የአንድ ሀገር ትንሳኤ የሚመነጨው የቀደመውን ዘመን የተሻለ የህይወት ተሞክሮ ዳግም ሕይወት መስጠት የሚያስችል መንቃትና ከዚሕ የሚመነጭ የአስተሳሰብ ልእልና መፍጠር የሚያስችል የትውልዶች መነሳሳት ሲኖር ነው። ለዚህ ደግሞ የቀደሙ ታሪኮችን በአግባቡ መረዳትና ፤ ለታሪክና ለባለታሪኮች ተገቢውን ስፍራ መስጠት ወሳኝ ነው። ከዚህ ውጭ ስለሀገር ትንሳኤ የሚደረጉ ዲስኮሮች በራሳቸው ትርጉም ሊኖራቸው አይችልም።
ትንሳኤ የሚለው ቃል ዳግም ለሕይወት መታጨትን የሚያመለክት ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ከሞት በኋላ ሌላ የህይወት አማራጭ /ዕድል/ መኖሩን ይጠቁማል ፤ የመመለስ ተስፋ እንዳለ ያመላክታል፤ ከኮረብታዎች ጀርባ ነገዎችን በተሻለ ተስፋ ማየት የሚያስችል ብርሃን ስለመኖሩም ይተርካል።
ትናንትን በአግባቡ ከመረዳት ፤ ከትናንት ስህተቶች መማርንና በትናንት ስህተቶች ውስጥ ላለመገኘት ከራስ ጋር በጠራ የእውነት እውቀት መታረቅን የሚጠይቅ ፤ ትናንትንም ከዛሬ ፤ ከነገ ተስፋ ጋር አስታርቆ ሙሉ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ሕይወትን ለመቀበል ሙሉ ዝግጁነትን የሚፈልግ እና ከፍ ያለ የሰብዓዊ እሴት ግንባታን የሚጠይቅ ጭምር ነው።
ጠንካራ በሆኑ የሞራል አሴቶች የሚገነባ፤ በመርህ መኖርን፤ ለግለሰባዊም ሆነ ለማህበራዊ ህይወት ከፍ ያለ ዋጋ መስጠትንና ከትናንት አሮጌ ማንነት ጋር በእውቀት እና ከፍ ባለ ተስፈኝነት ፍቺ የመፈጸም መነሳሳትንና ተግባራዊ ዕርምጃ ውስጥ መግባትን ፤ በያንዳንዱ ዕርምጃ መሀል የሚያጋጥም ተግዳሮትን አሸንፎ መሻገር የሚያስችል ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።
ከያንዳንዱ ፈተና በስተጀርባ ያለውን ተስፋ አቀጫጭ ፤ ዳግም ሞት አማጭ አስተሳሰቦችንና ከአስተሳሰቦቹ የሚመነጩ ገዳይ ተግባራትን በሕያውነት የትንሳኤ መርህ ማሸነፍና ከድል ወደ ድል በህይወት መርህ መጓዝን፤ ይህንንም በጠንካራ የህይወት ዲሲፕሊን መምራትና ማስቀጠል የሚፈልግ ነው።
እኛም እንደ ሀገር የጀመርነው የትንሳኤ ጉዞ ለዚህ እውነት የተገዛና በትንሳኤ የህይወት መርህ የሚመራ ነው። ለስኬቱም አልፋና ኦሜጋ የሚሆነው ይሄው እውነታ ይሆናል። ትናንቶቻችንን በአግባቡ መረዳት፤ ከትናንቶች መማር ፤ ነገዎቻችንን እስከ ተግዳሮታቸው ተስፋ ማድረግና ስለተስፋ ዋጋ መክፈልን መለማመድና ሀገራዊ ባህል ማድረግ ይጠበቅብናል።
ከትናንት የከፍታ ስፍራችን ወርደን ዛሬ ላይ ለምን የዝቅታ ዝቅታ ላይ ተገኘን ? ለዚህ የዳረገን ምንድን ነው ? ይህን እውነታ በአግባቡ ለመረዳት ለምን ዘመናት ፈጀብን ? ዛሬስ እውነታውን የተረዳንበት መንገድ በእውቀት እንደ ህዝብ ሊያሻግረን ይችላል ? ትናንቶች ላይ ያፈጠርነው ተስፋ የዛሬን ተግዳሮቶች አሸንፎ የመውጣት አቅም የገዛ ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች እንደ ህዝብ ምላሽ ልንሰጣቸው ይገባል፡፡
የጀመርነው የትንሳኤ ጉዞ ስለራሳችን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ያለንን የተዛቡ አመለካከቶች ማረምን ፤ ከትናንት ክፉ እና ደግ ታሪኮቻችን እኩል ለመማር የሚያስችል ለታሪክ የመታመን የማንነት ዝግጁነትን ፣ ከተዛቡ ትርክቶችና እነሱ ከፈጠሩት አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከወለደው ክፉ ደዌ ለመፈወስ በጎ ህሊናን ይጠይቃል።
የትንሳኤ ጉዟችን ሙት ከሆኑና በታሪክ ሄደት ውስጥ እንደ ህዝብ ሙት ካደረጉን አስተሳሰቦች ጋር በእውነትና በእውቀት ፍቺ የምንፈጽምበት ፤ወደ ትንሳኤ ካመጡንና እስከ ፍጻሜው ይዘውን ከሚጓዙ፣ የዛሬም ሆነ የነገ የትንሳኤ ጉዟችን ስኬት ምንጭ ከሆኑ እሴቶች ጋር የቃል ኪዳን ትስስር ማድረግና ለነሱና ለነሱ ብቻ ተገዥ መሆንን ይፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ትናንቶቻችንን ያበላሹብንን ፤ለዛሬ ተግዳሮት የሆኑብንን ፣ ከዛሬም ተሻግረው ነገዎቻችን የጨለሙብንን የተበላሹ የአስተሳሰብ መሰረቶች መንፈሳዊ ፣ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ መሰረታቸውን በትንሳኤው እውቀት በመግራት ማፍረስ ፤ ለዚህም የሚሆን ቁርጠኝነት መገንባትና በተግባር መግለጥ ወሳኝ ነው።
አሁን የጀመርነው የትንሳኤ ጉዞ ለሌሎች በከፋ ጨለማ ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦች የማንቂያ ደውል መሆኑን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል፤ የትንሳኤ ጉዟችን አልጋ በአልጋ እንደማይሆንም መረዳትም ይገባል፡፡
በቀደመው ዘመን በዓደዋ ያበሰርነው ድል ብዙ ወንድሞቻችን ለነፃነት ትግል እንዲነቁ፤ በመስዋዕትነታቸው ፍሬ የነፃነታቸው ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻለ ከመሆኑ አንጻር የዛን ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል አውቆ መዘጋጀትን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014