ለኢትዮጵያውያን ቃልን ማክበር ከፍያለ ማህበራዊ እሴታችን ነው። ከዚህ የተነሳም “ የተናገሩት ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚል ዘመናትን ያስቆጠረና አብሮን የኖረ ፤ዛሬም ህያው የሆነ አባባል ባለቤቶች ነን። አባባሉ ከአንደበት የወጣን ቃል ከትውልድ ጋር አነጻጽሮ ከማየቱ በላይ ለቃል የበለጠውን ስፍራ የሰጠ ነው። በዚህም ማህበረሰባችን እንደ ማህበረሰብ የቱን ያህል ለአንደበቱ ቃል ጥንቁቅ እንደሆነ አመላካች ነው ።
ይህ ማህበራዊ እሴታችን ባሳለፍናቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ እየተከተልናቸው ከመጣናቸው መጤና ዘመነኛ አስተሳሰቦች በብዙ መልኩ እየተሸረሸረ መጥቷል። በተለይም ላለፉት ስድስት አስርቶች የነበረው ሀገራዊ ፖለቲካ ይህንን እሴታችንን በመሸርሸር ከፍያለውን ስፍራ እንደሚይዝ ይታመናል። በዚህም ቀድሞውንም በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ለነበረው ሀገራዊ ፖለቲካ ተጨማሪ ችግር ሊሆን ችሏል።
በነዚህ ስድስት አሥርት ዓመታት ወደ ስልጣን የመጡ ቡድኖች ዋነኛ መለያቸው የነበረው በፍጥረታዊ ባህሪያቸው ሊፈጽሟቸው የማይችሏቸውን ቃሎች ለህዝባችን በመስጠት በህዝባችን ተስፋ መቆመር እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከዚህ የተነሳም ህዝባችን የፖለቲከኞችን ቃል ተስፋ አድርጎ ከመጠበቅ ይልቅ በቃላቸው ሲሳለቅ ኖሯል። ይህም የፖለቲካ ባህላችን አካል ሆኖ ቆይቷል።
ይህ እውነታ በተለይም በህወሓት የአገዛዝ ዘመን የመጨረሻና የከፋ ወደሚባል ደረጃ በመድረሱ ህዝብ በመንግሥት ቃል ፍጹም ያለመታመን ደረጃ ላይ የደረሰበት ፤ በዚህም በመንግሥት ተስፋ ማድረግ አቁሞ መንግሥትን እንደ መንግሥት ላለመቀበል በእምቢተኝነት አደባባይ የወጣበት ሁኔታ ደጋግሞ ተስተውሏል።
ይህንን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የሀገሪቱን ፖለቲካ ከዚህ የከፋ ችግር መታደግ የሚያስችል፤ የሕዝባችንን የትናንት ማንነት የሚመጥን እና ከማንነታችን የሚመነጭ የፖለቲካ አስተሳሰብና የድርጊት ቁርጠኝነት ይዞ በሀገራዊ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ብሏል።
ይህ አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ የፖለቲካ ህመም ለመፈወስ ግልጸኝነትንና ህዝባዊነትን፤ ከዚህም በላይ የቃል ታማኝነትን መሰረት ያደረገው የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለህዝቡ የገባውን ቃል በማክበር ሕዝባችን ለፖለቲካ መሪዎቹ የተሻለ ከበሬታ እንዲኖረው የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት ችሏል። በዚህም ሀገራዊ ፖለቲካው ትውልድ ተሻጋሪ ፈውስ እያገኘ ነው።
ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ለህዝባችን በብዙ ተስፋ የተሞሉ ቃሎችን ገብተዋል ፤ቃሎቹን ወደ ተግባር የመተግበሩ እውነታ በብዙ ፈተናዎች የተሞሉ ቢሆኑም ሁሉንም በጊዜያቸው እንደ ቃላቸው ፈጽመዋል ። ከቃላቸው ትልቁና ከፍያለውን ስፍራ የያዘው በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ ነበር። ይህ ሲወራ የሚቀል በባህሪው ግን ብዙዎችን ፈትኖ የጣለን እውነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን በማክበር በጽናት መሻገር ችለዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላና በቀደሙት ዘመናት ሀገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለው የህዝብ መንግሥት ምስረታን እውን እንዲሆን፤ የምርጫ ተቋማትን ነጻ ከማድረግ ጀምሮ በምርጫ ሀገርን እንደ ሀገር አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ስትራቴጂ በመንደፍ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት የሚያስችል የበሰለ አመራር ሰጥተዋል።
ከዚህም ባለፈ በምርጫው የተገኘው የአገር አሸናፊነት በመንግሥት ምስረታ ውስጥ እንደሚንጸባረቅ በገቡት ቃል መሰረትም በሰሞኑ የመንግሥት ምስረታ የተፎካካሪ ፖርቲ አመራሮች የሆኑትን ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ቀጄላ መርዳሳንና አቶ በለጠ ሞላን በፌዴራል መንግሥት፣ አቶ ግርማ ሰይፉንና አቶ የሱፍ ኢብራሂምን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አቶ ጣሂር መሀመድንና አቶ ተስፋሁን አለምነህን በአማራ ክልል እንዲሁም አቶ አራርሶ ቢቂላን በኦሮሚያ ክልል ካቢኔ ውስጥ በማካተት አዲስ የተመሰረተው መንግሥት አካታች እንደሆነ በተግባር አሳይተዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃልን በተግባር የመፈጸም ቁርጠኝነት የጀመርነው አዲሱ የፖለቲካ ባህል የአስተሳሰብ መሰረት የመሆኑ እውነታ በቀጣይ በመንግሥትና በህዝብ መካከል የነበረውን አለመተማመን ከማስወገድ ባለፈ ፤መንግሥት እንደ መንግሥት ለሚገባው ቃል ብዙ እንዲያስብና ቃሉንም ለመፈጸም በብዙ እንዲተጋ የሚያደርገው ይሆናል።
ይህ እውነታ በራስ ለጀመርነው የሀገር ብልጽግና ጉዞ ከፍ ያለ አቅም የሚፈጥር ፤በብዙ መልኩ የተዳከመውን የሥራ ባህል የሚያነቃቃ ፤ አስፈጻሚ አካላትንም ከተኙበት የሚያነቃና መንግሥት እንደ መንግሥት ለህዝብ ለሚገባው ቃል ተፈጻሚነት ከፍ ባለ ኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ አቅም ያለው ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጡበት መንገድ ፤ ለቃላቸው የሰጡት ከፍያለ ትኩረትና በትኩረቱ ያስመዘገቧቸው ታሪካዊ ስኬቶች በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከፍያለ ስፍራ እንደሚኖረው ግልጽ ሲሆን አሁንም በዚሁ መንገድ ቃላቸውን አክብረው በመቀጠል ነጻና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር፣ ሌብነትን ለማስወገድና አካታችነትን ለማጠናከር የገቡትን ቃል በጽናት ሊቀጥሉበት ይገባል!
አዲስ ዘመን መሰከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም