የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ የሚያስገነዝበን ሀቅ የጎሪጥ ሲተያዩ እንጂ አብረው ሲሰሩ አይደለም። ገዥው ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የትኛውንም አይነት ሀሳብ በጤና አይመለከትም፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የገዥው ፓርቲን መጥፎ ጎኖች ካልሆነ በቀር ጥሩውን ጨርሶ ሲጠቅሱ አይስተዋሉም ነበር።
አሁን ይህ ታሪክ እየተቀየረ ነው። በ2010 ዓ/ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት መጥበብ ጀምሯል። የለውጡ መንግስት በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመዘርጋት የገባውን ቃልና ያከናወናቸውን የለውጥ ተግባሮች ተከትሎ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት ተፈጥሯዊ ወደ መባል እየተሸጋገረ ይገኛል።
ይህ ግንኙነት በተለይ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ይበልጥ ተጠናክሮ በሀገሪቱ በቁጥር ስድስተኛ፣ በአይነቱ የመጀመሪያ የተባለለትን ምርጫ ማካሄድም ተችሏል። የለውጡ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት ነጻ፣ ተአማኒና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዜጎች ሲናፍቁት የኖሩትን የዴሞክራሲ ጅራት አስጨብጧል። ጅራቱን እንደ ነብር ጅራት መመልከት ነው። የነብር ጅራት ከተያዘ አይለቀቅም። ቀሪው ስራ ይህን ጅራት እንደያዙ መዝለቅ ይሆናል።
በአዲስ መንግስት ምስረታው ደግሞ በምርጫው ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚሰራ መሆኑን በሚገባ ያመለከተ ትልቅ ተግባር ተፈጽሟል። የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በገቡት ቃል መሰረት በአዲሱ መንግስት ካቢኔያቸው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን በኃላፊነት በመሾም ቃላቸውን ጠብቀዋል። የክልል መንግስታትና ከተማ አስተዳደሮችም እንዲሁ በመሰረቱት ካቢኔ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በማካተት በኃላፊነት ቦታ ላይ አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት አብሮ ከመስራት እንደማይከለክል አስታውቀው፣ መንግስታቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ የካቢኔ ምስረታም አረጋግጠዋል።
የመንግስት እርምጃ ባለፉት የለውጡ ሶስት ዓመታት ጊዜያትም መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ሲሰራ የነበረበትን ሁኔታ ይበልጥ ያጠናክራል። መንግሰት በተለያዩ የመንግስት ሃላፊነት ቦታዎች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችንና ምሁራንን በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ እንዲሰሩ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። የአሁኑ የመንግስት እርምጃ ይህ አሳታፊነቱ ይበልጥ ተጠናክሮ መምጣቱን ያመለክታል።
ይህ የመንግስት የአካታችነት እርምጃ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል። በእርግጥም አብሮ ለመስራት የተጀመረ ታላቅ ጉዞ ነውና አድናቆት ሊቸረው ይገባል።
የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የዴሞክራሲ ስርዓት ጥያቄ ነው። ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው ጉዳይ ያለገደብ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ አንዲመጣ ሲጠይቁ ኖረዋል። ዛሬ ላይ ያ የተናፈቀ ቀን ደርሶ አብሮ መስራት መጀመሩ ይህ የመንግስት ቁርጠኝነትና ቃል አክባሪነት ያመለክታል።
ያለፉት መንግስታት በብዙ መልኩ አደራ በልተዋል፤ ቃላቸውን አጥፈዋል። ለህዝብ የገቡትን ቃል ወደ ጎን እየተው የቡድን ፍላጎታቸውን ሲፈጽሙ ነው የኖሩት። ይህ ሁኔታ የብዙዎችን መስዋዕትነትን ቢያስከፍልም ቆይቶም ቢሆን ይዟቸው ሂዷል። የአሁኑ የአዲሱ መንግስት የአካታችነት እርምጃ ይህ እየተቀየረ መሆኑን ያመለክታል። ህዝቡም በቀጣይም በቃሉ የሚታመን መንግስት ያለ መሆኑን እንዲያስብ ያደርጋል።
ቃልን መጠበቅ ትልቅ ስፍራ አለው። አበው ቃል መጠበቅ ታላቅነት መሆኑን ሲናገሩ ‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ይላሉ። መንግስት ቃል ጠብቆ ስለፈጸመው ታላቅ ተግባር በሁሉም ወገን ምስጋና ሊቸረው ይገባል።
በክልልና በፌዴራል መንግስቱ ካቢኒዎች የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት መሪዎች መካተታቸው በሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ጉዞ ስለመምጣቱ አንድ ትልቅ ማሳያም ነው። የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ምርጫ ሲመጣ ብቻ ይንቀሳቀሱ ከነበረበት ሁኔታ ወጥተው በሀገር ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፉ መልካም እድል ይፈጥራል። ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቻችለው የሚጓዙበትን መንገድ ይጠርጋል፤ ይበልጥ አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታም ያመቻቻል።
አካታችነቱ መንግስት ይህችን ሀገር ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር በሚያከናውነው ተግባር ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በሚገባ ያመለክታል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከመንግስት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል።
ይህን አይነቱ ማካተት በጭንቅ ጊዜ ይፈጸም አንደነበር ማስታወስ ይገባል። ሀገራዊ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት ኢህአዴግ ጭንቅ ውስጥ በነበረ ጊዜ በተደጋጋሚ ይቀየር በነበረው ካቢኔ ውስጥ የፓርቲው አባላት ላልሆኑ ምሁራን ሹመት ይሰጥ ነበር። ይህ ሲደረግ የነበረው ሲጨንቅና ለማታለል ነበር።
አሁን መንግስት ያደረገው ማካተት ግን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ካለው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ ነው። ጽኑ ፍላጎቱ ደግሞ ሀገርን መለወጥ ማበልጸግና በዴሞክራሲ ጎዳና ማራመድ ነው። መንግስት ይህን ያህል ርቀት ተጉዞ ቃሉን ፈጽሟል።
በአካታችነቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል በሚገባ ታይቷል። የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን አዲስ የፖለቲካ ባህል በሚገባ በመጠቀም ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የምታደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክራችሁ ለመቀጠል ቃል መግባት ይኖርባችኋል። የቤት ስራ እንዳለባችሁ ተገንዝባችሁ ከዚህ የተሻለ የፖለቲካ ተሳትፎ የምታደርጉበት ሁኔታ እንዲመጣ መስራትም ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም