በዓለም ላይ ታዋቂ ከሆኑትና አዝናኝ ከሚባሉ የጎዳና ሩጫዎች መካከል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተጠቃሽ ነው። በ‹‹ሯጮቹ ምድር›› የሚካሄደው ይህ ሩጫ በአፍሪካ በግዝፈቱ ቁጥር አንድ ውድድር ሲሆን፤ ታላላቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ እንዲሁም ተስፋ ያላቸው ታዳጊ አትሌቶችን በማሳተፍም ይታወቃል። ይህ ዓመታዊ ውድድር ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ በመጪው ህዳር ወር ይካሄዳል፤ ይህ ወቅት የጎዳና ላይ ውድድሮች የሚካሄዱበት በመሆኑ በመላው ዓለም ያሉ ሯጮችን በእጅጉ የሚጋብዝ ውድድርም ነው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ አትሌቲክስ ስፖርት ለምትታወቀው ሀገሪቷ አንድ የውድድር መድረክ ከመሆኑም ባለፈ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ውድድር መሆኑም ትልቅ ዋጋ ያለው ሀገር በቀል ውድድር ያደርገዋል። የሀገርን ገጽታ በመልካም ከመገንባቱም ባለፈ የስፖርት ቱሪዝምን በመሳብ እንዲሁም ሕዝቡ በስፖርት አካላዊና አእምሯዊ ጤናውን እንዲገነባ የሚያደርግ መድረክም ነው።
ከውድድሩ መካሄድ ጋር ተያይዞ ተጠቃሚ የሚሆኑት በርካታ አካላት ናቸው። ከሩጫው ዓላማዎች መካከል አንዱ የሆነው ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደመሆኑም ላለፉት ዓመታት ለበርካቶች መድረስ የቻለ ውድድር መሆን ችሏል።
ይህ ውድድር በየዓመቱ የተለያዩ ማህበራዊ መልዕክቶችን ከማንሳትም በተጨማሪ ገንዘብ በማሰባሰብም ለተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እርዳታ ይሰጣል። ከዚህ ቀደም ከውድድሩ ጎን ለጎን በሚሰራው ገቢ ማስገኛ ከኢፌዴሪ ሴቶችና ሕፃናት ሚኒስትር ጋር በመሆን ለተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህ ውድድር ዘንድሮም ለ‹‹ወጣቶች አትሌቲክስ ፕሮጀክት›› እንዲሁም ‹‹ግሬስ ለልጆችና ቤተሰቦቻቸው ማዕከል›› እርዳታ ለማድረግ መታቀዱን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰጠው መግለጫ ተመላክቷል። በዚህም መሰረት ‹‹ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ›› የሚለው መርሃ ግብር ዘመቻ ይሆን ዘንድ የተወሰኑ የመሮጫ ቲሸርቶችን በተጨማሪ ዋጋ ለመሸጥ የተዘጋጀ ሲሆን፤650ሺ ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ይህንን በተመለከተም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ዳግም ተሾመ ‹‹ሩጫውን ሲወዳደሩ እርዳታ ለሚያሻቸው ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን መታሰቢያነት አድርጎ መሮጥ ደስታን ይሰጣል። ታላቁ ሩጫ ባለፉት ዓመታት ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ የተለያዩ ድርጅቶችን ረድቷል። ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆነው በዋግህምራ ዞን ያሰራው ትምህርት ቤት ነው›› ብለዋል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይህንን ተግባር ለ16 ዓመታት ሲያከናውን ቆይቷል።
በተጨማሪም ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ተናፋቂው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ ከዓለም አቀፉ ተራድኦ ድርጅት ዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ‹‹መጸዳዳት በሽንት ቤት›› የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። ይህም አካባቢን ከብክለት ነጻ እንዲሁም ለሕፃናት ተስማሚ እንዲሆን የሚያበረታታ እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ በመጠቀምና በማጽዳት ራስንና አካባቢን ከተላላፊ በሽታ ለመጠበቅ የሚረዳ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ይሆናል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ዕውቅና በሚሰጠው ድርጅት (AIMS) ዕውቅና ያለው አባልም ነው።
ዘንድሮም ለ20ኛ ጊዜ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ዓመታዊ ሩጫ ይካሄዳል። ህዳር 5/2014 ዓ.ም ለሚካሄደው ሩጫ የቲሸርት ምዝገባ የተጀመረው በሐምሌ ወር ሲሆን፤ ምዝገባው ተጠናቆ ሯጮች የሩጫውን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጥንቃቄ መንገዶች በተከተለ ሁኔታ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ 300 የሚሆኑ አትሌቶች ሲሳተፉ፤ 100 የሚሆኑት ሴቶች እንዲሁም 200 ዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ሯጮች በተለያየ ሰዓት ሩጫቸውን እንዲጀምሩ ሲደረግ፤ መነሻውም እንዳለፉት ዓመታት በመስቀል አደባባይ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ሩጫዎች ባለፈ በእንጦጦ ፓርክ በየወሩ ተከታታይ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድሮችን ያካሂዳል። በአካል በስፍራው መገኘት ላልቻሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ሯጮችም በበይነመረብ አማካኝነት በሩጫው ተሳታፊ የሚሆኑበትን መንገድ አመቻችቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014