በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው የከተማው ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ዛሬ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎቹን ያደርጋል። ከምድብ አንድ ለግማሽ ፍጻሜው ያለፈው ጅማ አባ ጂፋር ከምድብ ሁለቱ ባህርዳር ከተማ ጋር ሲገናኝ እንዲሁም መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያደርጉት ጨዋታ ለዋንጫው የሚደርሱ ክለቦች ይለያሉ።
ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተዋል። ዛሬ የሚካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከየምድባቸው ያለፉት ክለቦች ለዋንጫው ፍልሚያ ለመብቃት ዛሬ ይፋለማሉ። በቅርቡ ታድሶ ለአገልግሎት ክፍት በሆነው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተደረገ በሚገኘው በዚህ ውድድር ከምድብ አንድ ያለፈው ጂማ አባ ጅፋር ከምድብ ሁለት ለግማሽ ፍጻሜው ከበቃው ባህርዳር ከተማ ጋር በ7 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል።
አዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር በተደለደሉበት የመጀመሪያው ምድብ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ያሸነፉት መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር ማለፋቸውን አስቀድመው ማረጋገጣቸው ይታወሳል። በሶስተኛው የምድብ ጨዋታም ክለቦቹ እርስ በእርሳቸው ሲገናኙ፤ በጅማ አባ ጅፋር የ3ለ1 አሸናፊነት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። ጅማ አባ ጅፋር ከእረፍት መልስ ተጠናክሮ መመለሱን ከዚህ ቅድመ ውድድር መረዳት የሚቻል ሲሆን፤ ለከተማው ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው። በአንጻራዊነት የተሻለ ፉክክር በታየበት ምድብ ሁለት ለግማሽ ፍጻሜው የበቃው ባህርዳር ከተማም ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን ይገመታል።
በ9፡00 ሰዓት የሚከናወነው ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ ጫወታው ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ መካከል ይደረጋል፡፡
በምድብ ሁለት አስቀድሞ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ፈረሰኞቹ ሶስተኛ ምድብ ባህርዳርን 3ለ0 በማሸነፍ የዋንጫ ግስጋሴያቸውን አጠናክረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ለስድስት ጊዜ በማንሳት የበላይነትን የያዘው ክለቡ የዋንጫው ተፋላሚ ለመሆን ዛሬ ከመከላከያ ጋር ይጫወታል።
በአጓጊው ጨዋታ ቀላል ግምት የማይሰጠው ጦሩ ለእሁዱ ጨዋታ ለመድረስ ፈታኝ ፉክክር ያደርጋል በሚል በተመሳሳይ ይጠበቃል። ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ክለቡ በምድቡ ሁለት ጨዋታዎች አሸናፊ በመሆን ለግማሽ ፍጻሜው ማለፉን አስቀድሞ ያረጋገጠ ቢሆንም፤ በሶስተኛው ጨዋታ በጅማ አባ ጂፋር የመጀመሪያ ሽንፈት ማስተናገዱ የሚታወስ ነው።
ውድድሩ የሚከናወንበት የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በምሽት ጨዋታዎችን ማስተናገድ የማይችል በመሆኑ እንዲሁም የጥሎ ማለፉ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ከሆነ ተጨማሪ ደቂቃ መውሰዱ የግድ በመሆኑ ምክንያትም የዛሬዎቹ ጨዋታዎች ከተለመደው ሰዓት ቀደም ብለው የሚካሄዱ መሆኑን የውድድሩ አዘጋጅ አካል አስታውቋል።
15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በመጪው እሁድ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።በውድድሩ ስምንት የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል። ክለቦቹ በዚህ ውድድር መሳተፋቸው ጥቅምት 07 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚጀመረው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቡድኗቸውን አቋም እንዲመለከቱ እንዲሁም ተጫዋቾቻቸውን ለማዋሃድ ምቹ እድል ይፈጥርላቸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2014