ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እያካሄደች ከምትገኘው ጦርነት ባሻገር በዲፕሎማሲው መስክ ከውጭ ሃይሎች ጋር የምታደርገው ፍልሚያ ሌላው ፈተና ነው። ከዚህ አንጻር በተለይ አሜሪካና ምዕራባውያን ሀገራት አጋጣሚውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት በአንድ በኩል በትግራይ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሽፋን በማድረግና በሰብአዊ ድጋፍ ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያደርጉት ሀገርን ለማዳከም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽና ወዳጆቿ አጋጣሚውን በመጠቀም የአባይ ውሃን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ እየሰሩ ይገኛሉ። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ የመልማት መብቷንም ሆነ ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የሚሹ ሃይሎችን ቦታ ሳትሰጥ ስራዋን ስትሰራ ቆይታለች። በዚህም መሰረት ሁለተኛውን ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሰላማዊ መንገድ አከናውናለች፤ መላውን ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ምርጫም በማካሄድ የመንግስት ምስረታ ሂደት ላይ ደርሳለች። የዛሬው ልዩ እትማችንም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። በዚህ ልዩ እትማችንም በተለይ ከዲፕሎማሲ ስራችን ጋር ተያይዞ እንግዳ ጋብዘን የሰጡንን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፤- እስኪ ራስዎን ያስተዋውቁንና ከእሱ እንጀምር፡፡
ዶ/ር ዳርእስከዳር ፤– ዳር እስከዳር ታዬ እባላለሁ።በስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲቲዩት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና ተመራማሪ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን ፤- ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦ ፖለቲካዊ ቦታ በጣም ወሳኝ በመሆኑ አይን ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል ይባላል።ይህንንም ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎች ባለስልጣናትም ሲናገሩት ሰምተናል።እርስዎ እንደ ምሁር ይህን ሁኔታ ሲመለከቱት እኛ ያለንበት ቦታ በዚያ ልክ ወሳኝነት አለው?
ዶ/ር ዳርእስከዳር ፡– ልክ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከስትራቴጂ አንጻር አስፈላጊ ቀጠና ነው። ከዚህም በተጨማሪ ታላላቅ የሚባሉ የዓለም ሀገራት መቆጣጠር የሚፈልጉት ቀጠና ነው። ምክንያቱም ይሄ ቀጠና ቀይ ባህርን ይይዛል። በተመሳሳይ ከዓለም ከፍተኛውን የነዳጅ ክምችት የያዙ ሀገራትም መገኛ ናት ። የዓለም 20 በመቶ ሸቀጦች የሚንቀሳቀሱትም በዚሁ ቀጠና በኩል ነው። ስለዚህ ይህን ቀጠና መያዝ የዓለምን ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ያህል ጠቀሜታ አለው፡፡
ሌላው ይህን ቀጠና ልዩ የሚያደርገው ድህነት የተንሰራፋባቸው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የያዘ መሆኑ ነው።እንደ አባይ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችንም አቅፏል።እንዲህ አይነት ቀጠና አስፈላጊና ትኩረትን ይስባል።
ስለዚህም በተለይ ዓለም የሁለተኛው የዓለም ጦርንትን ካካሄደች እና ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ከገባች በኋላ አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ተጠናክሯል። የመቆጣጠር ፍላጎቱም ስላለ ሃያላኑ ወደዚህ ይመጣሉ። የሚመጡ ሀገራት የተቃረነ ፍላጎት ስላላቸውም ወደ ግጭት የመግባት ዝንባሌ አለ። ቀላል ምሳሌ ብጠቅስልህ በፈረንጆች አቆጣጠር ከፈረንጆች 1974 በፊት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ወዳጅ ሀገር ነበረች። በዚያ ወቅት የአሁኗ ሩሲያ የያኔዋ ሶቪየት ህብረት ደግሞ ከሶማሊያ ጋር ጥሩ ወዳጅ ነበረች።
ስለዚህ በቀዝቃዛው ጦርነት ሁለቱ ሀገራት የሚያደርጉት ፉክክር እዚህ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ላይ በግልጽ ይታይ ነበር።በ1974 ላይ በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ መጣ።ከዚያ ሶማሊያ ደግሞ በፈረንጆቹ 1977 (በኛ 1969) ላይ ኢትዮጵያን ወረረች። ያ ወረራ ሲጀመር የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበረችው አሜሪካ ወደ ሶማሊያ ደጋፊነት ዞረች ፤ ሩሲያ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጣች።ይህም ትልልቆቹ ሀገራት በቀጠናው ላይ ፍላጎት እንዳላቸው ያመለክታል።
አሁን ላይ ደግሞ ቻይናና እና አሜሪካ እዚሁ ጅቡቲ ላይ የጦር ሰፈር ገንብተው ታያቸዋለህ።ስለዚህ ቀጠናው በጣም ስስ ነው። በዚያ ላይ ድህነት የተንሰራፋባቸው እና የወደቁ ሀገራት ያሉበት ነው። በዚያ ላይ ዓለም የሚፈልገው ሀብት ያለበትም ነው። ከዚያ አንጻር ቀጠናው ስትራቴጂያዊ ጠቃሜታ አለው ተብሎ ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እዚህ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው ለእነሱ ፍላጎት የሚመች መንግስት በስልጣን ላይ የማስቀመጥ ፍላጎት ይኖራቸዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል?
ዶ/ር ዳርእስከዳር፡– ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም። ቢችሉ የነሱን ፍላጎት ብቻ የሚፈጽም መንግስት ቢኖር ፤ ከዚያ በመለስ ደግሞ ከነሱ ጋር ተባብሮ የሚሰራ መንግስትን የመመስረት እና የመደግፍ ከዚያ በተቃራኒ የሚሆንን መንግስት ደግሞ ተቃውሞ እንዲነሳበት እና በተለያየ መጠምዘዣ መንገድ ለእነሱ ፍላጎት እንዲሰራ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመንግስት ባለስልጣናትን በተደጋጋሚ መንግስት የመቀየር ፍላጎት ያላቸው ሀገራት እንዳሉ ይናገራሉ። አሁን ያለውን መንግስት በሌላ መንግስት የመቀየር ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ያሉ ይመስልዎታል?
ዶ/ር ዳርእስከዳር፡– በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ከምእራ ባውያን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደሌላት ይታወቃል። ምእራባውያን በ2012 ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ አስገዳጅ ውል እንድትፈርም በትራምፕ አስተዳደር ከሞከሩ ወዲህ ግንኙነታችን እንደሻከረ ይታወቃል። ከዚያ ደግሞ ከትግራይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብዙ ጫናዎችን እየፈጠሩ ነው።እነዚህ ሀገራት የመንግስት ለውጥ እስከመፈለግ የሚደርስ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል ወይ? ካልክ አዎ ሊኖራቸው ይችላል።በተለይም ስልጣን የያዘው አካል ነው ለኛ ችግር የሆነው ብለው ካመኑ እስከዚያ ድረስ ሊሄዱ ይችላሉ።እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ደረጃ በደረጃ ጫናው እየጨመረ መጣ እንጂ እዚያ ላይ የደረሰ አይመስለኝም።እንግዲህ የሚሆነውን አብረን እናያለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንግዲህ እርስዎ እንደ ተናገሩት ሀገራችን ላይ እየተደረጉ ያሉት ጫናዎች እየተበራከቱ ነው።ነገር ግን ያንን ጫና መቋቋም የሚችል ዲፕሎማሲዊ ቁመና ላይ ያለን ይመስልዎታል?
ዶ/ር ዳርእስከዳር ፡– በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞቿ ምን ላይ ናቸው? የትኞቹስ ጥቅሞቿ ናቸው ከእነሱ ጋር አላሰማማ ያሏት? የሚለውን ማየት ይሻላል። አሁን ላይ እንደ ሀገር ያሉንን ሀብቶች የመጠቀም እና ሀገራዊ ሉአላዊነትን የማስቀጠል መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉን፡፡
ይሄን ለማድረግ ስትንቀሳቀስ ደግሞ የሌሎች ሀገራትን ፍላጎት ልትነካ ትችላለህ።ለምሳሌ በአባይ ላይ ያለን ጉዳይ የማልማት እና የመጠቀም ጉዳይ ነው።እሱን ስታለማ ደግሞ የዚህ ወንዝ ተጋሪ የሆኑ ሀገራት ቅር ሊሰኙ ይችላሉ። ከአሜሪካ ጋር ያለን ችግርም ጎልቶ መውጣት የጀመረው ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይሄ ጉዳይ የልማት ጉዳይ ነው ብትልም የግብጽ መንግስት ግን በሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አሜሪካንን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል።አሜሪካ ደግሞ ግብጽ የመካከለኛው ምስራቅ ዋና አጋሯ ስለሆነች ለግብጽ ወግናለች። አሁን እዚህ ጋር እኛ የመልማት ጥያቄ አለን ፤ ግብጽ ደግሞ በወንዙ ላይ የበላይነቷን እውነታን እያስረዱ ፤ የድርድር አቅምን እያሻሻሉ ፤ የቋንቋ ችሎታንም እያሻሻሉ በተገኘው መድረክ ሁሉ ራስን መግለጽ አዋጭ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ኢትዮጵያ ኤምባሲዎቿን በተለያዩ ምክንያቶች የመቀነስ ውሳኔ ውስጥ እንደገባች ይገለጻል።በዚህ የዲፕሎማሲ ስራ ይበልጥ መስፋት ባለበት ወሳኝ ወቅት ይህን ማድረግንስ እንዴት ይመለከቱታል?
ዶ/ር ዳርእስከዳር፡- ይሄ አዲስ ነገር አይደለም። ኤምባሲ መዝጋት ወይም አምባሳደርን መጥራት ተለምዷል።በሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሲበላሽ ሀገሮች እንደዚህ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በቅርቡ የፈረንሳይ እና አሜሪካንን ጉዳይ ማየት እንችላለን።በሌላ መልኩ ሀገራት በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሲገቡም እንደዚህ ያደርጋሉ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከኤምባሲዎች ጋር እየተፈጠረ ያለው ነገር ምንድን ነው ከተባለ ኢትዮጵያ በብዙ ኤምባሲዎቿ ላይ ዲፕሎማቶችን እየቀነሰች ነው።ባለኝ መረጃ ብዙ ኤምባሲዎች አይዘጉም ፤ የተወሰኑ ሚሲዮን መስሪያ ቤቶች እና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ግን ይዘጋሉ።ኢትዮጵያ አሁንም ወደ ሃምሳ የሚሆኑ ሀገራት ላይ ኤምባሲዎቿን ታስቀጥላለች። የሚኖረን የዲፕሎማቶች ቡድን ግን እንደ በፊቱ ብዙ ሰዎችን የያዘ ላይሆን ይችላል፡፡
መርሳት የሌለብን በቅርብ ጊዜያት ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል።ነገር ግን እርዳታ ሲከለክሉን እና ማእቀብ ሲጥሉብን እስከሁን ከየትም ሀገር አምባሳደር አልጠራንም። ማኩረፋችንንም አልገለጽንም። ምክንያቱም ቀስ በቀስ በውይይት የሚፈታ ችግር ነው በማለት ነው።አሁን ያለው የኤምባሲ መቀነስ ሁኔታ ከፋይናነስ ጋር የተገናኘም ሊሆን ይችላል ፤ ማኩረፍህን ለማሳየትም ሊሆን ይችላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ቁልፍ ሀገራት ስለሆኑ ኤምባሲህን የማትዘጋባቸው አንዳንድ ሀገሮች አሉ። ለምሳሌ አሜሪካን ብናይ የተመድ ጽ/ቤት ያለው እዛ ነው ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያንም እዚያ አሉ ፤ ኢኮኖሚዊ ጥቅምም አለው ፤ ሚዲያውንም በቀላሉ ለማግኘት ግፊት አለ። እንግዲህ እነሱ ምን አስበው ይህን እንደፈለጉ ማወቅ አንችልም። ነገር ግን የነሱ ተመራማሪዎች ከሚሉት ተነስተን አንዳንድ ነገሮች ማለት እንችላለን፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ተመራማሪዎቻቸው የሚሉትን ብናይ ኤርትራ ለረዥም ዓመታት የምእራባውያንን ጫና ተቋቁማ መዝለቅ ችላለች። ጫና የሚያደርጉባት የነሱን ፍላጎት የምታንጸባርቅ እንድትሆን ነው። ግን የኤርትራ መንግስት የነሱን ጫና እምቢ እያለ የራሱን ፍላጎት እያስጠበቀ ይቀጥል ነበር። ስለዚህ አሁን ዶ/ር አቢይ ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ሲመሰርት የኢሳያስን አይነት ባህሪ ይላበሳል ፤ ለአሜሪካ እና ለምእራባውያን ፍላጎት እምቢ ብሎ የሚቆም መንግስት ይሆናል የሚል ፍርሃት አላቸው።
እንዲያውም አንዳንዶቹ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስን ትልቁ መጥፎ ወንድም (a bad big brother) የሚል መጠሪያ ነው የሚሰጧቸው። ሌላም ኢሳይያስን የሚከሱበት ብዙ ነገር አለ።ዶ/ር አቢይ የዚያን አይነት ባህሪ ይላበሳል የሚል ስጋት አላቸው።ያ ባህሪ ወደ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ይመጣና ለምእራባውያን ፍላጎት የማይንበረከክ መንግስት ኢትዮጵያም ውስጥ ይፈጠራል የሚል ስጋት አላቸው። እነሱ ደግሞ የሚፈልጉት ልክ በቀደመው ጊዜ እንደነበረው ከነሱ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እነሱ የሚፈልጉትን እሺ እያለ የሚሰራ መንግስት ነው፡፡
ለእኛ አሁን ከኤርትራ ጋር ጥሩ እድል ተፈጥሯል። ነገር ግን እነሱ እንደሚሰጉት ከነሱ ጋር ጨርሶ የሚለያየን ነገር እንዳይፈጠር ደግሞ ተጠንቅቀን መስራት አለብን።ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት በመርህ እና በህግ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ፤ ከሶማሊያም ጋር እንደዛው። ከኤርትራ ጋር እንደምናደርገው ግንኙነት ሁሉ ከአሜሪካ ከቻይናም ጋር ግንኙነት ማድረግ ይኖርብናል።
ያስፈልጋል። ከዚያ ባለፈ በዓለም አቀፉ ሥርዓት ላይ ቻይና አለች አሜሪካ አለች ፤ አንዱን በአንዱ ሳናስኮርፍ እንዴት አድርገን እንቀጥላለን የሚለውንም በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህን ነገሮች ለመስራት ግን መጀመሪያ እጃችን ላይ ምን ካፒታል አለ የሚለው መታየት አለበት።ለምሳሌ በውጭ ግንኙነታችን ስኬታማ እንድንሆን በውስጥ አስተማማኝ ሰላም መኖር አለበት ፤ ጥሩ ኢኮኖሚ መኖር አለበት ፤ ጠንካራ መከላከያ /ሚሊተሪ/ ይፈልጋል ፤ የሰለጠነ ማህበረሰብ ይፈልጋል።እነዚህ ነገሮች ሲኖሩህ ፍላጎትህን ለመፈጸም የተሻለ አቅም ይኖርሃል። በአጠቃላይ የውጭ ፍላጎትህን ለማሳካት የውስጥ ጥንካሬ ያስፈልጋል ፤ ስለዚህ የውስጥ ጉዳይ ላይ አትኩሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ዲያስፖራው በዲፕሎማሲው ስራ እንዲያግዝ ጥሪ እየቀረበ ነው።በዚህ በኩልስ የሚታሰበውን ያህል ውጤት ማምጣት ይቻላል።በሌሎች ሀገራት ያለው ተሞክሮስ እንዴት ነው?
ዶ/ር ዳርእስከዳር፡– ከሌሎች ሀገራት አንጻር ከፍተኛ ውጤታማ ተጽአኖ ፈጣሪ ዲያስፖራ ያላት እስራኤል ናት። የእስራኤል ዲያስፖራ አንደኛ ሀብታም ነው።ሁለተኛ በምእራቡ ዓለም ፖለቲካ እጁ ረዥም ነው።ተጽእኖ ለመፍጠር እውቀቱም ገንዘቡም አለው።ምእራባውያን ከነሱ ጎን እንዲቆሙ ከማድረግ አንጻር የተሳካ ስራ ሰርተዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ዲያስፖራውን መጠቀም ይቻላል ወይ? ሲባል መልሱ አዎ ይቻላል ነው። ዲያስፖራው በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በፖለቲካው ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። ነገር ግን እንቅስቃሴው የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካ በመደገፍ እና በመቃወም ላይ ነው የሚያተኩረው። አሁን ዲያስፖራውን ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም እንጠቀም የምንል ከሆነ አንደኛ ዲስፖራው በደንብ መደራጀት አለበት።ሁለተኛ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆን አለበት፡፡
አሁን ዲያስፖራውን መጠቀም የምንችለባቸው ብዙ እድሎች አሉ። አንደኛው የቴክኖሎጂ እድገት ነው። በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ መፍጠር የሚፈልጉ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይጽፋሉ ፤ ከዚያ ያን ተከትሎ ጫናው ይመጣል። ይሄው መድረክ እዚህ ላሉ ኢትዮጵያውያንም ውጭ ላሉትም ክፍት ነው። ስለዚህ ዲያስፖራው በዚሁ መድረክ እነዚህን ፖሊሲ አውጪዎችን ለማግኘት ይረዳዋል።
የተደራጀ ሲሆን ደግሞ በየትኛው ጉዳይ ላይ በማን በኩል የትኛውን ሴናተር ወይም ህግ አውጪ ማግኘት አለብኝ የሚለውን መለየት ይችላል።ይህ ግን የተደራጀ መረጃ እና ጥሩ የተግባቦት ብቃትም ይጠይቃል።ዝም በሎ በመጯጯህ አይደለም።የእስራኤል ዲያስፖራ ሲጮህ አታየውም፤ ግን የፈለገውን ያስፈጽማል።በዚህ መልኩ የኛ ዲስፖራም ከተንቀሳቀሰ ውጤታማ መሆን እና አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡– አዲስ የሚመጣው መንግስት ጥንካሬው ወደፊት የሚታይ ሆኖ በመጪው 5 ዓመት ውስጥ በዓለምአቀፍ ፖለቲካው በኩል ለኢትዮጵያ ያለው እድል ያይላል ወይስ ተግዳሮት ነው ያለው?
ዶ/ር ዳርእስከዳር፡- ተግዳሮትን ማስቆም አንችልም። ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ለውጦችን አንተ መቆጣጠር አትችልም።ለምሳሌ በትግራይ እና በአባይ ግድብ በኩል እየመጣ ያለውን ጫና በምትስራው ስራ ልታስቆመው ትችላለህ።ነገር ግን ሱዳን ውስጥ መንግስት እየተዳከመ ነው።እሱ በኛ ቁጥጥር ስር አይደለም።
የቻይና እና የአሜሪካ ፉክክር ከኛ ቁጥጥር ውጭ ነው። እንዲህ እንዲህ አይነት ነገሮች እኛን ተግዳሮት ውስጥ ይከቱናል። ስለዚህ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ምን ይመስላል ቢባል ግምቴ 50 – 50 ነው። ውስጥ ያለውን ችግር በስራችን ልናስቆመው እንችላለን ፤ የውጭውን ግን የመከላከል አቅማችንን በማጠናከር መዘጋጀት አለብን።
የቻይና እና የአሜሪካ ፍትጊያ ቢቀር እንኳን ሌላ ነገር መፈጠሩ አይቀርም።የሆነ ጊዜ ሶቪየት ሲቪየት ሶቪየት ነበር ፤ የሆነ ጊዜ ሽብርተኝነት ሽብርተኝነት ሽብርተኝነት፤ አሁን ቻይና ቻይና ቻይና እየተባለ ነው። ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ አይታወቅም።የኛ ተጠቃሚነት የሚመነጨው የሚመጡ ፈተናዎችን እንዴት አድርገን ወደ እድል እንቀይራለን ከሚለው በመነሳት ነው።የሆነ ሆኖ ከተግዳሮት ነጻ የሆነ ዓለም መጠበቅ የለብንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ
ዶ/ር ዳርእስከዳር ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014