አፍሪካውያን እንደ አንድ ትልቅ ህዝብ ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በራሳቸው እጣ ፈንታቸውን የመወሰን አቅም ተነፍገው ፣ሌሎች እየወሰኑላቸው ለከፋ ችግርና መከራ የመዳረጋቸው እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዘመናት ውስጥም ይህንን ችግር ሰብሮ ለመውጣት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልም ብዙ እንቁ የአህጉሪቱ ልጆች የህይወት ዋጋ ከፍለዋል።
የአህጉሪቱን ህዝቦች የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት በመቀራመት የጀመረውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል አይኑን አፍጥጦ ያለ ሀፍረት በአደባባይ ሞግዚት ሆኖ የተገለጠው የምዕራቡ አለም ፣ ይህንን ዓላማውን ለማሳካት የሄደበት የሴራ መንገድ የአህጉሪቱን ህዝቦች ለከፋ ድህነት ከመዳረግ ባለፈ ያመጣለት አንዳችም ትሩፋት አልነበረም።
በእነዚያ የቅኝ ግዛት ዘመናት አፍሪካውያን ካሳለፉት ድህነት እና ከድህነቱ ከሚመነጭ ሰቆቃዎች ባለፈ ስለማንነታቸው ከተፈጠሩ የተዛቡ ኢ- ሰብአዊ ትርክቶች አንጻር በማንነታቸው ምክንያት አንገታቸውን እንዲደፉና እጣ ፈንታቸው የተገዥነት የሆነ እስኪመስል ድረስ ከፍ ባለ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
ይህንን አስተሳሰብና አስተሳሰቡ የወለደውን አስከፊ ድርጊት ለማስወገድ አፍሪካውያን ከፍ ያለ መስዋእትነት ከፍለዋል። በተለይም ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል በአድዋ ድል አድርገው በሽንፈት ከመለሱ ማግስት አንስቶ አፍሪካዊያን ከዚያም በላይ መላው ጥቁር ህዝቦች ከተጫነባቸው የጭቆና /የተገዥነት / ቀንበር ቀና ማለት የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል። ራሳቸውን ገዥና የበላይ አድርገው ለሚያዩ ምዕራባውያን እምቢ ለማለት የሚያስችል መንፈሳዊ አቅም መገንባትም አስችሏል።
የምዕራቡን ዓለም የቅኝ አገዛዝ ለማስወገድ በተደረገው እልህ አስጨራሽ የወስዋዕትነት ትግል በኋላም ቢሆን አፍሪካውያን በደማቸው ነጻነታቸውን ማስከበር ቢችሉም ብዙ መስዋዕትነት የጠየቀው ነጻነታቸው በብዙ ሴራዎች ከእጃቸው እንዲወጣና ነፃነቱ ከቋንቋ ባለፈ ትርጉም ወደሚኖረው እውነታ እንዲሻገር ተደርጓል።
በአንድ በኩል አፍሪካውያኑ ራሳቸውን ለመሆን ያደረጉት ትግል ለምዕራቡ ዓለም ምንደኛ በሆኑ አፍሪካውያን ምሁራንና መሪዎች አማካኝነት እንዲዳከም የተደረገ ሲሆን ፤ከዚህም ባለፈ ስለ ህዝባቸውና ስለ አፍሪካ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙ መሪዎችን ድምጽ በማፈን እንዳይሰሙና በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲወገዱም ሆነዋል።
ይህ ታሪካዊ እውነታ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የቀጠለ ፤ በየዘመኑ መልኩን እየቀየረ ብዙ አፍሪካውያንን ዋጋ ያስከፈለ፤ ለአፍሪካውያን ትንሳኤ ዋነኛ ተግዳሮት የሆነ ነው። አፍሪካውያን እንደ ህዝብ የራሳቸውን እጣ ፈንታ እንዳይወስኑና በነገዎቻቸው ተስፈኛ እንዳይሆኑም ያደረጋቸው ዘመን የተሻገረ ችግር ነው።
የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ገዥ ነው በሚባልበት፤ ሰጥቶ መቀበል የዓለም አቀፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረት ነው እየተባለ በሚነገርበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፤ በዘመነ ግሎባላይዜሽን እንደቅኝ ግዛት ዘመን በራስ ወዳድነት አስተሳሰብ የተቃኙ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ዓለም አቀፉን መድረክ አጣበው ማየት የተለመደ ሆኗል።
ስለ ሰብአዊነትና አለም አቀፋዊነት ደክሟቸው እስኪዝሉ ድረስ የሚሰብኩ ሀገራትና መንግስታት ሳይቀሩ የትናንት ያልተገቡ ጥቅሞችን ለማስቀጠል የአህጉሪቱን ህዝቦችን ተስፋ በሚናጠቅ መልኩ በኢፍትሃዊነት አደባባችዮችን ሞልተው ሲንቀሳቀሱ ማየት የለት ተዕለት ክስተት ከሆነ ሰንባብቷል። ለዚህ ኢፍትሃዊ ተግባራቸው ስኬትም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ሳይቀር እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ከዓለም አቀፍ ህግ እና ከሰው ልጆች መሰረታዊ የሞራል እሴት የሚጋጨው ይህ የሀገራቱ ተግባር በየትኛውም መመዘኛ የሚወከሉትን ህዝብ የሚያሳንስ ከመሆኑም ባለፈ ፤ በብዙ የመስዋዕትነት ዋጋ አፍሪካውያን የተሻገሩትን ዘመን የመመለስ ክፉ ሀሳብና ምኞት የተሸከመ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሊያወግዘው የሚገባ ነው ።
በምንም መመዘኛ አፍሪካውያን ራሳቸውን የመሆኑ ተፈጥሯዊ መብት ባለቤት ናቸው። ይህንን መብት ለመጎናጸፍ የሚያደርጓቸው ትግሎች ተግዳሮቶችም የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆንም መጨረሻው በስኬት መጠናቀቁ የማይቀር ነው።
ይህ እውነታ ከለውጥ ማግስት ጀምሮ በኢትዮጲያ የፖለቲካ መድረክ ላይ በግልጽ እየተንጸባረቀ የሚገኝ ነው። በህዝብ ትግልና የመሆን መሻት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ሀይል በፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሳብ ላይ በመመስረት እንደ ሀገር የሀገሪቱን እጣ ፈንታ መወሰን ያለበት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው በሚል የጀመረውን እንቅስቃሴ ለማፈን ብዙ ሴራዎች ተጎንጉነው ተተግብረዋል።
ከሁሉም በላይ የፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ ገድለን ቀብረነዋል ብለው በሚያስቡ ሀይሎች አስተሳሰቡ በኢትዮጵያ ትንሳኤ የማግኘቱ እውነታ ብዙ ያሳሰባቸው እና ያስደነገጣቸው እስኪመስል ድረስ ከፍ ባለ ቁጣ እና ዛቻ በየዕለቱ እያየናቸውና እየሰማናቸው ነው። የዓለምን መድረክ የሞላው የነዚህ ሀይሎች ቁጣና ዛቻ የኢትዮጵያውያንን ራሳቸውን የመሆን ተፈጥሯዊ መብት ሊያሳጣቸው የሚችል አይሆንም።
ከዚህ ይልቅ አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ለሚያደርጉት ትግል ተጨባጭ ተሞክሮ በመሆን ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠል ዘመናት ያስቆጠረውን ተስፋቸውን በመጨበጥ ነገዎቻቸውን ከፍ ባለ ተስፋና ጽናት እንዲጠብቁ የሚያስችል የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው!
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም