አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምጣት፣ ከብድርና ከተፈጥሮ ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥራት ያለው ዕድገት እንዲመጣ እና ንግዱን ለማሳለጥ የሚያስችል ተጨባጭ ርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።
በአገሪቱ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚገመግመውና አቅጣጫ የሚሰጠው ኮሚቴ ያለፈውን አንድ ወር የንግድ አፈፃፀም ትናንት ገምግሟል።
በግምገማው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የእስካሁኑ የአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ አወዛጋቢ ነበር። መንግስት የአገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ ቢያቅድም በተግባር ግን አዳዲስ ቢዝነሶች ወደ መስመሩ አልገቡም።
ዜጎች የንግድ ሃሳብ ቢኖራቸውም አሳሪ በሆነው ህግ ምክንያት ወደ ተግባር ለመቀየር ይቸገራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የአገልግሎት አሰጣጡ ኋላ ቀር ፣ቢሮክራሲውም አሳሪ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች የንግድ ሁኔታውን ምቹ ለማድረግ አዳዲስ ሃሳቦችንና አሰራሮችን በመተግበር ትርፋማ ለመሆን እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፤ የፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢ፣ የበጀት ጉድለትና በጀትን የማጣጣም ስራም እንደሚከናወን ገልጸው፣ መንግስት የግብር ሥርዓቱን ለማስፋት አሰራሩን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። አገሪቱ የተጫናትን እዳ ለመቀነስም ገቢን ለማሳደግና የመንግስት ወጭ ለመቀነስ ይሰራል ብለዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ የግሉን ባለሀብት ተሳትፎ በመጨመር የዜጎች ህይወት እንዲለወጥ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምር የማድረግና ቢሮክራሲውን ማነቆ ለመፍታት ይሰራል። በመንገድና በሃይል አቅርቦት ረገድም የግል አልሚዎች ወደ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማፍሰስ ፍላጎት አሳይተዋል።
የንግዱን ሁኔታ ቀላል ማድረግ ዋና ዋና አልሚዎች ወደ አገሪቱ በመምጣት በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በማዕድን ልማት እንዲሰማሩ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው፤ በአጭር ጊዜ ንግድን ለማቀላጠፍ እንዲቻል ሰማንያ ጉዳዮች ለማስተካከል መለየታቸውን ተናግረዋል። ኮሚቴው ከስምንት የመንግስት ተቋማት ጋር አንድ በአንድ ቁጭ ብሎ መወያየቱን ጠቁመው፣ ውይይቱ ከተካሄደባቸው ተቋማት መካከል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል፣ የግብር ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ አስተዳደርና ሌሎች መሆናቸው አመልክተዋል።
በውይይቱም አስር አመላካች ነጥቦችንም መለየታቸውን የጠቀሱት አቶ አበበ፣ እነዚህም የንግድ ፈቃድ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ ንብረትን የማስመዝገብ ሂደት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የብድር አቅርቦት፣ ግብር መክፈልና አከፋፈል፣ ዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኪሣራና ዕዳን ማደራጀት፣ የአነስተኛ ባለ አክስዮኖች ጥበቃ እንዲሁም ውል ማስፈጸም መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ እነዚህ ነጥቦች እስካሁን የአዋጅ፣ የመመሪያና ደንብ ማሻሻያ በማድረግ ንግዱን ለማሳለጥ አመላካች በመሆናቸው ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር በመሆን አዋጁ ተረቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል። በቅርቡም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ተቋማትን የማዘመን ስራ በቅርቡ ይጠናቀቃል።
ኢትዮጵያን በፖሊሲና በህግ ረገድ በቀላሉ ንግድ ሊሰራባት የምትችል አገር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑና በቀጣይ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንደምትሆን ተስፋቸውን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህ አሰራር እንዲፋጠን መመሪያ መስጠታቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር