በሁነቶች የአንድ ሀገር አሸናፊነት የሚሰላው የተገኘው ድል ሕዝብና እና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አቅም ሲኖረውና ይህም በተጨባጭ መታየት ሲችል ነው። ሀገርን እንደ ሀገር ማሻገር እንዲሁም ሕዝባዊ መነቃቃት መፍጠር ሲችልና ለዚህም ዜጎች በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው ነው።
በተለይም በመስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመች ሀገር ዜጎቿ ከፍ ባለ ግራ መጋባትና ከዚህ በሚመነጭ አለመረጋጋት ውስጥ በሚሆኑበት ወቅት የሚገኝ ሀገርን አሸናፊ የሚያደርግ ድል አሻጋሪነቱ፤ ከዛም ባለፈ ለቀጣይ ሀገራዊ ጉዞ የተፈተነ ተሞክሮ እንደሚሆን ይታመናል። በታሪክ የሚኖረው ድርሻ የጎላ፤ ፈዋሽነቱ ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል።
ሀገራችን ባለፉት 60 አመታት ከመጣችባቸው አባጣ ጎርባጣ እና ዋጋ አስከፋይ መንገድ እና መንገዱ ጥሎት ከሄደው ጠባሳ አንፃር ህዝባችን ይህንን እውነታ የሚክስ እና ተሻጋሪ አዲስ የህይወት ምእራፍ መጀመርና ለመጪው ትውልድ የተሻለ የሚባል የፖለቲካ ባህል መፍጠርና ማዳበር ይፈልጋል።
በርግጥ በነዚህ ስድስት አስርት አመታት የህዝባችን መሻት ይኸው ቢሆንም በተጨባጭ የታየው እና የኖረበት እውነታ ከዚህ የሚጻረር ከመሆን ባለፈ፤ ከመጀመሪያው ስህተት የኋላው እንደሚባለው በተደጋጋሚ ስህተቶች ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል ተገዷል።
በተለይም ከደርግ ውድቀት በኋላ በመንግስትነት የተሰየመው አሸባሪው ህወሓት ከመጣበት የሴራ መንገድና መንገዱ ከፈጠረው ልበ ደንዳናነት የተነሳ ሀገሪቱን እንደ ሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። አሸናፊነትን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ የሚያስበው ቡድኑ ለአሸናፊነቱ ሀገርን መስእዋት አድርጎ እስከ ማቅረብ የደረሰ ጭካኔ ውስጥ ገብቶም ታይቷል።
በዚህም በሀገሪቱ ታሪክ ባልታየ መልኩ፤ ከማህበረሰባችን የስነልቦና መዋቅር ባፈነገጠና ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባልሆነ የክፋትና የጥፋት መንገድ ሀገርና ህዝብን ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሏል። በህዝቡ ውስጥ የዘራውም የክፋት ዘር በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የነበረውን ከፍ ያለ የኢትዮጵዊነት እሴትና መንፈስ ተገዳድሯል።
በቡድኑ የተዘራው የክፋት ዘር በመላው ሀገሪቱ ፍሬ አፍርቶ ዜጎችን ለከፋ መከራና ስቃይ ዳርጓል። በዚህም በማያውቁትና ባልገባቸው ነገር የተገደሉ፣ ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረጉ፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ፣ ከፍያለ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ የገቡ ዜጎች ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም።
በዚህ ፈታኝ ሀገራዊ እውነታ ውስጥ የተፈጠረው የህዝብ እምቢተኝነት፤ እምቢተኝነቱ በፈጠረው የለውጥ ሀይል ተገርቶ ስርአቱን እንደ ስርአት ማስወገድ ተችሏል። አሸባሪው ቡድን ለሴራና ለጥፋት ካለው ትምክህት የተነሳ ስርአቱን የማስወገዱ ሂደቱ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። በብዙ ፈተና የተሞላና ብዙ ዋጋ መክፈልን የጠየቀ ነበር።
በተለይም የመጣንበት የፖለቲካ ባህልና ከዚህ የሚመነጨው ተስፈኝነት በንጹሀን ደም ላይ የተመሰረተና ለዚሁ የተገዛ፤ የቡድንን አሸናፊነት አልፋና ኦሜጋ አድርጎ የሚያይ በመሆኑ ለዚህ የተገዙ ቡድኖች በደመነፍስ የፖለቲካ መድረኩን በመቀላቀል አስተሳሰቡ ዳግም የፖለቲካ መርህ ሆኖ እንዲወጣ ሞክረዋል።
በሕዝባችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ሀይል ከስልጣን እና ለዚህ ከሚሆን አሸናፊነት ጋር ብቻ የተሳሰረውንና ዘመናት ያስቆጠረውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል በሀገር አሸናፊነት ላይ እንዲመሰረት፤ ይህም የሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ስርአትና ባህል እንዲሆን ረጅም ርቀት ሄዷል። የሄደበት ርቀትም በራሱ በሀገሪቱ የፖለቲካ የአስተሳሰብ ለውጥ መኖሩን በተጨባጭ ያመላከተ ነበር።
የሀገር አሸናፊነት አስተሳሰብ የወለደው በጎ ህሊናም ብዙዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ እድል ፈጥሯል። የተፈጠረውም እድል ሀገርን ካጋጠማት የህልውና ስጋት ከመታደግ ባለፈ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብና ከዚህ የሚመነጭ ባህል መፍጠር የሚያስችል እርሾ ሆኗል። ሕዝባችንም በነገዎቹ ላይ የተሻለ ተስፋ እንዲኖረው አስችሏል።
ይህ እውነታ ለአዲሱ መንግስት ምስረታ ሁለንተናዊ አቅም የፈጠረ ሲሆን፤ በመንግስት ምስረታው የታየውም አካታችነት በርግጥም በአዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ስለመገኘታችንና አስተሳሰቡም የሀገር አሸናፊነትን በተጨባጭ ማሳየት በሚያስችል ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ስለመገኘቱ የሚተርክ ሆኗል።
ከትላንት ችግሮቻችን ወጥተን ዛሬን በዛሬ መንፈስና ነገን በተሻለ ተስፋ መጠበቅ በሚያስችል የፖለቲካ ተሀድሶ ውስጥ የመገኘታችን እውነታ፤ የአዲሱ የፖለቲካ ታሪክ ዝማሪ ቢሆንም እንደ ህዝብ ካሉን ከፍ ያሉ ሰብአዊ እሴቶች አንጻር ጅማሬውን ወደ ትልቅ የታሪክ ምእራፍ ለመለወጥ የሚከብደን አይደለም።
በተለይም ስለ ሀገር አሸናፊነት የምንዘምረው ዝማሪ ሁላችንንም አሸናፊ ከማድረግ ባለፈ ሀገራችንን እንደ ሀገር ማሻገር የሚያስችል፤ ወደ ቀደመው የከፍታ ዘመናችን ለመመለስ ለምናደርገው ሀገራዊ ጥረት ትልቁ አቅማችንና የመንገድ ስንቃችን መሆኑን በሰከነ አእምሮና በሀላፊነት ስሜት ልንረዳው ይገባል።
ከዚህ መረዳት የሚመነጨው ተግባራችን ከኛ አልፎ የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው። ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ያለንን ዘመናት የተሻገረ መሻት እውን ለማድረግና የሰላም እንቅልፍ ለማንቀላፉት ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ እራሳችንን እንደ ህዝብ ልናዘጋጅ ይገባል!
አዲስ ዘመን መሰከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም