የአዲስ መንግስት ምስረታው እውን ሆኗል።ኢትዮጵያ የአምስት ዓመት መሪዋን በይፋ ሾማለች።ምንም እንኳ በመሪነት ብልፅግና ተመርጦ ዶክተር ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢሾሙም፤ አገር የማቅናት ስራው ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ ፓርቲ ብቻ እንደማይተው እሙን ነው።በመሆኑም ሌሎች ፓርቲዎችም አገር የማዳንና አገር የማቅናት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አያጠያይቅም።ከዚህ አንጻር ከአዲሱ መንግስት ብዙ ብዙ ይጠበቃል፤ እኛም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል ስንል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲን አነጋግረን እንዲህ አቅርበነዋል።
በኢዜማ የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር ባንተይገኝ ታምራት እንደተናገሩት፤ አዲሱ መንግስት በሚዋቀርበት ወቅት ማየትና መስማት ከምንፈልጋቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል የክልል አከላለል ስርዓትና በአጠቃላይ በክልል ደረጃ ያለው አስተሳሰብ በተሻለ መልኩ መቃኘት አለበት የሚለው ነው።በኢዜማ እምነት ክልሎች የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ መሆን አለባቸው።ነገር ግን ባለፉት 27 እና 28 ዓመታት ታሪክ እንደሚያሳየው ክልሎች የአንድ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ ተደርገው የሚወሰዱበትና የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብዙም ትኩረት የማያገኙበት ሁኔታ እና የክልሉን ቋንቋ በማይናገሩ ሰዎች ላይ ብዙ የአስተዳደር በደል የሚደርስበት ነባራዊ ሁኔታ ታይቷል፤ ይህ መቀየር አለበት።
እንደ ዶክተር ባንተይገኝ ገለፃ፤ ለአብነት ያህል ኦሮሚያ ክልል ላይ የተለያዩ ተወላጆች ይኖራሉ።የአማራ፣ የአፋርም ሆነ የትግራይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በክልሉ ይኖራሉ። ነገር ግን እነዚህ ብሔሮች በነበረው ሁኔታ የዛ ክልል ባለቤቶች አይደሉም።በዛ ክልል አሰራር ውስጥ ውሳኔ አይሰጡም።ኦሮሚያ ስለተባለ የሚሾመውም ኦሮምኛ መናገር የሚችል የኦሮሞ ክልል ተወላጅ ብቻ ነው።ይህ መስተካከል አለበት።መወሰን ያለበት በዛ ክልል የሚኖር ሰው ሁሉ መሆን አለበት ብሎ ኢዜማ ያምናል።በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ነው፡፡
ቋንቋና ብሔርን ማዕከል ያደረገ አከላለል ምን ያህል ኢትዮጵያን ዋጋ እንዳስከፈላት ይታወቃል።አሁን ህወሓት እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ጦርነትን አንደ አንድ መነሻ ማየት ይቻላል።ይህ አስተሳሰብ ዋጋ እያስከፈለ ነው።አዲሱ መንግስት ለወደፊቱም ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍል፤ ኢትዮጵያ የሁሉም የምትሆንበት አሰራር መዘርጋት አለበት።ይህንን አከላለል ለማሻሻል መነሻው ህገመንግስቱ በመሆኑ መሻሻል ያለባቸው አንቀፆች መሻሻል የሚችሉበት ዕድል መፈጠር አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡
አንድ ክልል ሲከለል ለአስተዳደር ምቹ ሆኖ መዋቀር አለበት።ክልሎች ሲከለሉ ዋናው ነገር ዜጎች ከአንድ ጠረፍ ሌላ ጠረፍ ሔደው ፍትህ ለማግኘት መጓዝ የለባቸውም። በቅርብ በአካባቢያቸው ፍትህ ማግኘትና መዳኘት አለባቸው። የቋንቋን ወይም የዘርን አስተሳሰብ አስወግዶ፣ የቆየ ባህላዊ ትስስርን መሰረት አድርጎ፤ እንዲሁም የመልክአ ምድሩን አቀማመጥ ምቹነት መሰረት በማድረግ መዋቀር እንዳለባቸውም ነው የሚናገሩት።
በተጨማሪ ዜጎች በየትኛውም ክልል ሰርተው የመኖር መብታቸው መረጋገጥ አለበት። ባለፉት 27 ዓመታት የታየው ግን አንዳንድ አካባቢ የቋንቋ ተናጋሪው በሰፈሩ ዓለቃ የሆነበትና እርሱ ሰፈር ያንን ቋንቋ የማይናገረውን የማግለልና እንደዜጋ ያለማየት ዝንባሌዎች ነበሩ። የትኛውም ኢትዮጵያዊ ውጪ አገር ሔዶ የመኖር መብቱ፤ መኖር ብቻ ሳይሆን በዛ አገር እኩል የመዳኘትና እኩል የመኖር መብቱን ለማስከበር ሲታገል ይታያል።በኢትዮጵያ ግን ከአዲስ አበባ ወጥቶ ጉዳይ ለማስፈፀም ጭንቀት ሆኗል የሚሉት ዶክተር ባንተይገኝ ፤ ክልሎች የመላው ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንጂ የግለሰቦች እና የብሔሮች አለመሆኑ መረጋገጥ የአዲሱ መንግስት ሃላፊነት መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
ህገመንግስቱ የብሔሮችን የበላይነትና የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጥ እንጂ የዜጎችንና የግለሰቦችን መብት በምን ያህል ደረጃ እንደሚጠበቅ አላሳየም።ይህንን አለማስቀመጡ ዋጋ አስከፍሏል።ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ዋጋ እንዳይከፈል መረባረብ የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል።ኢትዮጵያውያን ለ27 ዓመታት የተጎዳንበትን ስርዓት ማከም ያስፈልጋል።ይህ ካልሆነ ብልፅግና ተለውጫለሁ በሚለው ደረጃ ለውጡን ሊያሳየን አይችልም።ይህ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት።ይህ የፌዴራል መንግስቱ ሲዋቀር ብቻ ሳይሆን የክልል መንግስታትም ሲዋቀሩ እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
‹‹ ፓርቲያችን ቋንቋዎች መዳበር አለባቸው የሚል እምነት አለው።ብዙሃን የሚናገሯቸው ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ፍላጎቱ አለን፡፡›› ያሉት ዶክተር ባንተይገኝ ፤ ነገር ግን ትልቁ ጥፋት ቋንቋና ዘርን መሰረት ተደርጎ የተፈጠሩ ክልሎች በወቅቱ ለነበሩት አካላት የመጨረሻ ግብ መሆናቸው ነው ብለዋል።ይህ እንዲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደማይፈልጉ በማመልከት፤ የዛ ቋንቋ ተናጋሪ ያንን ቋንቋ በመናገሩ ቅድሚያ እንደሚያገኝ ወይም ተቀባይነት እንደሚኖረው መቁጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።ሌሎችን መጤ ብሎ የመውሰድ ሁኔታ ዜጎች ከሚናገሩት ቋንቋ ጋር በማስተሳሰር የመጣ መሆኑን አመላክተዋል።
ሌላው በዶክተር ባንተይገኝ የተነሳው ጉዳይ የክልል ልዩ ሃይሎችን የተመለከተው ጉዳይ ነው።በህገመንግስቱ እያንዳንዱ ክልል ልዩ ሃይል ያቋቁማል የሚል ሃሳብ የለም።የአካባቢውን ሰላም የሚያስጠብቁ ሃይሎች መኖር ይችላሉ።ነገር ግን ከህገመንግስቱ ውጪ ሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል፤ ከመከላከያ ያልተናነሰ ትጥቅ የታጠቁ ልዩ ሃይሎች እንዳሉ ታይቷል።ለምሳሌ ሶማሌ ክልል በነአብዲ ኢሌ ወቅት አብዲ ኢሌ እንደሶማሌ ክልል አስተዳደር ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ወደ 50ሺህ የሚደርሱ ልዩ ሃይሎች ነበሩት።ይህ ከመከላከያውም በላይ እየፈረጠመ በመሔድ በሁሉም ክልል ልዩ ሃይሉን ይበልጥ የማደራጀትና ከኔ በላይ ማን አለ? በሚል ስሜት ጉልበት የማፈርጠም ተግባር ሲታይ ቆይቷል።
ክልሎች ለሌሎች ፕሮጀክቶች ማዋል ያለባቸውን ገንዘብ ለልዩ ሃይል በማዋላቸው የተለያየ ፉክክር ውስጥ እየገቡ እስከ ግጭት እየደረሱ ነው።የህወሓት ቡድን ራሱ ወደ ግጭት የገባበት ዋነኛው ሚስጥር ለ27 ዓመታት የቆየው ልዩ ሃይሉን ሲያስታጥቅ እና አልፎ ተርፎ ምሽግ ሲቆፍር ራሱን ሲያጠናክር በመቆየቱ ነው።ይህ ወደ ጦርነት በድፍረት ፈጥኖ እንዲገባና የሌሎችንም ክልሎች እንዲደፍር አንደኛው ምክንያት ሆኗል።ስለዚህ በህገመንግስቱ ውስጥ ያልተካተተ በተራ ውድድር የተፈጠረው ልዩ ሃይል ለኢትዮጵያ ከምንም በላይ አደጋ በመሆኑ አዲሱ መንግስት በተቻለ አቅም የኢትዮጵያ መከላከያ ሆኖ ክልሎች ፖሊሶች ብቻ እንዲኖራቸው ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ይህ ልዩ ሃይል ወደ መከላከያ ወይም ወደ ፌዴራል ፖሊስ መቀላቀል አለበት፤ አለበለዚያ ዛሬ በትግራይ የታየው ነገ ደግሞ በኦሮሚያ ልዩ ሃይል ወይም በደቡብ ልዩ ሃይል ስላለመፈፀሙ ማረጋገጫ የለም።ከዚህ አንፃር ኢዜማ ይህ መስተካከል አለበት የሚል እምነት እንዳለው አብራርተዋል።
በተጨማሪነት የኑሮ ውድነት ጉዳይም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ዶክተር ባንተይገኝ፤ ይህ የኑሮ ውድነት አሁን የመጣ ጉዳይ ባይሆንም ብዙዎቹ የኑሮ ውድነቶች የሚመጡት ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ የተሻለ የመንግስታዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል ብለዋል።በተለይ በመንግስት አደረጃጀት ውስጥ ንግድና ኢንዱስትሪን የመሳሰሉ ተቋማት በተቻለ አቅም በነጋዴው የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪዎችን መቆጣጠር ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል።
ሌላው አገሪቱ በአጠቃላይ ያለውን ዋጋ ለማረጋጋት የሚያዋጣው ሰፋፊ ምርት የማምረት ሒደት ውስጥ መግባት መሆኑን በመጥቀስ፤ የአገሪቱ ግብርና ዘመናዊና የህብረተሰቡን የምግብ ፍላጎት እና ፍጆታ ለማሟላት የተሻለ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ ይገልፃሉ።እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት በሚመለከተው ደረጃ ሥራ መስራት አለበት።በተጨማሪ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል መፈተሽ መቻል አለበት።አገር ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት በተለይም ከምግብ ጋር ተያይዞ ያለው ሲታይ ህብረተሰቡ ገንዘቡን ለሌላ ጉዳዮች ከማዋል ጋር የተያያዘ ነው።ስለዚህ በተቻለ አቅም ዜጎች ገንዘባቸውን በምግብ ፍጆታ ላይ ማዋል አለባቸው።ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ቅድሚያ የመስጠት ባህልም መዳበር እንዳለበት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ዶክተር ባንተይገኝ እንዳብራሩት፤ መንግስት ለህዝብ ግልፅ መሆን መቻል አለበት።ይህ ማለት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግሮች በሚመለከት ከህዝቡ ጋር መወያየት አለበት።ምክንያቱም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ማህበረሰብ ጉዳዩን በደንብ እንዲያውቀው መወያየት መቻል አለበት።የመፍትሔ አካልም ሊሆን ይችላል ብለዋል።አያይዘውም የኢትዮጵያ ችግር ለአንድ ፓርቲ ብቻ የሚተው ችግር አይደለም፤ የሁሉም ድጋፍ አስፈላጊ ነው።በተለይ የኑሮ ውድነት ላይ የቁጠባን ባህል ለማሳደግ ከማህበረሰቡ ጋር መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሌላው ከምግብ ጋር የተያያዘው ችግር በምግብነት የምንጠቀመው ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። አንድ ምግብ ላይ ጥገኛ ከመሆን ብዙ አማራጮችን ማየት ይገባል።ልማድን መቀየር ያስፈልጋል።ሁሌ ከምንመገባቸው በተጨማሪ በአማራጭነት ሌሎችንም መመገብ ሌላኛው መፍትሔ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጨምረውም ከውጪ የሚገቡ ምግቦች ነጋዴው ከአቅም በላይ እያስወደደ የሸማቹን ማህበረሰብ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።ነጋዴውን ማሸማቀቅ ሳይሆን የመስራት ነፃነቱ ተከብሮለት ማትረፍ ያለበትን እንዲያተርፍ መደረግ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
ባንተይገኝ፤ ሰላምን ማስፈን የአንድ የብልፅግና ፓርቲ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ በመሆኑ ሁሉም የሚችለውን ያህል ስራ መስራት አለበት በማለት ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አገሪቱ በውስጥ ለውጪ ሃይሎች ጥቃት የተጋለጠችበት ሁኔታ አለ።በአማራ ክልል፣ በአፋርም ሆነ በኦሮሚያ ህዝቡ ሲንገላታ ታይቷል።አገርም አጣብቂኝ ውስጥ ቆይታለች።አሁን ደግሞ ከውስጥም ከውጪም በቅንጅት በመስራት ግልፅ ወረራ ተካሂዷል። በተጓዳኝ አገራዊው ሃይል እስከዛሬ ካለው በተለየ መልኩ ጠንከር ያለ ትብብር እያደረገ ነው።ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል የመከላከያ ሰራዊትን የማጠናከር፤ የደህነት መስሪያ ቤቱ አጠቃላይ ሰብአዊ ይዘቱ የተጠናከረ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት።
ወጣቶች የፌዴራል መከላከያን፣ የፌዴራል ፖሊስን አጠቃላይ የክልሎችን ፖሊስን እየተቀላቀሉ ተገቢው ስልጠና እየተሰጠ መሰራት ይኖርበታል።ነገር ግን ይህ የሰላም ማጣት ችግሮችን ከመከላከል አንፃር የሚጠቀስ ነው።ስለአዲስ መንግስት ሲነሳ በዋናነት የአገር ግንባታውን ፅንሰ ሃሳብና ለሁሉም የምትሆን አገርን መገንባት ላይ መሰራት አለበት።ከአፍራሽነት ምንም ትርፍ አይገኝም።አብን ትልቅ መርሃ ግብር ተነድፎ ተገቢ የሆነ የተረክ ማስተካከያ እንዲኖር መሰራት አለበት የሚል አቋም ያለው መሆኑን ይገልፃሉ።
ልዩነቶችን በጠመንጃ መፍታት የሚፈልጉ ቡድኖች አሉ።እነዚህን ቡድኖች ማሸነፍ የመንግስት ግዴታ ነው።የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አስፈላጊ ነው።ማህበረሰቡ በየአካባቢው እየተደራጀ አጋዥና ደጀን ሆኖ በየአካባቢው ለፀጥታ ሃይሉ አመቺ ሁኔታ መፈጠር አለበት። እነዚህን ሃይሎች በማባበል የሚሆን አይመስልም። መጀመሪያ ‹‹እኛ ከሌለን አገሪቱ ትፈርሳለች›› የሚሉበትን ሁኔታ ማሸነፍ ያስፈልጋል።ይህ እንደማይሆን ትምህርትና ስልጠና መስጠትን ይጠይቃል።የፀጥታ ሃይሉም ቢሆን ቁርጠኝነት ያስፈልገዋል።በጠላት ላይ የተዳከመውን አካል፤ በሰርጎ ገብ የተያዘ ክፍል ካለ አዲሱ መንግስት በአማራ በአፋር ክልሎች ታች ድረስ ወርዶ ማየት ከቻለ ግልፅ ነገሮችን ማግኘት ይችላል።
ወጣቱ የፈለገ ልዩነት ቢኖረውም፤ ሥራ ባይኖረው፤ መንግስት የሚፈልገውን ባያቀርብለትም ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፤ ልዩነቶችን አቻችሎ ይህን ጠላት ማሸነፍ እንደሚገባ የማህበረሰብ እይታ አለ።እርሱ ላይ አጠናክሮ ማህበረሰቡን በተለያዩ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤና ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማስገባት ያስፈልጋል። ሰላም ከአንድ በኩል ብቻ ሊመጣ አይችልም።የማህበረሰብ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከር፤ ፅንፈኞች የሁሉም ጠላት መሆናቸውን ገልፆ መታገል፤ ሃሳባቸውን በዋናነት ማሸነፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ የኑሮ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሻጥር ሲፈፀምበት የነበረች አገር መሆኗን አስታውሰው፤ አሁን ከስልጣን መንበሩ ተገፍቶ መከላከያ ላይ ጥቃት የሰነዘረው ሃይል እጁ ረዥም በመሆኑ መናቅ እንደሌለበት እና ዓለም አቀፍም አገር አቀፍም የሥራ ትስስር የነበረው ሃይል መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል። ‹‹የህወሃት የሽብር ቡድን ከፍተኛ ኢኮኖሚን የሚያንቀሳቅስ የወንጀል ድርጅት ነው።የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመተግበር ህዝቡን ለሥርዓት አልበኝነት ለማነሳሳት ሰፊ ስራዎች ሰርቷል፡፡›› ያሉት አቶ የሱፍ የውጪ ግብረአበሮቹም የአገሪቱን እጅ ጠምዝዘው እንዲህ ከተደረገ ይህንን ማዕቀብ እንጥላለን በሚል ዛቻ በውጪ ሃይሎች እገዛ የህወሓት የሽብር ቡድን በኢኮኖሚውም በኩል በተንኮል እየተዋጋ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ የሱፍ እንደገለፁት፤ ይህንን ችግር ማለፍ የሚቻለው በዋናነት ውስጣዊ አንድነትን እያጠናከሩ፤ እነዚህ ሃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የማያወላዳና በፍጥነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን አማራጭ በማሳጣት ወደ መንግስት ፊቱን እንዲመልስ ማድረግ ይቻላል።ይህ ሲሆን መልሰው የውጪ ሃይሎችም ወደ ትብብር መምጣታቸው አይቀርም።እርሱ ላይ ጠንከር ያለ ሥራ መስራት አለበት ብለዋል። በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የተፈናቀለ ህዝብ አለ፤ ሌላ አማራጭ የለም። ንብረት ወድሟል፤ ጤና ጣቢዎችና ሆስፒታሎች በአጠቃላይ የመንግስት ተቋማትን አቃጥለዋል፤ አበላሽተዋል፤ መሰረተ ልማትን አጥፍተዋል፤ ስለዚህ የመልሶ ግንባታና ማህበረሰቡን የማቋቋም ሥራውም በትብብር መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።የኢኮኖሚ አሻጥሩም ላይ ቢሆን፤ በሰፊው የሚሳተፉ የተደረሰባቸውም ገና ያልተደረሰባቸውም አካላት ስላሉ እነርሱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ አቶ የሱፍ ገለፃ፤ አገር ውስጥ ያሉ የኢኮኖሚ መሰረቶች እያቆጠቆጡ እንዲሄዱ መስራት ያስፈልጋል።አቅርቦትን ማሳደግ ወሳኝ ነው።ማህበረሰቡን ማደራጀት፣ የተበጣጠሱ ሥራዎችን ወደ አንድ ማምጣት፤ ማህበረሰቡ በትክክል ግብሩን እንዲከፍል ማድረግ ተገቢ ነው።በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚውም ያለው አንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም።ምዕራቡ እንደውም ዕርዳታም ሆነ ድጋፍ የሚሰጠው ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠ ነው።ስለዚህ ዓለም ሰፊ በመሆኗ አይንን ሰፋ በማድረግ ከሌሎችም ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብዝሃነት ፌዴራሊዝም አይደለም።ማህበረሰብን ለያይቶ አገራዊ የጋራ ማንነት እንዳያዳብር ተሰርቷል።ልዩነቶችን መሰረት አድርጎ ግጭቶችን የማንገስ ህዝቦች እንዳይገናኙ የማድረግ ሴራ ሲከናወን ነበር።ይህ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ፌዴራሊዝም አይደለም።እንደውም ተቃራኒ ነው።ፌዴራሊዝም የሚያዘውና መሆን ያለበት በሃቅ ላይ ተመስርቶ የማህበረሰብ ባህል፣ እሴትና እኩልነት መረጋገጥ ነው።በዚህ ጊዜ የዜግነት ፖለቲካ እየሰረፀ የሚመጣና እየተረጋገጠ የሚሔድ ይሆናል ብለዋል። የዜጎችን ደህንነት በማንኛውም ቦታ በየትኛውም የኢትዮጵያ ኮሪደር ሰርቶ የመኖር፤ ህጉ በሚጠይቀው መሰረት ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ያለምንም መሸራረፍ የሚከበርበት ጉዳይ ላይ፤ በክልል ደረጃ ያለው አስፈፃሚም ሆነ የክልል መንግስቱ ጠንከር ያለ አቋም መወሰድ ይርበታል።አገራዊ ማንነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በደንብ መሰራት አለበት ብለው እንደሚምኑ ተናግረዋል።ሁልጊዜም ቢሆን በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ከማዕከል የሚያርቅ አካባቢያዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፤ አገራዊ የጋራ በጎ ግንኙነት፤ የህዝብ ለህዝብ በጎ ትስስርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ከፌዴራል ስርዓት ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ኢትዮጵያ ቀድማ የነበረች አገር መሆኗን ይክዳሉ።ይህ ትክክል አይደለም፤ የፌዴራል ስርዓትን ስንተገብር ወደድንም ጠላንም የጋራ ማንነታችን ጠንካራ መሆን አለበት።ልዩነቶቻችን መካከል አገራዊ አንድነትን መሰረት ያደረገ በጊዜ ሒደትም ወደ ጋራ ማንነት እየተሰባሰብን የምንሔድበት አብረን የምንሰራበት፤ ሁላችንም የምንፈልገውን ማንነት እንደመስታወት የጋራ ማንነት ላይ የምናይበት እየሆነ የምንሰባሰብበት መሆን አለበት።ፌዴራሊዝም የምንገነጣጠልበት አገር የምናፈርስበት ፓኬጅ አይደለም ብለዋል።አቶ የሱፍ እንደገለፁት የጋራ ማንነት ላይ የተኮረ ፖለቲካ መሰራት አለበት።ይህንን የማህበረሰቡን ጥያቄ የግድ በተቃውሞ መልክ ብቻ ማየት የለብንም።በፍትህ በዴሞክራሲ አንደኛችን አንድ እርምጃ ተራምደን የምንደጋገፍበት፤ ትብብሮች የሚሳለጡበት ማዕቀፍ ያስፈልጋል።እዚህ አገር እንዳለመታደል ሆኖ እዚህ አገር ፌዴራሊዝም ሲጀመር ትክክለኛ ፅንሰሃሳብ ሆኖ መርሆቹን ባለመከተላችን ብዙ ተግዳሮት ተፈጥሯል።ፌዴራሊዝም በሚል ስም ኢትዮጵያ ሲባል ቃሉን መጥራት የማይወድ የፖለቲካ ሃይል በርካታ ነበር።እንዲህ አይነት ፌዴራሊስት ነኝ ብሎ ነገር አይሰራም።በየትም አገር የፌዴራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ፤ ባለብዙ ባህልም ሆነ ባለአንድ ባህል ማንኛውም ቢሆን አገራዊ ማንነት ላይ ያተኮረ፤ ነገር ግን ያሉ ልዩነቶችን የሚስተናገድበት ነው።
በማንኛውም ቦታ ዜጎች መብታቸው እየተከበረ መዋቅር ተዘርግቶ ወደ አገራዊ ማንነት በሂደት የሚያድጉበት እንጂ፤ ቅርቃር ውስጥ የሚያስገባ አስተሳሰብ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ አይደለም።የመገንጠል ሃሳብ የፌዴራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ አይደለም።ፌዴራሊዝም ልዩነቶቻችንን አቻችለን አብረን እንኖራለን የሚል መግባባት ነው።ፌዴራሊዝም እንደመወያያ መድረክ ነው።በዚህ መድረክ እኔ ያልኳት ስላልሆነ ረግጬ እወጣለሁ የሚል ልክ ለሌላ መደበኛ ስብሰባ የሚያገለግል ለአገር ግንባታ ግን የማይሆን ተቀባይነት የሌለው መርህ ነው።እነዚህ ነገሮች ላይ የህገ መንግስት ማሻሻያዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።ነገር ግን በተግባር በፖለቲካ ምሁሩ መካከል ረግጬ ወጣለሁ በሚል መልኩ ሳይሆን የሰለጠኑ ድርድሮችን በማድረግ አቻችሎ ለማለፍ መጣር ያስፈልጋል።
በርካታ አገራት ከብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ ወጥተው አገር ሆነው፤ በኢኮኖሚና በተለያዩ ጉዳዮች አድገዋል።ሁላችንም ለህዝብ የምናስብ ከሆነ ያንን ማምጣት ይቻላል።እዛ ላይ ትብብር ማድረግ ይርብናል። የተለያየ ሃሳብ አለን ማለት በአገር ጉዳይ ላይ አንስማማም ማለት አይደለም።በአገር ጉዳይ አንድ መሆን ያስፈልጋል።ከዛ ውጪ እኔ ከሌለሁ አገር ትፍረስ የሚለው ፖለቲካ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ብልፅግና የኢትዮጵያ ህዝብን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግርን በደንብ ተረድቷል።የአስር ዓመት የኢትዮጵያን ችግር የመፍቻና የብልፅግና ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል።በየዘርፉ ግብርናው ምን ይሁን፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የዜጎችን ህይወት ማሻሻል እንዴት ይደረግ፤ የዜጎችን ህይወት፣ ድህነት ቅነሳ እንዴት ይሁን? የሚለውን ሰፊ ፍኖተ ካርታን በዚህኛው የምርጫ ዘመን የሚያስፈፅመውን አዘጋጅቷል።
ብልፅግና የህዝብን ችግር ከመገንዘብ ጀምሮ፤ ችግሮችን መፍታት ጀምሯል።ስለዚህ አሁን የሚመሰረተው በብልፅግና የሚመራውና ሌሎችም የሚሳተፉበት መንግስት የኢትዮጵያውያንን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የመንግስት አደረጃጀቱን በደንብ አዘጋጅቷል።በዚህ የመንግስት አደረጃጀት በደንብ ገብተው መስራት የሚችሉ ከፌዴራል መንግስት እስከ ቀበሌ ድረስ ምን ዓይነት አመራሮች ናቸው? ከቅንነት፣ ከልምድ፣ ከችሎታና ከአስተሳሰብ አንፃር ምን ዓይነት አመራሮች ናቸው? ብሎ አስቦ አዘጋጅቷል።
ሃብት የማሰባሰብ በጀት በየደረጃው በመሰብሰብ ላይ ይገኛል።በቂ ስልጠናም ሲሰጥ ቆይቷል።ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ የሚሰጠው ስልጠና ይቀጥላል።ሃሳቦቻችንን ወደ ተግባር ለመቀየር ተከታታይ ሥልጠናዎች ይሰጣል።በጣም ጠንካራ የክትትል፣ የድጋፍና የተጠያቂነት ሥርዓት ይዘረጋል።የሚመጡ ውጤቶችን ከህዝብ ጋር በመነጋገር ለህዝብ ይፋ በማድረግ መልካም ውጤቶችን ህዝቡ እንዲያውቃቸው ፈተና የሆኑትን እና አሁንም ያልተፈቱትን ችግሮች ከታች ወደ ላይም ጭምር በማቅረብ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ያደርጋል።ጥርት ያለ በዕቅድ የተደገፈ ለዛ የሚሆን መዋቅር፣ አደረጃጀት፣ አመራርና በጀት እንዲሁም የተጠያቂነት ስርዓት ዘርግቶ ወደዛ እየገባ ስለሆነ ችግሮቹን ለመፍታት በጣም በመልካም ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቀጣዮቹ አምስታት ዓመታት በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ትልቅ መሰረት የተጣለ ሲሆን፤ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ አረጋግጠዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም