አዲስ አበባ፡- የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅ ህገ መንግስቱን የሚጥስ በመሆኑ እንዲጣራለት አቤቱታ ማስገባቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የህገ መንግስት አስተምህሮና የሰብዓዊ መብት ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ ወይዘሮ ፍረወይኒ ገብረእግዚአብሔር፤ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ የኮሚሽኑ መቋቋም ‹‹ህገ መንግስቱን ይጥሳል›› የሚሉ አሉና በዚህ ላይ ሃሳባቸው እንዲሰጡ ሲጠየቁ በሰጡት ምላሽ ፣የትግራይ ክልል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ማስገባቱን አንስተው ዝርዝር ማብራሪያ እንደማይሰጡ ገልጸዋል።
ማብራሪያ የማይሰጡበት ምክንያትም የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ በቀጥታ ምላሽ ሊሰጥበት ወይም አቤቱታውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያየው ሊልከው ስለሚችልና እርሳቸውም የምክር ቤት አባል ስለሆኑ የአስተሳሰብ ተጽዕኖ ላለማድረግ ለመጠንቀቅ መሆኑን አብራርተዋል። ለአቤቱታውም ሥርዓቱን ጠብቆ ምላሽ እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲጸድቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን “ይጥሳል ፣አይጥስም” የሚል ክርክር መካሄዱ፣ የትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መቃወማቸውና በአብላጫ ድምጽ መጽደቁ ይታወሳል። የትግራይ ክልል ምክር ቤትም አዋጁ ህገ መንግስቱን ስለሚጥስ እንደማይቀበለውና አቤቱታውንም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ መወሰኑ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ