ኢትዮጵያ ልትወጣቸው የማትችላቸው ከሚመስሉ በርካታ ችግሮች አልፋ አዲስ የመንግስት ምስረታ ላይ ደርሳለች። እንሆ አሁን በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል የተመረጠው የብልፅግና ፓርቲ መሪ ሆኖ መንግስት መስርቷል። የስራ አስፈፃሚዎች ተሹመዋል። አሸናፊው ፓርቲ በገባው ቃል መሰረት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በካቢኔው ውስጥ አካቷል። እኛም የአዲስ መንግስት ምስረታን ምክንያት በማድረግ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የሦስት ዓመት የለውጥ ጉዞ ተግዳሮትና ስኬት እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ቢቂላ፡- ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው የአገሪቱ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መልካም የሚባል አልነበረም። ይህ ማለት አገሪቱ ለዘመናት የፖለቲካ ህመም አዙሪት ውስጥ ነበረች። ከደርግ በፊት የነበረው የንጉሳዊ ሥርዓትም ሆነ ከንጉሱ በኋላ የመጣው ደርግ ፍፁም አምባገነናዊ እና ብዙ ትውልድ ያስገበሩ ስርዓቶች ነበሩ። ከእነርሱም በኋላ በትጥቅ ትግል እና በጉልበት ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ ስርዓትም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ስርዓት መልካም የሚባል አልነበረም። ከፖለቲካ አንፃር የሥብራት ዘመናት ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል።
ከሦስት ዓመታት በፊት ትውልድ እየጨረሰ ደም እያፋሰሰ የቀጠለ የፖለቲካ ስርዓት መስተካከል አለበት፤ ኢትዮጵያ የሰለጠነና ዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት ያስፈልጋታል፤ ይገባታል፤ በሚል የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ አጋጣሚ መግፋት ቀጠለ። ከውስጥ በተፈጠረ ፈቃደኛ የለውጥ ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተደረገ። በሽግግሩ ሦስት ዓመታት የለውጥ ኃይሉ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ስልጣን የመጣበት እና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ስርዓትና የሰላም ግንባታ ምዕራፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በኃላፊነት የተንቀሳቀሰባቸው ዓመታት ነበሩ። ከዚህ አንፃር በጣም በርካታ ስኬቶች ተገኝተዋል።
እውነት ለመናገር የአገራችን የፖለቲካ ድባብ ከመሰረቱ ተቀይሯል። አገራችን ከተከተለችው የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ የተነሳ የዛሬ ሶስት ዓመት ለመበታተን ጫፍ ላይ ደርሳ ነበር። ዘረኝነት ጫፍ የደረሰበት፤ ሰዎች ከወንድማማችነትና ከእህትማማችነት ይልቅ ጠላትነት፣ ባላንጣነት፣ መጠፋፋትን ከፍ አድርገው ያዩበት ጊዜ ነበር። ከትልቁ የኢትዮጵያዊነት ስዕል ይልቅ ሁሉም ወደየመንደሩ የወረደበት፤ ከጎኑ ያለውን ጎረቤቱን የረሳበት፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር መሆኗ የተረሳበት ጊዜ ነበር።
ይሄን እሳቤ በጉልበት ሲያስቀጥል የነበረው ቡድን መጀመሪያም የሚፈልገው ይህንን እሳቤ ስለነበር ስለመብት፣ ስለእኩልነት እና ስለነጻነት ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎችን በሙሉ ግማሹን ገድሎ፤ ግማሹን አሰቃቂ በሆነ መንገድ እስር ቤት አጉሮ፤ ግማሹን ከአገር አሰድዶ፤ ግማሹ አድራሻው እንዲጠፋ አድርጎ ነበር። ኢትዮጵያውያን የጋራ ነገር ሳይኖራቸው መብት እና እኩልነታቸው ተደፍጥጦ፤ ኢትዮጵያውያን ሞራላቸው ላሽቆ አንገታቸውን ዝቅ አድርገውና ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲኖሩ ያደረገ ኃይል ነበር። ኢትዮጵያ ፈጣሪ ደርሶላት ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው የለውጥ ኃይል ከመጥፋት ታደጋት እንጂ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበረች።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድባብ የቀየሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ዋናው ነገር በዚህች አገር ላይ ኢትዮጵያውያን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን እንድንሔድ የሚያስችለን ጠንካራ መሰረት ተጥሏል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለውን ማረጋገጥ ችለናል። ሊያፈርሷት የሚችሉ ኃይሎች በሙሉ እንደማያፈርሷት ተገንዝበዋል። በእርግጠኝነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች በፍፁም ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችሉ አረጋግጠዋል። ለዚህ ፈጣሪም ታክሎበት
በተግባር ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ ታይቷል። ስለዚህ የወንድማማችነትና የአብሮነት ስሜት፤ የአንዱ ህመም የሌላው ህመም፤ የአንዱ ችግር መከራ የሌላው ችግር መከራ የሚሆንበት አስተሳሰብ ተፈጥሯል። ጋምቤላ ላይ ያለው ዜጋ አፋር ላይ ያለው ዜጋ አጥንቴ ነው የሚልበት፤ ኦሮሚያ ላይ ያለው ዜጋ አማራ ክልል ላለው ዜጋ ወንድሜ ነው ስጋዬ ነው የሚልበት፤ ብንደኸይ የደኸየነው አብረን ነው፤ ብንቸገርም የተቸገርነው አብረን ነው፤ ፈተናችንም የጋራ ነው ስለዚህ ከፈተና መውጣት የምንችለው አብረን ከተባበርን ብቻ ነው የሚል ስሜት ባለፉት ሦስት ዓመታት መፍጠር ተችሏል።
የአገራችን የፖለቲካ ወይም የዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓቱ ከመጠፋፋትና ደም ከመፋሰስ ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ እንዲሻገር ተደርጓል። እነዛ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተወሰዱ እርምጃዎች አሁን ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል። ለምሳሌ ወደ 100 ሺህ ሰዎች ከእስር ቤት ተፈቱ። ውጭ አገር የሚኖሩ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ብንበር እንኳ እንመታለን ብለው የሚሰጉ የቤተሰባቸውን ኀዘን መካፈል እና እናትና አባታቸውን መቅበር የተከለከሉ አካላት ወደ አገር እንዲገቡ ተደረገ። ወደ አገር መመለስ ብቻ አይደለም፤ በሚመሰረተው መንግስት መሾም አለባችሁ ተብለው እየተሾሙ እየታየ ነው።
ለዚህች አገር የፖለቲካ ህመም ፈውሱ ቅንነት፣ ደግነት፣ አርቆ አስተዋይነት እና የዛሬውን ትውልድ ሳይሆን የነገውን ትውልድም አሻግሮ ማየት ነው። ለልጆችና ለልጅ ልጆች የሚሆን አገር መገንባት፤ ለዚህም ዛሬ የሚከፈለውን ዋጋ መክፈል። ወንድማማችነትና እህትማማችነት ዝምድናንና መተባበርን ባህል ማድረግ ተምረንበታል። ይህ ሲታይ ከፖለቲካና ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንፃር በጣም ትልቅ ስኬት ተገኝቷል። በእርግጠኝነት ህብረብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት መገንባት እንደምንችል በተግባር አረጋግጠናል። በብዝሃነት ውስጥ የደመቀች ኢትዮጵያን የምትመስል፤ የምስራቁን፣ የምዕራቡን፣ የደቡቡንና የሰሜኑን ሁሉንም የምትመስል ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያካተተችና ያሳተፈች ያቀፈች፤ ነገር ግን አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን በመገንባት በኩል በጣም ትልቅ ስኬት ተገኝቷል። ይህ የሚያኮራ ነው።
ኢኮኖሚውም እንደፖለቲካው ሁሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከውድቀት ተርፏል። ምክንያቱም አገራችንን ሲያስተዳድር የነበረው የህወሓት ቡድን ይጠቀምበት የነበረው የአመራር ዘይቤ የሴራ፣ የተንኮል፣ ሀብት የማሸሽ፣ ጥቂቶችን የማበልፀግ፣ በህገወጥ መንገድ የመክበር፣ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ለጥቂቶች የማከፋፈል፣ ብክነት
ሌብነት በብዙሃኑ ደም ጥቂቶችን የማክበር አካሄድን ይከተል ስለነበር፤ የአገራችን ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ ቆይቷል። ለውጡ በመጣባቸው ጊዜያት በግልፅ መታወቅ ያለበት በቋሚነት ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር። የአገሪቱ ካዝና ተራቁቶ በትንሹ በየወሩ ለመንግስት ሰራተኞች የሚወጣው ቋሚ ወጪ መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር። ለአገሪቱ ዜጎች በህይወት መቆያ መድሃኒት ከውጭ ማስገባት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። የአገሪቱ የውጪ ዕዳ አፍንጫ ድረስ ደርሶ አገሪቷ መሻገር የማትችልበት ፈተና ላይ ደርሳ ነበር።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ መበደር ስለማትችል፤ ከውጪ አገር ጋር የብድር ግንኙነት አይኖራትም የሚል ስጋት አጥልቶባት ነበር። የለውጥ ኃይሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት እነዚህን የቀለበሱ እርምጃዎችን ወስዶ አስተካክሏል። በዚህም ምክንያት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከደረሰበት የውድቀት አፋፍ በመመለስ እንዲያገግም እና ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ ተችሏል። ለአገሪቱም ተስፋ የሚሆን የለውጥ አመራሩም በዚህ እንዲበረታታ ተስፋ እንዲታየው የሚያደርጉ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ ክምችታችን በእጅጉ እንዲሻሻል፤ የአገሪቱ የገንዘብ አቅም እንዲጨምር፤ ከአበዳሪ አካላት ጋር በመነጋገር የአገሪቱ የብድር አመላለስ እንዲስተካከል ብድሮች እንዲሰረዙ ወይም የመክፈያ ጊዜአቸው እንዲራዘም፤ አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት አማራጭ ወጥቶ ሥራ ላይ በማዋሉ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ መታደግ የቻለ እርምጃ ተወስዷል። አሁን ከአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ አንፃር እጅግ በጣም አስጊ የሆነ ችግር የለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ ችግሮች መልክ እንዲይዙ ተደርጓል። በእርግጥ አሁን ካለው ህግ ማስከበር፣ ከኑሮ ውድነት እና ከዋጋ ንረት ጋር የተያያዙ ዜጎችን በመፈተን ላይ ያሉ ነገሮች ቢኖሩም፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከውድቀት ለማዳን የተቻለበት ስኬት ተመዝግቧል።
ከኢትዮጵያውያን ማህበራዊ መስተጋብር አንፃርም በርካታ መሻሻሎችና ለውጦች መጥተዋል። ማህበራዊ ሕይወታችን በእጅጉ እንዲሻሻል ተደርጓል። ፖለቲካው የሰዎችን ማህበራዊ ግንኙነትና አኗኗርም ጭምር ለውጦታል። በፊት ሰዎች በጥላቻና በጥርጣሬ የጎሪጥ ይተያዩ ነበር። አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ማዶ ለማዶ የሚተያይበት አይነት ግንኙነቶች እንዲቀየሩ ተደርጓል። ለምሳሌ በሃይማኖቶች መካከል በክርስትና እምነት ውስጥ ጠንካራ ህብረትና እርቅ ተመልሶ እንዲመጣ አንድ ሲኖዶስ እንዲኖር ተደርጓል። በእስልምና እምነት ውስጥም እርቅ እንዲኖር፤ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የነበሩ አለመግባባቶችየአገሪቱን የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ተከትለው እነዛ አለመግባባቶች በእውነትና ከልብ በሆነ እርቅ እንዲታለፉ ማድረግ ተችሏል።
ሰዎች እርስ በእርስ እንዲታረቁ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከልም፤ በአንድ ሃይማኖት ውስጥም በተለያዩ አካላት መካከል የነበሩ አለመግባባቶች ጭምር የይቅርታ፣ የምህረትና ስለነገ ሲባል የዛሬ አለመግባባቶችን በመፍታት መርህ ነገሮች ወደ ዕርቅ ስሜት እንዲመጡ የተደረገበት መንገድ አገራችን ላይ በተለያየ መንገድ ውጪ አገር ተሰደው የነበሩ ኢትዮጵያውያንም በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ እንዲያድርባቸው አድርጓል። ሰው አገሩን እንዲወድና ወደ አገሩ እንዲመለከት አድርጓል። ስለዚህ ሰው ሰው የሚሸት ለውጥ ነበረ። ስለሕፃናት፣ ስለወጣቶች፣ ስለሽማግሌዎች የሚያስብ ስለአገራችን ሕዝቦች በሚገባ የሚያስብ እና ህመማቸውን የሚረዳ ለውጥ ነበር። በዚህ ምክንያት የለውጡ ስሜት በየደጃችን ደርሷል። ቤታችንን አንኳኩቷል። ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማን አድርጓል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ስለነበረው ፈተና ሲመጣ ማንኛውም ለውጥ የራሱ መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ በለውጥ ሒደቱ መካከል የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ይኖራሉ። ለውጥን አስቦ ፈተናን ሸሽቶ አይቻልም። የተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎች የየራሳቸው ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች ነበሩባቸው። አንዱ ቀድሞ ለሰላሳ ዓመታት የተሰራው የፅንፈኝነት እና የአክራሪነት የፖለቲካ አሰራር የደቀነው ፈተና ነው። የዋልታ ረገጥነት በተሻለ መልኩ ይገልፀዋል። ይህ የዋልታ ረገጥነት ስርዓት የፈጠረው ስጋት ከባድ ነበር። ብዙ ሰዎች በዋልታ ረገጥነት አቋራጭ በፅንፈኝነት፣ ሰዎችን በማጋጨት፣ ደም በማፋሰስ፣ የጠላትነትና የባላንጣነት ስሜትን በሰዎች ውስጥ በመዝራት ስልጣን ላይ የቆዩ አካላት የእርቅና የሰላም አስተሳሰብ ሲመጣ ፈተና ሆነው መጥተዋል። የለውጡ ሒደት ሰዎችን መጨፍለቅና ማጥፋት እንደሆነ፤ ህብረ ብሔራዊነትን ትቶ እንደሚጨፈልቅና አሀዳዊ ስርዓት እንደሆነ አስመስለው በመስበክ ፅንፈኛ ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርገዋል።
ይህ ትውልድ የማይረሳው ጠባሳ ትቶ ያለፈው ባለፉት 27 ዓመታት አገርን በጉልበት ሲያስተዳድር የነበረው የህወሓት አሸባሪ ቡድን የደቀነው አደጋ የሚናቅ አይደለም። በዚህ ምክንያት በክፋት በተንኮልና በሴራ ሲመራ የነበረው ስርዓት ሲፈርስበት የተከተለው መንገድ እዚም እዚያም ዜጎች እንዲባሉ አቅዶ ሰርቷል። ይህ ፈተና ነው። ዜጎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በብሔር፣ በማንነት፣ በትውልድ ቦታ፣ እርስ በእርስ እንዲጋጩ ሲያቅድና ሲተገብር ነበር። አምና መስከረም 30 ላይ የጥፋት ሰነድ ወጥቶ በቅርብ ከታየ በኋላ እጅግ የሚያስቆጭ እና የሚያንገበግብ ለካ ይሄ ቡድን ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ አበክሮ ምን ያህል ሲሰራ እንደነበር ማረጋገጥ ተችሏል። በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች በብዙ የአገራችን አካባቢዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማድረግ ሙከራ አካሂዷል። በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ በግጭቱ ምክንያት በጣም ብዙ ንፁሃን ዜጎቻችን ተጎድተዋል። ለፍቶ አዳሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የከተማና የገጠር ድሃዎች፣ ነገ ለአገር ጋሻና መከታ መሆን የሚችሉ ወጣቶች ተጎድተውብናል። ይህ የሚያሳዝን የሚቆጭ እና የሚያንገበግብ ነው። አንዱ ፈተና በለውጡ ሒደት ውስጥ ክፋት እና ሴራው ሲጋለጥበት ተገፍቶ የወጣው አሸባሪ ቡድን የደቀናቸው የጥፋት የአመፅ፣ ዜጎችን የማጋጨት እና ደም የማፋሰስ የተንኮል ተግባራት ናቸው። እንደዛም ሆኖ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተንኮልና ሴራን አቅደው ቢያካሂዱም፤ ኢትዮጵያን ማፍረስ አልቻሉም። ይልቁንም ኢትዮጵያውያን ተባብረው ጠንካራ ሆነው የጋምቤላው፣ የቤኒሻንጉሉ፣ የአፋሩ፣ የሶማሌው አታፈርሱንም ብለው ወጥተው መዋደቃቸው ታይቷል።
ሌላው ፈተና በለውጥ ሂደቱ ውስጥ ሆደ ሰፊነት፣ ይቅርታ፣ ምህረትና ይሔን የለውጥ ሂደት በአብዮት መንገድ ሳይሆን በማሻሻል (በሪፎርም) መንገድ እንምራው፤ በመቻቻል መንገድ እንምፈራው በመባሉ የተፈጠረው የፖለቲካ ድባብ አላግባብ የመጠቀም አዝማሚያዎች የፈጠሩት አደጋ ነበር። ሲጀመር ጥፋት አለ፤ ነገር ግን ሌሎቹ ስርዓቶች ሲያደርጉ እንደነበረው እስር ቤት በማጎር፣ በመግደል ወይም በማሳደድ አናልፈውም። ኢትዮጵያ የሚገባት ይቅርታና ምህረት ነው በሚል ለውጡ የተመራበት የይቅርታ፣ የምህረት፣ የመቻቻልና ስለቀጣዩ ትውልድ ማሰብን መሰረት ያደረገው ፍልስፍና አለአግባብ በመተርጎም የተከፈተውን የፖለቲካ ድባብ ወዳልተፈለገ አውድ በመውሰድ እዚም እዚያም ስጋት እንዲፈጠር የተደረገበት ሁኔታ ተስተውሏል።
በሰላማዊ የፖለቲካ ሜዳ ታግለው ለትውልድ የሚተርፍ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይገነባሉ ተብለው የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ዕድሉን እንደተጠቀሙት ሁሉ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሥርዓቱን የማፍረስ የተፈጠረውን ዕድል የማባከን እና የመረበሽ እና ለዜጎች ስጋት የመሆን አዝማሚያን ያጫሩ አሉ። አንዳንዶቹ የፅንፈኝነት ፖለቲካ ለአገራችን አያዋጣም ሲባል ፅንፈኝነታቸውን ተሸክመው መጥተዋል። ስለዚህ በየሜዳው ስሜቶችን ማጫር በዜጎች መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ማድረግ ላይ አተኩረዋል። በለውጡ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዓመትም ላይ ዜጎችን ስሜት ውስጥ የመክተት አንዱ ሌላው ላይ የጠላትነት ስሜት እንዲኖረው ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አመራር ግለሰቦች ነበሩ። አንዳንዶቹ ተጠያቂ ተደርገዋል። ይህም ፈተና ነበር። ከዚህ ፈተና የተማርነው ነገር፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ሽግግሩ እጅግ በጣም በጥንቃቄና በብልሃት መመራት አለበት ብለን እናምናለን። ከዚህ ተምረን ብዙዎቹ ነገሮች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።
ስለዚህ አሸባሪው ቡድን ደም መፋሰስን፣ ጥፋትን፣ ዜጎችን መግደልን፣ አካል ማጉደልን፣ ንብረት ማውደምን አቅዶ እንደሰራው ሁሉ የተከፈተውን የፖለቲካ ሜዳ ባልተገባ መንገድ የተጠቀሙ አካላትም ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ጉዳት አስከትለዋል። በግለሰቦች ምክንያት ከተሞች አካባቢ ነውጥ ተነስቶ የዜጎች ህይወት የጠፋበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሊደገም አይገባም። ትውልድ ከዚህ ሊማር ይገባል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የስሜት ሳይሆን የሃሳብ ነው። የማስጨብጨብ የማስጮህ ሳይሆን የዜጎችን ችግር በአግባቡ ተረድቶ በሰከነና ኃላፊነት በተሞላው አካሔድ የመምራት አካሔድ ነው።
ሌላው ለውጥ በመሆኑ ምክንያት በተፈለገው ደረጃ የኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ በሚፈለገው ደረጃ ባለመምጣቱ ያጋጠሙ ፈተናዎች አሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዋናው ፈተና የኢኮኖሚ ስርዓቱን ዘመናዊ ማድረግና የአቋራጭ ንግድንና ህገወጥነትን በሚገባ መልክ ማስያዝ ላይና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከፍ ማድረግ ላይ ብዙ ለውጦች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ ስላልተጓዝን ለዜጎች ፈተና የሆኑ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አጋጥሟል። ይህን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ይገነዘበዋል። የለውጥ ሂደቱ በሁለት ምክንያቶች በኢኮኖሚው ላይ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ እንዳያመጣና ዜጎች በተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዳይኖሩ አድርጓል። አንዱ ባለፉት 27 ዓመታት አሸባሪው የህወሓት ቡድን እዚህ አገር ላይ የተከለው የዘረፋ፣ የሌብነት፣ የአጭበርባሪነትና በአቋራጭ የመክበር የኢኮኖሚ ስርዓት የፈጠረው አደጋ ነው። ይህ አደጋ በህግና ስርዓት የሚመራ ኢኮኖሚ ሳይሆን በተንኮል፣ በዘረፋ የተካኑ የኢኮኖሚ ቡድኖች እንዲፈለፈሉ አድርጎ ቆይቷል። ይህ ብቻ አይደለም፤ አሁንም በአገራችን ላይ ጦርነት በከፈተበት ወቅት እንደአንድ የጦር ግንባር አድርጎ የሚጠቀመው የኢኮኖሚ ግንባር ውጊያውን ነው።
ቡድኑ ለ27 ዓመታት የተፈጠራቸው ኔትወርኮች አሉ። የወጪ ንግድ ኔትወርክ፣ የገቢ ንግድ ኔትወርክና የአገር ውስጥ የሸቀጣሸቀጥ ኔትወርኮች አሉ። እነዚህን አሁንም እንደ አውደውጊያ እየተጠቀመባቸው ነው። ለምሳሌ ባለፉት 27 ዓመታት ለእርሱ የሚመች መዋቅር በመዘርጋቱ የውጭ ምንዛሬንና ከውጭ አገር የገቡ ምርቶችን የመደበቅ እና የማሸሽ፤ የንግድ ስርዓቱን የማዛባት፤ አለአግባብ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ ዜጎችን የማማረር ተግባርን እንደውጊያ ስልት እየተጠቀመበት ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ የህገወጥ ንግዱና የዘረፋ ኔትወርኩ አሁን እያጋጠመ ላለው ፈተና አንዱ መነሻ ነው።
ሌላው በአገራችን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአቅርቦት ስርዓቱን ከፍ ማድረግ ላይ በአብዛኛው ባለመሰራቱ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ውስጥ የአቅርቦት እጥረት አጋጥሟል። ምርቱ አንሶ የዜጎች ፍላጎት በየቀኑ እየጨመረ ሔዷል። በዚህ ምክንያት ዜጎች በቀላሉ ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት ይጋለጣሉ። በአገር ውስጥ የሚመረቱትም ሆነ ከውጭ የሚገቡት ምርቶች አንዳንድ ጊዜ ካለው ፍላጎት ጋር በእጅጉ የተራራቁ በመሆናቸው፤ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ነገሮች ላይ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር ላይ እና ሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በመሰረቱ የምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አቅርቦትን ከፍ ማድረግ ላይ በሚፈለገው ደረጃ መሔድ ያስፈልጋል። ይህ አንዱ የፈተናው ምንጭ ነው።
የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፈተናዎቹ እነዚህ ናቸው። በተባበረ ክንድ እነዚህ ሁለቱንም ችግሮች ለመፍታት ትልቅ እርምጃዎች እየተወሰዱ መጥተዋል። ፅንፈኝነቱና አክራሪነቱ የደቀነውን አደጋ ለመከላከል እርምጃ ተወስዷል። በዚህም የዕለት ተዕለት የደህንነትና የስጋት ፈተናዎች እየተቀረፉ ይገኛሉ። ሁለተኛ ዜጎቻችን እያጋጠማቸው ያለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመከላከል 24 ሰዓት እየተሰራ ነው። እነዚህ ዋና ዋና ራስ ምታት ሆነው የቆዩ ፈ ተናዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫውና የአዲስ መንግስት ምስረታው ከታሪክ አንፃር ምን የተለየ ትርጉም ይኖረዋል?
ዶክተር ቢቂላ፡– ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው ለውጥ አጠቃላይ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሽግግር ስናደርግ የቆየንበት ነው። የአዲስ ምዕራፍ ሽግግሩ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጫው ደግሞ የሰኔ 14ቱ ምርጫ ነው። ይህ ምርጫ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም በአገራችን ታሪክ ምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፤ ቦርዱ ስርዓት ያወጣል፤ ሰዎች ይመዘገባሉ፤ ፕሮግራም ይወጣል፤ እጩዎች ይቀርባሉ፤ ከዚያ ሰዎች ይመርጣሉ። በመጨረሻ በቃ ምርጫ ይህ ነው ተብሎ አምስት ምርጫዎች አለፉ።
ስለእውነት ግን ዜጎች ነፃ ሆነው ማንም ሳያሸማቅቃቸው እና ስለሚመርጡት ሳይነግራቸውና ሳያስጠነቅቃቸው በነፃነት መርጠዋል ወይ የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ ያጠያይቃል። ከዚህ በፊት የምርጫ አስፈፃሚ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ነበሩ ማለት አይቻልም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፈፀምናቸው በጣም መልካም ነገሮች መካከልና ለነገም የሚተርፈው የዴሞክራሲ ተቋሞቻችን ነፃ፣ ገለልተኛና ሞያተኛ ሆነው ይስሩ በሚል ያቋቋምናቸው የዴሞክራሲ ተቋማት እንደምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ፍትህና የፀጥታ ተቋማት ዓይነቶቹ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ አግዘውናል።
መታየት ያለበት የሰኔ 14ቱ ምርጫ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በፊት የተሰሩ የተቋማት ግንባታ ሥራዎች፤ የዴሞክራሲ ተቋማት አደረጃጀት፣ አሰራር፣ ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው፤ ተቋማዊ ብቃታቸውን የማሻሻል ሥራ ላይ የሰራናቸው ሥራዎች በጣም በርካታ መልካም ነገሮችን አምጥተውልናል። በምርጫው የተገኘውን የገለልተኝነት፣ ተቋማት በነፃነት ሞያ ላይ ተመስርተው ሥራ የመስራትና ምርጫን አቅዶ ያለጣልቃገብነት የማስፈፀም መልካም ጅምራቸው በፍፁም ወደ ኋላ መመለስ የለበትም። ምርጫው በአብዛኛው ስኬታማ እና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነበር። በአገራችን የፓርቲ ፖለቲካ በሚገባ ባለመዳበሩ ምክንያትና ፓርቲዎች በመበታተናቸው 47 በመሆናቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው ትልቅ ድምፅ አግኝተው ወደ መሃል ፖለቲካው ባይገቡም፤ ጅምሩ የሚበረታታ ነው።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበት ፓርላማ ይኖራል። በተለያየ አጋጣሚ ድምፅ ያገኙ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክር ቤቶች የሚታዩበት በአንዳንድ የክልል ምክር ቤት ውስጥ ድምፅ የምንሰማበት የምርጫ አካሔድ ነበር። ባለፈው ምርጫ ከምንም በላይ የአምባገነናዊነት ድባብ ተገፎ የዴሞክራሲያዊነት ድባብ መጥቷል። ይህ ምርጫ እንደመነሻ ሆኖ ከዚህ በኋላ እየተሻሻለ ይቀጥላል። ከዚህ በታች አይወርድም። ስለዚህ ምርጫው በዚህ መልኩ ተከናውኖ ሲያበቃ መንግስት የሚመሰርተው እና ከዚህ በላይ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ በግልፅ ታውቆ ከ410 በላይ ድምፅ ተገኝቶ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ዝግጅት እየተካሄደ ነው። የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ዕድል መፈጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ብልፅግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ አግኝቷል። ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ አገኘ ማለት ኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ ናት ማለት አይደለም። ወይም ኢትዮጵያን ለመምራት ብቸኛ ኃላፊነት ያለበት ብልፅግና ነው ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የዜጎቿ እንጂ፤ የብልፅግና ፓርቲ አለመሆኗን ሊገነዘቡት ይገባል።
ብልፅግና በኢትዮጵያውያን ዜጎች አደራ የተሰጠው ፓርቲ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ ብልፅግናን ሲመርጥ አገር የመምራት ኃላፊነት የብልፅግና ፓርቲ ብቻ አለመሆኑን እንገነዘባለን። በዚህ ምክንያት መንግስት ስንመሰርት ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ብልፅግና ሲያስብ ቆይቷል። ሕዝቡ እንደዛ ግልብጥ ብሎ 40 ሚሊዮን አካባቢ ሕዝብ ለመራጭነት ሲመዘገብ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን እስከ ምርጫው ዕለት በተረጋጋ መንፈስ በኃላፊነት ቆይቶ በዕለቱም ከሌሊቱ 11 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት በድቅድቅ ክረምት ዶፍ ዝናብ እየዘነበና በረዶ እየጣለ ተሰልፎ ሲመርጠን፤ ሕዝቡ ለፓርቲያችን ምን መልዕክት እያስተላለፈ ነው የሚለውን መሰረት ያደረገ መንግስት ለመመስረት ጥረት ተደርጓል። ሕዝቡ በምርጫው ወቅት ያስተላለፈውን መልዕክት መሰረት ያደረገና የሚመጥን መንግስት እንመሰርታለን።
ሁለተኛው ሕዝቡ እንደዚያ ግልብጥ ብሎ ብልፅግናን ሲመርጥና ድምፅ ሲሰጥ ብዙ ነገሮች ተመልሰውለት በኢኮኖሚው፣ በአኗኗሩ ተመችቶትና ረክቶ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ ከእርካታና ከደስታ ይልቅ አደራና ኃላፊነት እንደሰጠን እንረዳለን። ዕድል ቢሰጣቸው ከሌሎቹ ፓርቲዎች በተሻለ ሁኔታ ኢትዮጵያን ያሻግሯታል በሚል መልዕክት እንደሆነ በሚገባ እንገነዘባለን። በዚህ የተነሳ የሚመረጠው መንግስት በዋናነት አራት ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሆኖ ተመስርቷል። አንደኛ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የታየውን የለውጥ እንቅስቃሴና የተስፋ ጭላንጭል በማስፋትና በማስቀጠል፣ ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ ማኖር ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንዳለብን እናምናለን።
ይህ ማለት ኢትዮጵያውያን መለያየት፣ መበታተን፣ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ቁርሾንና ደም መፋሰስን አይፈልጉም። የሚፈልጉት ሰላምን መቻቻልን አብሮነትን መተባበርን እጅ ለእጅ ተያይዞ ችግሮችን መጋፈጥን ህብረብሔራዊ አንድነትን ነው። ከዚህ አንፃር ሕዝቡ የሚፈልገውን እናስቀጥላለን። የኢትዮጵያን አንድነት እናስቀጥላለን። የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ እንሰራለን። ስለዚህ የሚመሰረተው መንግስት ዘመናዊ፣ ዜጎች እፎይ የሚሉበት፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት አብሮነት መተጋገዝ፣ መተባበር ባህል እንዲሆን የሚሰራ ይሆናል።
በአገራችን መሰረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች አሉ። ድህነት እና የዋጋ ንረት እንዲሁም የኑሮ ውድነት አለ። ዜጎችን በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ውስጥ እየፈተናቸው ያለ የኢኮኖሚ ችግር አለ። ዜጎች አረፍ እፎይ ማለት አለባቸው። በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ናላቸው መዞር የለበትም። ይህን የሚቀርፉ እርምጃዎችን አዲሱ መንግስት የሚወስድ ይሆናል። ይህንን በሚገባ ተረድቶ ዜጎቻችን በአቅማቸው መኖር የሚችሉበትንና ከመኖር አልፈው በየደረጃው ወደ ብልፅግና የሚሸጋገሩበትን ስርዓት ለመገንባት አዲሱ መንግስት ትልቅ የቤት ሥራ አለበት።
ከዚህ በፊት በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ተግባር ውጤት ሕዝቡን አርክተናል ብለን አናምንም። ችግሮች አሉ። አሁንም በብዙ ቦታዎች ላይ ዜጎች ከመንግስት የሚጠብቁትንና መብታቸው የሆነውን አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ ይታያል። በከተሞች፣ በክፍለ ከተማዎች፣ በዞኖች በተለያዩ ቦታዎች ዜጎች ሲቸገሩ ይታያል። ይህን የሚቀርፍ ጠበቅ ያለ ሪፎርም መውሰድ አስፈላጊ ነው። የአደረጃጀት ሪፎርም የአሰራር ለውጥ የአመራርና የሰው ኃይል ለውጥ በመውሰድ የዜጎችን ሮሮና ምሬት መቅረፍ ይገባል። የሚመሰረተው
መንግስት እዚህ ላይ ትኩረት ያደርጋል። በተለይ ሌብነት እና ሙስናን አምርሮ ይታገላል። ተጠያቂነትን ያሰፍናል። በተጨማሪ የህግ የበላይነትንና የዜጎችን ሰላም ማረጋገጥ ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል። ከላይ እንደገለፅኩት አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ጨምሮ ሌሎች የአገራችን ሰላምና ለዜጎች ደህንነት አደጋ የደቀኑ ነገሮች እዚም እዚያም አሉ። በሰሜኑ በኩል ያለውን ችግር በዘላቂነት የመፍታት፤ ችግሩን የፈጠረው ቡድን ጋሻ ጃግሬዎች ደግሞ በተለያዩ የአገራችን ክፍል የደቀኑትን የዜጎች ሰላምና ደህንነት ችግርን በሚገባ መፍታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መንግስት ይሆናል። ይህ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ መንግስት አገራዊ ታሪክን ከማስቀጠልና ከማደስ አንፃር ምን ይዞ መጥቷል?
ዶክተር ቢቂላ፡- የኢትዮጵያ የአገረ ምስረታ ታሪክ በተለያየ መንገድ ከታሪክ የምንማራቸው፤ መማር ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፋቸው በጣም በርካታ በጎ ስኬቶች አሉት። የሚመሰረተው መንግስት እነዚህ በአገራችን ታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደርጋል። የአገራችን ታሪክ ዛሬ ለደረስንበት ስኬትም ሆነ ፈተና እንደማጣቀሻ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው። በታሪካችን ብዙ መልካም ነገሮች አሉ። አርበኝነትን ከታሪክ ወስደናል። ለአገር ክብር መዋደቅንና በአንድነት መቆምን ከታሪክ ወስደናል። በክፉ በደጉ አብሮ መቆምን፤ የመተጋገዝ የመከባበር ባህልን ከታሪክ ወስደናል። እነዚህ ነገሮች መቀጠል አለባቸው። መቀጠል ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ሂደታችን ዋልታና ማገር ሆነው ማገልገል አለባቸው።
በታሪክ ውስጥ መታየት፣ መታረም መስተካከል ያለባቸው ትርክቶች ካሉም ከሕዝቡ ጋር እየተወያዩ መስተካከል ባለበት ቦታ እያስተካከሉ መሔድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የትናንትም የዛሬም የነገም ናት። ትናንት ለዛሬ መግቧል። ዛሬ ደግሞ ለነገ በሚገባ መመገብ አለበት። መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ካሉ ልሒቃን እየተወያዩ፣ እየተነጋገሩ፤ ሕዝባችን እየተወያየ እየተነጋገረ እያስተካከልን የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታና አብሮነት በጋራ ቅርፅ እያስያዝን እንመጣለን ማለት ነው። ብልፅግና ፓርቲ በዚህ አጥብቆ ያምናል። ትናንት ውስጥ መልካም መልካም ነገሮች አሉ። መልካም መልካሞቹን አጠናክረን እናስቀጥል። የትናንት ታሪክ ላይ መስተካከል ያለባቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ መጪው ትውልድ ያልተስተካከለ ነገር እንዳይወርስ እያስተካከልንለት እንሄዳለን። የምንገነባው ቀጣይነት ላይ ያተኮረ የጋራ ትርክት እየፈጠርን እንሂድ የሚል እምነት አለን። በዚህም ብዙ ስኬቶችን አስመዝግበናል።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ የመንግስት ምስረታ በየዘመኑ ብዙዎች መስዋትነት የከፈሉበት የዴሞክራሲ ግንባታ እውነተኛ ጅማሬ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል?
ዶክተር ቢቂላ፡– ትክክል ነው። ሁልጊዜም በታሪክና በዘመናት መካከል ዜጎች የሚያነሷቸው በጣም በርካታና ጠንካራ ጥያቄዎች አሉ። የዛሬ ሦስት ዓመት ዜጎች ያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎችን፤ የዛሬ 40 እና 50 ዓመትም ጭምር በወቅቱ የነበሩ ዜጎች ያነሷቸው ነበር። በጣም በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ። ፍትህ፣ ፍትህ… እያሉ የተሰዉ ብዙ ሰዎች አሉ። እኩልነት፣ ነፃነት፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራችን ትሁን እያሉ የተሰዉ በጣም በርካታ ሰዎች አሉ። ይሄ ነገር እየተንከባለለ መጥቶ ትውልድ ዋጋ እየከፈለበት፣ እየተሰደደበት፣ አካሉ እየተጎዳበት፣ እየተሰዋ እዚህ ደርሷል። ለዚህ ነው፤ የዛሬ ሦስት ዓመት የነበረው ለውጥ ከዚህ አዙሪት እንውጣ የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ያነሳው።
በጣም ብዙ ትውልድ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህን ፈልጎ ዋጋ ሲከፍል ኖሯል። አሁንም ትውልድ ይህን ዋጋ እየከፈለ ነው። በወቅቱ የነበረው የለውጥ ኃይልም ያለው ይህን አዙሪት ሰብረን እንውጣ የሚል ነበር። ስለዚህ ጥያቄው ትክክል ነው። የዛሬ ሦስት ዓመቱ ጥያቄ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው። እውነተኛ ፍትህ እዚህ አገር ይኑር፤ እውነተኛ ነፃነትና እኩልነት ይኑር፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤ ለሁላችንም ትሁን የሚል ነበር። ፍትህና እውነት አይዛባ የሚል ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ጥያቄ በአቋራጭ ጉልበተኞች እየገቡ ሲሰብሩት ነበር። ደርግ በአቋራጭ መጥቶ ሰበረው፤ አሸባሪው ህወሓት በአቋራጭ መጥቶ ለ27 ዓመታት ሰበረው። የዜጎች ጥያቄ በመሃል ሳይመለስ ቀረ። ስለዚህ እውነት ነው። አሁን የመጣው ለውጥ ለዘመናት በትውልድ መካከል ሲከፈል ለነበረው ዋጋ መልስ የተገኘበትና የወደፊቱ ትውልድም የሚገነባበት ነው ብሎ መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ከመልካም አስተዳደር ግንባታ አንፃር የአስተዳደር መዋቅሮች የሰው ኃይል ምደባ ምን ያህል የተጠናበት ነው? ለዚህስ የሚሆን የሰው ኃይል ማግኘት ቀላል ነው?
ዶክተር ቢቂላ፡– በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። መጀመሪያ እንዳነሳሁት ልክ ምርጫው እንደተጠናቀቀ፤ በተለይ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ማሳወቅ እንደጀመረ ብልፅግና ፓርቲ ይጠይቅ የነበረው ይሄን የሕዝብ ጥያቄ መመለስ የምችለው ምን አድርጌ ነው? የሚል ነበር። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአደባባይ ተናግረውታል። ለእኛም በተለያየ አጋጣሚ ነግረውናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ድምፅ ሲሰጠን ምን እያለን ነው? ብለው ነግረውናል። ስለዚህ ምን ብናደርግ ነው ይሄን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄውን የምንመልስለት? የሚል ጥያቄ አንስተን ስንወያይ ነበር።
የመጀመሪያው ጥያቄ ለሕዝቡ ምን እንደምንሰጥ ነው። የሚሰጠው ይታወቃል። በምርጫ ፉክክሩ ወቅት ለሕዝባችን ምን እንደምንሰጥ በየአደባባዩ በየመድረኩ በየቴሌቪዥኑ ተናግረናል። ማኒፌስቶ አዘጋጅተን በሁሉም ቦታ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው በማህበራዊ ዘርፉ ይሔን እንሰራለን፤ በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲያችን ይሔን ይሔን እንሰራለን ብለን ተናግረናል። መናገር ብቻ አይደለም። የ10 ዓመት የልማት ፍኖተ ካርታ በግልፅ ተዘጋጅቷል። አንድ ፓርቲ የሚመረጠው ለአምስት ዓመት በመሆኑ ከአሥር ዓመቱ ውስጥ ለሕዝቡ ቃል የገባነውን የምንመልስበት የ5 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። በዚያ ውስጥ አደረጃጀታችንና አሰራራችን እንዴት ቢሆን ይሻላል ስንል ጥናት አስጠንተናል።
ዋና መነሻው የሕዝባችንን ጥያቄ እንዴት እንመልስ የሚል ነው። እርሱን መሰረት አድርገን የመንግስት አደረጃጀት ሲጠና ቆይቷል። የፌዴራል መንግስቱ እንዴት ይደራጅ፤ የክልል መንግስታትስ እንዴት ቢደራጁ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሕዝባችንን ጥያቄ ሊመልሱ ይችላሉ የሚለው ሲሰራበት ነበር። በዚሁ መሰረት እንደታየው በከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ላይ የአደረጃጀት ማስተካከያ አድርገዋል። የፌዴራል መንግስቱም የአደረጃጀት ማስተካከያ አድርጓል። የአደረጃጀት ማስተካከያው ዋናው መነሻ ምክንያት የሕዝባችንን፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት እና የአገልግሎት ጥያቄን ለመመለስ በሚያስችል መንገድ ሲጠና ነበር።
በኔ በኩል በቂ ጥናት ተደርጓል ብዬ አምናለሁ። ይህ ማለት ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ፤ የዜጎች ሀብት ለመንግስት መዋቅር ሳይሆን የዜጎችን ችግር ለመመለስ እንዲውል፤ ቀልጣፋና ውጤታማ ተቋማት እንዲፈጠሩ፤ አደረጃጀታችን ራሱ መዋቅሩ የመንግስትን ሀብት የሚበላ ሳይሆን፤ መዋቅሩ ያለውን የሕዝብ ሀብት ወደ አገልግሎት መቀየር እንዲችል በሚያስችል መንገድ የመንግስት አደረጃጀት ጥናት ተደርጎ ተጠናቋል። አንዳንዶቹ ክልሎች ወደ ሥራ ገብተዋል። የፌዴራል መንግስትም አዲስ የአስፈፃሚ አካላት አወቃቀርን ተግባራዊ አድርጓል። አወቃቀሩ ውጤታማነት፣ ቅልጥፍና እና የአገልግሎት ተደራሽነትን መሰረት በማድረግ የሀብት ብክነት መቀስን መሰረት በማድረግ የተመሰረተ ነው። ይህ በሚገባ ሕዝብን ለማገልገል የገባውን ቃል ለመተግበር በሚያስችል መንገድ ሲሰራበት የቆየ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህን አመራር ማግኘት ቀላል ነው?
ዶክተር ቢቂላ ፡- የአገራችን የአመራር ቋቱ ሕዝቡ ነው። ከሕዝቡ የሚወጣ ነው። ሌላ ቋት የለውም። በሕዝብ ደረጃ ካዘጋጀነው ቋት አውጥተናል። ስለዚህ በተቻለ መጠን በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የተፈተኑ፤ በተለያየ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ መጥተው ልምድ ያገኙ፤ በተቻለ መጠን ለሕዝብ ቅንነት ያላቸውን ለማዘጋጀት ሙከራ ተደርጓል። የአመራር ክህሎትና ብቃት የማስፈፀም አቅም በአንድ ሌሊት ተጠናቆ የሚልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚፈጅና የራሱ ሒደት ያለው ስለሆነ፣ ይህን ልምድ እያገኙ ይመጣሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት በጣም ብዙ ቁርጠኝነት ያላቸው፤ ለማወቅ፣ ለመረዳት፣ ከሕዝብም ጋር ወረድ ብለው ተቆራኝተው ለመማር፣ ልምድ ለመውሰድ አቅም አግኝተው ለመምራት የሚችሉ በርካታ አመራሮች የወጡበት ዘመን ነው። በእነዚህ ዓመታት ውጣ ውረዶቹ እንደተጠበቁ ሆነው በጣም ጥሩ የአመራር አቅም የተገነባበት ነው። ስለዚህ በዚያ ተፈትነው የወጡ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ የሚሆኑ አመራሮች እየተዘጋጁና እየተመደቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ፓርቲዎችን ማሳተፍን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ዶክተር ቢቂላ፡– በትክክል ብልፅግና ፓርቲ እና የለውጥ አመራሩ ሲገባ የነበረውን ቃል ወደ ተግባር እንደሚለውጠው ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ የብልፅና ፓርቲ ብቻ ሳትሆን የመላው የኢትዮጵያውያን ናት። ኢትዮጵያን ለመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ለብልፅግና ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቅንነት ያላቸው መልካም ነገር የሚያስቡ ኢትዮጵያ እንድትሻገር፣ እንድትለማ እንድትበለፅግ የሚፈልጉ ቅን አሳቢ ዜጎች ኢትዮጵያን ለመምራት እድል ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ ብልፅግና ያምናል።
በኦሮሚያ ክልል ጠንከር ያለ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራር የካቢኔ አባል ተደርጎ ተሹሟል። የመንግስትን በጀት፣ የመንግስትን ሥራ የመንግስትን ምስጢሮች በሙሉ ይመራል ማለት ነው። ይህ ሰፊ ትንታኔ ሊሰራበት የሚገባ ነው። እውነት በታሪክ ይሄ ነበር ወይ? እንዲህ ያለ ነገር ነበረን ወይ። መንግስትን አሸንፎ ሊመራ የነበረን ሰው ይህንን ቢሮ ከነበጀቱ፣ ከነሰራተኛው፣ ከነእቅዱ አንተ ምራው መባል ተጀምሯል። አዲስ አበባ ላይም ከሦስት ወር በፊት መንግስትን በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ለመያዝ ሲታገሉ የነበሩ ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማን ኢንቨስትመንት አንተ ምራው ተብለዋል። ሌላኛው ደግሞ የከተማዋን ንብረት አስተዳደር ከነበጀቱ፣ ከነሰራተኛው ከነዕቅዱና ከነምስጢሩ አንተ ምራው ተብሎ ተሰጥቶታል። ይሔ ከምንም በላይ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሲሻው በምርጫ ሲሻው በጉልበት ሲሻው በመንግስት ግልበጣ እየመጣ የሁሉ ነገር ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ ከእኔ ወዲያ ለአሳር የሚለውን አስተሳሰብን የሰበረ ነው። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ናት። ቅን ያሰበ መምራት ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ ያረጋገጠ ነው። በዚህ ደረጃ ዝግጅት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ብልፅግና በምርጫው ወቅት ለሕዝቡ የገባውን ቃል ለመፈፀም የሚያስችል ቁመና ላይ ነው የሚል ግምገማ አለ?
ዶክተር ቢቂላ፡– አንድ የፖለቲካ ቡድን ለሕዝቤ መልካም ሃሳብ አለኝ፤ ሕዝቤ እድል ከሰጠኝና ድምፅ ካገኘሁ ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ይነሳል። በዚያ ደረጃ ብልፅግና ፓርቲ በጣም በርካታ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች ምንድን ናቸው? ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች በተሻለ ሁኔታ በሚገባ በደንብ አሰባስቦ በጥናት ለይቶ፤ የመፍቻ መንገዶቹን አካቶ በርካታ መፅሃፍት አዘጋጅቶ አሳትሟል። ራሱም ችግሩን ተረድቶ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲረዳው ያደረገ ፓርቲ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግርን በደንብ እንረዳለን። በዚህ ምክንያት በጣም በርካታ ችግሮችን የምናስገነዝብባቸው ዕድሎችን አግኝተን መፅሃፍ ከማሳተም አልፈን እስከ ታች በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ስልጠና ሰጥተናል። ይህ ችግሩን ሰው እንዲረዳ በማሰብ የተዘጋጀ ነው። የአስር ዓመት የኢትዮጵያን ችግር የመፍቻና የብልፅግና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። በየዘርፉ ግብርናው ምን ይሁን፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የዜጎችን ህይወት ማሻሻል እንዴት ይደረግ፤ የዜጎችን ህይወት፣ ድህነት ቅነሳ እንዴት ይሁን? የሚለውን ሰፊ ፍኖተ ካርታን በዚህኛው የምርጫ ዘመን የምናስፈፅመው ተዘጋጅቷል።
ብልፅግና ይችላል ወይ? ካልን የሕዝብን ችግር ከመገንዘብ መጀመር አለብን፤ እናም ብልፅግና በደንብ ችግሩን ተገንዝቧል። ችግሩን ከመገንዘብ አልፎ መፍታት ጀምሯል። ስለዚህ አሁን የሚመሰረተው በብልፅግና የሚመራውና ሌሎችም የሚሳተፉበት መንግስት የእነዚህን ሃሳቦች ለመፈፀም የሚስችል የመንግስት አደረጃጀት በደንብ አዘጋጅቷል። በዚህ የመንግስት አደረጃጀት በደንብ ገብተው መስራት የሚችሉ ከፌዴራል መንግስት እስከ ቀበሌ ድረስ ምን ዓይነት አመራሮች ናቸው? ከቅንነት፣ ከልምድ፣ ከችሎታና ከአስተሳሰብ አንፃር ምን ዓይነት አመራሮች ናቸው? ብሎ አስቦ አዘጋጅቷል።
ሀብት የማሰባሰብ በጀት በየደረጃው በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። በቂ ስልጠናም ሲሰጥ ቆይቷል። ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ የሚሰጠው ስልጠና ይቀጥላል። ሃሳቦቻችንን ወደ ተግባር ለመቀየር ተከታታይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። በጣም ጠንካራ የክትትል፣ የድጋፍና የተጠያቂነት ሥርዓት ይዘረጋል። የሚመጡ ውጤቶችን ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ለሕዝብ ይፋ በማድረግ መልካም ውጤቶችን ሕዝቡ እንዲያውቃቸው ፈተና የሆኑትን እና አሁንም ያልተፈቱትን ችግሮች ከታች ወደ ላይም ጭምር በማቅረብ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል። ጥርት ያለ በዕቅድ የተደገፈ ለዛ የሚሆን መዋቅር፣ አደረጃጀት፣ አመራርና በጀት እንዲሁም የተጠያቂነት ስርዓት ዘርግቶ ወደዛ እየገባ ስለሆነ ችግሮቹን ለመፍታት በጣም በመልካም ቁመና ላይ የሚገኝ ነው፤ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አመራር ምደባ ሲሉ፤ ሕዝቡ ውስጥ ለስልጣን ያለውን የተዛባ አስተሳሰብ ለመግራት ምን ስራ ተሰርቷል፤ በቀጣይስ ምን ለመስራት ታስቧል?
ዶክተር ቢቂላ፡– በጣም ትክክል ነው። አንድ በጣም መልካም ያልሆነች እስከዛሬም እየተንከባለለች የመጣች አባባል አለች። ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው አባባል ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ ብትፋቅ ደስ ይለኛል። ይህን ሁልጊዜ የምለው ነው። ይህ ከሕዝቡ ውስጥ የወጣ አባባል ነው። ነገሩ በትክክል ሕዝቡ እንደዚህ ዓይነት ባህል ኖሮት አይደለም፤ በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ይሔን ተግብረው አሳይተው በሕዝቡ ውስጥ አስርፀው በመሔዳቸው ነው።
በአሁኑ ሰዓት ሕዝቡ ውስጥ ይህን ያህል የገነነ አስተሳሰብ አለ ብዬ አላምንም። እውነት ለመናገር በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ መጀመሪያ ተለማምደን መውጣት ያለብን ማንኛውም ሰው የሕዝብ አገልጋይ ነው የሚለውን ነው። ሕዝብ ያስቀመጠህ አደራ አገልግለኝ ብሎ ነው። ስለዚህ ሕዝብን ለማገልገል መጥተህ ሕዝቡን አትስረቅ አትብላው የሚል መልዕክትን በውስጣችን መለማመድ አለብን። እንደብልፅግና ፓርቲ በዚህ ላይ መስራት አለብን። 9 ሚሊዮን የብልፅግና ፓርቲ አባላት አሉን። እነዚህ አባላት ይህ እሳቤ ሊገባቸው ይገባል። እኔ የሕዝብ አገልጋይ ነኝ፤ ይህ ሕዝብ ድሃ ነው። ድሃን አልሰርቅም፤ አላንገላታም፤ አላመላልስም የሚል እሳቤን በውስጣችን መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህን እሳቤ ለመፍጠር በጣም ረዥም ሥራ ይጠይቃል። እስከታች ያሉ አባሎቻችን ተደጋጋሚ ስልጠና በመስጠት ሕዝብን ለማገልገል ቅን ልቦና ንፁህ እጅ እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ አተኩረን መስራት አለብን የሚል እምነት አለኝ። ይህ ከተደረገ በኋላ ግን ሕዝቡ ውስጥ ያለ የአገልግሎት አሰጣጥ ስሜት ላይም ጭምር መሰራት አለበት።
እኛ ካላበላሸነው በስተቀር ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝቡ በጣም የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና የሰለጠነ ዜጋ መሆኑን በተለያየ አጋጣሚ አሳይቶናል። ይህን እሴት ማጎልበትና ያልተስተካከሉ ነገሮች ካሉም በውይይት እያስተካከሉ መሔድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመንግስት አገልግሎቶችን ለግለሰቦች ስሙኒ ሳይሰጥ የማግኘት መብት አለው። መታወቂያ ለማውጣት መታወቂያ ለሚያትመው ሰው ለኪሱ ሃምሳ ሳንቲም መስጠት አይጠበቅም። መታወቂያ መስጠት ሥራው ነው። መንጃ ፈቃድ የሚያድሰው የመንግስት ደሞዝ አለው፤ ተገልጋይ እንዲያጎርሰው አይጠበቅም። ንግድ ፈቃድ ለማደስ፣ ለማውጣት፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ዜጎች በምንም ዓይነት መንገድ እጅ መንሻ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም።
በተወሰነ መልኩ በሕዝብ በኩልም መስተካከል ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በእርግጥ በዚህ ላይ እኛም አልሰራንም። ዜጎቻችን የመንግስት አገልግሎቶችን መንግስት ከሚያስከፍለው የአገልግሎት ክፍያ ውጪ እጅ መንሻ እያቀረቡ በአቋራጭ የመገልገልና የአገሪቱ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲዛባ የማድረግ ዝንባሌዎች በተለያዩ ቦታዎች አሉ። ዜጋ ከመንግስት አገልግሎት የማግኘት መብት አለው። ይህንን መብቱን መጠቀም ላይ መለማመድ አለበት። እርሱ ሲያውቅ ደግሞ በተለያየ መንገድ እርሱን በማመላለስ፣ ሰነዱን በመደበቅ፣ ፊት በመንሳት እጅ መንሻን የሚገፋፉ አካላትን ደግሞ አብሮ መታገል መቻል አለበት። አብሮ በመታገል እነዚህን ሰዎች ወደ ፊት በማቅረብ እንዲዋረዱ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ዜጎች ማድረግ አለባቸው። ንፁህ መንግስት ንፁህ ዜጋን ይፈልጋል፤ ንፁህ አመራር ንፁህ ሕዝብ ይፈልጋል፤ በዚህ ደረጃ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- እጅመንሻ ካለመስጠት ባሻገር አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ስኬታማ እንዲሆን ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ቢቂላ፡– መጀመሪያ ላይ እንዳነሳሁት ይሄ ለውጥ ከሰማይ የወረደ ሳይሆን ሕዝቡ ዋጋ ከፍሎ ልጆቹን ገብሮ በየአደባባዩ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮሆ ያመጣው ለውጥ ነው። ሌላው ነገር ቀርቶ በምርጫ ዕለት ከጠዋት እስከ ማታ የተሰለፈው ዜጋ ከባድ ዋጋ ከፍሏል። ነፍሰጡሮች ለምርጫ ተሰልፈው ምጣቸው መጥቷል። ይህን ዋጋ እየከፈለ፣ እየተቸገረ መስዋትነት እየከፈለ ለመመስረት የበቃውን መንግስት እንደአይናቸው ብሌን በማየት መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። በደንብ እንዲያቅድ፣ እንዲረጋጋ፣ ሥራ እንዲሰራ፣ ችግሮቹን እንዲፈታ፣ ቀረብ ብሎ እንዲረዳቸው እንዲያዳምጣቸው በሚገባ ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል። በዚህ ሒደት ውስጥ ዜጎች በሚገባ ዕውቅና ሰጥተው ድጋፍ ያልሰጡት መንግስት ብዙ ርምጃ ሊራመድ አይችልም፤ ይቸገራል። ምክንያቱም መንግስት የሚመሰረተው ለዜጎች ነው። ዜጎች ካልደገፉት ከጎኑ ካልቆሙ ካልመከሩት ካልገሰፁት መንግስት ከባህር የወጣ ዓሣ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ሕዝቡ ዋጋ ከፍለን ያመጣነው ለውጥና የመሰረትነው መንግስት ፍሬ እንዲያፈራ ከጎኑ እንቁም እንደግፈው እንተባበረው ማለት አለባቸው።
እንተባበር ብቻ ሳይሆን የሚገስፅ የሚቆጣ የሚተች ሕዝብ ያስፈልጋል፤ ይህም ድጋፍ ነው። ችግር ባጋጠመ ጊዜ በወረዳ፣ በክፍለከተማ፣ በክልሎችና በፌዴራል መንግስት ይሔ ተበላሽቷልና ቶሎ አስተካክሉ የሚል ግብአት የሚሰጥ መሆን አለበት። ራሱ ያቋቋመው መንግስት በመሆኑ አባት ልጁን እንደሚቆጣ እንደሚገስፅ ቅርፅ እንደሚያሲዝ ሕዝቡ ወደ መንግስት ቀረብ ብሎ መገሰፅ፣ መምከርና ሁሉንም ነገር የጋራ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ጥሩ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ የሚገስፅ እንዲሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይኖራል ወይ ?
ዶክተር ቢቂላ፡- ትክክል ነው፤ በዚህ ለውጥ ውስጥ አንዱ እርምጃ መንግስት ለሕዝቡ ቅርብ መሆን አለበት የሚለው ነው። ቅርብ ብቻ ሳይሆን ክፍት መሆን አለበት። ሁለቱ ነገር ላይ በተደጋጋሚ እንሰራለን። ብዙ ነገር ተሰርቶ አልቋል ብዬ አላምንም። እውነት ለመናገር ታች ያለው እዚህም ያለው ገና ልምዳችን ያልዳበረ በመሆኑ መንግስትን ለሕዝብ ከፈት አድርጎ ያለው ይሔ ነው የሚል፤ መንግስትን ለሕዝብ ቀረብ አድርጎ ይኸውላችሁ እዚህ ነኝ የሚል አይነት ስርዓት በሚገባ እንዘረጋለን። በየአካባቢው ባለው አደረጃጀት በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በክፍለ ከተሞች፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ በአገልግሎት መስጫዎች ጭምር ሕዝብ ባይተዋር እንዳይሆን ያለውን መልካም ስኬት የሚያውቅበትና የሚረዳበት ማወቅ ብቻ ሳይሆን ተበረታቶ መልካም ነገሮችን እውቅና የሚሰጥበት የተበላሹ ነገሮችን በተበላሹበት ወቅት ድምፅ የሚሰማበትን አሰራር እስከታች እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው አገር አሸናፊ እንድትሆን ያሳዩትን ከፍ ያለ ቁርጠኝነት አዲሱ መንግስት እንደአገር ውጤታማ እንዲሆን እንዲደግሙት የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ?
ዶክተር ቢቂላ፡– ልክ ነው፤ ትልቁ ነገር እሳቤያችንና ፍልስፍናችን ነው። ኢትዮጵያ የ115 ሚሊዮን ዜጎቿ ናት። በዚህ ምክንያት ነው እስር ቤት ያሉ ኑ ውጡ ይህች አገር የናንተም ናት። ውጪም ያሉ ኑ ግቡ አገራችሁን ለመምራት ያላችሁን ሃሳብ አቅርቡ ተሳተፉ የሚል እሳቤ የመጣው። ከዚህም ባሻገር በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እውነት ለመናገር በጣም ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ለዚህ ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል።
በእርግጥ ከጅምሩ አንስቶ ከፅንፈኝነት መላቀቅ አቅቷቸው፤ አቋራጭ የስልጣን ጥማቱ አሳውሯቸው፤ በተለያየ አጋጣሚ የግል ክፋት ነገሮችን ሰውረውባቸው፤ አጥፍተው የጠፉ አካላት አሉ። በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም በጎ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ለእነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማመስገን እፈልጋለሁ። በሽግግር ሂደት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው አባሎቻቸውን አደራጅተው አባሎቻቸውን አወያይተው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ይዘን ቀርበናል በማለት ከብልፅግና ውጪ ሌላ አማራጭ ይዞ መቅረብ ራሱ ስኬት ነው። ከብልፅግና ሌላ እኛ ይህ ሃሳብ አለን ብለው 47 ፓርቲዎች ቀርበዋል።
ሌላው የምርጫ ሂደቱ ላይ ለኢትዮጵያ የምናቀርበው አማራጭ ሃሳብ የተለያየ ቢሆንም አገራዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ቆመናል። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው። የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በጋራ አንድ አቋም፤ ኢትዮጵያን ለመጣል የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኃይሎች ሲረባረቡብን ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ አቋም ይዘዋል። ‹‹በህዳሴ ግድብማ አትምጡብን የጋራችን ነው›› ብለዋል። ይህ ትልቅ ነገር ነው። አገራችን ስትወረርና አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲጥር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንድ ድምፅ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልግን አንፈልግም ብለዋል።
አንዳንዶቹ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች አሁንም ድረስ ግንባር ቆመው የኢትዮጵያን ሉዓዋላዊነት ለማስጠበቅ ከብልፅግና ጎን ቆመው እየሰሩ ነው። ይህ ትልቅ ነገር ነው። በምርጫው ሂደትም ምርጫው በሰላም እንዲጀመር፣ እንዲካሔድ፣ ከተጠናቀቀ በኋላም ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ሲሆን ይህ የራሳችን ክፍተት ነው፤ በሚቀጥለው ውስጣችንን ፈትነን እንመጣለን የሚል አቋም በመያዝ ከምርጫ ማግስት ሊመጣ ይችል የነበረውንና የተለመደው ነውጥ እንዳይመጣ አድርገዋል። ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል። ለዚህ ብልፅግና ፓርቲ እውቅና ይሰጣል። ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን በሕዝባችን ውስጥ ይህ ባህል እየሰፋ ሔዶ አንጡራ ባህላችን ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይሰራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ቢቂላ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014