተሰጠ ነው።በቀጣይም ሌሎች ክልሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ስልጠናው እንደሚቀጥል እንዲሁም የ”ሲ” ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠናም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሚያወጣው ፕሮግራም መሠረት የሚካሄድ እንደሚሆንም ነው ፌዴሬሽኑ በድረገጹ ያስነበበው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2014