የአፍሪካ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እንዳስታወቀው፤ የአፍሪካ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ ቻምፒዮናው ከጥር 14 – 20 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሳውንደርስ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ሌሎች ባለሙያዎች የውድድሩን ቅድመ ዝግጅት ለመገምገም አዲስ አበባ ተገኝተዋል።
የአህጉር አቀፉ ፌዴሬሽን አመራሮች በአዲስ አበባ ተገኝተው የመስክ ምልከታም አድርገዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች እንዳሏት አረጋግጠዋል፡፡ ውድድሩን በተሻለ የተሟላ ለማድረግም መስተካከል ይገባቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ግብረመልስ መስጠታቸውም ተጠቁሟል፡፡
አህጉር አቀፉን ውድድር የምታስተናግደው ኢትዮጵያም ውድድሩን በብቃት ለመወጣት ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ይህን ያረጋገጡት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጂሎ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም በአህጉር አቀፉ ፌዴሬሽን የሰጣቸውን አስተያየቶች መሠረት በማድረግ የጎደለውን ለመሙላት እንደሚሰራ እንዲሁም ውድድሩ የተሳካ እንዲሆንም ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም ኮሚሽኑ አስታውቋል ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2014